Monday, 28 March 2022 00:00

ቦይንግ በቻይናው የአውሮፕላን አደጋ ዋጋው ቀንሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ንብረትነቱ የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ባለፈው ሰኞ 133 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ ጉዋንግዚ ጉዋንግ በተባለው የቻይና ግዛት ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የአምራቹ ኩባንያ ቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ በ5.6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
አውሮፕላኑ 9 የበረራ ሰራተኞችንና 123 መንገደኞችን አሳፍሮ ኩሚንግ ከተባለችዋ የቻይና ከተማ በመነሳት ለአንድ ሰዓት ያህል ወደ ጉዋንግዡ ከበረረ በኋላ ድንገት ከፍታውን በፍጥነት በመቀነስ ቁልቁል ወርዶ በደን በተሸፈነ ተራራማ ቦታ ላይ መከስከሱን ተከትሎ፣ የእሳት ቃጠሎ እንደገጠመውና ስብርባሪው ብቻ እንደተገኘ የዘገበው ቢቢሲ፤ አደጋው ከአውሮፕላኑ ዲዛይን ችግር ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነው ተብሎ እንደማይጠበቅና ምርመራው እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጧል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ ይሄኛው አደጋ ያጋጠመው በኢትዮጵያና በማሌዢያ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ለ3 አመታት ከበረራ ታግዶ የነበረውን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑን ለቻይና ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እያለ መሆኑን የጠቆመው ብሉምበርግ፣ ይህም በኩባንያው ላይ ተጨማሪ ኪሳራንና ወጪን ሊያስከትልበት እንደሚችል አመልክቷል፡፡
ቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ለ7 አመታት ያህል አገልግሎት በሰጠው አውሮፕላኑ ላይ አደጋው መከሰቱን ተከትሎ፣ ሁሉንም ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖቹን ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ከበረራ ያገደ ሲሆን፣ አደጋው በቻይና ከ12 አመታት ወዲህ የተከሰተ የከፋ አደጋ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ 737-800 ኤንጂ በመባል የሚታወቀውን አውሮፕላኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ ያዋለው እ.ኤ.አ በ1997 እንደነበር ያስታወሰው ብሉምበርግ፤ የደህንነት ታሪኩ ጥሩ የሚባል መሆኑንና ከ7 ሺህ በላይ ከሚሆኑ አውሮፕላኖች የከፋ አደጋ ያጋጠማቸው 11 ብቻ መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
አደጋውን ተከትሎ የህንድ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በቦይንግ አውሮፕላኖች በሚያደርጋቸው በረራዎች ለየት ያለ ከፍተኛ የደህንነት ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያድርግ ያስታወቀ ሲሆን፣ ሌሎች አየር መንገዶችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተዘግቧል፡፡


Read 1878 times