Saturday, 26 March 2022 15:51

“ከባዶ ላይ መዝገን” - አጭር ዳሰሳ

Written by  ቴዎድሮስ አጥላው
Rate this item
(0 votes)

     መግባቢያ
ይህ ጽሑፍ “ከባዶ ላይ መዝገን - የዘመን ስካር ቅንጣቶች” የተባለው የደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ አዲሱ የ“ፍልስፍናዊ፣ ሂሳዊ እና ተብሰልስሎታዊ” መጣጥፎች መድበል፣ ወደ ሰው እጅ ገብቶ መልሶ መወያያ፣ መነጋገሪያ፣ መማማሪያ እና መወቃቀሻ እንዲሆን ከመሻት የመነጨ የማስተዋወቂያ፣ ከደራሲው እና ከሥራዎቹ የማግባቢያ ዳሰሳ ነው፡፡
በዚህ ጽሑፍ  የመጽሐፉን የመጨረሻ ረቂቅ ሳነብ ያገኘኋቸውንና መጽሐፉን ለአንባቢ ይጋብዙልኛል ብዬ ያሰብኳቸውን ሐሳቦች አመቺ በመሰለኝ ቅጥ አቀርባለሁ፡፡
መጽሐፉ ደራሲው ያዕቆብ ብርሃኑ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ለአንባቢ ያደረሳቸውን ሃያ መጣጥፎችና አንድ ከመጣጥፎቹ ተርታ ሊመደብ የሚገባውን ቀዳሚ ቃል የያዘ መድበል ነው። በጋዜጦችና መጽሔቶች ታትመው የነበሩ መጣጥፎችን ሰብስቦ በመጽሐፍ ቅርፅ ማሳተም የአንድ ሰሞን ፋሽናችን የነበረ፣ የችርቻሮ አሳታሚዎች ሳይቀሩ የጋዜጣ ጽሑፍ የላችሁም ወይ እስኪሉ ተፈላጊም የነበረ ዘዴ ነው፡፡ ያዕቆብ ሥራዎቹን በስብስብ/ በመድበል ቅርፅ ሲያደራጅ፣ በእያንዳንዱ መጣጥፍ ላይ ሐሳቦቻቸውን የማዳበር፣ ቋንቋቸውንም በጥቂቱ የመቃኘት፣ ቅርጻቸውንም የመጽሐፍ የማድረግ ክለሳ አድርጎባቸዋል፤ ልዩነቶቹን በዝርዝር ለማየት ንጽጽራዊ ንባብ ቢጠይቅም፣ በምሳሌነት ግን መጽሐፉን የገለጠ ሁሉ የሚያያቸውን የግርጌ ማስታወሻዎች ማንሣት ይበቃናል፡፡
መጣጥፎቹ እንዴት ያሉ ናቸው? ዓላማዎቻቸው (ስለምኖቻቸው/ ግቦቻቸው/ ተግባሮቻቸው) ከመሰሉኝ ነገሮች አንጻር የሃያዎቹን መጣጥፎች ባሕርያት በ3 መድቤ እንደሚከተለው ቃኝቻቸዋለሁ፡-
አስረጅ - በያኝ
ቀዳሚ ቃል ባለው መግቢያው ላይ ያዕቆብ፣ “በእነዚህ ገጾች ላይ የምታነቧቸው ሀቲቶች ለመተከዣ የሚሆኑ ጥቂት የነገር ሰበዞች ማቀበል ከተቻለ በሚል ቀና ምኞት የተሰነዘሩ የአንድ ወጣት ትንፋሾች ናቸው” ብሎ ሥራዎቹን በጥቅሉ ያስተዋውቃል፡፡ እንዳለው በዚህ መጽሐፍ የተለያዩ “የነገር ሰበዞች” ተመዘዋል፡፡ ያዕቆብ መላልሶ ያሰበባቸውን፣ የተብሰለሰለባቸውን፣ የቆዘመባቸውን ሐሳቦች እስከጻፈባቸው ጊዜ ድረስ በተረዳውና ባመነው ልክ በዚህ መጽሐፉ አቀብሎናል፡፡ አበክሮ የሚበይናቸው፣ ማስረጃዎችና ደጋፊ ሐሳቦችን ከተጻፉም ካልተጻፉም ምንጮች እየጠቀሰ የሚያብራራቸው በርካታ ሐሳቦች በዚህ መጽሐፍ አንስቷል፡፡ ውበት እና ከንቱነት፣ ለብቻ መቆም እና መጀመል፣ አንሶስያት (በእግር መንሸራሸር) ድርሰት፣ ራሷ ኪነት እና ከያኒነት፣ ሐዘን እና ፈጠራን የመሳሰሉ ሐሳቦችን በመጣጥፎቹ ውስጥ ተንትኗል፡፡ ለድምዳሜዬ ጥልቅና የመስመር በመስመር ንባቦች ድጋፍ ያስፈልገኛል እንጂ፤ በእስካሁኑ ዕይታዬ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተደጋግመው ከሚመላለሱ (recurring) ሐሳቦች አንዱ የብቻነት (solitude) ሰበካው ነው፡፡
በያዕቆብ ንግግሮችም ሆነ ጽሑፎቹ ውስጥ የመጀመል ወይም በወል የመነዳት ጥላቻና ነቀፌታ አድምጫለሁ፤ አንብቤያለሁ፡፡ በዚህ መጽሐፉም ተደጋግመው የሰማኋቸው ድምጾች ቢኖሩ ማንም ሰው ከመንጋ ተነጥሎ ብቻውን መቆም አለበት የሚሉ ናቸው። ብቻ መቆምን ከሥልጣኔ፣ ከኪነትና ከሕይወት ጋር እያስተያየ ሲበይነው፣ ሲተነትነውና ፕሪስክራይብ ሁሉ ሲያደርገው እናነባለን፡፡
በዚህ ረገድ “መነጠል እና መጀመል” (`Solitude and Crowd`) ያለው ሥራው ዋነኛ የተደጋጋሚ ሐሳቦቹ መቋጠሪያ ወይም ማረፊያ ይመስለኛል፡፡ ካሙን ጠቅሶ፤ “አያትህን መብለጥ ካልቻልክ እስካሁንም ሞተህ መቀበር ነበረብህ” በማለት የታሪክ ዛዝላህን ከላይህ ላይ አላቅቀህ፣ የዛሬውን አንተን ነኝ ብለህ በራስህ ቁም ይላል፡፡ አንግሥ ማርቲንን ምስክር ጠርቶ ደግሞ፤ “መልካም ነገሮች የሚከሰቱልህ ብቻህን ስትሆን ነው” በማለት ከጀመዓው ነጠል በል፣ ከክራውዱ ወጣ በልና የኪነት ጥሪህን አድምጥ፤ የወል ሳይሆን የግልህን ከይን፣ ፍጠር ይላል፡፡
በራሱም ብያኔ ያዕቆብ፣ ሥልጣኔ የመነጨው የሚጸናውም በኅብረት ሳይሆን ራሳቸውን ከመንጋ በነጠሉ ግለሰቦች እንደሆነ እንዲህ በማለት ይበይናል፡- “ዘመናዊውን ዓለም የገነቡት ነጠል ብለው መቆም የቻሉ፣ ሌላ ዐይነት የሕይወት ቅኝት የነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡”
በርግጥ ታላላቅ የኪነጥበብና የሥነ ጥበብ ማስተርፒሶች የብቸኝነት ሳይሆን የፈቃድ ብቻነት ውጤቶች እንደሆኑ ብዙ ጽሑፎች ላይ እናነባለን፤ አንዳንዶች እንዲያውም “ማንኛውም ከያኒ/ደራሲ የላቀ ሥራ ማበርከት ከሻ በሕይወቱ አንዴም ቢሆን ረዘም ያለ የብቻነት ጊዜ ሊያሳልፍ ይገባል# ብለው የሚያዙም አይጠፉም፡፡
በሥነ ጽሑፋዊ አቋሙ፣ በጠባዩ፣ በድርሰቶቹም፣ በማኅበራዊ ግንኙነቱም መነጠልን እንደ ሕይወት ልምምድ የያዘው የሚመስለው ያዕቆብ፤ “መነጠል እና መጀመል” ውስጥ ከብርሃኑ ድንቄ “ብቻዬን ቆሜያለሁ” የተዋሳት የምትመስለውን ለብቻ መቆም የተባለች ሐሳቡን ያወድሳታል፡- “ለብቻ መቆም ውበት ነው፡፡ ጽናት ነው፡፡ ጥንካሬ ነው፡፡ ለብቻ መቆም መሟላት እንጂ መነጠል አይደለም፡፡”
ሞጋች/ አፍራሽ
መጽሐፉ ከዳር እስከዳር ያዕቆብ ራሱን ከውጭ አቁሞ አስተሳሰቦችን፣ ሐሳቦችን፣ ታሪኮችን፣ አኗኗሮችን፣ ፈጠራዎችን ለመመርመር፣ ለመፈተሽ፣ ለመሞገትና ለመተቸት የሞከረባቸው መሣሪያዎቹ ናቸው፡፡
በምሳሌነት “እውን ኢት. ሥልጡን አገር ነበረችን?” የሚለውን ድርሰት እንመልከት፡-
በጥያቄዎች የተሞላ ድርሰት ነው። ኢትዮጵያ ሥልጡን ነበረች የሚለውን እምነት፣ ከሥልጣኔ/ዘመናዊነት ትርጉሞች አንጻር እየፈተሸ፣ እሺ ነበረች እንበል፣ ነገር ግን ነበረች ማለት አይበቃም፤ ሥልጣኔዋ ምን ድረስ ነበር? ሥልጣኔዋ ቢያንስ የሕዝቧን ሕይወት የሚያሠለጥን/የሚያዘምን ምን በረከት ጥሎ አለፈ? ያልነበረ እስኪመስል ድረስ ለምንስ ተቆራረጠ? ብሎ ይጠይቃል፤ የነቃ የታሪክ መርማሪም እኒህንና መሰሎቹን ጥያቄዎች እንዲጠይቅ ያሳስባል፡፡ እንዲህ ያለ ደፋር ድምዳሜም ይሰጣል፡-
የኢትዮጵያ ስልጣኔ የሰጡትን ለምን ሳይል የሚያቅፍ፣ ያጎረሱትን ሳያላምጥ የሚውጥ ነበር፡፡ የእኛ ስልጣኔ ከመጠየቅ ጋር አይተዋወቅም፡፡ ከማድነቅ ጋር ኩርፍ፣ ከመመርመር ጋር ሆድና ጀርባ ነው፡፡ ቀለሙ ዝንቅ፣ የሆነ ድቅል መልክ ነበረው፡፡
ሌላኛው ምሳሌያችን “የስብሃት ለአብ የአርባ ዓመት ቁዘማ” ነው፡፡ ስብሃት ሃናን ካጣ በኋላ የኖረው “ዕብደት የሚመስል ግርታ የታከለበት የዝግመት ኑረት ልሕቀት ወይስ ውድቀት?” የሚል ደፋር ጥያቄ አንሥቶ በአጭር ቁመት ያዋቀራትን መጣጥፉን በእኔ ዕይታ ብሎ የሚሰነዝረውን መሞገቻ ሐሳቡን/ ድምዳሜውን በሚያጠናክሩለት ሐሳቦችና ገጠመኞች/አስተያየቶች ይሞላታል፡፡ ይህ የእሱ ዕይታ “ስብሃት በዕድሜ ዘመን ሙሉ የሚሳሳለትን መጫወቻ በጭካኔ ተነጥቆ ረዳት አጥቶ እንደሚያነፈርቅ ሕፃን ነበረ” የሚል ነው፡፡ በዚህ መጣጥፉ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር ያለ ሐና የኖረበትን የአርባ ዓመት ሕይወት ያለረባ ፍሬ ያለፈ ነው ብሎ፣ በልሃ ልበልሃ ከአንባቢው ጋር ይገጥማል፡፡
እነዚህ በጥያቄዎችና በሙግቶች የተዋቀሩ ድርሰቶች ስለሆኑ ነጥለን አነሣናቸው እንጂ፣ ከሃያዎቹ ድርሰቶች በአብዛኞቹ ያዕቆብ አሳንሶ ከሚያየው፣ ምናልባትም የሚንቀው ከሚመስለው ማኅበረሰብ ሐሳቦችና አስተሳሰቦች በተቃራኒ ቆሞ ሲሞግት፣ ሲተችና ትክክል ያለውን ሲያቀብል እናገኘዋለን፡፡
ሥነ ጽሑፋዊ ኂሳዊ
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ መጻሕፍት ሐሳቦቻቸውንና ተረኮቻቸውን ለያዕቆብ ሐተታ ማዳበሪያነት፣ ለሙግቶቹም ምስክርነት ቢያዋጡም፤ በደራሲው ኂሳዊ ንባብ የተተነተኑ ኢትዮጵያዊም የውጭም ሥራዎች ተካትተውበታል፡፡ ኂሶቹ በአብዛኛው የመተንተን እንጂ የመመዘን ባሕርይ የላቸውም፡፡ አብዛኞቹም ለንባብ ከቀረቡት መጻሕፍት አንድ የሐሳብ/የአኔክዶት ሰበዝ መዝዞ፣ በእሷው የጌጥ/የሥነ ውበት ሙዳዩንም፣ የታላላቅ ሐሳብ ገበታውንም፣ ኪነት ማንፈሻ ሰፌዱንም የሚሠራባቸው/ የሠራባቸው ንባቦች ናቸው።
ከእነዚህኞቹ ምሳሌዎችን ብንጠቅስ መጀመሪያ የምንጠራው “ከዲያብሎስ ጋር መደነስ” የሚለውን መጣጥፍ ነው። የትንታኔ መነሻ የተደረገችው ስንዱ አበበ የተጻፉላትን ደብዳቤዎች አደራጅታ ያሳተመቻት “የኔ ማስታወሻ” የተሰኘች መጽሐፍ ስትሆን፤ የያዕቆብ መጣጥፍ ከመጽሐፏ በመጥቀስና መጽሐፏን በጥቂት ቃላት በማስተዋወቅ ይጀምራል፡፡ ከዚያ በኋላ መጽሐፏን አልፎ አልፎ እያነሣ፣ በደብዳቤዎቹ ውስጥ ያገኛቸው ሐሳቦች፣ ስሜቶችና አቀራረቦቻቸው ውስጡ የፈጠሩትን መረዳት ሳይሆን ንሸጣ እየተከተለ በሦስት ንኡሳን አርእስት ውበትንና መለኮትን፣ የኪነት ጣዖት ያላትን ሚዩዝንና ወሲብን እያጣመረና እያፋታ ሲበይን፣ ሲገልጽና ሲተነትን እናገኘዋለን፡፡ “የኔ ማስታወሻ” ውስጥ ያሉ ደብዳቤዎች ወይም የተጻፈላት ስንዱ ለያዕቆብ የንሸጣ ወይም የጥያቄ መነሻዎች እንጂ ትንታኔውን የሚያጥርባቸው መዳረሻዎቹ አይደሉም - ትቷቸው ርቆ እስከ መሄድ ይደርሳልና፡፡
በዚሁ መልክ “የዚያ ትውልድ መርገምት” የተሰኘውን በአያሻረው “ከደንቢያ ጎንደር፣ እስከ ዋሺንግተን ዲሲ” ሁለት ቅፆች ላይ ተነሥቶ ሌሎችንም ምንጮች ጠቃቅሶ የአብዮቱን ዘመን ትውልድ የሚበይነበትን መጣጥፉን ልታዩት ትችላላችሁ፡፡
በያዕቆብ ኂሳዊ ዐይን የታዩ ያዕቆብም መነሻም መድረሻም አድርጎ ያስተነተናቸውን ሁለት ሥራዎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እናገኛለን፡- እነዚህም የሳሙኤል ቤኬት “Waiting for Godot” እና የዓለማየሁ ገላጋይ “ሐሰተኛው በእምነት ስም” ናቸው። በእኔ ንባብ በያዕቆብ አረዳድ ልክ የተሟላ ኂሳዊ ትንታኔ የጻፈባቸው መጣጥፎቹም ስለነዚሁ መጻሕፍት ያቀረባቸው ናቸው፡፡
የቤኬትን “ዌይቲንግ ፎር ጎዶት” የተባለች ተውኔት፣ በፊልም መልክ ለአምስት ጊዜ ከተመለከተ በኋላ የተነተነበት መጣጥፉ “ጊዜን መሸከም” የሚል ጥያቄ የሚያጭር ርእስ የሰጠው ዘለግ ያለ ሥራው ነው። በድርሰቱ ውስጥ የሚጠበቀው ጎዶት ምንን ለመመሰል፣ ምንን ለመወከል እንደገባ ያስረዳል፤ ለጥበቃቸው “ጊዜን መሸከም” የሚል መቋጠሪያ አበጅቶ የተውኔቱን ትርጓሜ ያስሳል፤ ተረዳሁ ባለውም ልክ ይተረጉማል፡፡
ያዕቆብ “ከሞት ጋር መደነስ” በሚል ኂሳዊ ትንታኔው፣ የዓለማየሁን “ሐሰተኛው”ን ማንበብ “የሚያጠናግር ግራ መጋባት ውስጥ ይከትሃል፡፡ አንብበህ ስትጨርስ ሁሉንም ነገር መካድ ይዳዳሃል…” ብሎ ተንደርድሮ፤ የትረካውን ፋታ ነሺነት፣ የታሪኮቹን/የገጸባሕርያቱን ከጽልመት ማሕጸን መወለድ፣ የእግዜርን እንዳጥቢያ ዳኛ ለፍርድ መቅረብ እያስተነተነ ይዘልቃል፡፡ የአለማየሁ ትሪሎጂ/ሦስቶሽ አካላት ወደሆኑት ወደ በፍቅር ስም እና ወደ ታለ፡ በእውነት ስም እየተመላለሠ ድርሰቶቹን ያፍታታል፤ ይፈክራል፤ የኔ የሚለውን ብያኔም ያክላል፡፡
በአጠቃላይ፡-
በዚህ ስብስብ ውስጥ የተካተቱ ሥራዎች፣ ያዕቆብን (መጀመሪያ በአሉታም ቢሆን) ልብ ማለት ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ ሐሳቦቹ፣ መረዳቱ የአጻጻፍ ክሂሉም እያደገ መምጣቱን የመሰከሩልኝ ናቸው፡፡ ነገር ግን የያዕቆብ አቅም በምልዓት የተገለጡባቸው ሥራዎች ናቸው ለማለት ግን እቸገራለሁ፡፡ በሥራዎቹ ውስጥ ያየኋቸው፣ ከተገናኘንባቸው ውይይቶች የተረዳኋቸው አቅሞቹ ገና በወጉ አልወጡም ባይ ነኝ፡፡ እነዚህ ሥራዎች የነገውን ያዕቆብ ጭምር እንድንናፍቅ ተስፋ የሚሰጡን ናቸው፡፡
እዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ግን ሥነጽሑፍ፣ ፍልስፍና፣ በጥቅሉም መጠየቅን የሚያደንቅ አንባቢ የሚደነቅባቸውን ሐሳቦች እንደሚያገኝ አምናለሁ። በሃያዎቹም መጣጥፎቹና በጥልቅ መግቢያው ላይ የተስተነተኑ፣ የተሞገቱና የተጠየቁ ሐሳቦች በተናጥል ውይይቶችን እንደሚጋብዙም እጠብቃለሁ፡፡ ሥራዎቹን ያዕቆብ በሚመኘውና በማይመኘው ልክ አብጠልጥለን የምንተቻችበት ሌላ መድረክ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
(በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የቀረበና ለንባብ እንዲያመች በመጠኑ የተቃኘ)

Read 8419 times