Sunday, 03 April 2022 00:00

በአለማችን ከሚከሰቱ እርግዝናዎች ግማሹ ያልተፈለጉ ናቸው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በየአመቱ በመላው አለም ከሚከሰቱ እርግዝናዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ያልተፈለጉ እንደሆኑና በአለማችን በየአመቱ 121 ሚሊዮን ያህል ያልተፈለጉ እርግዝናዎች እንደሚከሰቱ ሰሞኑን የወጣ አንድ የተመድ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነህዝብ ተቋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው የ2022 አመታዊ የስነህዝብ ሪፖርት እንዳለው፣ በየአመቱ ከሚከሰቱ 121 ሚሊዮን ያህል ያልተፈለጉ እርግዝናዎች 60 በመቶ ያህሉ በጽንስ ማቋረጥ የሚጠናቀቁ ሲሆን፣ 45 በመቶ ያህሉ ጽንስ ማቋረጦችም ደህንነታቸው ያልተጠበቀ በመሆኑ በርካታ እናቶችን ለሞት በመዳረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአለማችን ያልተፈለጉ እርግዝናዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲበራከቱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችና የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች በበቂ መጠን አለመዳረሳቸው እንደሚገኝበት የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ በመላው አለም 257 ሚሊዮን ያህል ሴቶች የእርግዝና መከላከያ ለመጠቀም ቢፈልጉም ማግኘት እንዳልቻሉ ያትታል፡፡
ያልተፈለገ እርግዝና እንዲጨምር ከሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች መካከል ግጭትና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚገኙበት የሚናገረው ሪፖርቱ፤ ጥናቱ በተሰራባቸው አገራት በስደት ላይ ከሚገኙ ሴቶችና ልጃገረዶች መካከል ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት የወሲባዊ ጥቃት ሰለቦች መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉንም ያስረዳል፡፡

Read 1852 times