Saturday, 26 March 2022 12:40

ዊሊያም አሳንጄ በወህኒ ቤት ሊሞሸር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የበርካታ አገራት መንግስታትን፣ ግለሰቦችንና ባለጸጎችን የግል ሚስጥራዊ መረጃዎች እየጎለጎለ በአደባባይ በማስጣት የሚታወቀው የዊኪሊክስ ድረገጽ መስራችና ባለቤት ዊሊያም አሳንጄ፣ በእስር ላይ በሚገኝበት የለንደን እስር ቤት ጋብቻውን ሊፈጽም መዘጋጀቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከ10 አመታት በፊት ወታደራዊና የደህንነት መረጃዬን ዘርፎ አሰራጭቶብኛል በሚል ስታሳድደው የኖረችውና 18 ክሶችን የመሰረተችበት የ50 አመቱ አውስትራሊያዊ አሳንጄ፣ ከረጅም ጊዜ የፍቅር ወዳጁ ስቴላ ሞሪስ ጋር በእስር ላይ በሚገኝበት የእንግሊዙ ቤልማርሽ እስር ቤት በመጠነኛ ሰርግ እንደሚሞሸር ነው የተነገረው፡፡
በጥንዶቹ የሰርግ ስነስርዓት ላይ የሚታደሙት 2 አፈራራሚዎችና 2 ጠባቂዎች ብቻ እንደሚሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ ዊሊያም አሳንጄ ከአሜሪካ መንግስት ለማምለጥ 7 አመታት ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ መቆየቱንና ካለፉት 3 አመታት ወዲህ በቤልማርሽ እስር ቤት እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡ የሙሽሮችን አልባሳት ያዘጋጀችው ታዋቂዋ ብሪታኒያዊት የፋሽን ዲዛይነር ቪቬኒ ዌስትውድ መሆኗን የጠቆመው ሮይተርስ፤ የአገሪቱ መንግስት አሳንጄን ለአሜሪካ አሳልፎ እንዳይሰጥ ሲወተውቱ ከነበሩ ታዋቂ ዝነኞች አንዷ መሆኗንም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 3468 times