Saturday, 14 May 2022 00:00

ኢሰመኮ በሶማሌ ክልል በጎሳ አባላት ላይ በፀጥታ ሃይሎች የተፈጸመውን ጥቃት አጋለጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


              በሶማሌ ክልል ፈፋን ዞን ጉርስም ወረዳ፣ ቦምባስ ከተማ  ባህላዊ ስነ ስርዓት የጎሳ መሪ (ሱልጣን) ለመምረጥ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ መጋቢት 11 እና 12 ቀን 2014 በክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በተወሰደ  የሃይል እርምጃ 11 ሰዎች ሲገደሉ 33 በፅኑ መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በክልሉ መንግስት የፀጥታ ሃይሎች በተወሰደው ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ ምክንያት የሰው ሕይወት ማለፉ  በርካቶች መቁሰላቸው የክልሉን የፀጥታ  ሃይል ተጠያቂ እንደሚያደርገው ኢሠመኮ በሪፖርቱ አስግንዝቧል፡፡
ኮሚሽኑ ችግሩ መፈጠሩን የሚያመለክት መረጃ ከደረሰው በኋላ ከሚያዝያ 7  እስከ ሚያዝያ 12 ቀን 2014 ባለሙያዎችን ወደ ስፍራው ልኮ ምርመራ ሲያከናውን መቆየቱን፣ በምርመራው  ወቅትም የዓይን  ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችንና የሐገር ሽማግሌዎችን በግልና  በቡድን ማነጋገር መቻሉን፣ በተጨማሪም ከሆስፒታል ምንጮች መረጃ ማሰባሰቡን እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ማብራሪያና ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ የሆኑ የክልሉ ሃላፊዎችን ማነጋገሩን አመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን መቃብር ስፍራ መጎብኘቱን፣ በዚህም በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የተገደሉ ሰዎች የተቀበሩበትን የጅምላ መቃብር የምርመራ ቡድኑ መመልከቱ ተገልጿል፡፡
ችግሩ ያጋጠመው ከጅግጅጋ በ50 ኪ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጉርስም ወረዳ ውስጥ በሚኖሩና ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል ስር፣ ይተዳደሩ በነበሩ፤ ኋላም በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረሰን የድንበር ስምንት መነሻ በማድረግ ከ2011 ጀምሮ በሶማሌ ክልል እየተዳደሩ ባሉት የአኪሾ ጎሳ አባላት ላይ መሆኑን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ የግጭቱ መነሻም የአኪሻ ጎሳ አባላቱ የራሳቸውን የጎሳ መሪ ለመምረጥ የምርጫ  ስነ ስርዓት ማዘጋጀት እንደሚፈልጉ ለጉርሱም ወረዳ አስተዳደር ያሳውቃሉ፤ የወረዳው አስተዳደርም “የአኪሾ ጎሳ በወረሁሜ  ጎሳስርዓት ስር የሚተዳደር በመሆኑ አዲስ መሪ መምረጥ አያስፈልግም” በሚል ምክንያት ዝግጅቱ እንዳይደረግ ይከላክላል። የጎሳ አባላቱም ጉዳዩን ለፋፈን ዞን እንዲሁም ለክልሉ መንግስት ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ቢሮ እና ለፀጥታ ቢሮ እንዳሳወቁ ተገልጿል፡፡
ከክልሉ የፀጥታ ቢሮ ሃላፊም  “ይህን ማከናወን መብታችሁ በመሆኑ እዚህ መምጣትም አይጠበቅባችሁም ነበር” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና በ20 ቀናት ውስጥ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው የሃገር ሽማግሌዎች አስረድተውኛል ብሏል - ኢሰመኮ በሪፖርቱ።
በሌላ በኩል የወረ ሁሜ ሱልጣን የተወሰኑ የአኪሾ ጎሳ አባላት አቤቱታቸውን ለወረዳው አስተዳደር፣ ለፋፈን ዞን አስተዳደር፣ ለክልል መስተዳደር አካላት  ያቀርባሉ በምላሹም “ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባችሁ በወረ ሁሜ ህግ አልተፈቀደላችሁም  ስለዚህ የጎሳ መሪው ጋር  ሂዱ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው፤ የወረ ሁሜ ጎሳ ሱልጣን በበኩላቸው ለኢሠመኮ በሰጡት  ማብራሪያ የአኪሾ ጎሳ አባላቱ ወደ እሳቸው መጥተው እንደነበርና በወረሁሜ ባህላዊ ህግ መሰረት ሌላ ሱልጣን መምረጥ እንደማይችሉ በመግለፅ እንደመለሱላቸው አስረድተዋል፡፡
ሆኖም የጎሳው አባላት የራሳቸውን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅታቸውን መቀጠላቸውን ለባህላዊ ሥነስርዓቱ ድግስ  ግመሎችና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ግብአቶችን በማዘጋጀት ጭምር ለምርጫ የተያዘውን ቀን ሲጠባበቁ እንደነበር የኢሠመኮ የምርመራ ቡድን ለመረዳት ችሏል፡፡
ይህ ውዝግብ እልባት ባላገኘበት ሁኔታ ከምርጫው ቀን 4 ቀናት ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ቦምባስ ከተማ በመግባት ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበርና ከልዩ ሃይሉ ውጪ ሌላ የፀጥታ ኋይል በከተማው ውስጥ ያልነበረ መሆኑን ኢሠመኮ የአይን እማኞች ነግረውኛል ብሏል ፡፡
የምርጫው እለት መጋቢት 11 ቀን 2014 በግምት ከጠዋቱ 1 ሰዓት  አካባቢ  ቦምባስ ከተማ ቀበሌ 02 ዋና መንገድ ላይ የጎሳውን ሱልጣን ለመምረጥ ቁጥራቸው በግምት 4 ሺህ የሚደርሱ የኢኪሾ ጎሳ ተወላጆች መሰባሰባቸውን፣ዝግጅት ከተጀመረ ጥቂት ቆይታ በኋላ በግምት ከጠዋቱ 2 ሰዓት አካባቢ ሲሆን የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ወደ ስብሰባው ቦታ መጥተው “የጎሳ አባላቱን “ስብሰባውን አቋርጠው ይበተኑ” በማለታቸው አለመግባባት እንደተፈጠረ ተመልክቷል፡፡
ህዝቡም አንበተንም በማለቱ የልዩ ሃይሉ አዛዥ በአካባቢው ለነበሩ የልዩ ሀይል አባላት ትዕዛዝ በመስጠት በግምት እስከ 5 ሜትር ርቀት ላይ በመሆን በቀጥታ ወደ ህዝቡ ጥይት መተኮስ መጀመሩን የአይን እማኞች  ለኢሰመኮ የምርመራ ቡድን አስረድተዋል፡፡
የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን  ያነጋገራቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩላቸው፣ “ተሰብሳቢዎች መንገድ ዘግተውና በብዛት መሳሪያም ታጥቀው እንደነበር፤መንገድ ለምን ትዘጋላችሁ በሚል በፖሊስና በተሰብሳቢዎቹ መካከል ግብግብ መፈጠሩን፤ በዚህ መሃከል ከተሰብሳቢዎቹ ጥይት መተኮሱንና ኮሎኔል ወሊዩ የተባለ የፖሊስ አባል በጥይት መመታቱንና ፖሊሶችም ስሜታዊ በመሆን ተመጣጣኝ ሊባል የማይችል እርምጃ ሊወስዱ  እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ በተፈጠረው ሁከት ከክልሉ ልዩ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት 8 ሰዎች ግንባራቸውንና ሆዳቸው ላይ በጥይት ተመተው ወዲያውኑ መሞታቸውን፣ በተጨማሪም ሁለት ሰዎች ከወደቁበት እንዳይነሱ ፖሊሶች በመከልከላቸው ደማቸው ፈሶ በማለቁ መሞታቸውን፤ 22 ሰዎችም መቁሰላቸው ተመልክቷል፡፡
የሟቾች  የቀብር ስነስርአት በበነጋው መጋቢት 12 ቀን 2014 መካሄዱን፣ በእለቱ ከቀብር በፊት የጎሳ መሪዎች ምርጫ እያለ  የታጠቁ ግለሰቦች ተኩስ ከፍተው አንዲት አረጋዊት ሴት ህይወት  ማለፉንና  11 ተጨማሪ ሰዎች መቁሰላቸውን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
በአኪሾ ጎሳ አባላት ላይ ድብዳባ፣ የአካል ጉዳትና የሕይወት መጥፋት ያስከተሉ ግለሰቦች በሙሉ  የአስተዳደርና የፀጥታ አካላትን ጨምሮ ግልፅ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ፣ የወንጅል ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና ለወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይከሰት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢሠመኮ አሳስቧል፡፡

Read 864 times