Saturday, 26 March 2022 10:13

“የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን የማጽናት አላማን አንግበናል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 *የዜግነት መብት ቅድሚያ ሲሰጠው ኢትዮጵያዊ ማንነትም ይጎለብታል
           *ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን ማስታረቅ ያስፈልጋል

          ቀድሞ በእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎና ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ ሃሳብ ተጠንስሶ ብዙም ያልተራመደው፣ ኋላም የዛሬ 10 ዓመት ነዋሪነታቸውን አሜሪካ ባደረጉ ኢትዮጵያውያን በድጋሚ የተቋቋመው "ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት (ኢትዮጵያዊነት)"፤ ከሦስት ዓመት በፊት በስፋት ወደ እንቅስቃሴ የገባ ሲሆን ድርጅቱ በተለይ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን የማጽናት አላማን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለመሆኑ "ኢትዮጵያዊነት" የተባለው ድርጅት ምንድን ነው? ለምን ዓላማ ተቋቋመ? እሳቤውና ፍልስፍናው ምንድን ነው? ለአገርና ለህዝብ ምን ፋይዳ አለው?  የድርጅቱ አመራር አቶ ተስፋ ሚካኤል መኮንን፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡  እነሆ፡-


                እስቲ  ድርጅቱ መቼና እንዴት እንተቋቋመ ይንገሩን?
“ኢትዮጵያዊነት” የተመሰረተው ወይም ደግሞ ተጠናክሮ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ2013 በሰሜን አሜሪካ ነው። የተቋቋመበት ምክንያትም በዋናነት በብሄር ማንነት ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚደረጉ ሁኔታዎች ስላላማረንና አገሪቱንም ወደ አጉል አቅጣጫ እየወሰደ በመሆኑ፣ ያን ሚዛን የሚያስጠብቅ ደግሞም ነባሩን የኢትዮጵያን እሴቶች የሚያጎላ ንቅናቄ አስፈላጊ ነው ብለን በማመናችን ነው። በነገራችን ላይ “ኢትዮጵያዊነት” የተመሰረተው በኛ አይደለም። በ1984 ዓ.ም በታዋቁ አባቶቻችን በእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ፣ በእነ ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ፣ በእነ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ዮዲት እምሩ፣ ፀሃይ ብርሃነስላሴና በመሳሰሉት ነው።
በሰሜን አሜሪካ የዛሬ 10 ዓመት ድጋሚ ስንመሰረት ግን ወደ 16 የሲቪክ ድርጅቶችን አነጋግረን፣ በመጨረሻም አራት ድርጅቶች ተዋህደው ነው፣ኢትዮጵያዊነት ብለው ድርጅቱን ያቋቋሙት። ከመስራቾቹ መካከል እነ ዶ/ር ጌታቸው ሃይሌ፣ እነ ዶ/ር አክሊሉ፣ እነ ዶ/ር ፀሃይ ይጠቀሳሉ።
የ"ኢትዮጵያዊነት" ዋነኛ አላማና ግቡ  ምንድን ነው?
ዋነኛ ዓላማው፤ ኢትዮጵያዊነትን በኢትዮጵያ እንደገና ለማጽናት ነው። በአንድ በኩል የዜግነት መብት እንዲከበር፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት በጣም ጥልቅ የሆነ ህዝብ እየኖረው ያለ ግን በጋራ ወጥቶ ያልታየ ስለሆነ፣ ያንን አጉልቶ ለማሳየት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሰረቱ ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት የመጣው ብሄር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ትርክት፣ ወጣቱን መሰረቱን እያሳጣው ስለሆነ፣ ያንን ሚዛን የማስጠበቅ ግብና ዓላማ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው።
በምን መልኩ ነው ይሄን አላማችሁን የምታሳኩት?
እንግዲህ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እናደርጋለን። አንዱ ትውልድን ማስተማር ነው። በሌላ በኩል፤ የቃልኪዳን ሰነድ ወይም አሜሪካኖች ቢል ኦፍ ራይትስ የሚሉት አይነት ለማዘጋጀት ነው እቅዳችን። እነዚህ  በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የሚቀመጡ አንቀጾች የማይሻሩ የማይለወጡ ናቸው። በዚህ መልኩ ሰነዱ በምሁራን ተዘጋጅቷል። ይሄን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተቀብለው አጽድቀውታል። ይሄ የቃልኪዳን ሰነድ ሁሉም ተወያይቶ ከተቀበለው ሃገራችንን በጽናት ለማስቀጠል በጣም ወሳኝ ነው።
አሁን በሥራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት ተቋማችሁ እንዴት ይመለከተዋል?
እኛ በህገ-መንግስቱ ያሉ ሁሉ ትክክል አይደሉም የሚል ድምዳሜ የለንም። ነገር ግን ከእሳቤው ጀምሮ በርካታ አንቀጾች መሻሻል ይገባቸዋል ብለን በዝርዝር አስቀምጠናል።
ለምሳሌ የትኞቹ?
አንቀጽ 39  አንዱ ነው፣ የዜግነት መብትን በተመለከተ፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የሃገር ባለቤትነትን የሚገድቡ የክልል ህገ-መንግስቶች ላይ የሰፈሩ አንቀጾች ተጠቃሽ ናቸው። በርካታ መሻሻል ያለባቸው አንቀጾች አሉ።
ኢትዮጵያዊነት ባለፉት 30 ዓመታት የገጠመው ፈተና ምንድን ነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው ትላላችሁ?
እኛ በጉዳዩ ላይ በርካታ ውይይቶች አድርገናል፤ እናደርጋለን። በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ የገጠሙን ችግሮች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ባለፉት 30 ዓመታት እንዲደበዝዝ፣ ብሄር እንዲጎላ ተደርጓል። የኢትዮጵያዊነት እሴቶች እንዲደበዝዙ ተደርገዋል። ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ማንነትም ነው። የያዘን የጋራ ማንነት አለን። ህዝባችን በደም የተዋሃደ፣ ሲበላለቅ የኖረ ነው። በእነዚህ ዘመናት ሁሉ ያዳበራቸው የጋራ እሴቶች አሉት። በዘረመል ደረጃም እንለካው ከተባለ እጅጉን ተመሳሳይ ነው። በልዩነት ላይ ብቻ ስለተሰበከ ልዩነታችን ብዙ ይመስላል እንጂ የጋራ ማንነታችን እጅግ ትልቅ ነው።
የዘውግ ብሄርተኝነትንና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማስታረቂያው መንገድ ምንድን ነው? እናንተስ እንደ ተቋም በዚህ በኩል ምን ልትሰሩ አስባችኋል?
ሰዎች የዘውግ ብሔርተኛ መሆናቸው ችግር የለውም። ችግር የሚሆነው የዘውግ ብሔርተኝነቱ ዋነኛ የፖለቲካ ማቀንቀኛ መሳሪያ ሲሆን ነው። ተቋማችን “ኢትዮጵያዊነት”፤ በግለሰብ መብት፣ በአገር አንድነት፣ በአብሮነት፣ በኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲሁም በዲሞክራሲ ያምናል። በአካባቢ ደረጃ ቋንቋዎች መከበር አለባቸው። ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ መማራቸው ምንም ችግር የለውም፤ ግን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ሊቃረን አይገባውም። ኢትዮጵያዊነት በአንድ በኩል የዜግነት መገለጫ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማንነት ነው።
የዜግነት መብት ቅድሚያ ሲሰጠው ኢትዮጵያዊ ማንነትም ይጎለብታል። በአለም ላይ ሁሉም ሃገሮች ሊባል በሚችል ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጡት ለዜግነት መብት ነው። በእኛ ሀገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ለብሔሮች መብት ነው። የብሔሮች መብት መከበሩ ትክክለኛና ተገቢ ነው። ነገር ግን ዜግነትንና ኢትዮጵያዊ ማንነት በሚጠላት መልኩ ችግር ይፈጥራል። ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን ማስታረቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ምሁራን ቁጭ ብለው ሊወያዩና ሊመክሩ ይገባል።

Read 11926 times