Tuesday, 29 March 2022 00:00

"ለህልውናዬ ካሰጋኝ ኒውክሌር ልጠቀም እችላለሁ" ሩሲያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


            ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ለጦርነት የተጠቀመች የመጀመሪያዋ የአለም አገር የሆነችው  ሩስያ፣ የህዝቧን ደህንነትና አገራዊ ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል የከፋ ነገር ካጋጠማት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን፣ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫውን አደገኛ ብሎታል፡፡
የሩስያ ጦር ሃይል ባለፈው እሁድም ኪንዛል የተሰኘውንና ከደምጽ በአምስት እጥፍ ይፈጥናል የተባለውን ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤል በድጋሚ በማስወንጨፍ በዩክሬን የሚገኝ የነዳጅና የጦር መሳሪያ መጋዝኖችን ማውደሙ የተነገረ ሲሆን፣ ሚሳኤሉ እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ሊያጠቃ እንደሚችልም ተዘግቧል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፤ #የሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ዩክሬን ለማስገባት መሞከር እጅግ የከፋ ጥፋት ያስከትላል; ስትል ሩሲያ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ኔቶን አስጠንቅቃለች፡፡
ሩስያ ባለፈው ሰኞ በዩክሬኗ ስትራቴጂካዊ የወደብ ከተማ ማፓሪፖል የመሸጉ የዩክሬን ወታደሮች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ ዩክሬን ግን ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በትግሏ መጽናቷን ሩስያም ከተማዋን በአሰቃቂ ሁኔታ መደብደብና ዶግ አመድ ማድረጓን መቀጠሏ ነው የተነገረው፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እንደሚለው፤ የዩክሬን ወታደሮች የሩስያ ጦር በቁጥጥሩ ስር አድርጓቸው የነበሩ የአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎችን ለማስለቀቅ ስኬታማ ትግል እያደረጉ እንደሚገኙና ከመዲናዋ ኬዬቭ በ40 ማይሎች ርቃ የምትገኘውን ማካሪቭ ከተማ መልሰው መያዛቸውን ሀሙስ እለት ያስታወቀ ሲሆን የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ በበኩላቸው፤ የሩስያ ጦር ከዩክሬን ብርቱ መከላከልና ጥቃት እንደገጠመውና ወደፊት መግፋት እንዳልቻለ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ከሰሞኑ ለጃፓን ፓርላማ አባላት በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር፤ የሩስያ ጦር ቼርኖቤልን ጨምሮ በተለያዩ የኒውክሌር ማብላያ ማዕከላት ላይ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችልና ይህም እጅግ አደገኛ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ጃፓን ከዩክሬን ጎን እንድትቆም ጠይቀዋል፡፡ በማሪፖል ከተማ ከ100 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች በጭንቅ ውስጥ እንደሚገኙ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ባለፈው ረቡዕ እነዚህን ዜጎች ከአደጋ ለማውጣት የሚያስችል ነጻ መስመር ለመክፈት ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክቷል፡፡
የሩስያ ጦር ጦርነቱን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ 10 ሆስፒታሎችን ሙሉ ለሙሉ በድብደባ ማውደሙን የዩክሬን መንግስት ማስታወቁ የተዘገበ ሲሆን፣ ዩክሬን ከ15 ሺህ በላይ የሩስያ ወታደሮችን መግደሏንም አስታውቋል፡፡
አንድ የሩስያ ጋዜጣ በበኩሉ፤ ሩሲያ በጦርነቱ 9ሺህ 861 ወታደሮች እንደሞቱባትና 16ሺህ 153 እንደቆሰሉባት ቢዘግብም፣ የአሜሪካ የስለላ ተቋም ግን የሟቾችን ቁጥር ወደ 7ሺህ ዝቅ እንዳደረገው ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከአውዳሚው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተሰብስቦ እጅ ከማውጣት ያለፈ የረባ ነገር ሲሰራ ያልታየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከሰሞኑም ሩስያን የሚያወግዝ መግለጫ ለማውጣት ድምጽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማብረድና ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት የተጀመረው ጥረት ይህ ነው የሚባል ውጤት ባያስገኝም፣ ችግሩን በድርድር መፍታት እጅግ አስቸጋሪ ተልዕኮ ቢሆንም በአገራቱ መካከል በየደረጃው የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውንና የተወሰኑ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ባለፈው ረቡዕ በቴሌግራም ቻናላቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያውን የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ማድረጋቸውን ቲአርቲ የዘገበ ሲሆን፣ የሩስያ ጦር አግቷቸው የነበሩትን የዩክሬኗ ሜሊቶፖል ከተማ ከንቲባ በመልቀቅ በምላሹ በዩክሬን የተማረኩ 9 ሩሲያውያን ወታደሮችን ማስመለሱን አመልክቷል፡፡
አለም በሁለቱ አገራት ጦርነት ሳቢያ ያለ ዕዳዋ ገፈት መቅመሷን ቀጥላለች፡፡ የጦርነቱ ጦስ የነዳጅ፣ የምግቦች፣ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡ የአለማችን ኢኮኖሚ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካደረሰበት ጉዳት እንዳያገግምና እድገት እንዳያስመዘግብ ጦርነቱ ሰበብ ይሆንበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ አስታውቋል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ጦርነት በዚሁ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ፣ በመላው አለም የሚገኙ 40 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አገራት ህዝቦች ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ እንደሚችሉም ከሰሞኑ የወጣ አንድ መረጃ አመልክቷል፡፡
ሴንተር ፎር ግሎባል ዲቨሎፕመንት የተባለው ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገ ተቋም ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ የሁለቱ አገራት ጦርነት የምግብና የሸቀጦች ዋጋን በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳናረውና ይህም 40 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ዜጎችን ወደ ከፋ ድህነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
ዩክሬን ወደቦቿ በሩስያ ጦር ቁጥጥር ስር በመዋላቸው ምክንያት የጥራጥሬ እህሎች ምርቶቿን ለውጭ ገበያ መላክ ባለመቻሏ ብቻ 6 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ እንደምታጣም ተነግሯል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ሩስያን የአለማችን ባለጸጋ 20 አገራት ከተካተቱበት ቡድን 20 አባልነት ለማስወጣት እያሴሩ እንደሚገኙ የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም፣ "ማንም ማንንም ማባረር አይችልም" ስትል የሩስያን ከቡድኑ መባረር በይፋ ከተቃወመችው ቻይና በስተቀር ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የቡድኑ አባል አገራት፣ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም አለመታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የቡድን 8 አገራት ከ8 ወራት በኋላ በኢንዶኔዢያ ጃካርታ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ የተነገረ ሲሆን የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ መነገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሩስያ ከ8 አመታት በፊት ክሪሚያን መጠቅለሏን ተከትሎ፣ ከቡድን 8 አገራት አባልነቷ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን ሙሉ ስምምነት መባረሯንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ፖላንድ በበኩሏ በስለላ ተግባር ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል ያለቻቸውን 45 የሩስያ ዲፕሎማቶች ለማባረር መወሰኗን ያስታወቀች ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረትም ከሰሞኑ ተጨማሪ አዳዲስ ማዕቀቦችን በሩስያ ላይ ለመጣል ማሰቡ ተነግሯል፡፡

Read 7008 times