Monday, 09 May 2022 00:00

ያልተነገረው የ2ኛው የዓለም ጦርነት የሠብዓዊነት ትሩፋት

Written by  አቤንኤዘር
Rate this item
(1 Vote)

  ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጋር የተያያዘ፣ ወጣ ያለና ያልተለመደ ግን ደግሞ የብዙ ህፃናትን ህይወት የታደገ ሰብዓዊ አድራጎት። እውነታው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ለታሪኩ ባለቤቶችም ጭምር የተደበቀና ያልተገለፀ ታሪክ፡፡ ታሪኩ ከወቅቱ ወጣት የለንደን ነዋሪ እንግሊዛዊው ኒኮላስ ዊንተን ጋር ይያያዛል፡፡ ወጣቱ የሁለተኛ ዓለም ጦርነት አይቀሬነትን ተረድቶ ወደ ቼኮዝላቪያ መዲና ፕራግ በማምራት፣ 669 አይሁዳውያን ህፃናትን ከተረጋገጠ ሞት የታደገበት የጀግንነት ታሪክ፡፡  
እንደ ግሪጎሪያኑ የዘመን ስሌት በ1938 መባቻ፣ መላው አውሮፓ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጠርዝ ላይ የቆመበትና የባሩድ ጠረን አፍንጫን ሊሸነቁጥ እየጋመ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ በአይሁዳውያን ላይ የሚደርሰው ማዋከብና ግፍ እየተባባሰ የሄደበትም ወቅት ነበር፡፡ በአራቱ ሃያላን ሃገሮች የተደረሰው የሙኒክ ስምምነት (ጀርመን፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን)፤ ሱዲትንላንድ ተብላ የምትጠራውን የቼክ ግዛት ጀርመን በወረራ እንድትይዝ ፈቃድ የሚሰጥ ነበር፡፡ በዚች የቼክ ግዛት ሱዲትንላንድ የዘር ሃረጋቸው ከጀርመን የሚመዘዝ ቁጥራቸው እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በወቅቱ ይኖሩባት ነበር፡፡ ይህ ስምምነት የጀርመኑ የወቅቱ መሪ አዶልፍ ሂትለር ወደ ቼክ እንዲዘምት መንገድ የጠረገና ለሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጅማሮ ፊሽካን ያበሰረ ነበር፡፡
በለንደን ኒኮላስ ዊንተን ነገሮችን በጥሞና እየተከታተለ ነው፡፡ ከሱዲትንላንድ ወደ ፕራግ በሽሽት የገቡ አይሁዳውያን ስደተኞች በስጋትና በአስፈሪ የማነቆ ቀለበት ውስጥ የገቡበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ጊዜ ነው ወጣቱ ኒኮላስ ዊንተን ወደ ቼኮዝሎቫኪያ ያቀናው፡፡ የጉዞው ዋነኛ ዓላማም እነዚህን በአስፈሪ ማነቆ ቀለበት ውስጥ የገቡ ሰዎችን ሊረዳ የሚችልበትን መንገድ ለመቃኘት ነበር፡፡ አዎ! በእርግጥም ነብሳቸውን የታደገላቸው፣ ከሞት ያተረፋቸው፣ ህይወታቸውን ያስቀጠለላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ኒኮላስ ይሄን ስኬቱን ለ50 ዓመታት ያህል ደብቆ ለማንም ሳይነግር ከራሱ ጋር አቆይቶታል፡፡ የታደጋቸው ህፃናትም ለግማሽ ክፍለዘመን ህይወታቸውን ማን እንዳተረፈላቸው አያውቁም ነበር፡፡ ነገሮች እንዴት እንደተከወኑም የሚያውቁት ታሪክ አልነበረም፡፡
እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ኦክቶበር 1/1938 የጀርመን ናዚ ወታደሮች ወደ ቼኮዝሎቫኪያ ሱዲትንላንድ ዘመቱ፡፡ የቼኮዝሎቫኪያ ዋና መዲና ፕራግ የሚያደርጉትን በማያውቁና በደነገጡ፣ ነፍሳቸውን ለማትረፍ በሚሯሯጡ የቼክ አይሁዳውያን ስደተኞች ተጥለቀለቀች፡፡ በጣም የታደሉ ጥቂቶች ቀድመው ልጆቻቸውን ከቼክ ማስወጣት ችለዋል፡፡ ወደ ፕራግ የመጡትና የናዚ ጦር ወዳሉበት ከተማም መጥቶ እንደሚጨርሳቸው እርግጠኛ የነበሩ ወላጆች ራሳቸውን ማትረፍ ባይችሉም፣ ለልጆቻቸው የነገን ህይወት ተመኝተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ታዲያ በወቅቱ በጥቁርና ነጭ ፎቶግራፍ የፕራግን ምስቅልቅል እያነሳ ለታሪክ የሚያስቀምጠው የፎቶግራፍ ባለሙያ፣ አንድ ነገር በአጋጣሚ አንስቶ አስቀምጧል፡፡ ከፕራግ ጎዳናዎች በአንዱ የ29 ዓመት ወጣት ለንደናዊ፣ አንድ ጥቁር የሹራብ ኮፍያ ያደረገ ህፃንን ታቅፎ የሚያሳይ ፎቶግራፍ። ያ የለንደን ወጣት ኒኮላስ ዊንተን ይባላል፡፡
ኒኮላስ "60 ሚኒት" ከተባለው ቻናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “የማውቀውና የማስታውሰው ነገር ቢኖር ያገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ፣ ከዛ ለቀው መውጣት ያልቻሉና፣ ቢያንስ ልጆቻቸውን ለማትረፍ የሚመኙ እንደነበሩ ነው።” ብለዋል፡፡
ኒኮላስ ዊንተን ይህን ታሪክ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በህይወት ኖረው ከመሰከሩ ጥቂት ዕድለኞች አንዱ ናቸው፡፡ ወጣቱ ኒኮላስ ከህይወት መርሁ አንዱ፤ የማይቻሉና የማይደፈሩ ነገሮችን ማድረግ የሚል ነበር፡፡ በለንደን ውጤታማ ታዋቂ የአክሲዮን ሽያጭ ባለሙያው ኒኮላስ ዊንተን፤ መልካምና የተደላደለ ኑሮ ያለው ከመሆኑም ባለፈ፣ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የማድረግ ተሰጥኦ የነበረው ብርቱና ቀልጣፋ ወጣት ነበር፡፡
የያኔው ዋና የመረጃ ምንጭ የነበሩት ጋዜጦች ስለ ጀርመን ወረራ፣ ስለ አይሁዳዊያኑ ስደት፣ ቀጣይ ጊዜያት ይዘውት ስለሚመጡት መከራ የሚያቀርቡት ዘገባ ኒኮላስን በፅኑ ያስጨንቀው ነበር፡፡ ለእነዚህ ስደተኞች አብዛኞቹ የዓለም መውጫ በሮች ተዘግተዋል፡፡ ቀዝቃዛና በረዶማ የአየር ጠባይና የተፋፈገ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሁኔታ ከ150,000  በላይ የሆኑ ስደተኞችን ህይወት እንደፈተነው፣ በተለይ ህፃናቱ የከፋ መከራ ላይ መሆናቸውን ኒኮላስ በቦታው ተገኝቶ ተመለከተ፡፡ ምንም እንኳን የህፃናቱ ተጋላጭነት ይበልጡን የከፋ ቢሆንም ከህፃናቱ ወላጆች ውጪ ለጉዳዩ አፅንዖት የሰጠው አካል አልነበረም፤ ወጣቱ ኒኮላስ በቦታው ተገኝቶ ነገሮችን እስከገመገመበት ጊዜ ድረስ።
ዊንተን ወደ ፕራግ ባቀናበት ወቅት በጥንታዊቷ ፕራግ ባለ አንድ ሆቴል ውስጥ አነስተኛ ፅ/ቤት ከፈተ፡፡ ቀጥሎም የተወሰኑ ስደተኞችን ቋሚ ሥጋት ወደሌለባቸው ሌሎች አገራት የሚያዘዋውርበት ሁኔታዎችን ማጥናት ጀመረ። በተለየ ሁኔታ ደግሞ ህፃናት ላይ ትኩረቱን አደረገ። ከፍተኛ የሆነ ቢሮክራሲያዊ ውጣውረድና አካላዊ አደጋ የነበረውን ይህን ተልዕኮ፣ ያለምንም ልምድ ለመፈፀም ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ያቀናው ወጣቱና ልበሙሉው የሰብዓዊነት ልዕልና የተጎናፀፈው ኒኮላስ፤ ነገሮች ቀላል እንደማይሆኑለት ማንም ሊገምተው የሚችለው ነው፡፡
ኒኮላስ አዲስ በከፈተው ጽ/ቤት ያቋቋመው ድርጅት ዋነኛ ዓላማ የተቻለውን ያህል ብዛት ያላቸውን ህፃናትን በከፍተኛ ፍጥነት ከሃገሪቱ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር ነበር። ቁጥራቸው የበዛ ወላጆች ወደ እርሱ ይጎርፋሉ፡፡ ሁሉንም ለማግኘት ጊዜው በቂ አይደለም፡፡ ጠዋት ማልዶ ይነሳል፣ ማታም ዘግይቶ ወደ መኝታው ይሄዳል። ሁሉም ወላጆች አንድ ጥያቄን ግን ደግመው ደጋግመው ይጠይቁታል፡- “እባክህ የኔን ልጅ ውሰድልኝ፤ አትርፍልኝ” በማለት፡፡
የስደት ሂደቱን እያቀላጠፈ ባለበት ወቅት ወደ ትውልድ ቀዬው ለንደን የበርካታ ህጻናትን ስም ዝርዝር ይዞ በመመለስ የለንደንን ጎምቱ ባለሥልጣናት ስለሁኔታው አስረድቶ፣ ጉዳዩን በአንክሮ እንዲያዩት ለማድረግ ይጥር ነበር። በለንደንም በተመሳሳይ በስደተኛ ህፃናት ላይ ከሚሠራ ተቋም ጋር ግንኙነት ፈጠረ፤ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማቀላጠፍ እንዲረዳው። ህጻናቱን ከቼኮዝሎቫኪያ የሚያወጣ ጽ/ቤት በለንደንም አቋቁሞ እናቱን ዋና የበጎ አድራጎት ስራ አስተባባሪ በማድረግ ሥራውን ያቀላጥፍ ያዘ፡፡
በአንድ በኩል በወቅቱ ከነበረው የብሪታንያ አስቸጋሪ የመንግሥት ጽ/ቤቶች ቢሮክራሲ ጋር እየተጋፈጠ፣ ጎን ለጎን የአሜሪካኖችን ቆንፅላ ሃላፊዎች በማግኘት ለማግባባት ቢጥርም ጉዳዩን ከቁብ ሳይቆጥሩለት ቀሩ፡፡ በዚህም ግን ተስፋ አልቆረጠም፡፡ ለአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት፣ ስደተኛ ህፃናትን እንዲቀበሉ በደብዳቤ ተማፀነ፡፡ ነገር ግን በለንደን የነበሩት የቆንስላ ሰራተኞች፣ ያንን ማድረግ እንደማይችሉ ቁርጥ አድርገው ነገሩት፡፡
ሃገሩ ብሪታንያም ከረጅምና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ የዊንተንን ጥያቄ በቅድመ ሁኔታ ተቀበለችው፡፡ ይህም ህፃናቱን ወደ እንግሊዝ እንዲያመጣ፣ ነገር ግን ከመምጣታቸው በፊት ለእያንዳንዳቸው በጉዲፈቻ የሚያሳድጋቸው ወላጅ ቀድሞ እንዲያገኝላቸው። ዊንተን ጊዜ አላጠፋም፤ የህፃናቱን ፎቶ በየአካባቢው ልብ ከሚነካ መልዕክት ጋር ለጠፈ።
የጉዲፈቻ ወላጆችን ለማግኘት ባይቸገርም፣ የብሪታንያ መንግሥት የጉዞ ሰነዶችን በማጓተቱ ከጊዜ ጋር እየተዋጋ ላለው ዊንተን ሌላ ፈተና ጋረጠበት፡፡ አማራጭ ያልነበረው ዊንተን፤ ፎርጅድ የጉዞ ሰነዶችን ለመጠቀም ተገደደ፡፡ ይሄ ከጊዜና ከህልውና ጋር እልህ ለተጋባው ወጣት፣ ብቸኛ ያልተቀደሰ፣ ግን የተባረከ መፍትሄ ነበር። በዚህም የመጀመሪያዎቹን 20 ህፃናት ማርች 14/1939 ማውጣት ተቻለ፡፡ በቀጣይ ቀን የጀርመን ጦር የቼኮዝሎቫኪያን ዋና ከተማ ፕራግን ተቆጣጠረ፡፡ አዶልፍ ሂትለር በክፍት መኪና በፕራግ ከተማ እያለፉ ሰላምታ ሰጡ፡፡
ሄጎ ማይዜል የተባሉ በወቅቱ የ10 ዓመት ታዳጊ የነበሩ የለንደን ነዋሪ፣ ያቺን ቀን እንደ ትላንት ነው የሚያስታውሷት፡፡ ሂትለር በክፍት መኪና ቆመው ሰላምታ እየሰጡ ሲያልፉ ተመልክተዋቸዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ አስገድዶ የጉልበት ሥራ ማሰራት፣ ማሰቃየት የመሳሰሉት ድርጊቶች በቼኮዝሎቫኪያ አይሁዳውያን ላይ መፈፀም ጀመረ፡፡
ነገር ግን በእነዚህ ጭንቅ ሰዓቶች መካከል ያልተረጋጋው የናዚው አስተዳደር፣ የዊንተን የማደጎ ህፃናትን የያዘ ባቡር ከቼክ በልዩ ፈቃድ እንዲወጣ ፈቀደ፡፡ እ.ኤ.አ በ1939 ላይ በነበሩት የአውሮፓ የበልግና ፀደይ ወቅቶች፣ በሰባት የባቡር ምልልሶች ከ600 በላይ ህፃናትን ወደ ሆላንድ ማድረስ ተቻለ፤ ከዛም ወደ ታላቋ ብሪታንያ፡፡ ስምንተኛውና 250 ተጨማሪ ህፃናትን የያዘው ባቡር በሴፕቴምበር 1 ለመንቀሳቀስ መርሃ ግብር ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ያን ቀን ጦርነቱ በመጀመሩ በባቡሩ ተሳፍረው የነበሩት ህፃናትም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ በባለሥልጣናቱ ተነግሯቸው እዛው ቀሩ፤ ክፉ አጋጣሚ!
በቼኮዝሎቫኪያ የቀሩት ሁሉም ህፃናት እንዳለቁ ይታመናል፡፡ ከወረራው ሦስት ዓመት በኋላ ናዚ የተገበረው የመጨረሻው መፍትሄ (Final Solution) ተብሎ የሚጠራው ዘግናኝ ዘመቻ፣ ሁሉንም የአውሮፓ አይሁዳውያን መግደል የሚል ነበር፡፡ በዛም ዘመቻ በቼክ የነበሩ 90,000 የሚደርሱ የቼክ አይሁዳውያን፣ በአሽዊት የመግደያ ካምፕ ህይወታቸው እንዲያልፍ ሆነ፡፡ ከዛ ውስጥም ኒኮላስ የታደጋቸው ህፃናት ወላጆች እንዲሁም ሊያድናቸው የነበሩ 250 ተጨማሪ ህፃናት (በጦርነት መቀስቀስ መጓዝ ያልቻሉት) ሙሉ ለሙሉ እንዳለቁ ይታመናል።
ወደ ታላቋ ብሪታንያ ያቀኑት ህፃናት በጉዟቸው ጅማሮ ለሦስት ወይም አራት ወራት በዓል (Holiday) ለማክበር እንደሆነ በወላጆቻቸውና በዊንተን ሰዎች ስለተነገራቸው፣ የተፈጠረውንና ሊፈጠር የነበረውን ነገር የሚያውቁት ሊያተርፏቸው የወደዱት ወላጆቻቸውና ኒኮላስ ዊንተን ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ ህፃናት የእንግሊዝ ጉዟቸው ሚስጥር ለብዙ ዘመናት እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ኖረዋል፣ አንዳንዶችም ምላሽ ሳያገኙ ቀድመው አልፈዋል፡፡ ብዙዎቹ በጨቅላ አዕምሮአቸው የተቀረጸባቸውን የወላጆቻቸውን ፊት እያስታወሱ ሲያለቅሱ ኖረዋል፣ የተዋቸው መስሏቸውም ወቅሰዋቸዋል፡፡ የብዙ አስርት ዓመታት ሚስጥር፡፡
የተሰውት 77,300 የቼኮዝሎቫኪያ አይሁዳውያን ስም በፒንከስ ሲናጎጉዉ  መታሰቢያ ሃውልት ግድግዳ ላይ ሰፍሯል፡፡ በዛም ቀድመን የጠቀስነው የሂጎ ማይዜል የስጋ ወላጆች ስምም ሰፍሯል፡፡
በቀጠለው የጦርነት ወቅት ኒኮላስ የቀይ መስቀል በጎ ፈቃደኛ የአንቡላንስ ሹፌር ሆነው አገልግለዋል። ከዛም የሮያል ኤር ፎርስ አብራሪ ፓይለት፡፡ ኋላም አግብተዉ ወልደው የተደላደለ ኑሮን መርተዋል፡፡ ነገር ግን ለ50 አመት የሰሩትን የበጎ አድራጎት ሠብዓዊ ምግባር ለማንም አልተናገሩም፡፡ “ለምን ሚስጥር አደረጉት?” ተብለው ሲጠየቁ፤ “እኔ ምስጢር አላደረኩትም፤ ግን ለማንም ተናግሬው አላውቅም” ብለዋል፤ በ104ኛ ዓመታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽ፡፡

ነገሮች እንዴት ገሃድ ወጡ?
በ1988 ቢቢሲ ስለ ዊንተን ታሪክ መረጃ አገኘ፡፡ ከዛም አንድ ሰዎች የተሰባሰቡበት ዝግጅት አካል እንዲሆኑ ጋበዛቸው፤ ነገር ግን 80 ዓመት የተጠጋቸው ዊንተን፣ በአዳራሹ የታደሙት ሌሎች አዛውንቶች የዛሬ 50 ዓመት እርሳቸው ህይወታቸውን የታደጉላቸው ህፃናት እንደነበሩ ፈፅሞ አያውቁም፡፡
ከዛም ጋዜጠኛዋ እድምተኞቹን አንድ ጥያቄ ጠየቀች፤ “እዚህ ካላችሁ እድምተኞች መሃል  የኒኮላስ ዊንተን የህይወት ዘመን ዕዳ ያለበት ሰው ይኖር ይሆን? ካለ እባካችሁ ተነሱ”፡፡ አዛውንቱ ዊንተን በፊት ለፊት ረድፍ ነበር የተቀመጡት። በአዳራሹ ዊንተንን ከበው የነበሩ እስከ ግማሽ ረድፍ የሚደርሱ አዛውንቶች ብድግ ብድግ አሉ፡፡
ጋዜጠኛዋ ደግማ ጠየቀች፤ “አቶ ዊንተን እባክዎን አንድ ጊዜ ዞር ብለው ይመልከቱልኝ” ዊንተን ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ወደ ኋላ ተመለከቱ፡፡
ጋዜጠኛዋ ቀጠለች፤ “እነዚህን ሰዎች ሁሉ ወክዬ ከፍ ያለ ምስጋናን አቀርብልዎታለሁ” አለች፡፡
ከፍተኛ ጭብጨባ ተከተለ፡፡ አዛውንቱን ሳግ እየተናነቃቸው እንባቸው ፈሰሰ፡፡ በህይወቴ በጣም ስሜታዊ የሆንኩበት ወቅት ነበር ይላሉ፤ ሁኔታውን ሲያስታውሱት። የተሰበሰቡት ሰዎችም ለመጀመሪያ ጊዜ በህይወት የመቆየታቸው ሚስጥር የነበሩትን ሰው በአካል ተመለከቱ፣ አብዛኞቹም በዛን ወቅት ልጅና የልጅ ልጅ ለማየት የታደሉ ነበሩ፡፡ በእርግጥም የኒኮላስ ዊንተን ድፍረት፣ ቅልጥፍና እና በከፍተኛ ሰብዓዊ ርህራሄ የተሞላ አድራጎት ባይኖር፣ በዛ አዳራሽ የነበሩት ሰዎች በሙሉ ከ50 አመት በፊት ህይወታቸው አብቅቶ ነበር፡፡
ዊንተን ከዛ በኋላ በነበሩት አመታት የአዕምሮ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ሲረዱ፣ ለአዛውንቶች ቤት ሲገነቡም ኖረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 በአገረ እንግሊዝ በጣም ለተከበሩ ሰዎች የሚሰጠውን የ“ሰር” ማዕረግ ከእንግሊዝ ንግሥት እጅ አግኝተው፣ “ሰር ኒኮላስ ዊንተን” ተብለዋል። በቼክ ሪፐብሊክ "ብሔራዊ ጀግና" በሚል ይታወቃሉ፡፡
ሰር ኒኮላስ ዊንተን ጁላይ 1, 2015 ባደረባቸው ህመም በእንግሊዝ ዌክሰሃም ፓርክ ሆስፒታል፣ በተወለዱ በ106 አመታቸው አርፈዋል፡፡
Read 10738 times