Monday, 18 April 2022 00:00

የዛሬ የኑሮ ውድነት? ወይስ የወደፊት የብልፅግና ተስፋ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • “ዙም ኢን”፣ “ዙም አውት” ማድረግ ያስፈልጋል - አጥርቶና አሟልቶ ለማየት።
   • በአንዲት አንቀጽ ብቻ፣ አገሩ ሁሉ እንዲቀየር፣ ሕዝቡ ሁሉ እንደ አዲስ እንዲወለድ እንመኛለን። በሌላ በኩልስ?
   • “ሰማይ ምድሩ ካልተገለባበጠ”፣ “የምፅዓት ጊዜ” ካልደረሰ በቀር፣ ቅንጣት ለውጥ የማይኖር ይመስለናል።
        

           “አድቅቀህ አስብ” እንላለን። እያንዳንዷ ጠብታና የአሁኗ ደቂቃ፣ እያንዳንዷ ዝርዝርና ምንዝር ናቸው፤ ህይወትና ሞት ማለት! እነዚሁ ናቸው፤ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄዎች። ነጥብ ነጥቡን መናገር ነው፤ አዋቂነት።
ይህን አስተሳሰብ፣ “የነጠብጣብ ፍቅር ያደረበት፣ የጠቃጠቆ አስተሳሰብ” ብለን ልንሰይመው እንችላለን። በሌላ አገላለፅ፣ “Life is Here and Now” ይላሉ። ወይም ደግሞ፤ “The Devil is in the Detail” የሚለውን አባባል መጠቀም ይቻላል።
ይቺኛዋ አንዲት ህግ፣ ይህቺኛዋ ነጠላ አንቀጽ፣ እለታዊዋ ግንባታ፣ የዛሬዋ ጥቃት፣ እዚህች ቦታ እንት መንደር ላይ የተጎዱ ሰዎች፣ የዘይት የኮታ መጠን፣ የዳቦ የዋጋ ተመን፣ የረፋዱ ፀሀይ፣ የአመሻሹ ዝናብ፣…. የሆነች ቦታ በነጠላ፣ አንዲት ቁንፅል ጉዳይ፣ ቅንጣቷ ደቂቃ፤… የሁሉም ነገር ቁልፎች ይመስሉናል።
በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “አስፍተህ አስብ፤ ዘመናትን አሰላስል፣ አሟልተህ አገናዝብ” እንላለን። ሁለት ሺ ዓመት የኋሊት፣ ሁለት ሺ ዓመት ወደፊት ማሰብ…ጥሩ ነው። ግን “አነሰ” እንላለን። ወንዝና ተራራን አሻግሮ፣ አገርን አቅፎ፣ ጎረቤቶችን ጭምሮ ማሰብ፣…. ይሄም ጥሩ ነው። ግን፣ ገና ብዙ ይቀረዋል። ከአገር አልፈን፣ ከጎረቤትም ባሻገር አስፍተን፣ አህጉርንና ባህር ማዶን ሁሉ ብናስብ እንኳ አይበቃም። ሀሳባችን ይበልጥ መስፋፋት አለበት እንላለን።
እገሌና እከሊት ብለን፤ በአካልና በግል የምናውቃቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ “የሰው ልጅ ማለት… እንዲህ ነው፣ የሰው ተፈጥሮ እንደዚያ ነው” ብለን በጥቅሉ በሰፊው እናወራለን። እኛ መንደር ወይም እዚህ አገር ውስጥ፣ ከመሃል እስከ ጠረፍ የሚገኙ ሰዎችን ብቻ አይደለም። በመላው ዓለም፣ ከዳር እስከ ጫፍ፣ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ነዋሪዎችን፣ በጠፈር ያሉ ሰዎችንም ጭምር ያጠቃልላል - ሰፊው ሃሳባችን።
ከአጠገባችን ዛሬ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን፤ ወደኋላ በታሪክ እየቃኘን፣ በየዘመናቸው በሁሉም የኖሩና የሞቱ ቢሊዮን ሰዎችን ያካትታል - “ሰው” ብለን ስናስብ። ወደፊት የሚወለዱ ቢሊዮን ሰዎችንም ሁሉ ይጨምራል።
እንግዲህ ምን ይሻላል? ነገረ ስራችን ሁሉ፤ ዥዋዥዌ ይመስላል።
አንዲት ቁንጽል ጉዳይና አንዲት ነጠላ ህግ ላይ፣ ቅንጣት አንቀጽና አንዲት ነጥብ ላይ፣ ሙጭጭ እንላለን። ግን ደግሞ፤ “የሕግ የበላይነት”፣ “በሕግ አምላክ” እያልን፤ በድንበር በዘመን ያልታጠረ፣ ሰፊ ሃሳብ መያዝና ማውጠንጠን ይመስጠናል።
አንዴ፣ በቁንፅልና በገረፍታ፤ ሌላ ጊዜ፣ በምልዓትና በጥልቀት ነው ነገራችን። አንዴ፣ የቅርቡ ይስበናል። ሌላ ጊዜ፣ የሩቁ ይማርከናል። እንግዲህ፣ ይሄ ምን ይባላል?
“እዚህና እዚያ፣ አሁንና ወዲያ፣ ነጥብና ምልዓት”… በተቃራኒ አቅጣጫ የሚፈራረቁብን ነገሮችን ምን እናድርጋቸው? ወደ አንዱ ማዘንበል፣ ወይም ወደ ሌላው መንጋደድ፣ መፍትሄ እያመጣልን አይደለም።
አዎ፤ የቅርብ የቅርቡ፣ የቅፅበት የእለቱ፣ ቁንፅል ብጣሽ ጉዳይ ላይ አፍጥጠን፤ ሌላውን ሁሉ በጭፍን ትተን፣ “ክውክው” ማለት እንችላለን።
የሩቁንና ሰፊውን፣ የረዥም ጊዜ ጉዞውን፣ የእድሜ ዓመታትንና የታሪክ ዘመናትን ቸል ብለን፣ እዚያው በዚያው፣ የአሁንና የወዲያው ብጥስጣሽ ቅንጥብጣቢ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንሻማለን። በጠብታዎችና በነጥቦች መሃል እንደናበራለን።
ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ ከጠብታ መውጣት ያምረናል። ሰፊው ባህር ይስበናል።
የምልዓተ ዓለሙ እውን ተፈጥሮን፤ ዘላለማዊው እውነታን፣ በሃሳብ እናስሳለን። የሰው ልጅ እውነተኛ ሕልውናን፣ እንዲሁም ዘላለማዊ ክቡር የሰው ሕይወትን እናሰላስላለን።
ለሁለንተናዊ የሰው ተፈጥሮ ተገቢ የሆነ፣ ለክብሩም የሚመጥን፣ ለሁሉም ቦታ የሚበቃና መቼም የማይደበዝዝ፣ የእውቀት ብርሃንን እናልማለን።
የዘመን ብዛት የማይሸረሽረው የተቃና የመልካም ተግባር መንገድን፣ በረዥሙ መቀየስ ያምረናል። ከዓመት ዓመት በንፅህና የታነጸ ድንቅ ስብዕናን፣ ጊዜ የማይሽረው ዘላለማዊ ቅዱስ ማንነትን፣… በምናብ እንቀርፃለን።
በአጠቃላይ፣ ሁሉን አቀፍ ዘላለማዊ እውነትን እና የእውቀት ብርሃንን፣
በሁሉም ቦታ፣ ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ጉዳይ ላይ፣ ሁልጊዜ ተገቢ የሆነ ዘላለማዊ የስነ ምግባር መንገድን፣
የተሟላ አኗኗርና እጅግ የላቀ የበቃ ስብዕናን…
“የእውነት ብርሃን፣ የተቃና መንገድ፣ የሕይወት ጣዕም” የምንላቸው ነገሮች፣… ከሁሉም በላይ ይበልጥቡናል - አንዳንድ ጊዜ። እንግዲህም አለ ለማለት ፈልጌ ነው።
እናም፣ አዎ፤ ሁለንተናውን፣ ምልዕተ ዓለሙን፣ ፍጻሜ የሌለው ዘመንን፣ በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር ለዘላለም ለመጨበጥ፣ በሰፊው ለማቀፍ፣ በረዥሙ ለመቃኘት፤… መምረጥ እንችላለን።
ግን ምን ዋጋ አለው?
“የቆምንበትን ቦታ፣ ከፊት ለፊት የተጋፈጠብንን ነገር፣ የአሁኑን ተግባር፣ የዛሬውን ኑሮ፣ የያዝነውን ጉዳይ”… እነዚህን ነጥቦችና ዝርዝሮች ወዲያ ትተን፣ የዘለለም ብዥታ ውስጥ እንሟሟለን። ምንም ሳንጨብጥ፣ ሁለንተናዊ ጉም ውስጥ እንንሳፈፋለን።
በእርግጥ፣ ሰፊው ባህር ውስጥ ጠፍተን ከምንቀር፣ ከባህር ሸሽተን፣ ጠብታ ወደ መቁጠር መመለስ አያቅተንም።
የቅርብ የቅርቡ፣ የአሁን የዛሬው፣ ነጠላ ዝርዝር ጉዳይ ላይ ብቻ በፍቅር መጠመድ፤ ሌላውን መጥላት ወይም መጣል፣…. እንችላለን።
እንደገና፣ የሩቁን፣ የዘላለሙን፣ የምልዓተ ዓለሙን እየናፈቅን፣ የሁለንተና ወዳጅ ሆነን፣ የእለት ተእለቱን መዘንጋት ወይም ማናናቅ፣…. ይህንም እናደርጋለን።
እንዲህ፣ ከአንድ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት እየተምታቱ የመላተም ዥዋዥዌ፣ የሰዎች ሁሉ ሸክም ይመስላል። ነገር ግን፣ ይህንን ሸክም ማሸነፍም፣ የሰዎች ተፈጥሯዊ አቅምና ፀጋ ነው።
የቅርቡን ብቻ ሳይሆን የሩቁን፣ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የዘመናትን፣ ነጠላ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ምልዓተ ዓለሙን፤ እለታዊውን ብቻ ሳይሆን የዘላለሙን፣ ማስማማትና ማዋሃድ ይችላል - የሰው ልጅ። አቅሙ አለው። ጠብታና ባህርን፣ ነጥብና ማዕቀፉን፣ ነጠላውንና ምልዓቱን፣… እንደየመልኩና እንደየልኩ አጣጥሞ ማገናዘብ፣ በቅጡ እያዋሃዱ እውቀትን መገንባት ይቻላል። በዚህ መንገድ፣ “ዝርዝርንና ጥቅልን” አዋህዶ በስርዓት ማሰብ፣ መስራትና ማንነትን ማነፅ ይቻላል።
ይህን ይመስለኛል፤ “ጥበብ” የሚሉት። ጥበብ ማለት፣ ባለ ብዙ ዝርዝር፣ የብዙ ነገር ማዕቀፍ ነው።
እውቀትና ሃሳብን፣ ተግባርንና የስራ ውጤትን፣ የግል ብቃትንና የማንነት ክብርን ሁሉ የሚያጠቃልል ቃል ነው - ጥበብ የሚለው ቃል።
ውሎና አዳርን፣ ከረዥም ዓመታት ኑሮና ከእድሜ ልክ ብቃት ጋር እንደ ማዋሃድ ቁጠሩት።
ለእለት ለእለቱ፣ ለቀንና ለማታ፣ መዋያና ማደሪያ ያስፈልጋል። የእለት ጉርስና መጠለያ፣ የሕይወት ጉዳይ ናቸው። “እዚህና አሁን”፣ ለሕልውና ያስፈልጋሉ።
“ሙያ እና መተዳደሪያ” የምንላቸው ነገሮች ደግሞ አሉ። እለታዊውን የስራ ጥረት፣ ከእድሜ ልክ የሙያ እድገት ጋር የሚያስተሳስር ነው - ሙያ ማለት። እለታዊውን ኑሮ፣ ከህይወት ዘመን ጋር ያዋህዳል - መተዳደሪያ መላት።
ሙያ፣ ቀን ተቀን የስራ ተግባር፣ በሚያስገኘው ፍሬ፣ እንዲሁም በእለት ጉርስ ይመነዘራል። መዋያ ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
ሙያ፣ የእለት ጉርሻ ብቻ ሳይሆን፣ የዓመታት የህይወት ዋስትና ነው። የእድሜ ልክ ማንነትን ለመቅረፅና ለመገንባት የሚያስችል፣ ወደ ላቀ ብቃት የሚወስድ የረዥም ጉዞ መንገድ ነው - ሙያ ማለት።
በአጭሩ፣ ነጠላ ዝርዝሮችናና ሰፊውን ማዕቀፍ፣ የቅርቡንናና የሩቁን፣ በጋራ አስማምቶ በትክክል እንደማዋሃድ ቁጠሩት - ሙያ ወይም መተዳደሪያ።
መዋያ እና ሙያ፤ ማደሪያ እና መተዳደሪያ፤ አንዱ የሌለው ጠላት፣ አንዱ የሌላው ተቃራኒ ወይም ተፃራሪ መሆን የለበትም።
ጥሩ ፋብሪካዎች በቅርባችን ሲበረክቱ፣ መዋያም፣ የሙያ መተዳደሪያም ናቸው። ለዛሬም፣ ለወደፊትም ነው ፋይዳቸው። ፋብሪካዎች ከቅርባችን ቢሆኑም፣ ከሩቅ አገራት ጋር መገበያያት እንዲችሉ ስናደርግ ደግሞ አስቡት። ይሄ፤ የጥበብ መንገድ ነው።
የቅርቡንና የራቁን፣ የእለት ጉርስና የረዥም ጊዜ መተዳደሪያ ሙያን፤ ጊዜያዊ ክፍት የስራ ቦታንና የመጪው ዘመን የኢኮኖሚ እድገትን አጣጥሞ ማዋሃድ፤ የስኬት ብቻ ሳይሆን፣ የክብር መንገድም ነው - የጥበብ መንገድ።
በሌላ በኩልስ?
“የሰሜን ዋልታ በረዶ እንዳይቀልጥ እንዝመት” በሚል ሰበብ፣ አጠገባችን ያሉ ፋብሪካዎችን ከማበራከት ይልቅ ማሽመድመድ፣ የእለት እንጀራችንን መንጠቅ፤… ከጥበብ የራቀ አላዋቂነት ብቻ አይሆን። ከጥበብ የተጣላ የጥፋት መንገድ ይሆናል።

Read 9444 times