Saturday, 26 March 2022 10:24

ተጠያቂነትና በቡድን የ’ማሰብ’ አደጋ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ (ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ-አሜሪካ)
Rate this item
(0 votes)

  ይህን ምሳሌ በምናባችሁ አስቡት፡፡ ጎረቤት የሆኑ አባወራ (እማወራ) ናቸው፡፡ ዘወትር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ  ስለሚያስተዳድሩት ወይም ከልጆቻቸው ጋር ስለሚኖሩበት ቤት ይናገራሉ፡፡ «ቤቱ ስርዓት አጣ» ይላሉ በብሶት፡፡ ስለጽዳቱም አንስተው «በጣም ቆሽሾ መግቢያው ሁሉ ተበላሽቷል» ይሉና፣ ስለዕቃው አቀማመጥ ይሁን ስለአልጋ አዘረጋግም «አቀማመጡ ሁሉ ቅጥ አምባሩ የጠፋው» ብለው እየተመረሩ ሲናገሩ ዘወትር ትሰማላችሁ፡፡ ስትወጡና ስትገቡ ሰላም ባሉዋችሁ ቁጥር ስለቤታቸው ገመናና ችግር ሲናገሩም አሰልችተዋችሁ ይሆናል፡፡ በይሉኝታ ይሁን ብላችሁ ትሰማላችሁ፡፡ ብሶቱንና ምሬቱን በሰማችሁ ቁጥር ግን ለዚህ ሁሉ ችግርና ብሶት ዋናው ተጠያቂ ማን ይሆን? እያላችሁ ውስጣችሁን እንደምትሞግቱ እጠረጥራለሁ፡፡ የቤታቸውን እቃ እንዳሻቸው ቢያደርጉት - ጽዳቱንም ቢያከናውኑት - ስርዓቱንም ቢያስከብሩት ራሳቸው አባወራው እንጂ ሌላ ማን ተጠያቂ ይመጣል? እዚህ ሀገር የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሄነሪ ትሩማን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙበት አገላለጽ አለ፡፡ በእንግሊዘኛው «The buck stops here» ይላል - ብሎ ብሎ የኃላፊነቱ በትር እዚህ ይቆማል እንደማለት ነው፡፡ እና የዚያ ቤት ኃላፊነት ከአባ ወራው ጫንቃ ላይ ዞሮ፣ ዞሮ ይቀመጣል፡፡ ቤቱ አልጸዳም - ቤቱ አልተስተካከለም - ቤቱ ስርዓት አጣ - ሲባል ቀዳሚ ተጠያቂውና ኃላፊው አባወራው ናቸው እንላለን፡፡  
በብዙ አጋጣሚዎች ተጠያቂና ጠያቂ እየተደበላለቀ መቸገራችንን አያለሁ፡፡ የጉዳዩ ባለቤትና ዋነኛ አጋፋሪው አብሮን ችግሩን እየተናገረ ተጠያቂ የሚሆነው ጠፍቶ፣ ዙሪያ ገባውን እያየን የተደናገርንባቸው የማህበራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች እንደበዙብን እታዘባለሁ፡፡ ባለቤት የሌለው የሚምስለው ችግራችንና  - ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው (አካል)  አብሮን አመልካች እየሆነ መገኘቱ፣ ጭራሽ መወናበዳችንን አክፍቶታል፡፡ በተቃራኒው የአባወራውን ነገር አስቡት። ቤታቸው ቢያምርና ቢቆነጅ - ቢጸዳና በአግባቡ ቢዘገጃጅ - “እኔ እኮ ቤት አያያዜ ለጉድ ነው” ብለው ሊያዳንቁና እንድናጨበጭብም ሊያደርጉን ይጋበዛሉ። እዚህ ላይ ነው ዋናው ጥያቄ የሚነሳው ወይም የሚመጣው፡፡ - ‘እኔ’ የሚለው የባለቤትነት ስሜት ቤቱ ሲበላሽና ሲነትብም በ’ተጠያቂነት’ ብቅ ካላለ ችግር እንዳለ አመልካች ነው፡፡ አስፍተን በማህበራዊ - በኢኮኖሚያዊ ወይም በፖለቲካው ዘርፍ ካየነው፣ የ’መሪ’ ሰብዕና የሚባለው ድንቅ ድንቁን ለራስ አድናቆት ሰብስቦ ጥፋቱን ግን አሳቦ ሲያልፍ አይደለም፡፡ የልማቱም የጥፋቱም ባለቤት ሲሆን እንጂ፡፡
ታዲያ የተጠያቂነትና የጠያቂነት ወጉ የሚሰለጥነው መንገዱ የሚያምረው ነፃ አስተሳሰብ ሲኖር ነው፡፡ የ›መንጋ ወይም በቡድን ማሰብ (groupthink) ሲኖር ግን ተጠያቂነትን ነቅሶ ለማውጣት ያዳግታል። በዛሬ ጊዜ ከላይ እስከታች የሚስተዋለው የ’ቡድን አስተሳሰብ’ (groupthink) ይበልጡኑ የሁዋልዮሽ እያስጓዘን እንዳይሆን እንድንጠረጥር ያስገድደናል፡፡ ከዚህ መስመር ውጭ ማሰብ - አይፈቀድም የሚልና ራስንም ‘የገደበ’ ሁኔታ እንዲኖር መፍቀድ አደጋ አለው፡፡
ይህን ይበልጥ ማብራራት ያስፈልገዋል፡፡ በእኛ ሀገር የፖለቲካ ዘዬም ይሁን እንዲሁ ሰብሰብ ስንል ተያይዘን የመንጎድ ነገር እንደሚያጠቃን ይስተዋላል፡፡ ጉዳዩ ወይም አጀንዳ ተብሎ የቀረበውን የምንወያይበትን ጉዳይ በግልጽና በይፋ ተወያይተን ለመሄድ - ቅር ያለንም ቅርታችንን ገልጸን ለመገላገል ብዙ ወጥመዶች ያሉብን ይመስላል፡፡ ከቡድኑ ወይም ከስብስቡ ወጣ ያለ ሀሳብ ካለን ዝምታችንን ታቅፈን፣ ደጋፊ መስለን ከጎርፉ ጋር መጉረፍ ይቀናናል፡፡ እርግጥ የቡድን አስተሳሰብ በፍጥረቱ ነፃ ሃሳብንና ነጻ አሳቢን የመደፍጠጥ አዚም አለው፡፡ መስማማትን ብቻ የሚሻ ባህርይ ስላለውም ገለልተኛ ሀሳብን ያከላክላል፡፡ በስብሰባ መሀል ተቀምጣችሁ፣ የማትስማሙበት ለእናንተ እውነት ያልሆነ ነገር ተነስቶ ሲነገር - የቡድኑን አካሄድ በማደናቀፍ እወነጀላለሁ - ወይም ከስብስቡ እገለላለሁ ብላችሁና ፈርታችሁ፤ እጃችሁን አጣምራችሁ እግራችሁን አንጥፋችሁ የተቀመጣችሁ ትኖራላችሁ፡፡ ደግሞ የብዙ ፖለቲካዊ ውይይቶች የተሳታፊዎቻቸውን ጉረሮ (ኑሮ ማለቴ ነው) የያዙ ናቸውና ከቡድኑ እሳቤ በተለዩ ቁጥር አንገት የሚያንቅ ሁኔታ ይከሰታልና እንደ’ቡድኑ ማሰብ’ ግዴታም ይመስላል፡፡ የቡድን አስተሳሰብ ዋናው መልኩም ይዘቱም ይኸው ነው፡፡ ‘ንጉሡ ራቁታቸውን ናቸው’ የሚል ግልጽ አንደበትም ይጠፋል፡፡ ቢኖርም የሚሰማው ጆሮ - የሚናገርበትም መድረክ ይጠፋል፡፡
የስነ ልቡናው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኢርቪንግ ጃኒስ በአሜሪካ የፖለቲካ አምባ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩትን የፖለቲካ ቅሌቶች መለስ ብለው በተለይ ከ›ቡድን አስተሳሰብ› ጋር የተያያዙትን ካጠኑት መካከል ‹Bays of Pigs invasion› በሚል የሚታወቀው ክስተት ይገኝበታል፡፡ በሚያዚያ ወር በ1961 እ.ኤ.አ. በአሜሪካው የወቅቱ ፕሬዝደንት ኬኔዲ መንግሥት አማካይነት የኪዩባ ፕሬዘደንት ፊደል ካስትሮን መንግሥትን ለመገርሰስ ተቃዋሚ የሆኑ አንድ ሺህ አምስት መቶ የሚጠጉ የኪዩባ አማፅያን ተደራጅተው የተላኩበትና ወዲያው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እነዚህ ተዋጊዎች የተማረኩበት አሳፋሪ የሆነ የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ ፕሬዝደንት ኬኔዲና አማካሪዎቻቸው በአሜሪካ ፖለቲካ እጅግ ጎበዝና አዋቂ ከሚባሉት የሚመደቡ ናቸውና ‘እንዴት ይህን መሰል ስህተት በእነዚህ ታላላቅ የፖለቲካ ሰዎች ሊፈጠር ቻለ’? የሚል ወትዋችና ሞጋች  ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ታዲያ ተመራማሪው፤ እጅግ በተቀራረቡና የቡድን ስሜትን (መንፈስን) በፈጠሩ መካከል (ባለማወቅ) “የአይበገሬነት ቅዠት” ይፈጥራሉ ይላሉ፡፡ እና በቡድን ማሰቡ ያይልና ‘ግፋ ወደፊት’ ብቻ ይሆናል ዜማው፡፡ እና ጥልቅና አማራጭ ሀሳብም የሚሾልክበት ዕድልም ጠበበ፡፡ ይሁንና ውድቀቱ ከደረሰ - መንገዱ ከተፋለሰ በሁዋላ “የተለየ ሀሳብ ነበረኝ” የሚሉ ብቅ ቢሉም ካለፈ በሁዋላ የሚባለው ሁሉ ጉንጭ አልፋ ነው፡፡  
እኛም በታሪካችን ይሁን ወይም አሁን በምንገኝበት መሰል ገጠመኞችና ኹነቶችን አስረጂ የምናደርገው ላናጣ እንችላለን፡፡ ብዙውን የሀገር ታላላቅ ጉዞዎች የመደናቀፍ ዕድላቸው የሚሰፋውና የመውደቅ ዕጣቸው የሚከፋው ከቡድኑ ያለመነጠል - ነፃ ሃሳብን ያለማስተናገድና ያለማበረታታት ችግር ሲኖር ነው፡፡ ከቡድኑ ተነጥሎ በጠላትነት ላለመታየት - ከቶም ‘ድርጅቱን’ እጎዳለሁ በሚል (ይበልጡን ከግራ ዘመሙ የተወረሰ እሳቤ ነው) ጠቃሚ ሀሳቦችና አማራጮችን ባለማቅረብ ስንቱ መልካም እሳቤ ወደ መቃብር ተሸኝቶ እንደቀረ መገመትም እንችላለን፡፡ የፖለቲካ ባህላችን የፈጠራቸው ተግዳሮቶች ደግሞ ይህንን ጉዞ አስቀጥሎታል፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ የመጣንበት ጎፃ ጎፅ መንገድ በእጅጉ ነፃ አስተሳሰብን በማፈን የሚታወቅና ለማጥፋት ከላይ እስከታች የዘመተ አይነት ነበር፡፡ ውይይቶች ለይስሙላ መድረክ ተከፍቶላቸው በሉ ‘ሀሳባችሁን’ አንሸራሽሩ’ እየተባለ - ‘የሰብሳቢውን አካል ወይም የቡድኑን ሀሳብ መስመር’ የሚፈትን ጥያቄም ሆነ አስተሳሰብ ሲቀርብ “ይሄማ ...ፀረ-ምንትስ...” ተብሎ የተፈረጀበትን ሂደት የምናውቀው ነው፡፡ እስካሁን በዘለቀውና አሁንም ፖለቲከኞቻችን ያደጉበት የግራ ዘመሙ የፖለቲካ ሂደት፣ ጥቁርና ነጭ በሚል ለክቶ ሀሳብን ከዚህ ወይም ከዚያ ጎራ የሚል አጥር በማበጀት የተደራጀ ነው፡፡ ፖለቲካችን አዳዲስ ሀሳቦችንና አማራጮችን የመቀበል ጫንቃውም የሳሳ ከቶም የሌለ የሚባል አይነት ነው፡፡ በደርጉ ዘመን ኮለኔል መንግሥቱ በእርሳቸው ውሳኔ ለእርሻ ‘ይኼኛው መሬት ይታረስ’ እስከሚሉበት ትዕዛዝ ያደረሳቸው - አዲስ ሀሳብና አማራጭ ለማቅረብ የደፈረ ወይም የእርሳቸውን ‘አይሆንም’ የሚል በመጥፋቱ ጭምር ነው። በዚህ በሰሞኑ የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት ወቅት፣ በሩሲያ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ላይ ሩሲያዊቷ የቴሌቪዥን ሠራተኛ ዜና በሚነበብበት ሰዓት ‘ጦርነት ይቁም’ ብላ መፈክር ይዛ በድፍረት ስትወጣና ድምፁዋን ስታሰማ፣ ድርጊቷን እንደግፍም እንቃወምም፣ ነፃ አሳቢነቷንና ድፍረቷን ማድነቅ ግን እንገደዳለን፡፡ ዛሬ ቆም ብለን የፖለቲካ አውዱን መቃኘትና ለራሳችን መመለስ የሚገባን ጥያቄ - ስለእውነት እኛስ ምን ያህል ነፃ ነን? የሚለውን ነው፡፡
ጤናማ በሆነ ስርዓት ውስጥ ‹ከቡድን› ውስጥ ‹የቡድኑን አስተሳሰብ› የሚፈታተን አዳዲስ ሀሳብ ይፈልቃል። ይስተናገዳልም፡፡ ለዚህ ዓይነተኛው መንገድ ‹ዲሞክራሲያዊ› የሆነ አሠራር ነው፡፡ ዲሞክራሲን መለማመድ፣ ፈተናውን መውደቅና መነሳትም ይጠበቃል። «አዲስ ትራስ የገዛ በእግረ መንገዱ ይንተራሰዋል» የሚል ምሳሌ አውቃለሁ፡፡ ቡድኖች ይሁኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሕዝብም ዲሞክራሲ እናመጣለን ከሚለው ግብ አስቀድሞ ዲሞክራሲያዊ አሠራርን በውስጣቸው ሊለማመዱት - እንደ አዲሱ ትራስም በቅድሚያ ሊንተራሱትም ይገባል፡፡  የ›ቡድን አስተሳሰብ› እየተስፋፋ  ለነፃ ሃሳብ ቦታ በታጣ ቁጥር የምንፈራው የ’ማንአለብኝነትና የትዕቢት’ ስርዓት እንደሚጀመር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ አድሮ ሰንብቶ በ’እኔ’ አምሳልና ቅርጽ ሁሉም ይከናወን ወይም ይሠራ ማለት ይመጣና እንደ ስርዓት ተመልሰን ነፍሳቸውን ይማረውና ፕ/መስፍን እንደሚሉት ከ’ዝንጀሮ ዋሻ’ እንገባለን፡፡
ይህ ደግሞ አይሆንም አይባልም፡፡ የሀገራችን አቅምና የምንካፈለው የሀብት መጠን ወይም የሚያኖረን ብዕል እጅግ አናሳ ነው፡፡ የሀብቱና የመኖሪያ ዋስትና ምንጫችን ውስን መሆን ደግሞ በፖለቲካዊ አለቃ (ኤሊት) መካከል የመነጣጠቂያ ዋነኛ ምክንያት ይሆናል፡። ከዚህ የሚብሰው ደግሞ የ’ቡድን አስተሳሰብ’ በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ የዚህ ጥቅም ተቋዳሽ የሆነው ክፍል አብሮ የመነዳት ‘ባህሉን’ ያጠብቀዋል። እንደ ድርጅቱ ወይም እንደ ቡድኑ ተነሱ - እንደ ቡድኑ ልበሱ - እንደ ቡድኑ አንጥሱ ማለት ይመጣል፡፡ ትውስ ካላችሁ ‘ዲሲፕሊን’ በሚል ቃል ተመንዝሮ እንደ መንጋ አንድ አይነት እሳቤና ልብስ የታዘዘበት ዘመንንም እናውቃለን፡፡ ያ ኹነት መልኩን ለውጦ በይዘት ግን ተመሳስሎ ሊከሰትና ሊመጣ ይችላል፡፡ አጥብቀን መስጋት ያለብን የሚነገረውና የምናየው ዱባና ቅል እየሆነብን ሲመጣ - ‘ለምን?’ የሚሉ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ እነዚህ ለምን የሚሉ ደግሞ ከመሪዎቻችን አጠገብ - ከቡድኑ ውስጥ - ከተሰበሰበው መካከል ማየትን እንሻለን፡፡ ከአንድ ጣቃ ጨርቅ የተቀደደ የሚመስል ሀሳብን ብቻ ይዘው የሚመጡ ሰዎችን ሳይሆን - የሚጠይቁ - የሚፈትኑ - የሚቃወሙና ለበለጠው የሚተጉትን እንናፍቃለን፡፡ ለመሪዎችም የሚፈትናቸውና የሚያሰልጣቸውን ተቃዋሚ ሊያቀርቡት በርታ ሊሉት ይገባቸዋል፡፡ እዚህ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩትና በፖለቲካ አመራራቸው ጽንፎችን በማገናኘት ብልህነት የሚደነቁት ሊንደን ጆንሰን፤ ተቃዋሚ ሀሳብና የተለየ አስተሳሰብ ያላቸውን ወደ ካቢኔያቸውና አመራሩ በብዛት ያስገቡ ነበር አሉ፡፡ ስለፖለቲካ አመራር መጽሀፍ የጻፈችው ዶሪስ ጉድዊን፣ ፕሬዝደንት ጆንሰን “ተቃዋሚዎች ወይም ተፃራሪ አስተሳሰብ ያላቸው ከውጭ ሆነው ወደ ድንኳኑ ሽንታቸውን ከሚሸኑ ከውስጥ ሆነው ወደ ውጭ ቢሸኑ ይሻላል” ማለታቸውን ዋቢ ያደረገችውን አንብቤያለሁ፡፡ ቁም ነገሩ የፖለቲካችን ድንኳን የተለያዩ እሳቤዎች የሚፋጩበትና ተዋናዮቹ የሚማማሩበት - ከቶም በሂደቱ የሚሞረዱበት የሚሰልጡበት እንዲሆን እንጂ በገደል ማሚቶነት የምንጠቅሳቸው እንዲሆኑ አያስፈልግም፡፡ የአንድ ሀሳብ ክቡድነትና ፋይዳ የሚታወቀው በተቃርኖው እሳት ተለብልቦ ለመውጣት ዕድል ሲኖረው ብቻ መሆኑንም ልብ እንበል፡፡ ተከታይ አለኝ ማለትም በቡድን አስተሳሰብ በአንድ ቦይ ብቻ የሚፈስ ሳይሆን ለተለያዩ እሳቤዎች የተከፈተ ልቡና ያለውና የሚፋጭ እንዲሆን ማበረታታት ያሻል፡፡     
ያለንበት የታሪክ አጋጣሚ ወይም ወቅት ወሳኝ ሽግግሮችን ይጠብቃል፡፡ በነበረው ሙዚቃና ዚቅ የሚደነስበት ሆኖ የሚቀጥል እንዳይሆን ምኞትና ተስፋ በብዙዎች ዘንድ አለ፡፡ ሀገራዊ ራዕይ ከዳር እንዲደርስ ስንፈልግም የተለያዩ እሳቤዎችን ማስተናገድ ሊገደንና ሊኮሰኩሰን አይገባም፡፡  አንድ ዓይነት ቅድ ወይም ዘይቤ ካለው እሳቤ አንወጣም በሚል የፖለቲካ አውዱን ቀይደንና ቀፍድደን ለአዳዲስ አማራጮች ቦታ ሳንሰጥ መጓዝ ዛሬ ባይሆን አድሮ ሰንብቶ ይጎዳናል፡፡ በተለይም ለቡድን እሳቤ የተጋለጡ ነፃ ሃሳቦችን ለማቅረብ የሚቻልባቸው ምቹ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ግድ ነው፡፡
ሀገርም የምትጠቀመው በዚህ ነው፡፡ ከመጣንበት የፖለቲካ ባህል የተቀዱና ‘የቡድን እሳቤ’ መጠቀሚያ የሚያደርጉ - በድርጅታዊ የውስጥ አሠራር የሰለጠኑ አካሄዶች እንዳያማልሉንና እንዳይጠልፉንም ንቁ መሆን ከወጥመዱ እንዳንወድቅ ይታደገናል፡፡  
( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

Read 1331 times