Saturday, 02 April 2022 11:46

የድሆች የጤና ዋስትና በሰሜን ሸዋ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ሣቢያ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የጤና ተቋማት ዋነኞቹ ናቸው፡፡  የህወኃት ታጣቂ ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በፈፀመው መጠነ ሰፊ ወረራ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪ ህዝብ፣ የህክምና አገልግሎትን ሲሠጡ የኖሩት እነዚህ ተቋማት፣ በአሸባሪው ሃይል ሙሉ በሙሉ እንዲወድሙ አሊያም ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡
ከእነዚህ በጦርነት ሳቢያ ለከፋ ጉዳት ተዳርገው አገልግሎት መስጠት አቁመው ከነበሩት የጤና ተቋማት መካከል በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማና ቀወት ወረዳ ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማትን  በማገዝ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በማድረጉ ረገድ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሚያከናውናቸው ተግባራት ከፍተኛ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ተቋሙ በነዚሁ ወረዳዎች ውስጥ በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስጎብኝቶ ነበር፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማና ቀወት ወረዳ ውስጥ በጦርነቱ ሳቢያ የገጠማቸው ችግር አልፈው ወደ መደበኛ ስራቸው የተመለሱ የጤና ተቋማት የጉብኝቱ አካል ነበሩ፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የሰሜን ሸዋ ዞን ቀውት ወረዳ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰይድ ሃሰን ገበየሁ እንደተናገሩት፤  በወረዳው ከሚገኙና በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ደርሶባቸው አገልግሎት መስጠት ካቆሙ የጤና ተቋማት መካከል 3 ጤና ጣቢያዎችንና 18 ጤና ኬላዎችን የጤና መድህን አገልግሎቱ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል፡፡ ተቋማቱ  በጦርነቱ የወደመባቸውንና ጉዳት የደረሰባቸውን የህክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶች በማሟላት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ በማድረግ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ጤና እና ህይወት ለመታደግ ችሏል፡፡
በሸዋሮቢት ከተማ በሚገኘው የጤና ጣቢያ ውስጥ ያገኛቸው በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነግሩን፤ በጦርነቱ ወቅት የጤና ተቋማቱ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ባለመቻላቸው፣ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት ተጋልጠዋል፡፡ ወራሪው የህወኃት ኃይል ከተማውን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ዘጠኝ ቀናት፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሸዋሮቢት ከተማ ጤና ጣቢያ ዛሬ በሙሉ አቅሙ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከ62 ሺ በላይ ለሆነው የሸዋሮቢት ከተማ ህዝብና ለቀወትና አጣዬ ወረዳዎች እንዲሁም በአፋርና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነዋሪ ለሆኑና ከ100 ሺ በላይ ለሚጠጉ ህዝቦች አገልግሎት በመስጠት ለይ የሚገኘው ይህንኑ ጤና ጣቢያ፤ የዞኑ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና  መድን ቢሮ ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ በማድረግ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡
በዚሁ ጤና ጣቢያ ህክምናቸውን ለመከታተል መጥተው ያገኘናቸው  የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በጦርነቱ ወቅት በጤና ጣቢያው ላይ በደረሰ ጉዳት ሳቢያ አገልግሎት መስጠት በተቋረጠባቸው ጊዚያት እጅግ ለከፋ ችግር ተጋልጠው   እንደነበር ነግረውናል፡፡ የአካባቢው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸውም ህክምና ለማግኘት  ያጋጥማቸው የነበረው ችግር ተቀርፎ ህመም በተሰማቸው ጊዜ ሁሉ ያለ ሃሳብ ህክምና ማግኘት መቻላቸውን ይገልፃሉ “እንደእኛ ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ምንም ጥሪትና አቅም ለሌለው ችግረኛ፣ የጤና መድህን የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው” የሚሉት  ነዋሪዎቹ፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ከቀን ወደ ቀን እየናረ የመጣውን የህክምና ወጪ ችሎ ለመታከም አንችልም ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአባላት ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ጉደታ አበበ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ማህበረሰብቡን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ፣ ህብረተሰቡ እንደ አቅሙ አዋጥቶ፣ እንደ በሽታው እንዲታከም በማድረጉ ረገድ የተሳካ ስራ  ተሰርቷል ብለዋል፡፡ በአማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና ደቡብ ክልሎች በ13 ወረዳዎች ውስጥ የተጀመረው የጤና መድህን አገልግሎት፤ በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በ853 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ 8.9 ሚሊዮን አባወራዎች ወይም እማወራዎችን አቅፎ በአጠቃላይ ከ40 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል፡፡
የጤና መድህን አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ለህክምናው የሚያወጣውን ያልተጠበቀ ወጪ በማሰቀረት ፍትሃዊ የሆነ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር ለማድረግ ያስችላልም ተብሏል፡፡ አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ለህክምና የሚጠየቀውን የከፍተኛ ወጪ ፍራቻ  ወደ ህክምና ተቋማት ከመሄድ እንዳይታቀብ በማድረግ፣ በማንኛውመ ጊዜና ሁኔታ ህመም ሲሰማው ወደ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በመሄድ፣ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እንዲችል ያደርገዋል ተብሏል፡፡

Read 374 times