Saturday, 19 March 2022 10:53

የእጩ መኮንን የመስክ ማጣሪያ (ፊልድ እስክሪን)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የምታየውን  ሁለት ኮከብ ወታደራዊ የማዕረግ ምልክት፣ በብሔር አስተዋጽፆ አልወሰድኩትም። በህዝብ ትግል የተሸኘው ቆሞ ቀር  አሊያም ለውጥ ተከትሎ የመጣ አዲስ ስርአት ገፀ በረከትም አይደለም። ኮኮቡ ከሰማይ ላይ ተንጠባጥቦ፣ ከብዙዎች መሀል መርጦ እኔ ትከሻ ላይም አላረፈም።
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከአስራ ሰባት አመቴ ጀምሮ አስራ ሰባት አመትን አገልግያለው። አስራ ሰባት አመት ስልህ፣ ህወሓት ጫካ የቆየበትን፣ ደርግ ሀገር የመራበትን ዘመን ያህል ማለት ነው። አስራ ሰባት ስልህ አስራ ሰባት መርፌ ቀድሞ ወደ ጭንቅላትህ ከመጣም ጣጣ የለውም።
ብቻ ምን አለፋህ፤ ይሄን የምነግርህ ሙገሳህንና አድናቆትህን ፈልጌ ከመሰለህም በእጅጉ ስተሀል።
ሌላውን ትቼ መኮንን ደረጃ  የደረስኩበትን ሂደት ብቻ በትንሹ ላጫውትህ እፈልጋለሁ። ጊዜው ካለህ በተከታታይነት የምከትብልህን አንብብ!
አንድ ወታደር በአጭር ኮርስ መስመራዊ መኮንን ለመሆን  በሰራዊቱ ውስጥ የሀምሳ አለቃ ማዕረግ መድረስ ይኖርበታል። በተጨማሪም በዚሁ ማዕረግ ከሁለት አመት በላይ የቆየ መሆኑ ለመታጫው መስፈርት ነው።
የሚወስደውን ጊዜ ከመሰረታዊ ወታደር አንስተን እስከዚኛው ጫፍ ካሰላነው፣ የሁለት ምርጫ ዘመን ያህል ይፈጃል። ቆይታውም ጦርነት በማያጣው በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም ኢትዮጵያ መሆኑን ልብ በል! መስፈርቱ በዚህ ብቻም አያበቃም። ባለ አንድ ኮከብ የምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ ትከሻህ ላይ ለመጫን በመከላከያ ደረጃ የሚሰጠውን የሳይኮሜትሪ ፈተና ማለፍና ከባዱን የመኮንነት ስልጠና ወስዶ መፈፀምም ግድ ይላል።
የእጩ መኮንን ስልጠና፣ በብዙ ወታደራዊ ትምህርቶችና ትንፋሽ በማይሰጥ አድካሚ  የተግባር ልምምዶች  ታጅቦ  ስድስት ወራትን ይወስዳል።       
በውትድርና ውስጥ ከባድ ከሚባሉ ስልጠናዎች መሀል የመኮንነት ስልጠና  አንዱ ነው። ስልጠናው የሚጀምረውም የማሰልጠኛ ማዕከሉን መግቢያ በር ከዘለቅህበት ቀንና ሰአት አንስቶ ነው፡፡  
እዚህ ቦታ ለይ በዋዛ ፈዛዛ  የሚባክን ሰአትና ደቂቃ ፈፅሞ የለም። በጊዜያዊ ችግር ምክንያት የአንድ ቀን ስልጠና  ቢያልፍህ፣ ሳይከፈልህ እንደ ቀረ ደሞዝ የኋላ ቀሪ  ተብሎ ይመጣልሀል።
ለሁሉም ሰልጣኝ የእረፍት ቀን በሆነው እለተ ሰንበት ጠርተው፣ ብቻህን  ያለፈህን ፕሮግራም ያካክሱታል። ምን ማለቴ ነው? ለምሳሌ በሳምንት የሚደረገው የሩጫ ፕሮግራም  በህመም ምክንያት ቢያልፍህ፣ በሳምንቱ እረፍት እሁድ ቀን ጠርተው፣ ሰአት ይዘው ብቻህን ያስሮጡሀል።
ሲጀመር በማሰልጠኛ ማዕከሉ  እሁድም ቢሆን፣ የእረፍት ቀን ነው ለማለት ያስቸግራል። የእስፖርት ውድድሮች  አዘጋጅተው፣ በክፍል ደረጃ እያጋጠሙህ  ሲያለፉህ ይውላሉ።
እንደዚህም አድርገው በስድስት ወር ውስጥ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ከስልጠናው የቀረህ ከሆነ፣ ምክንያትህ ምንም ይሁን ምንም አትመረቅም። የማሰልጠኛ ማዕከሉ ሀላፊዎችም ሆኑ  አሰልጣኞች  ያልተፃፈ የሚመሩበት መርህ አላቸው። “ወደ ማሰልጠኛችን ቦርጭ  ይዞ መግባት ይቻላል! ቦርጭ ይዞ መውጣት ግን ፈፅሞ አይቻልም!” የሚል ነው።
እውነትም  ስልጠናውን እንደጀመርክ፣ ወርህ ሳይገባ ቦርጭህ አይደለም፣ ስጋህ እንደ በጋ ዳመና ሳታስበው ይጠፋል። ፊት እና ኋላህ ተዛብቶ በሀምሳ ሜትር ላይ የተመለከቱህ ጓደኞችህ “እየመጣ ነው! እየሄደ ነው!” ብለው ሊወራረዱብህ  ሁሉ  ይችላሉ።
ወደ ስልጠናው ማገባደጃ ወራት ላይ በተለይ ስጋህ ብቻ ሳይሆን በሽታን የመከላከል አቅምህ ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ተሟጦ፣ በእራስህ ፈስ ጉንፋን ሊይዝህ ይችላል። ስታስነጥስ ቆመህ ከሆነ፣ እንደ ጀበና በአናትህ ትተከላለህ። ቁጭ ብለህ ከሆነ፣ አፍጢምህ ከጉልበትህ ጋር ይላተማል።
የሲቪል ጓደኞቼም ሆናችሁ ለመኮንነት ያልደረሳችሁ ጓዶቼ፤ የስልጠናውን የስድስት ወሩን ቆይታ ትቼ ከመጀመሪያው የሶስት ቀን የመስክ ማጣሪያ ሂደት፣ የአንድ ቀን ከግማሿን ብቻ በወፍ በረር ባስቃኛችሁ በቀላሉ ትረዱኛላችሁ ብዬ አስባለሁ። በብዙ ያጎደልኩት የረሳሁት እንጂ የጨመርኩት ፈፅሞ እንደሌለ ግን አስቀድሜ  ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።
(እቀጥላለሁ).

Read 1379 times