Saturday, 16 April 2022 14:26

ጮሃ የማታውቅ ወፍ አፏን የከፈተች እለት “እለቁ! እለቁ!” ትላለች!

Written by 
Rate this item
(4 votes)


           ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በሸዋም፤ በጎጃምም፤ በጎንደርም፤ በትግራይም የታወቀ ሊቅ አዋቂ ነው የተባለ ባለቅኔ፣ ዙፋን ችሎት ተከሶ ይቀርባል።
ከሳሹ ሰው ደግሞ ምንም እውቀት የሌለው፤ አዋቂ እያሳደደ በነገር የሚወጋ፣ ሆኖም ሹማምንቱ ሁሉ የሚፈሩት ሰው ነበር። ነገር- መጎንጎን ይችልበታል የሚባል ሰው ሥለሆነ ነው መፍራታቸው። ከሁሉም በላይ ግን አብዛኛውን ጊዜ “ለንጉሱ ቀረቤታ አለው፤ ንጉሱ ይሰሙታል” ሥለሚባል ነው። ንጉሱ፤ “እኔን ለማገዝ ብሎ ነው” በማለት ብዙ ጊዜ ያልፉታል።
አንድ ቀን እንደተለመደው ያ ነገር-ሠሪ፣ ንጉሡ ዘንድ ያን ባለቅኔ ክሥ ይዞበት ይቀርባል፡፡
ንጉሡ ወደ ነገር-ሠሪው ዞረው፤ “እሺ ክሥህ ምንድን ነው?”
ነገር-ሠሪ - “ንጉሥ  ሆይ፤ አንድ ቦታ ተቀምጦ ሲያንጎራጉር ሰምቼዋለሁ”
ንጉሥ- “ምን እያለ ሲያንጎራጉር ሰማህ?”
ነገር-ሠሪ “ንጉሥ  ሆይ !
“ኧረ ሰው አለቀ፤ ሰው አለቀ በሏት
እሷ ለታመመ፣ ለሞተም ግድ የላት!” እያለ ሲያንጎራጉር ሰምቼዋለሁ።
ንጉሥ -”ተከሳሽ ምን  ትላለህ? የተባለውን ብለሀል?”
ተከሳሽ -”አዎን ንጉሥ ሆይ!”
ንጉሥ  -”ከሳሽ፤ የክሥህ ጭብጥ ምንድን ነው?”
ነገር-ሠሪ - “በአገር አማን፣ በእርሥዎ ግዛት እልቂት አለ እያለ ሲያንጎራጉር በጆሮዬ ሰምቼዋለሁ።”
ንጉሥ  -”ተከሳሽ ምላሽህ ምንድን ነው?”
ተከሳሽ- “ንጉሥ  ሆይ ራሱ መልሶታል እኮ!”
ንጉሥ -  “እንዴት?”
ተከሳሽ- “ሲያንጎራጉር” አለዎት እኮ! በእርሶ ዘመን “አታንጎራጉሩ” የሚል አዋጅ ወጥቷል እንዴ? እርሥዎ በህይወት ቆመው እንዲህ ይደረጋል?”
ንጉሥ  - “አውቄዋለሁ! ይሄ ቀጣፊ ነገር-ሠሪ፣ ሊያሳስተኝ ነበር። ና አንተ አጋፋሪ! ይህን ነገር-ሠሪ ቅጣና መፈፀሙን አሳውቀኝ!”
ነገር-ሠሪው ተቀጣ። ግን ክሥ ይዞ መምጣቱን አልተወም። ሌላ ቀን ደግሞ ፤ዙፋን ችሎት ቀርቦ፤
“ንጉሥ  ሆይ ፤ያ ባለቅኔ እንዲህ ሲል ተሰምቷል፡-
“ኧረ ምን ተሻለን?
ማን ይፍረድልን?
እጅ ሥለሌለን ሳንሾም ቀረን!” ሲል ከሰሰ።
ንጉሡም ከሳሽ ተከሳሽን አሥጠርተው፤ በመጀመሪያ ነገር-ሠሪውን፤
“እሺ ጭብጥህ ምንድን ነው?” አሉት
ነገር -ሠሪውም- “ሁሉም የንጉሥ  ባለሟሎች የተሾሙት ብር፤ ጉቦ እየሰጡ፤ መታያ እያቀረቡ ነው፤ ሊልና እርስዎን ሊያሳጣ ነው” ሲል መለሰ።
ንጉሡም ወደ ተከሳሹ ዞረው፤ “አንተሥ  የተባለውን ብለሀል?”
ተከሳሽ -”አዎን ንጉሥ  ሆይ!”
ንጉሥ -  “አብራራልና?”
ተከሳሽ - “በዙሪያዎ ብዙ አጨብጫቢ ነው የተሰበሰበው። ሁሉም እሺ ባይ፤ ሁሉም ጊዜያዊ ሹመት ፈላጊዎች፤ ሁሉም ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው! ማለቴ ነው”
ንጉሥ  - “እድሜ የለህም እንጂ ያሳድግህ!” አሉና መረቁት ይባላል።
***     ***    ***
አገራችን ኢትዮጵያ፤ “ከአሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ” እስከ “ዳቦ በሙዝ ብሉ” ፖለቲካዊ ኢኮኖሚዋን ስታስተናግድ የኖረች አገር ናት። እንደ ፈረንሳዊቷ ንግሥት እንደ ሜሪ አንቷኔት፤ “ህዝቡ ምን ሆኖ ነው የሚጮኸው?” ብላ ሥትጠይቅ፤ “ዳቦ አጣን!” እያሉ ነው ሥትባል፤ “ታድያ ለምን ኬክ አይበሉም?!” አለች እንደተባለው ባይሆንም፤ “ጤፍ ተወደደ፤ ገበያ ላይ ጠፋ” ሲባሉ፤ “ታድያ በቆሎ መብላት ይልመዳ!” ያሉንም መሪ እንደነበሩን እናሥታውሳለን። “የወሎ ህዝብ በርሀብ አለቀ’ኮ  ምን ይሻላል?” ሲባሉ፤ “የወሎ ህዝብ መሰደድ ልማዱ ነው!” ያሉ ሚኒስትር የፓርላማ አባል እንደነበሩንም፣ የኃይለሥላሴ ዘመን ማክተሚያ፣ የ1966 የወሎ ረሀብና ድርቅ መራራ ትዝታችን ነው! በእንባ ማላገጥ ያገር ልማድ ነው፡፡
“ማመልከቻ ለክቡራን ኢትዮጵያውያን
 እዩልኝ ሥሙልኝ ፤ሥቃይ በደሌን
ወሎ ተርቦ፤እንደዚያ ሲያልቅ
በድብቅ ነበር፤እኛ ሳናውቅ!”
እየተባለ እየተዘፈነ ፓርላማው የዝሆን ጆሮ ይሥጠኝ ማለቱን ያመላክት ነበር። ሰሜኑ ክፍል ባያሌው የድርቅ፣ የቸነፈር፣ የጦርነትና የመፈናቀል ሰለባ እንደነበር አንድና ሁለት የሌለው ነው። ዛሬስ ? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው። ደረጃው ይለያይ፣ ይብስ ወይም ይሻል እንደሁ እንጂ ያው ነው!
ግጭቶች ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ አገሪቱን ማጥለቅለቃቸው የማይሸሽ እውነት ነው። ጎረቤቶቿ እንደ ግብፅ ቀን የሚጠብቁ፣ እንደ ሱዳን የሚሸምቁና መሪ ባፈራረቁ ቁጥር አዳዲስ ሰነድ የሚያፀድቁ፤ እንደ ሱማሌ “ቀዩዋን ያየ፣ ጥቁሯን ያየ!” ቁማር የሚጫወቱ፤ እንደ ኬንያ ከህንድ እስከ እንግሊዝ ዕቁብ የሚጣጡ፤ አገሮች የከበቡዋትና ተፈጥሮ አድሏት፤ አሳዳጊ የበደላት አገር ናት!፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሳይሞቅ ፈላ ነው። ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ነው። ኢኮኖሚስቶቿ “የአፍሪቃው ጠንቋይ” የሚባለው አይነት ናቸው! ህዝቧም ቢሆን “ፈጣሪ ጥሎ አይጥላትም ይቺን አገር!” ከማለትና፤
“ተመሥገን ይለዋል፤ሰው ባያሌው ታሞ
ካማረሩትማ፤ ይጨምራል ደሞ” ከሚል የመዲናና ዘለሰኛ ምህላ ሌላ መላ አላገኘም! ምናልባትም
“…ካገር እኖር ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት፤ ሚስቴን እቴ ብዬ!”
ወዳለው የዱሮ፣ የጣልያን ጊዜ ባላገር እንዳንመለስ ያሰጋል። ሹመት ሲበዛ መጠርጠርና መጠንቀቅ ደግ ነው። ደርግ ሊወድቅ አንድ ሐሙስ  ሲቀረው ሰባ አምስት ጄነራሎችን መሾሙን አንርሳ!
ሁኔታ ሲከፋ፤አንድም “ፓርቲው ራሱን ያሥወግዳል” (the party purges itself) አባላቱን መኮነን፣ መርገም፣ ከሥልጣን ማስወገድ ያመጣል፤ ራሱን ይቀጣል የሚለውን የፖለቲካ ጠበብት ብሂል እውን ያደርጋል፤እንደማለት ነው። አብርሀም ሊንከን ሥልጣኑን ሲለቁ፤
“እኔ ከዚህ ቤት ስወጣ፣ ደስ ያለኝን ያህል አንተ ወደዚህ መግባትህ አስደስቶህ ከሆነ ፤ታድለሀል።” ብሎት ነበር - ለተረካቢው ፕሬዚዳንት።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ቀደምትም ሆነ አሁን በፖለቲካ መንበሩ ዙሪያ አጨብጫቢው ብዙ መሆኑ አይካድም። አድር-ባይነት የአገራችን ካንሰር-አከል በሽታ ነው። ክፋቱ ደግሞ ተላላፊ፤ተዛማጅ በሽታ መሆኑ ነው። (opportunism is infectius and oscillates like a pendulum) አድር-ባይነት ዘለዓለም ዓለሙን እንደ ፔንዱለም ሲወዛወዝ ይኖራል እንዲል መፅሐፈ-ሌኒን፡፡ ያም ሆኖ መንግሥት ያዋከቡትና እፍ እፍ ያሉት ነገር እንደ ቡናም ትኩስነቱን ሲያጣና ቅመሙ ሲነፍሥበት እንደሚሆነው እንዳይሆን (decaffeinated እንዲሉ)  ሊጠነቀቅ ይገባዋል። ምነው ቢባል እፍ እፍ ባዮች፤ባህሪያቸውን ገጣሚው እንደሚከተለው የገለጠው ነውና፡-
ሲቃወም የነበር ፤ትላንት ጥግ ድረስ  
ይታያል ቀዝቅዞ ፤ዛሬ አሞቱ ሲፈስ
ሁሉም ይለጎማል ፤ወንበሩ ጋ ሲደርስ!
ይኼው ነው ሚሥጥሩ፤ ዘማኝ ሥልጣኔ
በየፓርኩ ደማቅ፤ ብርቅርቁ ቅኔ።
ከለም አገር ነሥቶ ፤እስከ ራቡ ጠኔ
ዘይት ያለቀበት፤ የሰም -ወርቅ ቅኔ!!
ከቶውንም ይሄ ካልተሰራ፣ይሄ ይሄ ካልተደረገ፣የሚሉ አዳዲስ ምልምል (ሙልሙል) ፖለቲከኞች ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ የሚል ብቻ ሳይሆን ፤”ጮሃ የማታውቅ ወፍ፤እለቁ! እለቁ! ትላለች” የሚል ተረት ያለው ህዝብ መሆኑን ከአደራ ጋር እንጠቁማቸዋለን!!!                


Read 12126 times Last modified on Saturday, 16 April 2022 20:06