Saturday, 02 April 2022 12:02

የዚያን ቀን...

Written by  ሚካኤል አዝመራው
Rate this item
(3 votes)

      ከስራ እንደወጣሁ ሻወር ወስጄ ቺፕሴን አቀራርቤ፣ ሪሞት አንስቼ ልክ ፊልሜን ሳስጀምር... አንድ ወታደር ብቻ የምትመራው ጄነራሏ ፍቅረኛዬ ደወለች።
"ላይብረሪ ውስጥ እያየሁህ አይደለም!" አለችኝ እንዳነሳሁት።
መርህ ትወዳለች። መርህ አልባ ሰው ደግሞ ትጠላለች። እኔም ከሷ እኩል ለመሔድ ከአባቱ ጋር ገበያ እንደሚሔድ ህፃን በሶምሶማ እከተላታለሁ።
"ገና አሁን ቤት መግባቴ ነው። ትንሽ ላረፍድ እችላለሁ!" አልኩ የቲቪውን ድምፅ እየቀነስኩ።
"ተነስ ተነስ አትስነፍ!  ረሳኸው እንዴ?...ይሔን ማስተርስ እንደጨረስን እንጋባለን’ኮ! አልጓጓህም?"
ያዝ እንግዲህ!
ወደ ላይብረሪ ልሔድ ስነሳ ጓደኛዬ ብሩክ እየተጣደፈ ገባ። ሩሀማ፤ “ከብሩክ ራቅ! ማሰቢያህን ደፍኖ በልቡ ብቻ የሚመራ በግ ነው የሚያደርግህ!” ብላ የመከረችኝ ትዝ ብሎኝ፣ ምንም ቢለኝ እሽ እንደማልለው ለራሴ ቃል ገባሁ።
"በፍጥነት ተዘገጃጀህ፤ ዴት አለብህ!" አለኝ ለመረጋጋት እየሞከረ።
"የምን ዴት?" አልኩ ግራ እየተጋባሁ።
"ማርቲን ላገኛት ነበር። አሁን ደውላ ‘ጓደኛዬ አብራኝ ነች፤ ጓደኛህን ይዘኸው ና’ ብላኛለች።"
"አላውቅልህም! እኔ ያንተ ማሟያ ነኝ እንዴ?"
"ይሔኮ ለጓደኝነት ብለህ የምታደርገው ነገር ነው። በዛ ላይ ልጅቷ ሁሉ ነገሯ አንተ የምታስባት አይነት ነች!"
"ሰውዬ፤ ብቻዬን መኖሬን ነው’ዴ የምታየው? ትዳር አለኝኮ!"
"እኔስ መች ተፋታ አልኩህ?"
"እና ምንድን ነው የምትለኝ?"
"እየውልህ! ፈተና ወድቃ ልታፅናናት ነው ያመጣቻት። ከፈለካት አንዴ ለምጠሀት ወደ ትዳርህ ትመለሳለህ። ካልፈለካት ደግሞ ማርቲን ለይቼ እስክወስዳት ብቻ ትይዝልኛለህ።"
“አልፈልግም” እያልኩ እየተከራከርኩት፣ ልብሴን ለባብሼ ወጣሁ። ሩሀማ እንደፈራችው፣ በቁሜ በግ ያደረገኝ መሰለኝ። ራሴን ጠላሁት። ሳወራ ራሱ “በኧኧኧኧ” የሚል ድምፅ ነው የሚሰማኝ።
ክለብ እንደገባን ማርቲ ቀድማ ተነስታ ሰላም ስትለን፣ ተንጠራርቼ፣ በማርቲ ትከሻ በኩል ልጅቷን ለማየት ሞከርኩ። እስከ እግሯ የሚደርስ ጃኬት ለብሳ፣ ፀጉሯ ላይ ሻርፕ ጣል አድርጋለች። ከቅላቷ ጋር የሶሪያ ስደተኛ ነው የምትመስለው። ሩሀማ ስትደውል፤ “ነገ እንገናኝ ደክሞኛል!” የሚል ቴክስት ላኩላት።
ልጅቷ አርባ ደቂቃ ያህል ምንም አላወራችም። ፊትለፊቷ የተደረደሩት ባዶ ጠርሙሶች እየጨመሩ ሲመጡ አፏ እየተላቀቀ መጣ። ማውራት ስትጀምር እንደገና ዝም ብላ የቆየችበት አርባ ደቂቃ ናፈቀኝ። ቆንጅዬ ደደብ ነች። በዚህ እውቀቷ ወደቅኩ ብላ ማዘኗ ገረመኝ! ምን ጠብቀሽ ነበር ሙኒት?
"ና እንደንስ!" አለችኝ ድንገት ከወንበሩ እየወረደች።
"እኔን?" አልኩ በድንጋጤ። ራሷን በአዎንታ ነቀነቀች።
"እንደሱ ብለሽ?" አልኳት ጃኬቷን እያየሁ።
አውልቃ አስቀመጠችው። ከጃኬቱ ውስጥ የሆነች የምታምር ሰው ወጣች። አባቴ በጋዜጣ ጠቅልሎ የሚያመጣልኝን ኬክ አስታወሰችኝ።
ስትውረገረግ ሰውነቷ ገረመኝ! መካከለኛ ቁመት፣ ሸንቅጥ ያለች፣ ነፍሰ ቀላል ነች። እንዲህ አይነት ሴቶች መኝታ ቤት ለአያያዝ ምቹ ስለሚመስሉኝ ይማርኩኛል፡፡
እየደነሰች በጨረፍታ አየት ታደርገኝና ፈገግ ትላለች። ጥርሷን ሳየው ደግሞ ልቤ ሙሙት ይልብኛል። የፈጣሪ ያለህ!
የፈጣሪ ያለህ!
የፈጣሪ ያለህ!
አዳሬን እንዲሁ ስል አነጋሁ። አዳም ሔዋንን ካወቃት በኋላ ለተወሰነ ደቂቃ “እንኳን ከገነት ተባረርኩ” የሚል ስሜት ተሰምቶት ነበር እየተባለ ይታማል። እኔም እንደዛች ያለች ሀሴት ተሰማችኝ። አንሶላ ውስጥ እንዳለሁ ያቺን ለማቀፍ የምትመች ሰው፣ ከጀርባዋ እቅፍ አደረኳት። አውቃለሁ እንደዚህ ማድረግ እንደሌለብኝ። ግን ራሴን ማስቆም አልቻልኩም። ሀምሳ ፐርሰንቱ እኔ፣ መቶ ፐርሰንት ወዷታል።
ወዲያው “ቀጭ” የሚል ድምፅ ከወደ በሩ ስሰማ ደንብሬ ተነሳሁ። የሆነ ሰው ገብቶ ተመልሶ የወጣ መሰለኝ! ያገኘሁትን ታጥቄ ወደ ሳሎን ወጣሁ። ማንም የለም። ዞር ስል የሳሎኑ በር ተከፍቶ እየተወዛወዘ ነው። በፍጥነት በመስኮቱ በኩል አየሁ። ሩሀማ ነች። ፈጠን ፈጠን እያለች ወጥታ ሔደች። አልተመለሰችም።
አንዳንድ ሰው እንደዚህ ነው። ሲገባ አታየውም። ሲወጣ ግን አፈራርሶህ ነው የሚወጣው።
መሔዱን ትሒድ እሺ! እንዴት ዝም ብላ ትሔዳለች? ምናለ ትንሽ ብታዋርደኝ? ምናለበት በሆነ ነገር አናቴን ብላኝ...ተፍታብኝ ብትወጣ? እንዴት ዝም ብላ ወጥታ ትሔዳለች?
***
ከዛን ቀን በኋላ...
ሙኒት ምን እንደተፈጠረ ስላላወቀች፣ ወደኔ ቤት መምጣቷን አላቆመችም።  እኔም ብቻዬን መሆን ስላልፈለኩ “አትምጭብኝ” አልላትም።
ንጥር ንጥር እያለች በአጠገቤ ስታልፍ ቅልም አድርጌ አንሶላ ውስጥ አስገባታለሁ። እሷ ደግሞ በአመቱ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ ታደርጋለች። በሁለት አመት ውስጥ ሁለት ወለድን።  
እበላለሁ፣ እጠጣለሁ፣ እተኛለሁ። በቃ። በግ በሉኝ። አሳማ በሉኝ። በሬ በሉኝ። ብቻ ሰው እንዳትሉኝ።
ሁሌም ቢራዬን ይዤ ቁጭ ስል የማስበው ስለዛች ምሽት ነው። ምናለበት የዛን ቀን ሙኒት “እንደንስ” ስትለኝ እምቢ ብዬ ቢሆን...ምናለበት ያ ብሩክ “ና ክለብ እንሒድ” ሲለኝ፣ “ሰውዬ ውጣልኝ...ቀጠሮ አለብኝ” ብዬ አስደንግጬው ቢሆን...ኧረ እሱንም ተውት፣ ምናለበት ቤት መቀመጡን ትቼ ላይብረሪ ሄጄ ቢሆን...!
***
አንድ የመጨረሻ ቀን...
ከስራ እንደወጣሁ ወደ ቤት ልገባ ስል ለልጆቹ ወተት ሸምቼ፣ ለኛ ደግሞ ቢራ ነገር ልያዝ ብዬ የሆነ ባር ውስጥ ገባሁ። ባርቴንደሩ ጋ ቆሜ እየገበየሁ አንዲት እየጮኸች የምታወራ ሴት ጆሮዬን ነጠቀችኝ። አውቄያታለሁ። ጀርባዋን ሰጥታኝ ስለተቀመጠች ሳታየኝ ለመውጣት ቸኮልኩ። ሁኔታዋ ግን ጥያት እንዳልወጣ ጠፍሮ ያዘኝ።
"ማነህ ና ሙላው ይሔን ብርጭቆ!" አለች እየጮኸች። መጥቶ ሲቀዳላት "ወደ ዳርም በደንብ እያፈሰስከው! እከፍልሀለሁ" አለችው። ልጁ እንደተባለው አደረገ። ከፊትለፊቷ ያለው ጎልማሳ እንደተናደደባት ያስታውቃል።
"አስደበርኩህ እንዴ ወንድሜ? chaos አትወድም?" ስትለው "አልወድም!" አላት!
"ታዲያ ኑሮ እንዴት እያደረገህ ነው?"
"ከባድ ነው!"
"ህግን መጣስ ካልለመድክ ገና እየከበደህ ይሔዳል!" ዝም ሲላት ቀጠለች። "ህግ ካልተጣሰ ምን ጥቅም?"
አሁንም ዝም አላት። በጣም እንደተናደደ ያስታውቃል።
"ዝም ብለህም ንዴትህን መቆጣጠር እንዳቃተህ ታስታውቃለህ። ለቀቅ በል ወዳጄ። እዚህ ላንተ ስሜት ግድ ያለው የለም። ቀውስ ውስጥ መኖርን ብትለምድ ይሻልሀል። የአጥብቆ መያዝ ትርፍ ከሁሉ ቀድሞ መልቀቅ ነው!"
ሹልክ ብዬ ልወጣ ነበር። ሰውዬው ቦግ ብሎ ሲነሳባት፣ ሳልፈልግ ጣልቃ ገባሁ። ስታየኝ ደንግጣ ፊቷን ደረቴ ውስጥ ደበቀች። የኔ ሩሀማ...የኔ ምህረት የሚገባት ሴት! እኔ አንገቴን ልድፋ!
ከባሩ አፋፍሼ ካስወጣኋት በኋላ ራይድ ጠራሁላት።
"በዚህ መልኩ ባታየኝ ደስ ይለኝ ነበር።" አለች በሚያሳዝን ድምፅ።
"እኔን ከዚህ በባሰ ሁኔታ አይተሽኝ የለ?" አልኩ!
"እእእእ.....ልጆቹ ደህና ናቸው?"
"ደህና ናቸው።"
"ጥሩ!"
ዝም ዝም ተባባልን። ዝም አባባሏ የበፊቱን ዝምታዋን እያስታወሰ ረበሸኝ።
"በጣም ይቅርታ!" አልኩ በጭንቀት!
አሁንም ዝም አለችኝ።
"አውቃለሁ ብዙ ነገር እንዳበላሸሁብሽ። ግን እመኝኝ፣ ያንቺ ብቻ አይደለም የኔም ህይወት ተመሰቃቅሏል። ዛሬም ድረስ እወድሻለሁ ሩሀማ። ያንድ ቀን ስህተት ነው ህይወቴን ያበላሸው። እወድሻለሁ ብያት ራሱ አላውቅም። እሷ ለኔ ሀላፊነት ብቻ ነች።"
ከመሄዷ በፊት የሚሰማኝን ሁሉ እንድታውቅልኝ ቀበጣጠርኩ።
እሷ ግን በዝምታዋ ፀናች። ራይዱ ሲመጣ ዝም እንዳለች ጥላኝ ልትገባ ስትል አልቻልኩም። "በናትሽ የሆነ ነገር በይኝ! ዛሬም በዝምታ ከሔድሽ አብዳለሁ!" ብዬ ጮህኩባት።
በቀስታ ወደኔ ዞረች።
"አይቼሀለሁ’ኮ የዛን ቀን!" አለችኝ በቀዘቀዘ ድምፅ። ፊቷ ላይ ያለው ጭካኔ ስካሯን አጥፍቶታል። ፍርሀት ተሰማኝ።
"አይቼሀለሁኮ የዛን ቀን! የአንድ ቀን ስህተትማ አይደለም። ድንገት የተሳሳተ ሰው፣ ጧት ሲነሳ እንደዛ አይደለም የሚሆነው። አንተ ማመን አልፈለግክም እንጂ፣ ከኔ ‘ህግ’ የበዛበት ህይወት ማምለጫ ስትፈልግ ነው የኖርከው...
"አይቼዋለሁ አስተቃቀፍህን! ከ’እወድሻለሁ’ም ይበልጣል። ‘ታስፈልጊኛለሽ’ ነው ያልካት። ለሴት ልጅ ከዚህ የበለጠ ምን አለ? ለዛ ነው በፍጥነት የወለደችልህ። ከንግግርህ ይልቅ አስተቃቀፍህ መተማመኛ ሰጥቷት ነው ያመነችህ። አንተም ቃል አውጥተህ እወድሻለሁ የማትላት ስለማትወዳት አይደለም። የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማህ ነው። በኔ በኩል ይቅርታ ካደረኩልህ ቆይቻለሁ። አንተ ነህ ራስህን ይቅር ያላልከው።" ብላኝ ወደ መኪናው ገባች።
መኪናው ሲሔድ እኔ ቆሜ ቀረሁ። መውጣት የጀመረው እንባዬ ደርቆ ሁለመናዬ ደነዘዘብኝ። የያዝኩትን ወተትና ቢራ መሬት ላይ አስቀመጥኩት። እኔም ተቀመጥኩ። ህመም ተሰማኝ። ያጠጣችኝ መድሀኒት መስራት ጀመረ።Read 720 times