Saturday, 16 April 2022 13:33

እናት ባንክና ራይድ አዲስ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    የራይድ አሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል
                      
             ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ11 ባለራዕይ ሴቶች የተመሰረተውና የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው እናት ባንክ፤ በዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት ቴክኖሎጂ አቅርቦት ግንባር ቀደም ከሆነው ከሀይብሪድ ዲዛይን (ራይድ) ጋር አዲስና የስራና የብድር ስምምነት ውል መፈጸማቸውን አስታወቁ፡፡
ተቋማቱ ይህን ያስታወቁት ትላንት በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል ስምምነቱንና በፈፀሙበት ወቅት ነው፡፡ አዲሱ የብድር ስምምነታቸው “እናት ራዕይ”፣ “እናት እፎይታ” እና “እናት ደራሽ” የተሰኙ ሲሆን ይህ ብድር አገሪቷ ላይ በተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት የራይድ አሽከርካሪዎች ላይ የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ጫና ከግምት በማስገባት ባንኩ የራይድ አሽከርካሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የብድር አገልግሎቶችን ማቅረቡን የተቋማቱ ሀላፊዎች አብራርተዋል፡፡
“እናት ራዕይ` የተሰኘው የብድር ዓይነት በራይድ ውስጥ ተመዝግበው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ባለራዕይ አሽከርካሪዎችን የሚመለከት ሲሆን ብድሩም ለአዲስ መኪና መግዣ የሚውል ሆኖ፣ የዚህ ብድር ተጠቃሚ ለመሆን፣ ለመግዛት ከሚታሰበው የመኪና ዋጋ 30 በመቶውን በአንድ ዓመት መቆጠብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ቀሪውን 70 በመቶ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፍሎ ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ታውቋል፡፡
“እናት እፍይታ” የተሰኘው የብድር ዓይነት ደግሞ የራይድ አሽከርካሪዎች ለዓመታዊ የግብር ክፍያ፣ ለመኪና ጥገናና ለተያያዥ ወጪዎች የሚውል ሲሆን የዚህ ብድር ተጠቃሚ ለመሆን አሽከርካሪዎች በትንሹ ለ3 ወር የእናትን ባንክ ደንበኛ መሆንና በቋሚነት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡ በዚህ የብድር አገልግሎት የራይድ አሽከርካሪዎች እስከ 10 ሺ ብር የሚደርስ ብድር ማግኘት እንደሚችሉም ነው የተገለፀው፡፡ “እናት ደራሽ” የተሰኘው ሶስተኛው አይነት የብድር አገልግሎት ደግሞ የራይድ አሽከርካሪዎች ለተዘዋዋሪ የስራ ማስኬጃ የሚያውሉት እስከ አንድ ሺ ብር የሚደርስ ብድር ሲሆን ይህ የብድር አገልግሎት አሽከርካሪዎች የራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት  በሚሰጡበት ወቅት የሚጠቀሙት ብድር ሲሆን ምንም አይነት የወለድ ምጣኔ የማይታሰብበትና ለተወሰደው ብድር በቀን አንድ ብር ብቻ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፍሉበት ነው ተብሏል፡፡
እናት ባንክ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ እምብዛም ትኩረት ያልተሰጣቸውን ሴቶች ታሳቢ በማድረግ ከ9 ዓመት በፊት ወደ ስራ የገባ ተቋም ሲሆን ካሉት 18 ሺህ ባለአክስዮኖች ከ64 በመቶዎቹ በላይ ሴቶች መሆናቸውንና  የባንኩ የባለፈው  ዓመት ያልተጣራ ትርፍ 289 ሚ ብር እንደሆነ የገለፁት ሀላፊዎቹ፤ የተከፈለ ካፒታሉም ከ1.5 ቢ ብር በላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በስራ ፈጣሪዋ ወጣት ሳምራዊት ፍቅሩ በ2007 ዓ.ም የተመሰረተው ሀይብሪድ ዲዛይን የቴክኖሎጂ ተቋም፣ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍና በማዘመን ረገድ ፈር ቀዳጅ ሲሆን እስካሁን  ለበርካቶችም የስራ እድል መፍጠሩ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

Read 1432 times