Saturday, 02 April 2022 11:15

በአይነቱ ለየት ያለው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ነገ ይጀመራል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   “ገብርሄር” የጤና እና ማህበራዊ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት፣ የአቢይ ፆምን ምክንያት በማድረግ፣ ከነገ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
በአጠቃላይ በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ፤ “በገብርሄር” አላማዎችና ተግባራት ዙሪያ ትናንት (አርብ)  የተቋሙ አመራሮች ለጋዜጠኞችና ለአርቲስቶች እንዲሁም ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከድርጅቱ መስራቾችና  አመራሮች አንዱ የሆኑት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የስነ አዕምሮ ሃኪምና መምህር የሆኑት  ዶ/ር እንግዳ ግርማ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡


                  ይህን ልዩ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ለማድረግ መነሻ ምክንያቱ ምን ይሆን?
መነሻው በጎ ማድረግ ቸርነት ነው። ፕሮግራሙም ሲዘጋጅ በዋናነት ለሰዎች በጎነትን ማሳየት ማበረታታት ነው፡፡ ሰዎች አንዱ ያላቸውን በጎነት የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ደግሞ ደም በመለገስ ነው። ስለዚሁ ከነገ እሁድ ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰፊው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ለማድረግ ነው ያሰብነው፡፡ ይሄን መርሃ ግብር ለማሳካት የተለያዩ ድርጅቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበንላቸዋል። ሠራተኞቻቸው ታማኝ፣ ቅን፣ ሰውን የሚያከብሩ እንዲሆኑ ለብዙ የጤና ድርጅቶች መልዕክት ልከንባቸዋል። እነሱንም በዚህ የተቀደሰ አላማ ይሳተፋሉ። ይሄ እንግዲህ የመጀመሪያችን ነው፡፡ ትልቁ አላማችንም በየአመቱ መከናወን የሚችል እንደ ባህል የሚሰርፅ መርሃ ግብር መጀመር ነው፡፡ ይሄ ባህል በየአመቱ “የገብርሔር” ሳምንት ብለን ሰዎች መልካም ነገርን የሚያደርጉበት ደግሞ ሠራተኛው ጠንካራ ስነ ምግባር ያለው የስራ ባህልን እንዲያዳብር መሰረት መጣያ  ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡
እንዴት ባለ ሁኔታ ነው መርሃ ግብሩን የምታከናውኑት?
ይሄ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ለሳምንት ነው የሚካሄደው፡፡ በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ማዕከላት ማህበረሰቡ፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲያቸው የደም ልገሳውን እንዲያከናውኑ ተመቻችቷል፡፡ ሌሎችም በስራ አጋጣሚ የሚንቀሳቀሱ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ካሉ የደም መለገሻ ቦታዎች ባሻገር በዋናነት ባምቢስ አካባቢ የቀድሞ ዮርዳኖስ ሆቴል አሁን መቅረዝ ሆስፒታል እየተቋቋመበት ያለው ሀንፃ ውስጥ መለገስ ይችላሉ  ደም መለገስ የሚችሉ ሁሉ ሳምንቱን በሙሉ በእነዚህ ማዕከላት መለገስ ይችላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በቀጣይ ቅዳሜና እሁድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስፋት ደም የሚለግሱበት መርሃ ግብር ይኖረናል። ከአዲስ አበባ ለሃይማኖት ጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱ ደግሞ ይኖራሉ፤ በተለይ  ማህበረ ቅዱሳን ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን ይዞ በሃይማኖታዊ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ውጪ ይጓዛል ። ስለዚህ እነሱም ይሄን ሃሳባችንን በየሄዱበት በህብረተሰቡ እንዲያሰርጹልን እንዲሁም እነሱም በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ያደርጋል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ የት የት አካባቢዎች መርሃ ግብሩ ይካሄዳል?
በአርባ ምንጭ፣ አዋሳ፣ አዳማ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ብርሃን፣ ጅማ ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ላይ ይካሄዳል፡፡
ቅዳሜና እሁድ በተለየ መልኩ የተመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው?
አዎ ቅዳሜና እሁድ ላይ በተለየ መልኩ ትኩረት ያደረግነው ብዙ  የሚጾሙ ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎች ፆም ላይ ውለው ወይም ፆም ላይ ሆነው ደም  ሲለግሱ ምናልባት በጾሙ ምክንያት ግፊታቸው የቀነሰ ነው የሚሆነው። በዚያ ላይ ደግሞ “ኑ እና ደም ለግሱ” ማለት ትንሽ ከጤና አንፃር አስቸጋሪ ነው፡፡ ራስ ማዞር፣ማጥወልወል የመሳሰሉት ችግሮች ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለን። ቅዳሜና እሁድ ግን በማንኛውም ሁኔታ ምግብ መመገብ ስለሚቻል ሰዎች ደም ለመለገስ አይቸገሩም፡፡
ይሄን ፕሮግራም በፆም ወቅት ለማካሄድ ለምን መረጣችሁ?
በቀጣይም መርሃ ግብራችን የሚሆነው በፆሙ ወቅት ነው፡፡ ይሄ የሆነው ብዙ ሰው መልካም ነገር ለማድረግ የሚነሳሱበት ወቅት ስለሆነ ነው፡፡ ይሄን የሰዎችን በጎ የማድረግ ፍላጎት መነሻ በማድረግ፣ በሃገራችን አዲስ ባህል እንዲፈጠር ነው የምንሻው፡፡ ሁሉም በየአመቱ እንዲህ  ቢያደርግ ፣መንግስትም ቢደግፈን  በጣም  ውጤታማ ባህል ማድረግ ይቻለናል፡፡
ምን ያህል ዩኒት ደም  ለመሰብሰብ ነው  ያቀዳችሁት?
እርግጥ ገና የመጀመሪያችን ነው፡፡ ልምዱ የለንም፡፡ በመሃል ሊገጥመን የሚችሉ ችግሮች ምን እንደሚሆኑ በጥልቀት አናውቅም፡፡ ግን እኔ እንደምገምተው ከ2 ሺ እስከ 4 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ እንችላለን፡፡ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡
“ገብርሄር” ተቋም መቼ ተመሰረተ? ምን አላማ አለው?አጠቃላይ ስለተቋሙ ይግለፁልኝ እስቲ?
“ገብርሄር” የተቋቋመው በ2013 ግንቦት ወር ነው፡፡ ገና አንድ ዓመት አልሞላውም፡፡ በመንግስት እውቅና ሰጪ አካል የተመዘገበና እውቅና ያለው ነው። ትልቁ አላማው ሰዎች በጎ የማድረግ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ፣ፍላጎታቸውን እውን  እንዲያደርጉ እንደ ድልድይ ሆኖ ማገልገል  ነው፡፡ ይሄ የአገር ውስጥ አቅም እያለን እስከመቼ ነው የውጭ ሀገራትን እጅ እየጠበቅን የምንኖረው? ለምን ይሄን የራሳችንን አቅም አንጠቀምም? በሚል ራሳችንን በራሳችን መርዳት እንችላለን በሚል ፍልስፍና ይዞ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡
ከተቋቋመ በኋላ እስካሁን ምን ተግባራት አከናውኗል?
ለጊዜው በማህበራዊና ፣በጤና ጉዳዮች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ የጤና ጉዳይን በተመለከተ እንግዲህ እዚህ ሃገር ላይ ባለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በስፔሻሊስት የሚታከም እንዳለ ሁሉ፣ ሃኪም እንኳ የማያየው በወረርሽኝ  የሚያልቅ ደግሞ አለ። ይሄን ሃኪም እንኳ አይቶ የማያውቀው በምን በኩል እንድረሰው ብለን ስናስብ፣ አንዱ መንገድ ድንገተኛ የጤና ዘመቻ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በየቦታው የጤና መስጫ  ማዕከላት ማቋቋምና ከተለያዩ አካላት የህክምና ቁሳቁሶችን አሰባስቦ ተቋማትን መደገፍ፣የተለያዩ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን በማሳተፍ የህክምና ዘመቻዎችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነቱ ዝቅተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎች ማድረግ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን የሰራናቸውን ለመጥቅስ ያህል ደግሞ በተለይ በጦርነቱ ወቅት፣ ጦርነቱ ሰሜን ሸዋ በደረሰ ጊዜና ደብረ ብርሃን ላይ በጣም ብዙ ተፈናቃዮች ተረጂዎች በነበሩበት ሰዐት 1.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መድሃኒትና ምግብ ነክ እቃዎች ይዘን ሄደን፣ ለህብረተሰቡ ሰጥተናል፡፡ ከዚያ በመለስ 65 የሚሆኑ ስፔሻሊስቶች አጠቃላይ ሃኪሞችና ነርሶች ይዘን ለመከላከያው ለህዝቡ ህክምና ሰጥተናል። ለዩኒቨርስቲው ሆስፒታልም የተለያዩ መድሃኒቶች  አስረክበናል። ከዚህ ባሻገር “ባዩሽ ኮልፌ” የሚባል የወጣቶች ድርጅት አለ፡፡ አረጋዊያንን ይረዳል፡  እነዚያን አረጋዊያንን አክመናል፤ የሚያስፈልጋቸውን  መድሃኒቶች ሁሉ ሰጥተናል፡፡ ከዚህ ባለፈ መድሃኒቶች በየጊዜው መግዛት ስለማይችሉ የጤና መድህን ገብተንላቸዋል በየአመቱ መድሃኒት በነፃ እንዲያገኙ ማድረግ ጀምረናል።
በማህበራዊ ዘርፍ ደግሞ  ብዙ እቅዶች አሉን። የድሃ ድሃ የተባሉ ሰዎችን ከወረዳዎች ጋር በመቀናጀት በየአመቱ እያሰለጠንንና የገንዘብ ድጋፍ እያደረግን፣ በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ማገዝ ነው እቅዳችን። ሁለተኛው ደግሞ የተቸገሩ ወላጅ አልባ ልጆችን በገንዘብ እየረዱ ባሉበት ቦታ ሆነው ማደግ የሚችሉ ሰዎችን አስተባብረን የምንሰራው ይሆናል፡፡ እኛ የልጆች ማሳደጊያ ማዕከል አንመሰርትም፡፡ ምክንያቱም በስነ ልቦናም አይመከርም፡፡ እኔ እንደ የስነ አእምሮ ሃኪምነቴ የምመክረው፣ ልጆች በአንድ ማዕከል ተሰባስበው እንዲያድጉ ማድረግ ነው፤ ስለዚህ እኛ እዚያው ባሉበት ለምሳሌ ወላጆቻውን ያጡ ነገር ግን  ከቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር ያሉ ልጆችን መዝግበን፤ የሚያስፈልጋቸውን ለይተን፤ ለአሳዳጊዎች አደራ እንሰጣለን፡፡
እስካሁን ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች 180 ልጆች በዚህ መልኩ መዝግበን እያሳደግን ነው፡፡ አንድ ልጅ ለማሳደግ 6 መቶ ብር በወር  ያስፈልጋል። ስለዚህ አንድ ሰው  በወር 6 መቶ ብር ከፍሎን አንድ  ልጅ የማሳደግ  እድል ያገኛል ማለት ነው፡፡ ይሄን ስራ የጀመርነው ከራሳችን የቦርድ አባላት ነው፡፡ ሁሉም የቦርድ አባላሎች በየወሩ 6 መቶ ብር እየሰጠን፤ የየራሳችንን ልጆች እናሳድጋለን። ከዚያ ባሻገር በጦርነቱ የፈራረሱ የጤና ተቋማት በተለይ ካላቸው ርቀት የተነሳ ማንም ሰው ሊረዳቸው አይችልም ያልናቸውን መርጠን፣ ወደ 18 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ለጤና ሚኒስቴር እና ለሌሎች ድጋፍ አድራጊዎች በመላክ ይሁንታ አግኝተን፣ አሁን ገንዘብ እያሰባሰብን ነው፡፡ ገንዘቡን ሰብስበን የጤና ተቋማቱን መልሰን እናቋቁማለን፡፡ በተጨማሪም በዋግኸምራ አካባቢ ያለውን ህብረተሰብ የስነ ልቦና እና የጤና ሁኔታን ለመመለስ የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፀንም እየተንቀሳቀስን ነው። ገብርሔር በቦርድ የሚመራ ድርጅት ነው 13 የቦርድ አባላት አሉት፡፡ የቦርድ አባላት የህክምና ፣የግብርና የትምህርት ፋይናንስ ባለሙያዎች ናቸው፡፡


Read 405 times