Sunday, 17 April 2022 00:00

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    • በአማራ ክልል 7 መቶ ሺህ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው
     • በትግራይ ክልል 1.4 ሚሊዮን ህጻናት ትምህርት ቤት አልገቡም
      • በአፋር ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከት/ቤት ውጭ ለመሆን ተገድደዋል
              
             በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አሁንም በጦርነት ስጋት ውስጥ ያለ በመሆኑ ቀጣይ ሁኔታዎችን ለመገመት አስቸጋሪ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት (ኦቻ)፤  ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ወደ ትግራይ፣ አፋርና አማራ አካባቢዎች እርዳታ እየተጓጓዘ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይ በትግራይና አማራ ክልል አካባቢዎች አንጻራዊ  ሰላምና መረጋጋት እየተስተዋለ ቢሆንም፣ ይህ  መረጋጋት ግን አስተማማኝ ዋስትና እንደሌለው ኦቻ፣ በአካባቢው ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በተነተነበት ሰፊ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
በአማራና ትግራይ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ ባይኖርም፣ በአፋር በኩል ግን አሁንም አልፎ አልፎ የከፋ የተኩስ ልውውጥ እንደሚካሄድ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በተለይ በአፋር ዞን 2 (ክልቢት) አካባቢ፣ አባላ ወረዳ፣ጉቢ ቀበሌ አካባቢ ጦርነቱ ሲካሄድ መሰንበቱን ገልጧል፡፡
የሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ  እየተጓጓዘ ያለውም በዚሁ ጦርነቱ አልፎ አልፎ እየተካሄደ ባለበት የአፋር መስመር መሆኑን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡
በአሁኑ ወቅት ለትግራይ ዋነኛው የሰብአዊ ድጋፍ ማስተላለፊያ ከሰመራ አባላ መቀሌ ያለው መስመር መሆኑን ያወሳው ኦቻ፤ ባሳለፍነው ሳምንት 670 ሜትሪክ ቶን ምግብና አልሚ ምግቦችን የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎች መቀሌ  መግባታቸውን አመልክቷል፡፡
ከምግብና የህፃናት አልሚ ምግብ በተጨማሪ 47 ሺህ ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ መግባቱን፣ ነገር ግን በትግራይ ለየወረዳና ዞኑ የሚከፋፈሉ የእርዳታ አቅርቦቶች ለማሳለጥ በሳምንት የሚፈጀው የነዳጅ  መጠን 2 መቶ ሺህ ሊትር እንደሆነና ከዚህ አንፃር  የነዳጅ አቅርቦቱ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡
 በሌላ በኩል፤ በትግራይ የተለያዩ የእርዳታ አገልግሎቶችን ለማሳለጥ 87 ሚሊዮን ብር መላኩን፣ ነገር ግን ይህ የገንዘብ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን ያመላከተው የኦቻ ሪፖርተር፤ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በትግራይ የእርዳታ አቅርቦት ለማሳለጥ 3 መቶ ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡
የትምህርት ሁኔታን በተመለከተ ደግሞ ትምህርት በተጀመረባቸው ጥቂት ትምህርት ቤቶች ቀድሞ ሲቀርብ  የነበረው የተማሪዎች ምገባ  ፕሮግራም  መቋረጡን፣ በ13 የትግራይ ወረዳዎች  የሚገኙ 80 ት/ቤቶች ዝግ መሆናቸውንና 641 ትምህርት ቤቶችም በምገባ ፕሮግራም መቋረጥ፣ ለመምህራን ደሞዝ ባለመከፈልና በትምህርት መሳሪያዎች ግብአት አለመኖር ምክንያት የመዘጋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተመልክቷል፡፡ በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት 1.4 ሚሊዮን ህጻናት ትምህርት ቤት መግባት ሲገባቸው እንዳልገቡ፣ 144 ሺህ ያህል የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች እንዲሁም 25 ሺህ የአጸደ ህጻናት ተማሪዎች አፋጣኝ ድጋፍ ካልተደረገላቸው ትምህርት የማቋረጥ ጫፍ ላይ መድረሳቸውን የኦቻ ሪፖርት ጠቁሟል።
በክልሉ በአጠቃላይ 46 ሺህ መምህራን በገንዘብ እጦትና በምግብ አቅርቦት ውስንነት ለችግርና ስቃይ መዳረጋቸው ተመልክቷል፡፡
የአፋር ክልል በወፍ በረር
በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ጦርነት ቢኖርም፣ የእርዳታ አቅርቦቶች ላይ እምብዛም እክል አለመፍጠሩን ያወሳው  የመንግስታቱ ድርጅት ተቋም ሪፖርት፤ በቅርቡ ለበርሃሌ፣ ዳሎልና ኮነባ ወረዳዎች የሚሆን 1 ሺህ ቶን የምግብ እርዳታ መድረሱን ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል በበርሃሌ፣ ኮነባ፣ መጋሌ፣ አራቢት እና  ዳሎል ወረዳዎች ከ294 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙና ለእነዚህ ተፈናቃዮች እየቀረበ ያለው የእርዳታ መጠን በቂ አለመሆኑ ተመልክቷል፡፡  
በአፋር ዞን 2 በሚባለውና ከላይ የተጠቀሱትን ወረዳዎች አጠቃሎ በሚይዘው አካባቢ በጦርነቱ ምክንያት መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ት/ቤቶችና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው በአካባቢው ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት አለመኖሩም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በአፋር ክልል ከጦርነቱ በፊት በአጠቃላይ 1 ሺህ 195 ት/ቤቶች ይገኙ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ ውስጥ  245 ያህሉ መዘጋታቸውን፣ በዚህም ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን መገደዳቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም አምስት ት/ቤቶች ወደ ተፈናቃዮች መጠለያነት ተቀይረዋል ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል በወፍ በረር
በአማራ ክልል ዋግህምራ ዞን፣ ሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ አሁንም በጦርነት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የእርዳታ አቅርቦቶች ለማሳለጥም ከጦርነቱና ከታጠቁ  ሃይሎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ  እንቅፋት መፍጠራቸውን አመልክቷል፡፡
በተለይ በዋግህምራ ዞን በሚገኙት አበርገሌ ፃግቢ ቀበሌዎች አካባቢ እንዲሁም በሰሜን  ወሎ ዞን ቆቦ አካባቢ፣ በሰሜን ጎንደር አዲ አርካይ አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታዎች በአግባቡ እየቀረቡ አይደለም ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋም ተግባር በተጠናከረ መልክ እያከናወነ መሆኑም በሪፖርቱ  ተጠቅሷል። በተለይ በቆቦና ሰቆጣ አካባቢ በጦርነቱ ከተፈናቀሉ 58 ሺህ ያህል ዜጎች ውስጥ 16 ሺህ የሚሆኑትን መልሶ ማቋቋም የተቻለ ሲሆን በዋግኽምራ ዞን 1800 ዜጎችን ማቋቋም ተችሏል ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል በአጠቃላይ ካሉ 9 ሺህ 889 ት/ቤቶች 558 ት/ቤቶች (በዋግኽምራ፣ በሰሜን ጎንደርና ሰሜን ወሎ የሚገኙ) እስካሁን ዝግ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ 97 ት/ቤቶች ከተለያዩ  ወረዳዎች ለተፈናቀሉ  ዜጎች ጊዜያዊ መጠለያነት እያገለገሉ ነው፡፡
በትምህርት ቤቶች መዘጋትና መውደም ምክንያት በአጠቃላይ በአማራ ክልል 7 መቶ ሺህ ያህል ተማሪዎች ከትምህርት  ገበታ ውጪ መሆናቸውንም የተቋሙ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

Read 2286 times