Friday, 15 April 2022 16:45

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዳቦ፣ የዳቦ አመጽና ግብጽ ያላቸው ዝምድና
                            ጌታቸው ወልዩ (ሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)
የዳቦ ዋጋን ተመን ለማውጣት የሚፈቅድ አሰራር የለንም›› ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡ -  አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን

                ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ትንታኔዬ፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መዘዝ በገጠመ የስንዴ እጥረት በግብጽ የተባበሰው የዳቦ አመጽን ለማርገብ፣ የአገሪቱ መንግሥት በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ ዳቦ ለሕዝቡ ለማቅረብ እየተከተለ ያለውን የመሿለኪያ መንገድና የግብጽ የዳቦ ሕልውና ምን ያህል በዩክሬንና ሩሲያ መዳፍ ሥር እንደሆነ ዘርዘር ያለ ጽሑፍ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ እና ትኩረት ሰጥታችሁ ትከታተሉት ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።
ውድ ወገኖቼ:- በዘመናዊቷ ግብጽ “ዳቦ” እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ መሠረታዊ የምግብ ዓይነቶች አንዱ (one of the most important food staples) ተብሎ የሚንቆለጳጰስ፤ በነገ በጠባ ከብዙ ሚሊየኖች ደጅና ጓዳ የሚዳረስ፤ በገበያ ላይ ሲኖር የመኖር ሕልውናን የሚያረጋግጥ፤ የኑሮ ውድነት ሲገጥም የፖለቲካ ሥልጣንን እንደ ቅቤ የሚንጥ ፖለቲካ አዘል ተወዳጅ ምግብ ነው።
ለዚህም ነው “ግብጽ ውስጥ ዳቦ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፦ ከላይኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሀብት ብዛት ከናጠጡ ቱጃሮችና በሥልጣን ማማ ላይ ከተኮፈሱ ሹመኞች አንስቶ እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ በመወደድ ዕለት ተዕለት ለምግብነት የሚውል፤ እጥረት ሲገጥም ብሶትን ወልዶ አመጽን የሚያበቅል፤ ፖለቲካዊ አንድምታው እጅጉን የሚያመዝን፤ የመንግሥት ሥልጣን መውጣትና መውረድ ቋንቋን የሚያቀነቅን፤ የብዙ ሚሊዮን ግብጻውያን መነጋገሪያ ቋንቋ ነው።” የሚሰኘው።
እነሆ ደግሞ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር ፌብሩዋሪ 24 ቀን 2022 ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 16 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተጀመረውን ጦርነት ተከትሎ፤ በዓለም አቀፍ ገበያ የስንዴ እጥረት በመግጠሙና ያለውም ዋጋው በመናሩ፤ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን ስንዴ በግንባር ቀደምትነት በመግዛት የምትታወቀው ግብጽ፤ የዳቦ አመጽ በርትቶና ገፍቶ፤ በ”ዳቦ እንፈልጋለን?” የሚሊዮኖች ተደጋጋሚ ጥያቄዎች መከራዋን እያየች ትገኛለች።
እናም! በአሁኑ ጊዜ በግብጽ ውስጥ ከ102 ሚሊዮን ከሚበልጠው የግብጽ ሕዝብ 72 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝብ በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ መሰል ዝርግ የግብጽ ዳቦ እንዴት ይቅረብለት? ለሚለው ከባዱ አሊያም ፈታኙ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እጅግ ከባድ ፈተና ሆኗል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴቭ ታራቬላ፣ የካቲት 19 ቀን 2014 ለቮክስ ዶት ኮም በሰጡት መግለጫ፤ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ከሚበልጠው የግብጽ ሕዝብ አሥር (10) ሚሊዮን የሚሆኑት በአገሪቱ በገጠመ የስንዴ እጥረት የተነሳ ለከፍተኛ የምግብ እህል እጥረት ተጋልጠዋል ብለዋል። ይህ ደግሞ ለግብጽ መንግሥት በቡሃ ላይ ቆረቆር ሆኖበታል።
ግብጽ በዋናነት ስንዴ የምትገዛው ከዓለማችን ትልቋና ቀዳሚዋ የስንዴ አቅራቢ ሩሲያና ከአራተኛና አምስተኛ ስንዴ አምራችነት እርከን ላይ ካለችው ዩክሬን ሲሆን፤ ሩሲያና ዩክሬን ደግሞ በጋራ ሩብ በመቶ የስንዴ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው። በዚህ መነሻነት ግብጽ ከፍላጎቷ ግማሽ ያህሉን ስንዴ ከሩሲያ ስትገዛ፣ ሰላሳ (30) በመቶ ያህሉን ደግሞ ከዩክሬን ታስመጣለች ማለት ነው።
በምኅጻረ-ቃል “ካፕማስ” የሚሰኘው የግብጽ የሕዝብ ሞቢላይዜሽን (ንቅናቄ) እና ስታቲስቲክስ ማዕከላዊ ኤጀንሲ፤ “የግብጽ ዋነኛ ስንዴ አቅራቢዎች ዩክሬንና ሩሲያ ሲሆኑ፤ ከ80 በመቶ በላይ እስከ 85 በመቶ ወይም ከአምስት እጅ 4 ነጥብ 25 ያህሉን ስንዴ የምትገዛው ከባድ ጦርነት ውስጥ ከገቡት ዩክሬንና ሩሲያ ነው!” ማለቱ የግብጽ የስንዴም ሆነ የዳቦ ማግኘት ሕልውና ክር ለአመታት በሩሲያና ዩክሬን ላይ ለመንጠልጠሉ አገርኛ ምስክር ይሆናል።
ለአብነት ያህል በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር በ2019 ግብጽ ከሩሲያ በ1 ነጥብ 44 ቢሊየን ዶላር፣ ከዩክሬን 773 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ስንዴ መግዛቷን፣ በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 25 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት የተነበበው የኢንቨስትመንት ሞኒተር ዘገባ አመልክቷል።
እንዲሁም በ2020 ላይ ዩክሬን ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ስንዴ መጠን ሦስት (3) ሚሊዮን ቶን ወይም 14 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ስንዴ የገዛችው ግብጽ ነበረች። በተመሳሳይ አመት፣ ግብጽ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከሩሲያ ገዝታለች።
በዚህም መሠረት፦ ግብጽ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር በ2020 ላይ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋ በዋናነት ከዩክሬንና ሩሲያ እንዲሁም ሌሎች አገሮች 12 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ገዝታ ወደ አገር ውስጥ ማስገባቷን የግብጽ የሕዝብ ሞቢላይዜሽን (ንቅናቄ) እና ስታቲስቲክስ ማዕከላዊ ኤጀንሲ ገልጿል።
የግብጽ ስንዴ ፍላጎትም እጅግ እየበዛ ከመጣው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አኳያ በየአመቱ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ በጎርጎሮሳዊያኑ አመት በ2021-2022 ላይ ግብጽ የሚያስፈልጋት የስንዴ ግዢ መጠን ከቀዳሚው የ2020-2021፤ በ2 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ ወደ 21 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ መጠን ከፍ ማለቱን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የውጭ ግብርና አገልግሎት (US Foreign Servive) አስታውቋል።
የግብጽ ገበሬዎች ማኅበር ሊቀመንበር ሁሴን አቦ ሣዳም፣ በፌብሩዋሪ 4 ቀን 2022 ለተነበበው አል-ሞኒተር በስልክ እንደገለጹት ደግሞ፤ ግብጽ በአገር ውስጥ ዘጠኝ (9) ሚሊዮን ቶን ስንዴ የምታመርት ሲሆን፤ ይህ የስንዴ መጠን እየሸፈነ ያለው አገሪቱ ከምትፈልገው የስንዴ መጠን ወደ ግማሽ ያህሉን ነው።
ለንጽጽር ያህል ኢትዮጵያን ብንመለከት፦ የብዙ የዓባይ ተፋሰስን ጨምሮ በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተፋሰሶች፣ ሐይቆችና ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ-ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ፤ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከምታቀርበው ስንዴ ሦስት አራተኛ እጁን ወይም 75 በመቶውን የምታመርተው በአገር ውስጥ እንደሆነ ለመገንዘብ እንችላለን። ኢትዮጵያ ቀሪውን የስንዴ መጠን ደግሞ ከውጭ የስንዴ ላኪ አገሮች ትገዛለች። እንዲሁም ደግሞ ከለጋሽ  አገሮች የስንዴ ዕርዳታ ትቀበላለች።
እንደሚታወቀውና ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ግብጽ አብዛኛውን ስንዴ ከሩሲያና ዩክሬን የምትገዛ ሲሆን ቀሪውን ወደ ሀያ በመቶ ገደማ ደግሞ በዋናነት ከፈረንሳይ፣ ሩማኒያና አውስትራሊያ ታስመጣለች። ይህ ደግሞ የግብጽ የውጭ አገር ስንዴ ምርት ሸመታ እጣ ፈንታና መዳረሻ ሩሲያና ዩክሬን ላይ ማረፉን በግልጽ ያመላክታል።
እዚህ ላይ በዓለምአቀፍ ስንዴ ገዢ አገርነት ጎራ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ተመሳሳይ ጉዳይ አለ። እርሱም የዐረብ አገሮች የሆኑት ግብጽና ሊባኖስ ከውጭ አገሮች ከሚያስገቡት የስንዴ መጠን ከአራት አምስተኛ በላይ ወይም ከሰማንያ (80) በመቶ የሚበልጠውን የሚያስመጡት ከሩሲያና ዩክሬን የመሆኑ ጉዳይ ነው።
ለዚህም ነው ፌብሩዋሪ 24 ቀን 2022 በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተጀመረውና በየዕለቱ የጥፋት አድማሱ እየጨመረ በመጣው ጦርነት የተነሳ እጅግ ለከፋ የስንዴ እጥረት ከተጋለጡ የዐረብ አገሮች መካከል ሊባኖስና ግብጽ ሊጠቀሱ የቻሉት።
ሌላ ተጨማሪ ማሳያ ማቅረብ ካስፈለገ፣ በሩሲያና ዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት በዓለም አቀፍ የስንዴ ገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ ያደረሰውን ጫና በማስመልከት ማብራሪያ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው፤ በጎርጎሮሳዊያኑ ዘመን በ2007-2008 ለተቀሰቀሰው የዐረቡ ዓለም የፀደይ አብዮት አንዱ መንስኤ የዳቦ አመጽ እንደሆነ አስታውሰው፤ አሁንም በሩሲያና ዩክሬን መካከል በሚካሄደው ጦርነት መዘዝ ከሁለቱ አገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ የሚያስገቡት ግብጽ፣ ሊባኖስ፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያና ሌሎች አገሮችም ለከፋ የስንዴ እጥረት ከመጋለጥ እንደማይድኑ ስጋታቸውን መግለጻቸውን አስመልክቶ አልጀዚራ መጋቢት 2 ቀን 2014  ያሠራጨውን ዘገባ መጥቀስ ይቻላል።
ስለዚህ ግብጽ ያጋጠማትን የከፋ የስንዴ እጥረት ለመቅረፍ የመጀመሪያ አማራጭ አድርጋ የወሰደችው እርምጃ በአገር ውስጥ እያመረተች ወደ ውጭ ትልካቸው የነበሩትን ስንዴና በቆሎን ጨምሮ የምግብ ዘይት ምርቶችን ከመጋቢት 3 ቀን 2014 አንስቶ እንዲታገዱ ማድረግ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ ምንም እንኳን የተወሰኑ እህል አምራች ገበሬዎችን ጠቅሞ አንዳንዶችን ቢጎዳም የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ የአገሪቱ መንግሥት ጫን ያለ ትዕዛዝ አስተላልፏል። የተጣለባቸውን የስንዴ ኮታ ላለማቅረብ የሚያንገራግሩ ገበሬዎችን ከማስፈራራት አንስቶ ለእስራት እስከ መዳረግ ተደርሷል።
የግብጽ መንግሥት የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች፣ ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ ያስተላለፈውን ውሳኔ ከደገፉት መካከል፦ በግብጽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእርሻና መስኖ ኮሚቴ ኀላፊ ሂሻም አል-ሁሳሪ፤ “የአገር ውስጥ ስንዴ አምራቾች ስንዴ ለመንግሥት እንዲሸጡ መወሰኑ ለግብጽ ሕዝብ ዳቦን ጨምሮ ሌሎች የስንዴ ውጤት የሆኑ የምግብ ዓይነቶችን ለማቅረብ በጣም ጠቃሚ ነው!” በማለት አወድሰው፣ መጋቢት 11 ቀን 2014  ለተነበበው ሚድሊስት አይ ድረ ገጽ ተናግረዋል።
ገና ሩሲያና ዩክሬን ወደ ጦርነት በገቡ በሦስት ሣምንታት ውስጥ ግብጽ ውስጥ የማይደጎመው ዳቦ ዋጋ በሃያ አምስት በመቶ በመጨመር አንድ የግብጽ ፓውንድ ይሸጥ የነበረው ቂጣ፣ አንድ ከሀያ አምስት የግብጽ ፓውንድ ሊሸጥ መብቃቱንና የዱቄት ዋጋም አሥራ አምስት በመቶ (15%) መጨመሩን፣ የካይሮ ንግድ ምክር ቤት የሥራ ኃላፊ አቲያ ሀማድ መናገራቸውን ሮይተርስ  ከካይሮ ዘግቧል።
ከዚህም አልፎ የግብጽ መንግሥት ቁርጥ የሆነ የዳቦ መሸጫ ዋጋ (ተመን) አውጥቷል። በዚህም መሠረት፦ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ፣ ከሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014  አንስቶ አንድ ኪሎ ግራም ዳቦ በ11.50 የግብጽ ፓውንድ ወይም በ66 የአሜሪካ ሳንቲም መሸጥ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በአዲሱ የመንግሥት ውሳኔ መሠረት፤ 45 ግራም ቂጣ በ0.50፤ 65 ግራም በ0.75፤ 90 ግራም በ 1.00 የግብጽ ፓውንድ እንዲሸጡ ትዕዛዝ ተላልፏል። 40፣ 60 እና 80 ግራም ከፊኖ ዱቄት የሚሠሩ ትናንሽ ቂጣዎች ደግሞ፤ በ0.50፣ በ0.75 እና በ1.00 የግብጽ ፓውንድ ሽያጭ ለገበያ እንዲቀርቡ መንግሥት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይህን ለሦስት ወራት የሚቆይ ትዕዛዝ የሚጥሱ ስንዴ አምጪና አከፋፋዮች፣ የዳቦ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶችና ማናቸውም ግብጻውያን፣ ከአንድ መቶ ሺ እስከ አምስት ሚሊዮን የግብጽ ፓውንድ እንደሚቀጡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ ጽሕፈት ቤት የወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በተጨማሪም፤የአገሪቱ መንግሥት ተጨማሪ የስንዴ ግዢ ከሕንድ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ሩማኒያ፣ ካዛክስታንና ሌሎች አገሮች ለማግኘት እጅግ እየተሯሯጠ ይገኛል።
የስንዴ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መጨመሩን ተከትሎ፣ የግብጽ መንግሥት ለስንዴ ግዢ የሚያወጣውን ሦስት ቢሊዮን ዶላር፣ ወደ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጉን የዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ዘገባ አመልክቷል።
በግብጽ ውስጥ 38 ጊዜ የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸው፣ ሕይወታቸው ተርፋ፣ ኦክቶበር 6 ቀን 1981 በአክራሪዎች በተተኮሰባቸው ተከታታይ የጥይት ተኩስ ሕይወታቸው በተቀጠፈው የፕሬዚዳንት አንዋር ሣዳት የአገዛዝ ዘመን የዳቦ አመጽ ተካሂዷል።
በፕሬዚዳንት አንዋር ሣዳት እግር የተተኩት ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ሁሴን ሙባረክ፤ ከሥልጣናቸው የተመነገሉት ሕዝባዊ የዳቦ አመጽ በወለደውና እ.ኤ.አ በ2010-2011 በተቀሰቀሰው በዐረቡ የፀደይ አብዮት (ዐረብ ስፕሪንግ) ፈጣን ጎርፍ የተነሳ ነው።
በ2013 መፈንቅለ መንግሥት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት መሐመድ ሞርሲ ከሥልጣን አስወግደው፤ በአንድ ቀን ጀምበር ከ800 በላይ ሰልፈኞችን ያስገደሉና ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን ለእስር የዳረጉ ጨካኝ ወታደራዊ አምባገነን መሪ በሚሰኙት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ የሥልጣን ዘመን ምንም እንኳን አፈናው ቢበዛም፣ በግብጽ የከፋ የዳቦ አመጽ እየተካሄደ ይገኛል።
አሁን የግብጽ ፈተና በየቀኑ 270 ሚሊዮን ቂጣ/ሽልጦ ዳቦ ለሕዝቡ እንዴት ይቅረብ? የሚለውን ጥያቄ ከመመለሱ ላይ ነው።
ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው ምግብ”፣ “በመላው ዓለም ምርጡ ምግብ” እና “ከዓለማችን እጅግ ተወዳጅ ጥንታዊ ምግቦች አንዱ” (one of the world’s oldest and most beloved foods.) ተብሎ የተንቆለጳጰሰውና የተወደሰው “ዳቦ”፤ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ፣ የዓለማችን የስንዴ ዳቦ አቅርቦት ፈትኖ ካብረከረካቸው አገሮች አንዷ የሆነችው ግብጽና መሪዎቿ፣ ይህን የዳቦ አመጽ እንዴት ይሻገሩት ይሆን? የነገ ሰው ይበለን! የዳቦ አመጹን ሂደት ወደ ፊት አስቃኛችኋለሁ። እስከዚያው ቸር ሰንብቱልኝ።
በመጨረሻም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠብቅልን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

_________________________________________
===============================

                        የፑቲን አለም!
                              ፉዣዥ


              ስለ ሳይቤሪያ ነብሮች እንቅልፍ የሚያጣው ቭላድሚር ፑቲን የሚመራው ህዝብ፥ የሚወዳት ሩሲያ እስክትጠፋ ድረስ ውጤት ላለው የኒውክለር ጦርነት መነሳት (እና ወዲያው መጠናቀቅ) ምክንያት ሊሆን ይችላል?
“አለም ዘጠኝ ናት አስር ሞልታ አታውቅም” ያለው ማን ነበር። ስጠረጥር ግን ትክክል ይመስለኛል። አለም ዘጠኝ ትመስለኛለች። አንደኛዋ አለም የፑቲን አለም ናት። ስምንተኛዋ አለም ሁሉ ትመስለኛለች። የፑቲን አለምን ለመረዳት የመጀመሪያው ስራ ፑቲን ምን እንደሚሻ፥ እንደሚፈልግ ማወቅ ነው።
ፑቲን ምን ይፈልጋል?
ህይወቱንና እጣፈንታውን በመቆጣጠር ራሱን መጠበቅ (መከላከል) ፑቲን ይፈልጋል።
ዋናው ግን ፍላጎቱ አይደለም። የሰው ልጅን ባህሪ (ሃሳብ ተግባር ንግግር) በአብዛኛው፥ በአመዛኙ የሚቃኘው ፍላጎት ሳይሆን ፍርሃት ነው።
ሰው እንቅልፍ የሚያጣው ስለ ፍላጎቱ እያሰበና እያቀደ ሳይሆን ስለ ፍርሃቱ እያሰበና እያቀደ ነው። የሚፈራው ነገር እንዳይደርስ በሃሳቡ፥ በንግግሩ፥ እና በድርጊቱ ሲታገል ወይም ሲሸሽ ነው የሚኖረው፥ የሰው ልጅ። ፑቲንን ጨምሮ።
እና ፑቲንን ምን ያስፈራዋል?
ፍርሃት የፍላጎት “የመስታወት ምስል” ወይም ግልባጭ ነው። በሌሎች መጎዳት ወይም ቁጥጥር ስር መዋልን ፑቲን ይፈራል። ዝርዝር ባህሪው የሚቀዳው ከእነዚህ ነገሮች ነው፥ በተለይ ከፍርሃቱ። እንደ ፑቲን አይነት ሰዎች ተገዳዳሪዎች ሊባሉ ይችላሉ። ሃሳቦቹንም ሆነ ሰዎችን የሚቀበሉትና የሚያከብሩት ብዙ ከተገዳደሩ በኋላ ነው። ለማያውቅ ሰው “ከእኔ ምን ነገር አለው ይህ ሰው” ሊል ይችላል። የሚገዳደሩት ካንተ ነገር ስላላቸው ሳይሆን አንተን ለመመርመር ነው። ሳይመረምሩ አያደንቁህም፥ አያከብሩህም።
ኮንዶሊዛ ራይስ እንዳለችው፤ ከፑቲን ጋር ተደራድረህ ጥቅምህን ለማስከበር እርሱ ሊያከብርህ ይገባል፥ አንተም ልታከብረው ይገባል። እንዲያከብርህ ደግሞ ሃይለኛ፥ ጠንካራ መሆን አለብህ። የምታስበውን በቀጥታ የምትናገር መሆን አለብህ።
እንደ ፑቲን ያሉ ሰዎች ዲፕሎማቶች አይደሉም፥ ፊት ለፊት ነው የሚናገሩት። የሆነ የተሞረደ፥ የሰለጠነ ሰው አይነት ንግግር ከእነ ፑቲን አትጠብቅ። የዱርዬ የሚባሉ ቃላትን ሊጠቀሙ ይችላሉ። እንዲሁም የሚናገርውን፥ ቃል የገባውን የሚፈፅም ሰው ፑቲን ያከብራል። ፑቲን የሚጠላው በሌሎች ቁጥጥር ስር መዋልን ነው። እርሱን የማዘዝ፥ የመቆጣጠር ሙከራ ነው ብሎ ያመነውን ማንኛውንም ነገር በፅናት ይታገላል።
ፑቲንን ስታከብረው፥ በእኩልነት ስትመለከተው፥ ደህንነት እንዲሰማው ስታደርግ፥ እና እርሱ ሲያከብርህ ውጤታማ ድርድር የምታደርግ ይመስለኛል። ሌሎችን በመርዳት፥ በማገልገል ስራዎች ላይ አጋር ልታደርገው ትችላለህ። ፑቲን አጋር የሆነባቸው አያሌ አለም አቀፍ ስምምነቶች ተደርገዋል፥ አሜሪካ የተሳተፈችባቸው።
በአንፃሩ አልተከበርኩም፥ እንደ ታናሽና ታዛዥ ተቆጠርኩ ብሎ ካመነ ድርድርን እርሳው። አሰቃቂ ግጭት ውስጥ ትገባለህ። ጨካኝ፥ ፈላጭ ቆራጭ፥ ወንጀለኛ፥ አጭበርባሪ፥ በቀለኛ፥ ነፍሰ ገዳይ፥ አረመኔ ሊሆን ይችላል። እንዲያም ሆኖ ባልከፋ ነበር። ግድየለሽነቱ፥ እጅ ከመስጠት ይልቅ የማይታዘዘውን ሁሉ የማውደም አዝማሚያው ግን ያስፈራል።
______________________________________________
-----------------------------------------------------------------------

                          አብየ መንግሥቱና በርትራንድ ረስል
                              እሱባለው አማረ

              ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹የመንግስቱ ለማ ትዝታዎቼ - በእንግሊዝና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ባለ አስራ አንድ ገጽ ትውስታ ይህን ይላሉ፦ስለ አብዬ መንግሥቱ ለማ (ካም ቲዩብ)-ግንቦት 25-2010 – kAMM Tube / ካም ቲዩብ/
“ሌላው መቼም የማልረሳው ትልቅ ቁም ነገር [መንግሥቱ ለማ] ከታላቁ የአውሮፓ ፈላስፋ ከበርትራንድ ረስል ጋር የተገናኘበትን አጋጣሚ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የወጣቶች ጀግና የነበረው ትልቁ ሊቅ የምዕራብና የምስራቅ አገሮች በሰላም መኖር የሚያስፈልጋቸው ስለመሆኑ ለመግለፅ ወደ ት/ቤታችን ይመጣል፡፡ ታዲያ ፈላስፋው ንግግሩን ይጀምርና እሱ የሚለው ዓይነት ሰላምና አብሮ መኖር በዓለማችን እንዲሰፍን ለማድረግ የሚቻለው ኃያላኑ አገሮች በተቻለ መጠን አንዱ ተሰሚነት ባለው ክልል ሌላው ጣልቃ እንዳይገባ በመከላከል ብቻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በዚህ መሰረት ሰላም ከተፈለገ ሶቪየት ህብረት በምስራቃዊ ግማደ ዓለም ‹‹ዶሚናንት›› እንደሆነች ትቀጥል ዘንድ ሊፈቀድላት እንደሚገባና በአንፃሩም ምዕራባዊያን ኃይሎች ደግሞ በአፍሪካና በአብዛኛው እስያ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዲኖራቸው መደረግ እንደሚኖርበት ይገልፃል፡፡ በዚያን ጊዜ ስብሰባው ይገመሳል፡፡ ጉባኤው በዚህ አስተሳሰብና ፕሮፓዛል መስማማቱና ሰላምን ለማምጣት ያለውም አማራጭ ይኸው ብቻ መሆኑን አሜን ብሎ የተቀበለ መሆኑ ግልፅ ይሆናል፡፡ ለመንግሥቱ ግን ሁኔታው እንዲያ አልነበረም፡፡ አጅሬ ተቀምጦ ከነበረበት አዳራሹ የኋላ አካባቢ ከማንም ቀድሞ በመነሳት ንግግር ማሰማት ይጀምራል፡፡ የአፍሪካ ህዝቦች የማንም ተፅዕኖና ‹‹ዶሚኔሽን›› ሳይኖርባቸው እንደማንም አገርና ህዝብ ነፃ ሆነው መኖር እንደሚፈልጉ በአፍሪካዊነቱ አብራርቶ ገለፀ፡፡ /ይህ የሚሆነው እንግዲህ አፍሪካን ከቅኝ ገዥዎች የማስለቀቁ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ ቢያንስ አንድ አስርት ቀደም ብሎ መሆኑ ሊታወስ ይገባል/ ታላቁ ፈላስፋ ወደደም ጠላ መንግስቱ ሆዬ ሀሳቡን በመቀጠል አፍሪካውያን ከዚያ በኋላ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ለመቀጠል አንዳችም ፍላጎት እንደሌላቸው በማስረዳት ተቃውሞውን በይፋ አሰምቶና ራስልን ያህል ሰው ተጋትሮ ቁጭ አለ፡፡”
እንግዲህ፣ አብየ መንግሥቱ ለማ በዘመኑ ገናን ፈላስፋ ተደርጎ ይሰፈር የነበረውን በርትራንድ ረስልን እንዲህ በዘመነ ሐሳብ በአደባባይ ረትተውት ነበር፡፡ ዛሬ በርትራንድ ረስልን የሚያደንቅ (ምናልባት የሚያመልክ)፣ አብየ መንግሥቱ ለማ ኃይሉ ወልደ ታሪክን የማያውቅ (ምናልባት ከነመፈጠራቸው) ኢትዮጵያዊ ብዙ ነው፡፡
ምን ይበጀናል?
__________________________________________

                  ያንድ ምሽት አሳብ
                       በእውቀቱ ስዩም
በጎረቤቱ የጨከነ ለቤተሰቡ አይራራም (በእውቀቱ ስዩም) - Bawza
በሺህ ፈረስ ጉልበት፥ በሺህ ግመል አቅም
ሺህ ጊዜ ቢራመድ፥ ሰው ከቤቱ አይርቅም::
ስጥል ዋልኩኝና፥ ስወድቅ አመሸሁ
ትግሉ ሲበረታ ፥ ወደ ቤቴ ሸሸሁ ፥
ሌቱ ጣራየ ላይ ፥ እንደ እንጀራ ሰፋ
እፍ አልኩት ኮከቡን ፥ እንደ ኩራዝ ጠፋ::
እንግዲህ ምን ቀረኝ?
ምንድነው ያማረኝ?
ወገግ
ፈገግ -ልበል?
ፊትሽን አስቤ?
አልጋ ላይ ልንበልበል
እንቅልፍን ከጎሬው ፥ እንደ ጋኔን ስቤ?
ወዲህ ውብ ትውስታ፤ ወዲያ ንጹህ አልጋ
የቱ ይመረጣል? ያም ተድላ፥ ያም ጸጋ
ገላ ሲስለመለም፤ ልብ ይቀሰቀሳል
ለጊዜውም ቢሆን
እንቅልፍ እና ፍቅር መከራን ያስረሳል።

Read 1986 times