Saturday, 07 May 2022 14:01

የርዕዮተ ዓለም ሙግት በኢዜማ እልፍኝ

Written by  ልጅ አቤኑ (አቤንኤዘር ጀምበሩ)
Rate this item
(0 votes)

በዕለተ ረቡዕ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የእጅ ስልኬ ላይ የፌስቡክን መተግበሪያ ከፍቼ መረጃዎችን ስበረብር፣ አንድ ጉዳይ ቀልቤን ሳበው፡፡ በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ በቀጣይ ቅዳሜ የክርክር መድረክ እንደተዘጋጀ በኦፊሺያል ፌስቡክ ገጻቸው ላይ አነበብኩ። የክርክሩ ርዕስ “ማህበራዊ ፍትህ ወይስ ሊበራል ዲሞክራሲ” የሚል ሲሆን፤ በኢዜማ ጽ/ቤት በመስፍን ወልደማርያም አዳራሽ በሚካሄደው የክርክር መድረክ ላይ ለመታደም የሚፈልግ ሰው በተቀመጠው ስልክ ቁጥር ደውሎ መመዝገብ ይችላል፤ ይላል ማስታወቂያው፡፡ ጊዜ አላጠፋሁም፤ በተጠቀሰው ስልክ ደውዬ ተመዘገብኩ፡፡
በዕለቱ ባጋጠመኝ የትራንስፖርት ችግርና የማላውቀውን የመስፍን ወልደማርያም አዳራሽ ሳፈላልግ ውይይቱ ከሚጀምርበት ሰዓት አስራ አምስት ደቂቃ ዘግይቼ ደረስኩ - 9፡45 ደቂቃ ላይ። በአዳራሹ ቁጥራቸው 30 የሚጠጋ እድምተኞች፣ አንድ አወያይና ሁለት ተከራካሪዎች ተቀምጠዋል። አወያዩ ተከራካሪዎችን እያስተዋወቁ ነበር፡፡ እስቲ የማውቀው ሰው ካለ ብዬ ዞር ዞር ስል፣ አቶ የሸዋስ አሰፋን ከፊት፣ አቶ ናትናኤል ዘለቀንና አቶ አንዷለም አራጌን ከወደ ኋላ ተመለከትኩ፡፡ ምናልባት እኔ የማውቃቸው የኢዜማ የፖለቲካ አመራሮች እነዛ ስለነበሩ ነው እንጂ ሌሎችም ተፅእኖ ፈጣሪ የኢዜማ ፖለቲከኞች በአዳራሹ እንደነበሩ ጥርጥር የለውም፡፡
በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የብሔር ተቆርቋሪ ነን በሚሉና ያለ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንፈርሳለን በሚሉ ሃይሎች ተቃርኖ የተወጠረ ፖለቲካ በገነነበት፣ ያም ሳይበቃ የእርስ በእርስ ግጭትና ጥላቻ በሚንጣት ሃገር ውስጥ ስለ ርዕዮተ-ዓለም መከራከር ቅንጦት ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ክፍት ሆኖ፣ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ ከሚለው አባዜ ተላቆ መወያየት፣ ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደ መጓዝ ነው። ይህን ዓይነት የውይይትና የክርክር መድረክ የመንግሥት ስልጣንን የያዘው ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ እንደ ኦፌኮ፣ አብን፣ ባልደራስና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊከተሉት የሚገባ መልካም ጅማሮ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ክርክሩ በአቶ ቸርነት ሰዒድ (የማህበራዊ ፍትህ አቀንቃኝ) እና በአቶ ያዕቆብ በቀለ (የሊበራል ዴሞክራሲ) አቀንቃኝ መካከል የተደረገ ነበር።
በአቶ ቸርነት ቸርነት ሰዒድ  የተነሱ አንኳር የማህበራዊ ፍትህ ርዕዮተ ዓለም መከራከሪያ ነጥቦች፡-
የርዕዮተ ዓለሙ ምሰሶ የሆኑት ነጥቦች ተደራሽነት፣ እኩልነት (በህግ ፊትና በሀብት ክፍፍል)፣ የዜጎች ተሳትፎ፤
ማህበራዊ ፍትህ የኢኮኖሚ ገደብ ሳይኖርብን ማህበራዊ እሴቶቻችንን እንድንጠብቅ ያደርገናል፤
ሁሉም ሰው መክፈል በሚችለው  ተመጣጣኝ ዋጋ ምርትና ግልጋሎትን ያገኛል፤
የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የግለሰብ ቢሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን መማር አይችሉም ነበር፤  
ኢትዮጵያ ምን አይነት ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና እንደምትከተል ማወቅ አሁን ላይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ስታገኝ ሊበራል ዲሞክራት ትሆናለች፡፡ “የሴፍቲ ኔት” እርዳታ ሲመጣ የማህበራዊ ፍትህ አቀንቃኝ ትሆናለች፡፡ የመደመር ፍልስፍናም ግልፅ አይደለም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የተፃፈው የመደመር መፅሐፍ መጨረሻ ላይ ዝርዝሩን ወደፊት በሌላ መንገድ እንደሚገልፅ ስለሚያስቀምጥ የጠራ መንገድ የለውም፤
አሁን በሀገራችን ላይ ያሉት ውዝግቦች መንግሥት "ይሄ የእከሌ ነው፣ ያኛው የእከሌ ነው" ብሎ በሚያስቀምጠው የተዛባ ትርክት የመጡ ናቸው፤
ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ተመሳሳይ የገንዘብ ኖቶችን በመጠቀም በውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚገጥመንን ተግዳሮት መፍታት ይቻላል፡፡
በአቶ ያዕቆብ በቀለ የተነሱ
መሠረታዊ የሊበራል ዴሞክራሲ የርዕዮተ ዓለም ነጥቦች፡-
ማህበራዊ ፍትህ የሶሻሊዝም ፍልስፍና ድንዛዜ (ያደረ ስካር) ያለቀቀው ነው፤
በሀገራችን የኒኦ ሊብራል እና የሊብራል አስተሳሰቦች ያለጥፋታቸው ተወቃሽ ሆነዋል፤
ግለሰባዊነት፣ መብትና ነፃነት (በህግ የበላይነት የተገደበ)፣ ውስንና የተገደበ ስልጣን ያለው መንግሥት፣ ያልተማከለ አስተዳደርና ነፃ ገበያ ዋና የሊብራል ዲሞክራሲ መገለጫዎች ናቸው፤
ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በሰፈነበት ሀገር ያለንን ምርትና አገልግሎት ከድሆች ቀንሶ ማከፋፈል ተገቢ አይደለም። በማህበራዊ ፍትህ መንግሥት ከሀብታሞች በሀይል የሚሰበስበውን ከፍተኛ ታክስ የሚያከፋፍለው ለድሆች ሳይሆን መካከለኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ነው፤
ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ባለሀብቶች ጥረት ያድርጉ እንጂ ድጎማ አያስፈልግም፤
ደመወዛቸው 5 ሺህ እና 6 ሺህ ብር የሆኑ ሰዎች በመቶ ሚሊዮን ብሮች ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ያ ለሙስና የተጋለጠ ስለሆነ መንግሥት በማህበራዊ ፍትህ አገልግሎቶችን በቁጥጥሩ አድርጎ ከሚቆይ ለግል ባለሀብቶች ቢሰጥ የተሻለ ይሆናል፤ የሚሉ ነጥቦች ከሞላ ጎደል ተነስተዋል፡፡
በመቀጠልም ከውይይቱ ታዳሚዎች አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ዘለቀ፤ ውይይቱ ከሀገሪቱ ወቅታዊ አውድ ጋር የተገናዘበ ቢሆን መልካም እንደነበር ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ የፊውዳል ስርዓት፣ ሶሻሊዝም፣ የአልባንያ አይነት ሶሻሊዝምና ልማታዊ መንግሥት የሚሉ ርዕዮተ አለሞች ማለፋቸውን በማስታወስ፣ አሁን ያለው መንግሥት ምኑም ያለየለት ነው ብለዋል - አንዳንዴ ሊበራል አንዳንዴ ደግሞ በሌላ ርዕዮተ አለም በመንሳፈፍ እዚህም እዛም እንደሚል በመጥቀስ፡፡
 የኢዜማ ሊቀ መንበሩ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በመንግሥት የሚተገበር የፖለቲካ ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና አለ ብለው ለመናገር እንደሚቸገሩ ጠቁመው፤ ተከራካሪዎቹ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ አፅንዖት መስጠታቸውን ተችተዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት ወጣት ፅዮን አንግዳዬ ሲሆኑ በሀገራችን እምብዛም ባልተለመደ መልኩ የክርክሩን ሰዓት ለመቆጣጠር የሄዱበት መንገድ የሚደነቅና ጥሩ ጅማሮ ሆኖ፣ ነገር ግን አከራካሪዋ (moderator) ሰዓት ከመቆጣጠር ባለፈ ለተከራካሪዎቹ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ቢሞግቱ መልካም ነበር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1477 times