Print this page
Saturday, 19 March 2022 11:08

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

        አንድ ነገር ልንገርህ? ቀና አትበል.. !!
                                መላኩ ብርሃኑ


           ኑሮ “ጣራ ነክቷል” ከሚለው ቃል ይልቅ “ሰማይ ረግጧል” የሚለው የበለጠ ይገልጸዋል። ትናንት እንደቀልድ “ድሮ” ሆኗል። ከሁለት ዓመት በፊት የተጋቡ ሙሽሮች “ኑሮ በኛ ጊዜ” እያሉ የሚተርኩባት ሃገር ላይ ነን ያለነው።
ብዙ ጊዜ እንደምለው “ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት ከዛሬ የተሻለ ነበር። ዛሬ ደግሞ በሁሉም መስፈርት ከነገ ይሻላል” ...
ይደክማል...በጣም ይደክማል...ሰርተህ ያጠራቀምከው መቶ ብር ባንክ ተቀምጦ በዓመት 35 ብር ይቀንሳል። ኪስህ ዳጎስ ብሎ ኮንደሚኒየም እገዛለሁ ብለህ ያጠራቀምከው ገንዘብ፣ ከባንክ ሲወጣ ቤት ቀርቶ የቤት እቃ ለመግዛት አይበቃህም። የዛሬ ሁለት ዓመት 350ሺህ ብር ሲሸጥ የነበረ ቪትዝ ለመግዛት አቅደህ በብድርም፣ በስራም ያገኘኸውን ገንዘብ አጠራቅመህ ‘ሞላልኝ’ ስትል ዋጋው ካለህ ገንዘብ በሁለት እጥፍ አድጎ ይጠብቅሃል። ያንተ ብር ለባጃጅም የማይበቃበት ቀን እየበረረ ሲቀርብ በአይንህ ታየዋለህ።
ትለፋለህ...አቀርቅረህ ውለህ አቀርቅረህ ታድራለህ...ጉልበትህ እስኪዝል ትሰራለህ...በታክሲ ተንከራትተህ ...ጸሃይ ጠብሶህ...በእግርህ ኳትነህ ከምታገኘው ጥሪት ላይ ነገን የተሻለ ለማድረግ ከራስህም ከልጆችህም ጉሮሮ ነጥቀህ ታጠራቅማለህ...ገንዘብህ ወደ ታች ሲጓዝ ኑሮ ወደ ላይ እየወጣ የማይገናኙ ‘”ደሃና ገበያ’ ይሆኑብሃል። አሁን ባለው ፍጥነት ኑሮን ግን በሩጫ አትቀድመውም... አንተ ባለ በሌለህ አቅም ብትሮጥም፣ እሱ ሁለት ሶስት ዙር በማራቶን ፍጥነት ደርቦህ ታገኘዋለህ። በዚያ ልክ እፈጥናለሁ ብትል..ልብህ ይፈነዳል።
እዚህ ሃገር በጣም ለፍቶ አዳሪዎች አሉ። በደንብ ታያቸዋለህ። ሲሰሩ..ሲታትሩ...ለመሻሻል ሲተጉ ታያቸዋለህ። ..ሰው ከደረሰበት ልድረስ ብለው ሳይሆን፣ ከትናንት በተሻለ ዛሬ ለመኖር የሚተጉ ሞልተዋል። እነርሱ ናቸው ብልሆች።
በዚያኛው ወገን ደግሞ ሃብት በላይ በላዩ ሲቆለል ታያለህ... ጎተራ ሞልቶ ይፈስሳል...ገንዘብ እንደወረቀት ይበተናል። አዲስ አበባ ለቅንጦት አልበቃው ብላ ውሎና አዳሩ ‘በምትመጥነው’ ዱባይ ላይ የሆነ ስንት ሰው አለ።
ወዳጄ! ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዉ ከመንግስት በላይ ሃብታም ሆኗል። የአዲስ አበባ አስፓልት ለጎማው ስለማይመች ብቻ ላምቦርጊኒ መግዛት ባለመቻሉ የሚያማርር ብዙ ነው። ደህና መንገድ ከሌለህ ላምቦርጊኒ...ሚዘራቲ... ሮልስሮይስ... አልፋሮሚዮ...መኪና ምችት ብሎህ አትነዳም!! ...ስለዚህ ልትማረር ነው ማለት ነው።
ወጣ በል እስኪ...ቦሌ አካባቢ...ለቡ..ሲኤም ሲ...ከሰሞኑ ደግሞ ለሚ ኩራ...ሂድ። መንገድ ላይ ሽንጠ ረጃጅም ...ቁመተ ግዙፍ መኪኖች አልበዙብህም? የሶስት ቪትስ ቁመት የማያህላቸው እነ ጂኤምሲ...ሬቮ...ፎርድ...ታኮማ በአጠገብህ የታንክ የሚያካክል ጎማቸውን ከአስፓልት እያፋጩ... በሞተራቸው እንደ አንበሳ እያገሱ አይተላለፉብህም?... ሃመር መኪናን ‘ፋሽኑ አለፈ’ ብለው የሚንቁ ሰዎች አልበዙብህም?...
አትያቸው! ፈጽሞ ቀና አትበል። አቅርቅርና የጀመርከውን ብቻ ጨርስ። የራስህን ኑር... የራስህን ስራ... ከነርሱ አትፎካከር። አይበልጡህም። በጭራሽ!!
ምክንያቱን ልንገርህ...
ቀና ብለህ ብታያቸው በቅንጦት መሪውን የሚዘውሩት አንገታቸው ላይ ሰንሰለት ጌጥ ያጠለቁ...ክንዳቸው በታቱ ያበደ...ሪዛቸው የረዘመ...መነጽራቸው መስኮት የሚያህል...ባለ ልዩ ኮፍያ ወጣቶች ናቸው። ብዙዎቹ ባንተ እድሜ ሳይሆን ካንተ እድሜ በታች ያሉ፣ በመድሃኒት ሃይል ሪዝ ካበቀሉ ገና ሁለት ዓመት ያላለፋቸው ወጣቶች ናቸው። ለአንድ መኪና 12 ሚሊዮን ብር ከየት አምጥተው ከፈሉ? አንድ ቤት በ60 በ70 በ 80 ሚሊዮን ብር ከየት አምጥተው ገዙ? ...እመነኝ ሌቦች ናቸው።
ሌብነት ከሰው መስረቅ ብቻ አይደለም...አጭበርብሮ መበደር.. በተጭበረበረ መያዣ በተገኘ ብድር ሃብት ማገለባበጥ...አጭበርብሮ መሬት መሸጥ... ባለጊዜ ሆኖ የህዝብ ሃብት መቀራመት... በስልጣን..በአምቻ ጋብቻ በሃገር ሃብት ላይ መጠቃቀም... በዘመድ ጨረታ ማሸነፍ...ቀረጥ ሳይከፍሉ እቃ አስገብቶ መቸብቸብ ...ይህ ሁሉ ነው ሌብነት።
ገንዘቡ የመጣው እንዲህና እንዲያ ሆኖ እንጂ ተሰርቶና ተለፍቶ አይደለም። አንድ የ28 እና 30 ዓመት ወጣት በኢትዮጵያ ኑሮና እድገት ለዚህ የሃብት ጣሪያ መድረስ እንዴት ቻለ?...ሌላው ሌላው ሁሉ ቀርቶ እድሜው ብቻውን አይፈቅድለትም እኮ!!
ለዚህ ነው ቀና አትበል የምልህ...ቀና ብለህ እነዚህን ካየህ ተስፋ ትቆርጣለህ... ልፋትህና ፍላጎትህ ተራርቆ ለዛሬ ስላልደረሰልህ ትናደዳለህ... የጀመርከውን ትተዋለህ... ያሰብከውን ትሰርዛለህ...እጅህን ታጣጥፋለህ.... ባንተ ተስፋ ያዘለ ቤተሰብህንና ስንት የሚጠብቀውን ጠንካራውን ራስህን የበለጠ ትጎዳለህ። በአጭር አማርኛ ብቻህን ማውራት ትጀምርና ‘ትለቅቃለህ’። ተስፋ መቁረጥን የሚያህል የሰው ልጅ ጠላት የለም። ተስፋ እንዳያስቆርጡህ!
ቀና እንዳትል። አቀርቅረህ የጀመርከውን መንገድ ቀጥል...የጥቂት አመታት ጉዳይ እንጂ ፍሬ ታፈራለህ። ይህ ሁሉ ወፍ ዘራሽ ፣ ንፋስ አመጣሽ ሃብት መራገፍ ሲጀምር ...ያኔ እንደ ማዕበል የሚናጠው... ከኢኮኖሚክስ ትንታኔ በላይ የሆነው... ያበደው ገበያ ጸጥ ይላል። ያኔ አንተም በተመኘኸው ልክ ባይሆንም በተሻለ ሁኔታ ትኖራለህ...በሰራኸው በለፋህበትና ባገኘኸው ገንዘብ ብቻ። ያ ቀን መቼ ነው? ዋቃ ያውቃል።
...ኢትዮጵያ ውስጥ ህይወት በጣም ያደክማል... በእያንዳንዱ ቀን ብዙ ሰዎች ከቤታቸው እርጥባን ጥየቃ አደባባይ እየወጡ ነው... በዚሁ ልክ መንገዱ በቅንጡ መኪኖች ጠቧል...ተዘግቶ የሚጠጣባቸው ቤቶች በርክተዋል... ገንዘብ እንደወረቀት ይበተናል። ሃብት እንደጉድ ይፈስሳል። መሬት ዋጋው አይቀመስም...ግን እንደጉድ ይቸበቸባል። 50 ሚሊዮን ብር የአንድ ቤተሰብ የወራት በጀት እየሆነ ነው። ፈረንጅ ሃገር ዘና ብሎ የሚኖረው ማነው? ዕድሜው ገፋ ያለው ሰው..ሞርጌጅ ከፍሎ የጨረሰው ሰው...ከእዳ የተላቀቀው ሰው ብቻ ነው። ወጣቱስ? ወጣቱማ ኑሮን ለመቋቋም ሲለፋ...ሲታገል ... ሲጥር ነው የምታየው። እኛ ሃገር ና። ... 40 ዓመት ሰርተው ጡረታ የወጡት ኑሮ ከብዷቸው (ካላቸው) ቤታቸውን እያከራዩ፣ ከሌላቸው ዘበኝነት ተቀጥረው ኑሮን ሲገፉ ወይም እንደደኸዩ ሲያልፉ ታያለህ። ገና እጁ አካፋ ያልነካው ወጣት ደግሞ በማይታመን ፍጥነት፣ ሰው ባላወቀው መንገድ ተጉዞ ወደላይ ‘ሲተኮስ’ ትታዘባለህ።
ኢትዮጵያ ሁሌም የተቃርኖ ሃገር ናት። ብዙ አብዮት ሄዶ ብዙ አብዮት ቢመጣም ለውጥ የለም። ከትናንት ዛሬ የማይሻልበት ህይወት የምትገፋባት ሃገር፣ የኛይቱ ኢትዮጵያ ናት።
እና ወንድሜ!! ...በቃ ...ቀና አትበል! ዘመነኞቹን አትያቸው! እርሳቸው። ተስፋ ያስቆርጡሃል...’ያጨልሉሃል’ ...ኑሮህን ዝም ብለህ ኑር። ስራህን ብቻ ስራ።
___________________________________________________

                     ኢትዮጵያን ለቀቅ፤ ግፈኞችን ጠበቅ!
                          ሙሼ ሰሙ


              ከትናንት ጀምሮ በማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ላይ እየተዘዋወረ የሚገኘው ምስል እንኳን ሙሉውን ለመመልከት ድርጊቱ መፈጸሙን ማሰብ እንኳ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ነውረኝነትና ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሰውን የሚያህል ክቡር ፍጡር በአሰቃቂ ሁኔታ በእሳት ከእነ ነፍሱ ማቃጠል በማንኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ነውረኛ ተግባሩን የፈጸሙት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብሔራቸውና ማንነታቸው ከየትም ይሁን ከየት ታድነው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግስትም አቋሙን በማያወላውልና ግልጽ በሆነ ቋንቋ መግለጽ አለበት፡፡ እንደዚህ አይነቱን አስነዋሪ ድርጊት እንደማይታገስና በሀገራችንም እንደማይደገም ቃል መግባት አለበት፡፡
እንደዚህ ዓይነት አረመኔዎችና የማህበረሰብ ኪሳራዎች በዓለም ላይ በሁሉም ሀገሮች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ትናንትም ነበሩ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። ሀገራችንንም ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚለያት አንዳችም ነገር ስለሌለ፣ እንደዚህ ዓይነት ነውረኛ የማህበረሰብ ኪሳራዎች ትናንትም ነበሩን፣ ዛሬም አሉን፤ ወደፊትም ይኖሩናል፡፡
ጥሬው ሃቅ ይህ ሆኖ እያለ ጥቂት አረመኔዎችና የማህበረሰብ ኪሳራዎች ለፈጸሙት ተግባር ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን በጅምላ ለመውቀስና ለማዋረድ መሞከር ግን አሳዛኝም አስተዛዛቢም ነው። ኢትዮጵያዊ ስንባል እኔንም፣ አንተንም እናንተንም የሚመለከት ስለሆነ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች እብደት የተነሳ ኢትዮጵያን ዝቅ ለማድረግ መሞከርን አልቀበለውም፤ ሊዋጥልኝም አይችልም፡፡ እጅግ በልጽገናል በሚሉና እራሳቸውን የዲሞክራሲ ቁንጮ ባደረጉ ሀገራት ውስጥም ከዚህ ያልተናነሰ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ሲፈጸሙ አይተናልም ታዝበናልም፡፡
ኢትዮጵያ ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት ትልቅ ሀገር ነች፡፡ ለበርካታ ወንድም ሀገሮችና ሕዝቦችም ምሳሌ መሆን የቻለች ተጠቃሽ ሀገር ናት፡፡ እጅግ የተወሳሰቡ ውብና ድንቅ ማህበራዊ እሴቶች፣ ማህበረሰባዊ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ያካበተችና ለዘመናት በርካታ ጠንካራ ባህሎቿንና ልማዶቿን ይዛ ሕልውናዋን ማስቀጠል የቻለች ሀገር ነች፡፡ የዛን ያህል የዘመናት የእርስ በርስ ግጭት፣ የመስፋፋት የመጥበብ፣ የመውደቅና የመነሳት ውጤት እንደመሆኗ መጠን ብዝሃነቷ ለተለያዩ ግጭቶች ቢዳርጓትም፣ ግጭቶቹ የውጣ ውረዶቿና የሂደቷ ዓይነተኛ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እንደማንኛውም ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥም ከማህበረሰባዊ ልምድ ባህልና ዘይቤ ያፈነገጡ ማህበረሰባዊ ኪሳራዎች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ካልሆነ በስተቀር በነዚህ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ምክንያት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚወቀሱበት አንድም ሰበብ ወይም ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ መፍትሔውም በጅምላ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ማዋረድ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለቀቅ አድርጎ ግፈኞችን፣ ወንጀለኞችንና ወንጀልን ጠበቅ ማድረግ ነው::

________________________________________________

                            ካንደኛው ፌርማታ ወዳንዱ ስሻገር፥
                               በእውቀቱ ስዩም


ይፈርስ የማይመስል፥ እስከ ዘላለሙ
አምና እዚህ ቦታ ላይ ፥አንድ ሱቅ ነበረ
የሱቁ ባለቤት ሚፍታህ ነበር ስሙ፤
ሙሉቀን ሲተጋ፥ በከፊል የሚታይ፥
እንደዜና አንባቢ፥ በሱቁ መስኮት ላይ
ከወገቡ በላይ፥እየተገለጠ
ለወጭ ወራጂው፥ ፈገግታ እየሰጠ
ሸቀጥ እየሸጠ
በጋዜጣ ቅዳጅ እየጠቀለለ
በልቃቂት አምሳል እየሸበለለ
“የሁለት ብር ሱካር ፥ የብር ካምሳ ዳቦ
ጢንጥየ ቅመም
ትንሽየ ለውዝ፥የሽልንግ አሻቦ፣
ከተጠቀለለው በልቃቂት አምሳል
ድሀውም ሀብታሙም ድርሻውን ያነሳል፤
“አደራው ጥብቅ ነው ፥ዱቤም አይከለክል
ባንክ አይታመንም የሚፍታህን ያክል’
“አንደበቱ ቀና፥ መዳፎቹ ትጉ
ከቶ እንደሱ የለም የትም ቢፈልጉ”
ይሉት ነበር ሴቶች ቡና ላይ ሲያወጉ
አሁን እዚህ ቦታ ፥ረጅም ፎቅ ቆሟል
ከፊት ያለው መንገድ ባዲስ ተሰይሟል
ሚፍታህ ጎዳናው ላይ ፥ዱካውን አልጣለም
የት ይሆን አድራሻው
የሚነግረኝ የለም፥
ካንደኛው ፌርማታ ወዳንዱ ስሻገር
ከሳር ከቅጠሉ የምሰማው ነገር ፥
‘የከንፈር ወዳጅህ ፥ባለፈው ተዳረች
ዘመድህ በስደት ባህር ተሻገረች
ጉልማ ታሰረ
ወንዴ ዘምቶ ቀረ
አመዴ ከሰረ
የሚል ብቻ ሆኗል
በኔ ሰውነት ውስጥ ስንት ህዋስ ከስሟል
ስንት ተስፋ ወድሟል
ስንት ስጋት ለምልሟል፥
ተጋርዶብኝ እንጂ ቀድሞ ባይታየኝ
“ደረስ ብየ ልምጣ፥ ጠብቀህ አቆየኝ”
ያልኩትን መካዱ
አደራ መብላት ነው የጊዜ ልማዱ::

____________________________________________

                       መለስ ዜናዊና ጋዜጠኛ ፖል ሄንዝ...2
                             ጌታሁን ሔራሞ


              ውሸትና አጭበርባሪነት የብሔር ፖለቲካ ነጋዴዎች ልዩ ምልክታቸው ነው፤ በዚህ በአንድ ወቅት የተሸወደ ትውልድ ይኖር ይሆናል፤ የአሁኑን ትውልድ ግን መሸወድና ማታለል አይቻልም።
ወደ መለስ ዜናዊ “ሸዋጅ” ቃለ መጠይቅ አንዴ እንመለስ እስቲ! መለስ... "የትግላችን ዋና ዓላማ የአማራን የበላይነት (Amhara domination) ማስወገድ ነው..." በማለት ለጋዜጠኛ ፖል ሄንዝ ከ30 ዓመታት በፊት የነገረው በዚህ መልኩ ነበር፦
“The country will have to be a federation and there will have to be recognition of the right of every people in it to have autonomy. We can no longer have Amhara domination.”
በዚህ ንግግሩ ግራ የተጋባው ፖል ሄንዝ ሌላ ጥያቄ ጠየቀው፦
“What do you mean by AMHARA domination? If this is your message, how do the people in the regions where you have recently advanced – – Lasta, Gaynt, Saynt, Manz, Merhabete, etc., all of which are inhabited predominantly by Amhara – – look on your movement?”
መለስ ይህን ሲናገር ላስታ፣ ጋይንት፣ ሳይንት፣ መንዝ፣ መርሐቤቴ ወዘተ በሕወሓት ቁጥጥር ውስጥ ነበሩ። ፖል ሄንዝ “ይህ ንግግርህ በተጠቀሱት አካባቢ በሚኖሩ አማሮች ዘንድ ስለ እንቅስቃሴያችሁ ያለውን ግንዛቤ አያበላሸውም ወይ?” ማለቱ ነበር። ያኔ መለስ አክሮባት ሰራና “ችግራችን ያለው ከሸዋ አማራ ጋር ነው፤ የጠቀስካቸውማ ጭቁን አማራዎች ናቸው” በማለት መለሰለት፦
“These Amhara are oppressed people. When we talk about Amhara domination, we mean the Amhara of Shoa, and the habit of Shoan supremacy that became established in Addis Abeba during the last hundred years.”
እዚህ ጋ መለስ የሆዱን ተናገረ፤ የአፄ ዮሐንስና የምኒልክ ፖለቲካን ስቦ ወደ ዘመኑና ዘመናችን አመጣው፤ በጣሊያኖችና እንግሊዞች የተዘራው የሸዋ-ትግራይ ፖለቲካ በቅሎ ስለማበቡ ይፋ አደረገልን።
የመለስ ውሸቶች፦
1. በፖል ሄንዝ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሱት መንዝና መርሐቤቴ የሚገኙት በሸዋ ውስጥ ነበር፤ በአንድ በኩል እነዚህንም አማራዎች ከላስታና ጋይንት አማሮች ጋር ደምሮ “ጭቁኖቹ አማሮች” እያላቸው፣ በተቃራኒው ደግሞ “When we talk about Amhara domination, we mean the Amhara of Shoa...”እያለ ይቀባጥራል። የሸዋ አማራ “dominant” ነበር ካለ የመንዝና የመርሐቤቴ አማራ በየትኛው ሎጂክ ነው እንደገና “ጭቁን” ሆነው የቀረቡት? አቤት ውሸት!
2. በሌላ አነጋገር መለስ በምላሹ አማራው በወቅቱ ገዢ መደብ ይጨቆን እንደነበረ በምላሹ አካቷል፤ እንግዲህ የፊውዳል መደብ ጭቆናው ለሁሉም ከተዳረሰ “የብሔር ጭቆና” ትርክቱ ምን ሊሆን ነው? የሸዋ አማራው የጋይንቱን ከጨቆነ፣ ጭቆናው የመደብ እንጂ የብሔር ሊሆን አይችልም። ደግሞ እዚህ ጋ የርስትና ጉልት የገባር ጭሰኛ ወዘተ ሙግት ይነሳ ይሆናል። እናስ በፊውዳል ሥርዓት በወቅቱ ንቃተ ሕሊና ሲመዘን ይህ ባይኖር ነበር የሚገርመን። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ያለፈችበት የታሪክ ምዕራፍ አይደለም። ለዚህም “The Making of Europe: Conquest, Colonization, and Cultural Change, 950-1350, by Robert Bartlett, 1994” ማንበብ የኛው ከአውሮፓው ጭምር የተለየ እንዳልሆነ ለመረዳት ያግዘናል። ግን ጥያቄ አለኝ፤ ያንን ለዚያው ዘመን ትተን ስንመለስ፣ ዛሬ በ21ኛውም ክፍለ ዘመን በሀገራችን ኢትዮጵያ የርስትና ርስት አልባ ትርክትን የፊውዳል ሥርዓት ነቃሾች የሆኑ የብሔር ፖለቲከኞች እንደመሠረቱልን ማገናዘብ ያን ያህል ይከብዳል? የዚህ ክልል መሬት ባለቤት እንትና የሚባል ብሔር ነው...በክልሎች ሕገ መንግሥት ሳይቀር የሰፈረው ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘ አይደለምን? ነባር ተብዬው ባለርስት፣ መጤና ሰፋሪው ርስት አልባ የሆነውስ መቼ ነበር? የኢትዮጵያዊነት የዜግነት ባለቤት መሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው ሉዓላዊ ድንበር ውስጥ ማንም መጤ እንዳይባል ያበቃ ነበር። ዕድሜ ለብሔር ፖለቲካ ይሁንና፤ ኢትዮጵያዊያን “ኢትዮጵያዊ “ ያልሆኑበት አያሌ ክልሎችን አስታቅፎናል። “ኢትዮጵያዊ ዜግነት” ሰፈርህና እትብትህ የተቀበረበት መንደር ላይ ብቻ የሚሰማህ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ጠብባ ወደ ሰፈርነት ተቀይራለች ማለት ነው። The stupid ethnolingustic federalism is accountable for this!
3. መለስ ዜናዊ ተልዕኮው የአማራን የበላይነት ማስወገድ ነው ብሎን ነበር? ግን እሱ በለስ ቀንቶት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ያሰፈነው የማንን ብሔር የበላይነትን ነበር? በአንድ ወቅት ጠ/ሚ ዐቢይ በተለይ በመከላከያው ውስጥ የሰፈነውን የአንድን ብሔር የበላይነት በፐርሰንት እያስቀመጡ የዘረዘሩትን እዚህ እንዘርግፈው? ታች እስከ ክልል ድረስ የተዘረጋውንስ የአንድን ብሔር መረብ ይፋ እናድርገው? “Domination”ንን አምርሮ የነቀፈ ሰው የከፋ “Domination”ንን ተክሎ ሲሄድ ምን እንበለው? አሁን ሥልጣን ላይ ያሉትስ ሌላ የ”Domination pattern” እየደገሙት ስለመሆኑ የሚወራውንስ በየትኛው ትከሻችን እናስተናግደው? በቋንቋና በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ የማታ ማታ የሚጠናቀቀው በ”Domination” ነው። ይህ ዕውን ካልሆነ በ”Ethnic head counting” ላይ በተመሠረተው በቀጣዩ ምርጫ ማን ይመርጣቸዋል? የብሔር ውክልናን ይዞ በሥልጣን መንበር ላይ የተቀመጠ ለብሔሩ “dominance” ባይታገል ይደንቀን ነበር።
4. ሌላው የመለስ ውሸት የተንፀባረቀው ከፓርቲ ስያሜ ጋር በተገናኘ ነው። መለስ ለፖል ሄንዝ ሕወሓት ማርክሲስት-ሌኒንስት አለመሆኑን ለማስገንዘብ በሄደበት ርቀት እንደ ማስረጃ ያቀረበው የፓርቲውን ስያሜ ነው...ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ...የሚለውን። በዚህ ስያሜ ውስጥ ማርክስንም ሆነ ሌኒንን አሊያም ርዕዮታቸውን የሚጠቅስ ነገር የለም ማለቱ ነበር።
“ We are not a Marxist-Leninist movement. We do not apply Marxism-Leninism in Tigray. The name of our organization does not include any reference to Marxism-Leninism”
ለአቶ መለስ የሚኖረን ምላሽ ፦ የፓርቲ ምደባ በስያሜ ብቻ አይከወንም...ውስጡን ለቄስ... እንዲል የሀገሬ ሰው!! በሕገ መንግስቱ መኸል ላይ እንደ ምሶሶ የሌኒንን “የብሔር መብቶችን እስከ መገንጠል” ቃል በቃል ኮርጆ ካስቀመጠ በኋላ “እኛ እኮ ሌኒንስት አይደለንም; ማለትን ምን አመጣው? ስያሜ ብቻ ሳይሆን የፓርቲ ማኒፌስቶም ለፓርቲ ምደባ ጥቅም ላይ ይውላል። እንዲያውም ለጊዜው ማርክስን እንተወውና ሕወሓት ድብን ያለ ሌኒንስት-ስታሊንስት መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ምርምር የሚያሻው አይደለም። በስያሜ መሸወድ አይቻልም!
በሌላ አንፃር አንድ ፓርቲ በስያሜው ብቻ ሀገራዊ ፓርቲም ሊሆን አይችልም፤ በዚህ ረገድ ስለ “Ethnic party categorization” በአንድ ወቅት አንድ መጣጥፍ ማካፈሌን አስታውሳለሁ። አንድን ፓርቲ የጎሳ/የዘውግ/ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመፈተሽ የሚረዱን አያሌ መንገዶች እንዳሉ ታዋቂዋ የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንትስቷ Kanchan Chandra እ.ኤ.አ. በ2011 “What is an ethnic party?” በሚል ርዕስ በለቀቀችው ጥናታዊ ፅሁፍ ውስጥ ከጠቀሰቻቸው አምስት ያህል መንገዶች ውስጥ ሶስቱ የሚከተሉት ናቸው፦
ሀ) በፓርቲው ስያሜ
ለ) በፓርቲው ማኒፌስቶ
ሐ) በፓርቲው የመራጮች ማንነት
ናቸው።
ለምሣሌ የፓርቲው ስያሜ ምንም ይሁን ምን በፓርቲው ማኒፌስቶ ውስጥ “የኔ ብሔር ፈርስት” የሚል መርህ ከተንፀባረቀ ፓርቲው የብሔር ነው ማለት ነው። እንዲሁም የአንድ ፓርቲ ስያሜ ..ባልደራስም ይሁን የኦሮሚያ ብልፅግና... ሆኖ የምርጫው መርህ ግን...ዘመድ ከዘመዱ አህያ ከአመዱ(Ethnic head count) ...እንደሚባለው ከሆነ፣ ያ ፓርቲ የብሔር ፓርቲ ነው ተብሎ ይመደባል። ማለትም አንድን ፓርቲ 100% ይሁን በአብላጫው አንድ ብሔር ብቻ ከመረጠው(Group Vote) ያ ፓርቲ የብሔር ፓርቲ ነው ተብሎ ይመደባል። ስያሜ ብቻውን ለፓርቲ ምደባ ጥቅም ላይ አይውልም። የፍተሻ ኬላዎቹ አያሌ ናቸው፤ እናም “ፍተሻ አለ!”። ትውልዱ የተባለውን ሁሉ እንደወረደ የሚያምን የዋህ ትውልድ አይደለም....ፈታሽ ነው።
መልካም ቀን!

__________________________________________

                             አንባቢ በሌለበት ሃገር …ታሪክ አይጻፍም !!
                               መላኩ ብርሃኑ


              ይህንን መረጃ አይቶ የማይደነግጥ ሰው ራሱን ይፈትሽ !!
ኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ህዝብ አላት። ይህ ህዝብ መስከረም 2013 ዓ.ም ላይ ሃገሩ ያተመችው ጋዜጣ ብዛት 6 ብቻ እንደሆነ አያውቅም። ቢያውቅም ግድ የለውም።
መጽሄቶቹ ደግሞ 9 ብቻ ናቸው። ሁለቱን ደምሯቸው …15 !! ….
(የኮፒውን ብዛት ተዉት! 5 ሺህ የዘለቀ ካለ ብረት ነህ በሉት)
የሚገርማችሁ ነገር ከ2001 ጀምሮ እስከያዝነው 2013 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በ10 ዓመት በአጠቃላይ የተመዘገቡና ታትመው የተነበቡ ጋዜጦችና መጽሄቶች ቁጥር 463 ብቻ ነበር።
ከነዚህ ውስጥ 352 ጋዜጦችና መጽሄቶች (ደፍሬ እናገራለሁ) በዋናነት ገዝቶ የሚያነባቸው ሰው ስላጡ ህትመት አቋርጠዋል፣ ሰርተፍኬት መልሰዋል፣ ፍቃድ ተሰርዞባቸዋል። በሌላ አነጋገር አብዛኞቹ በኪሳራ፣ በጣም ጥቂቶቹ በሟቹ ኢህአዴግ ጉልቤነት ተዘግተዋል።
እንደእንጉዳይ ፈልቶ የነበረ የጋዜጣና መጽሄት ዘመን ወገብ ዛላው ተሰብሮ ዛሬ ያለበትን እያየሁ የኢትዮጵያ የህትመት ሚዲያ የቁልቁለት ጉዞን ባሰብኩት ቁጥር እንደእግር እሳት ያንገበግበኛል።
በመጀመሪያ ዲግሪ ጥናቴ ስፔሻላይዜሽኔ ብሮድካስት ላይ ቢሆንም ነፍሴ አብዝታ የምትረካበት፣ “በፍቅር ጨርቄን የጣልኩለት” ዘርፍ የህትመት ጋዜጠኝነት ነው። ይህ ዘርፍ ጋዜጠኛ ሳትሆን ልዳክርብህ ብትለው በራሱ ጊዜ አንገዋልሎ የሚተፋህ፣ ማንም ባልታጠበ እጁ ሊንቧቸርበት የማይችልበት ዘርፍ ነው። ሁሉም ነገር ቀርቶ በጣም በትንሹ መመዘኛ እንየው ካልን ጥሩ ጸሃፊነትን ይጠይቃል። የጻፍኩትን ስታነቡ ያየሁት ካልታያችሁ፣ የሰማሁት ካልተሰማችሁ ምንም አልጻፍኩም ማለት ነው። ሙያው ይህን ያህል ይረቅቃል።
እንዳለመታደል ግን ኢትዮጵያ የህትመት ውጤቶች ቁልቁል የሚሽቆለቆሉባት ሃገር ሆናለች። ለምን ለሚለው ጥያቄ መልስ እዚሁ ማዘጋጀት አይቻልም። ጥናት ይጠይቃል። የማይካደው አንደኛው ምክንያት ግን አንባቢ አለመኖሩ ነው።
በተለይ በዚህ የፌስቡክ ዘመን የጋዜጣና መጽሄት ዕጣ ፈንታ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል። አንድ ርዕስ ስታነሳ ልተንትን ብሎ ትን እስኪለው የሚጋጋጠው ህዝቤ ከሁለት አንቀጽ በላይ ለማንበብ ኮሶ አጠጡኝ ባይ ነው። (ይህንን ጽሁፍ ማንበብ የጀመረው ሰው ራሱ 100 ቢሆን እዚህ ድረስ የዘለቀው ግን 25 እንኳ ከሞላ ጽድቅ ነው ፣ ከዚህ በኋላ የሚቀጥለው ካለ ደሞ በረከት ወረደ በሉ ..ቂቂቂቂ)
ያም ሆኖ.....
ዛሬም ድረስ ከዚህ መቃብሩ ውስጥ ገብቶ አፈር እየተጫነው ካለ የህትመት ጋዜጠኝነት ጋር ለመዝለቅ በእልህ አንገት ለአንገት ተያይዛችሁ ለምትንገታገቱ ጥቂት የሙያ ባልደረቦቼ ጋዜጠኞች በሙሉ በአክብሮት እጅ እነሳለሁ!!
አንድ ኤፍኤም ላይ ተጥዳችሁ አርሴና ማንቼ፣ ፎንቃና ቅናት፣ ሙዝና ፓፓያ …ምናምን ብትተነትኑ ወይም የሆነ ዩቲዩብ ላይ ተጥዳችሁ “ሰበር ዜና” ምናምን ብትሉ የሚግበሰበሰው ሰው ዛሬ እናንተ ጋ ባይኖርም አንድ ቀን፣ ሃገር ስትሰለጥን ግን we shall prevail !!

Read 1481 times
Administrator

Latest from Administrator