Saturday, 23 April 2022 14:29

EC-አፋጣኝ ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 Emergency contraceptive አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ በአንድ የወር አበባ ወቅት በምንም ምክንያት ከሁለት ጊዜ በላይ መወሰድ የለበትም፡፡  
Emergency contraceptive አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ ጥንቃቄ በሌለው መንገድ ወይ ንም በድንገት የወሲብ ግንኙነት ሲፈጸም ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል ሲባል የሚወሰድ መከላከያ ነው፡፡ አፋጣኝ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በተለይም ባላሰቡት ሁኔታ ተገድደው ለሚደፈሩ ሴቶች ወይንም ፈቅደውም ወሲብ ቢፈጽሙም ለእርግዝናው ግን እቅድ ከሌላቸው አለዚያም በግንኙነት ጊዜ የኮንዶም መበጠስ ቢያጋጥማቸው ከፕላን ውጪ እርግዝና እንዳይ ከሰት በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ በኢት ዮጵያ ለብዙ አመታት በሚባል ሁኔታ መንግስትና የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች መከላከያውን በመጠቀም ረገድ በመላ ሀገሪቷ የማስተዋወቅን ፤ተጠቃዎች እራሳቸውን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንዳይወድቁ ለማድረግ የሚያስችሉ መልእክቶችን በተለያዩ መንገዶች ሲያስተላልፉ መቆየ ታቸው እሙን ነው፡፡
European journal of midwifery /Julay 2021/ ላይ እነ ለገሰ አበራ እ.ኤ.አ በ2021 ማብ ቂያ ላይ ባወ ጡት የምርምር ስራ ላይ እንደተገለጸው አፋጣኝ ያልተፈለገ የእርግዝና መከላ ከያ መድሀኒቱ በኢትዮጵያ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሰርቶአል የሚባለው በተወሰነ ደረጃ በከተሞች አካባቢ መድሀኒቱ በሚገኝበት ቦታ ነው ማለት ይቻላል። በሌሎች አካባቢዎች መከላከያው እንደልብ አለመገኘቱ እንዳለ ሆኖ ብዙ ያልተፈለጉ ወይንም ያልታቀዱ እርግዝና ዎች ሴቶቹን ለጤና ጉዳት አልፎ ተርፎም ለህልፈት ሲዳርጋቸው ይታያል፡፡  
በአለም አቀፍ ደረጃ በየቀኑ በግምት 1000 ሴቶች ሊከላከሉት በሚቻል ግን ባልተከላከሉት ያልታቀደ እርግዝና እና ልጅ መውለድ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ በተለይም ወጣቶች እንዲሁም ታዳጊዎች በእድሜ ትልልቅ ከሆኑ ሴቶች በላይ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ የአ ለም የጤና ድርጅት WHO ግምት ያሳያል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት እንዳወጣው መረጃ ጽንስን በማስወረድ ምክንያት በሚፈጠር ውስብስብ የጤና ችግር የተነሳ የሆስፒታል አልጋ ከሚይዙት ሴቶች መካከል ቢያንስ ቢያንስ 33% የሚሆኑት እድሜአቸው ከ20 አመት በታች ያሉ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዙ ወጣቶች በተለይም የኮሌጅ ተማሪዎች በተለያዩ ምንያቶች ለወሲብ ድርጊት የተጋለጡ ናቸው፡፡ እድሜያቸው መድረሱ፤ ከወላጅ እንዲሁም ከአካባቢ ቁጥጥር ነጻ ነን ብለው ስለሚያስቡ በፍቅር መውደቅ እና ካለከልካይ ስሜታቸውን ለማርካት ሲሉ ከጋብቻ በፊት ካለ ምንም ጥንቃቄ ወሲብን ሊፈጽሙ ይችላለሉ፡፡ ወሲብ ከመፈጸማቸውም በፊት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ መከላከያዎችን አስቀድሞ ለመጠቀም ብዙዎች ለዚህ ያላቸው ዝግጁነት አናሳ ስለሚሆን ስሜታቸውን ካለመገደብ ድርጊቱን ይፈ ጽማሉ። ከዚያ በሁዋላ ደግሞ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያውን ለመውሰድ የማያስችሉአቸው ከእውቀት ጀምሮ መከላከያውን በፈለጉበት ቦታ አለማግኘትና የመሳሰሉት ተጨምረው ላልተፈለገ እርግዝና መጋለጣቸው እውን ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት እንዳረጋገጠው በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ እድሜአቸው ከ15-19 የሚደርሱ 16 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገ ረዶች ልጅ የሚወልዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በግምት 95% የሚሆኑት እና 11% የሚሆኑት አጠቃላይ ውልደቶች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚከሰቱ ናቸው፡፡
የእነ ለገሰ አበራ ጥናት እንደሚያሳየው አፋጣኝ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አጠቃቀም በተለይም በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ባሉ ተማሪዎች ዘንድ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የተቆጠረው ይበልጥ ስለ መድሀኒቱ እውቀት አለመኖር ነው፡፡ እውቀቱ በሌለበት ሁኔታ መከላከያውን ለመጠቀም ቢሞክሩ እንኩዋን በትክክለኛው ጊዜ፤ በተገቢው ሁኔታ እንዲሁም ምርጫን የማስተካከል ሁኔታ ያልተሟላ ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል ሴቶች ለመከላከያው ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ አፋጣኝ የእርግዝና መከላያውን እንዳይጠቀሙ ያደርጋቸዋል። ባጠቃላይም የእውቀት፤ ለመድሀኒቱ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ እና መከላከያን የመውሰድ ልምድ ማነስ በኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ለችግር ከሚዳርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ናቸው። ይህ ውጤት እንደማሳያ የተወሰደው ጥናቱ ከተደረገበት ከምስራቅ ኢትዮጵያ ከድሬደዋ ከተማ ነው፡፡
አፋጣኝ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያን አጠቃቀም በሚመለከት ከአሁን ቀደም በጋንዲ ሆስፒታል በመገኘት ሜዲካል ዳይሬክተሩን ዶ/ር ደረጀ አለማየሁን አነጋግረን ከሰጡን መረጃ መካከል የሚከተለውን ልናስነብባቸሁ ወደድን። ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
Emergency contraceptive አንዲት ሴት ተገድዳም ይሁን ፈቅዳ የግብረስጋ ግንኙነት በማድረግዋ ምክንያት ያልተፈለገ እርግዝና እንዲያጋጥማት እንደማትፈልግ ስትገልጽ የምትወስደው እንጂ እንደመደበኛ የእርዝና መቆጣጠሪያ የምትወስደው አይደለም፡፡ የግብረስጋ ግንኙነቱ ከተፈጸመ ከ72 ሰአት በላይ ከሆነ ግን መከላከያው አቅሙ ደካማ ስለሚሆን እና ምንም ጥቅም ስለማይሰጥ እርግዝናውን ይከላከላል በሚል መተማመን አይቻልም፡፡
አንዲት ሴት በግዳጅም ይሁን በፍላጎት ወሲብ ብትፈጽም ወይንም የኮንዶም መቀደድ ችግር ቢያጋጥማት ይህንን ግንኙነት ከማድረግዋ በፊት አስቀድማ እርግዝና ላይ ከሆነች መከላከያውን መውሰድ ምንም ጥቅም የለውም ዶ/ር ደረጀ እንዳሉት፡፡ ለምሳሌም የወር አበባዋን ካየች ከሁለት ወር በላይ ከሆናት አስቀድሞ የእርግዝና ምርመራ ሳያደርጉ አፋጣኝ መከላከያውን መውሰድ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ነገር ግን የወርአበባዋን ካየች ከአራት ሳምንት በላይ ካልሆናት መከላከያውን መውሰድ ትችላለች፡፡
ዶ/ር ደረጀ አበክረው እንደገለጹት ይህ Emergency contraceptive የአፋጣኝ ጊዜ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በምንም ምክንያት እንደመደበኛው የወሊድ መከላከያ የሚወሰድ መደሀኒት አይደለም፡፡ ይህ መከላከያ የተሰራው የግብረስጋ ግንኙነት ከመደረጉ በፊት እንዲወሰድ ሳይሆን ግንኙነት በተደረገ 72 ሰአታት ውስጥ እንዲወሰድ እና እርግዝና ሊፈጠር ካሰበ እንዲያጨናግፍ ነው፡፡ ይህ መከላከያ የሆርሞን መጠኑ ከመደበኛዎቹ መከላከያዎች የሚጨምር እና እንደመደበኛዎቹ መከላከያዎች ጥንካሬ ስለሌለው እርግዝናን አስቀድሞ የመከላከል አቅሙ ደካማ ነው፡፡ ለምሳሌም ሴቶች ግንኙነት ከፈጸሙ ከተጠቀሰው ሰአት ወይንም ከቀናት በሁዋላ መከላከያውን ቢወስዱ ከ20-30% ያህል ያላቸውን የማርገዝ እድል አይሸፍንም፡፡ ዶ/ር ደረጀ እንደገለጹት ይህ መከላከያ እርግዝናን የመከላከል አቅሙ ከ70-80% አያልፍም። መደበኛዎቹ የእርግዝና መከላከያዎች ግን የመከላከል አቅማቸው እስከ 99.5% ስለሚደርስ አስተማማኝ ናቸው፡፡ አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያው ግን ግንኙነቱ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ በተወሰኑ ሰአታት ወይንም ቀናት ውስጥ የሚወሰድ ቢሆንም ከ80% በላይ ግን እርግዝናን አይከላከልም፡፡
Emergency contraceptive አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ በትክክል ካልተወሰደ የሚያስከት ላቸው የጤና ችግሮች አሉ ብለዋል ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ፡፡
አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ Emergency contraceptive በትክክለኛው መንገድና በተገቢው ሁኔታ ካልተወሰደ፡-
የወር አበባ መዛባትን ሊያስከትል ይችላል። የወር አበባ ከተዛባ የእርግዝናን ሁኔታ መከታተል ያስቸግራል፡፡
መከላከያው የሆርሞን መጠኑ ከፍተኛ ስለሆነ ማስመለስ፤ ማቅለሽለሸና ቁርጠት ሊኖረው ይችላል፡፡  
በማህጸን ላይ እጢ ቢኖር በመድሀኒቱ ምክንያት ሊያድግ ይችላል፡፡
መድሀኒቱን የምትወስድ ሴት አልፎ አልፎ የሚፈስ ደም ሊኖራት ይችላል፡፡
በጡት ላይ የሚከሰት ችግርን ሊያባብስ ይችላል፡፡
መከላከያውን በተደጋጋሚ የምትወስድ ሴት ሲጋራ የምታጤስ ሴት ከሆነች፤ ቫሪኮስ ያለባት ከሆነች፤ እንዲሁም የደም ግፊትዋን ሊያባብሰው ይችላል፡፡
ዶ/ር ደረጀ በስተመጨረሻው እንደመከሩት አንዲት ሴት Emergency contraceptive አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያን በአንድ የወር አበባ ወቅት በምንም ምክንያት ከሁለት ጊዜ በላይ መውሰድ የለባትም፡፡  
የምናጠቃልለው European journal of midwifery ላይ ጥናታቸወን ያቀረቡት እነለገሰ አበራ ጥናቱን የደመደሙበትን በማስታወስ ይሆናል፡፡ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ በመፈጸም ረገድ ወጣት ሴቶች በተለይም በኮሌጅ ትምህርት ላይ ያሉት ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ገና ወጣቶች በመሆናቸው ወሲብ የመፈጸም ልምድ ስለሌላቸው፤ ግንኙነቱን ጥንቃቄ በተደረገበት መንገድ መፈጸምን አለማወቃቸው፤ ወይም ቀደም ሲል የተለያዩ መከላከያዎችን መጠቀም ያልጀመሩ ...ወዘተ Emergency contraceptive አፋጣኝ መከላከያውን በመጠቀም በኩል ዝቅተኛ ፍላጎትም አፈጻጸምም ይታይባቸዋል። ስለዚህ ወጣቶች በተገቢው መንገድ እውቀቱ እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

Read 11253 times