Sunday, 03 April 2022 00:00

ፅናትና እልኸኝነት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

"እልኸኝነት በእግዚአብሔርም የተጠላ ነው፤ እልኸኛ ሰው ከራሱ ጋርም የተጣላ ነው፡፡ እልኸኞች አጥፍቶ ጠፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም መንገዳችንን እንመርምር እንፈትን፣ በፅናትም ወደ መልካም ነገር እንገስግስ!"

              ፅናት ለሚለው (Perseverance) እልከኝነት /ግትርነት/ በሚለው ደግሞ (Obstinacy /Obstinate/) የተባሉት የእንግሊዝኛ ቃላት አቻዎቻቸው ናቸው፡፡
የፅናት መነሻውም መድረሻውም መልካምነት፣ሰላምና ዕድገት ነው፡፡ ፅናት አዎንታዊነት ይበዛበታል፡፡ እልኸኝነት ደግሞ መሠረቱ ቅናት፣ ተጋፊነትና ግድየለሽነት ነው። ዕድገትንም የሚያስበው በሌሎች መውደቅ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡
የቀደመው ዘመን የአሜሪካ ዕድገት፣ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ውድቀቷ በኋላ ጃፓን በአጭር ጊዜ የተቀዳጀችው ሥልጣኔ፤ የቻይና ከድህነት መላቀቅና ማደግ የፅናት ተምሳሌት ናቸው፡፡ በተለይም ቻይና ከሰባት መቶ ሰማንያ ሚሊዮን /780,000,000/ በላይ ሕዝቦቿን ከድህነት አዘቅት አውጥታ ለዛሬው ዕድገት መብቃት፣ የእነ አሜሪካ ኢኮኖሚስቶችና ባለሙያዎች ጭምር ጉድ የተሰኙበት ነው፡፡
እልኸኞቹ /ግትሮቹ/ የጀርመኑ ናዚ ሂትለርና የኢጣሊያው ፋሽስት ሙሶሊኒ ደግሞ ሃገራቸውን ጎድተው፣ የአለምንም ሕዝብ ጦርነት ውስጥ ማግደው ከፍተኛ እልቂት አድርሰዋል፡፡
ፅናት በግለሰብም ደረጃ ብናየው ግቡ ካለበት ዝቅተኛ ኑሮ፣ ራሱን በተገቢው መንገድ ጥሮ-ግሮ ማሻሻል ነው፡፡ ይኸውም በመማር፣ የመፍጠር ችሎታን በማሳደግ፣ ከሌሎች ተገቢ ድጋፍ በማግኘትና የመሳሰሉትን በመጠቀም ሊሆን ይችላል፡፡ እልኸኛው /ግትሩ/ ሰው ደግሞ እሱ ላለበት ዝቅተኝነት ምክንያቱ ሌሎች ናቸው በማለት ይጀምራል፡፡ ስለዚህ እኔ እንዳድግ ሌሎች መውደቅ አለባቸው ይላል፡፡
ከሃይማኖትም አንፃር ብንመለከት ፅናት ያለው ሰው፣ የራሱን ሃጢአት ይገነዘብና ከልብ ንስሃ ይገባል፣ ይፆማል፣ ይፀልያል። እልኸኛው /ግትሩ/ ግን ስለ ክፉ ሥራው ተፀፅቶ ሳይሆን፣ በግብዝነት ወይም በማስመሰል ይቀርባል፡፡
በፅናት አለም አቀፍ ድርጅቶችም ተወልደዋል፡፡ የቀይ መስቀል ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ አንድነት /ሕብረት/፣ የጤና ተቋማት፣ የኢሎምፒክ ውድድሮች፣ ኢንተር-ፖል ወዘተ፡፡ የዚህ ተቃራኒ ደግሞ አሉ፤ አክራሪና በዕልቂት ላይ የተመሰረቱ አካባቢያዊና አለም አቀፋዊ “ሃይማኖት" መልስ ድርጅቶች፣ ዶፒንግ ተጠቃሚዎች ወዘተ--
ልብ ካላችሁ፤ ለመልካም ነገር፣ በግለሰብም ይሁን በሃገር አቀፍ ደረጃ በፅናት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች፤ ጥርት ያለ አላማና ግልፅ የሆነ ስልት ስላላቸው፣ ዘለቄታዊ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ግትሮቹ አላማቸው ተለዋዋጭነት ይታይበትና፣ ስልታቸውም በሐሰት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ለትብብር አይመቹም፣ ገልበጥባጣ ናቸው፡፡
ድክመቱንም ጥንካሬውንም በግልፅ ስለሚያወያይበትና ለሕዝብ ክፍት ስለሚያደርግ፣ በፅናት የሚደረግ ጉዞ ክስረት አይበዛበትም፡፡ እልኸኛው ግን በተለይ ድክመቶቹን በሌላው ላይ ያላክካል፡፡ (Scapegoat)፣ እናም ማምለጫ ይፈልጋል እንጂ አያምንም፤ ስለዚህም ውሸትን በውሸት ላይ፣ ሽንፈትን በሌላ ሽንፈት ይደራርባል- እስከሚወድቅ ድረስ፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታም፣ ሌሎች ስፖርቶችም ከዚህ እውነታ አይርቁም፤ ተዘጋጅቶና በጥሩ ጨዋታ ብቻ ለማሸነፍ የገባ ቡድን በፅናት ቆይቶ፣ የባከነ ጊዜንም ተጠቅሞ ለድል ሊበቃ ይችላል-ይህ ቡድን አቤት የደጋፊው ብዛት!! ያኛው ግን - እልኸኛው ግን - በተለይማ በቅድሚያ ጎል ከገባበት፣ ፋውል ጨዋታ ያበዛና የመከላከልም ሆነ የማጥቃት ስልቱ ተበላሽቶበት ሊሸነፍ ይቸችላል፡፡
በሌላ በኩል፤ ጎበዝ ተማሪ የሚባለው በራስ መተማመን ያለው፣ በሚገባ አጥንቶ በፅናት ፈተናውን የሚያልፍ፣ ዝቅተኛ ነጥብ እንኳን አንዳንዴ ቢገጥመው፣ የእኔ ድክመት ነው የሚል ነው፡፡ ግትሩ /ሰነፉ/ ግን ሰበብ ያበዛል፣ ኮራጅ ነው፤ ደግሞም ከስህተቱም አይማርም፤ በዚሁ ከቀጠለ ለራሱም፣ ለቤተሰቡም . . . . አይበጅም፡፡
የሰከነ ውይይት፣ ግልፅ የሆነና ለሁሉም የሚታወቅ ስትራተጂ ለእልኸኞች አይጥማቸውም- ድብቅ ነገር አያጡምና!! ማንም ይሁን ምንም የሚደጉማቸው ከሆነ ወዳጅ ያደርጉታል፡ በፅናት የሚጓዘው ግን ከእነዚህ ነገሮች የፀዳ ነው፡፡ ለትውልዱ ያስባል፤ መልካም ነገርም ልተውለት ይላል-በፅናት የሚታገል ሰው፡፡ "እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" ደግሞ የእልኸኞች መርህ ነው- ለትውልድ ማሰብ አይሆንለትም፡፡
መልካሞች በትክክል ያፈሩትን ሃብታቸውን ለመልካም ነገር እንዲውል ይናዘዙና ይሰጣሉ- የኖቤል ሽልማት ድርጅት ምሥረታ ለዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ወይም ጊዜንና ሥራን ሁሉ ለመልካም ማዋል- ማዘር ቴሬዛ ምሳሌያችን ናቸው፡፡ የእኛዋ አበበች ጎበናም ጥሩ አርአያችን ናቸው፡፡
ቆም ብለን እናስተውል፤ አንዳንድ ጊዜ ለበጎ ነገር የተጀመረ የፅናት ጉዞ፣ የተወሰነ ውጤት ካመጣ በኋላ በአመራር ብልሹነት አቅጣጫ ሊስት ይችላል፡፡ አፍሪካችንን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ አብዛኞቹ የነፃነት ትግሎች በነጮቹ ገዥዎች ላይ ድልን ከተቀዳጁ በኋላ፣ ሥልጣን የጨበጡት የሀገሬው መሪዎች ከመሪነት ላለመውረድ ሲሉ ግትር ሆነው፣ ነፃ ምርጫን ከልክለው፣ ሕዝባቸውን በድህነት እንዲማቅቅ አድርገዋል፡፡
እልኸኝነት በእግዚአብሔርም የተጠላ ነው፤ እልኸኛ ሰው ከራሱ ጋርም የተጣላ ነው፡፡ እልኸኞች አጥፍቶ ጠፊዎች ናቸው። ስለዚህም መንገዳችንን እንመርምር እንፈትን፣ በፅናትም ወደ መልካም ነገር እንገስግስ!


Read 1351 times