Sunday, 13 March 2022 00:00

የሩስያ - ዩክሬይን አውዳሚ ጦርነት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   በኬዬቭ እሳት እየዘነበም፣ ሚሳኤል እያጓራም፣ እሪታ እየቀለጠም በጭንቁ መሃል ለአፍታ ብልጭ ብለው የሚጠፉ የሰላም ብርሃኖች፣ ለቅጽበት ተደምጠው የሚያልፉ የተስፋ ድምጾች አልታጡም፡፡
ሁለት ሳምንታትን በመከራ የገፋችው የዩክሬኗ መዲና ኬዬቭ፣ የክላሲካል ሲምፎኒ ሙዚቃ ኦርኬስትራ አባላት፣ ባለፈው ረቡዕ፣ ቆፈን እጅ እግራቸውን እየበረደውም፣ ስጋት ልባቸውን እያራደውም፣ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው ጭር ወዳለው የከተማዋ የነጻነት አደባባይ ወጡ፡፡
እሳት የሚያዘንብባቸው የኬይቭ ሰማይ ለሩስያ ገዳይ ጢያራዎች እንዲዘጋ ለመጠየቅና፣ አገራቸውን እየለበለበ ያለው የጦርነት እሳት ፈጥኖ ይጠፋ ዘንድ ድምጻቸውን ለማሰማት፣.ብሔራዊ መዝሙራቸውን በእንባ ታጅበው ዘመሩ። “የደስታ ስንኞች” የተሰኘውን የቤትሆቨን ተወዳጅ ሙዚቃ በተስፋና በምኞት ቅኝት በለስላሳው ሲያቀነቅኑ፣ ከስደት ይልቅ በአገራቸው አፈር ለመሞት ከወሰኑ የኬዬቭ ነዋሪዎች መካከል በጣት የሚቆጠሩት ዙሪያቸውን ከብበው ባንዲራቸውን እያውለበለቡ አጀቧቸው፡፡
ሙዚቃው ሲያበቃ፣ እሩምታው ግን ቀጠለ፡፡
ሁለተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የሩስያና የዩክሬን ጦርነት ከዕለት ወደ ዕለት እየተካረረ እንጂ እየላላ፣ እየተሟሟቀ እንጂ እየቀዘቀዘ የሚመጣ አልሆነም፡፡ ሁለቱም አገራት ያላቸውን የውስጥና የውጭ፣ የጦር ሜዳና የምጣኔ ሃብት አቅም ሁሉ አሟጥጠው በመጠቀም እስከ መጨረሻው ለመፋለምና በጀግንነት ለመውደቅ ወይ ለመቆም ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡
በጦር ሃይሏ አብዝታ የተማመነችው ሩስያ በአንድ እጇ ዩክሬንን፣ በአንድ እጇ የተቀረውን የምዕራቡ አለም በእልህ ተጋፍጣ ድል ለመንሳት ደፋ ቀናውን ስትያያዘው፣ ዩክሬንም ቤት ባፈራውም ወዳጅ ለክፉ ቀን ብሎ በላከውም ጦር መሳሪያና ዘማች ታግዛ ታላቋን ሞስኮ ለመገዳደርና እየገደለች ለመውደቅ ቆርጣ ተነስታለች፡፡
ለሩስያ አብረክራኪ ወታደራዊ ሃይል ያልተረቱት ባለካኒቲራው የዩክሬን መሪ ቮሎድሚር ዜለንስኪ፤ በዚያ በኩል እንባ በሚያራጭ ንቡር ጠቃሽ ንግግር፣ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ፣ የአየር ክልሏን ከበረራ እንዲዘጋላትና ከጎኗ እንዲቆም እየተማጸኑ፣ በዚህ በኩል ህዝቤን ይዤ በጀግንነት እሞታለሁ ብለው፣ ጦራቸውን እያበረታቱ፣ ጥቃት ሲመክቱ ሰንብተዋል፡፡
በተለይ ከሰሞኑ የሩስያን ጦር ባልተገመተ ሁኔታ መመከት መጀመሯ የሚነገርላት ዩክሬን፣ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ12 ሺህ በላይ የሩስያ ወታደሮችን መግደሏን በይፋ እያስታወቀች ቢሆንም፣ ሩስያ ግን የሞቱብኝ 500 ያህል ብቻ ናቸው ስትል ማስተባበል መያዟንና አሜሪካ በበኩሏ 4 ሺህ ይደርሳሉ ማለቷን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ተቋም ከፍተኛ ባለስልጣን፣ የሩስያ ጦር ወደ ዩክሬን ካዘመታቸው የጦር መሳሪያዎችና ተሸከርካሪዎች መካከል 5 በመቶ የሚሆኑት በዩክሬን መደምሰሳቸውን እንደተናገሩም ተዘግቧል፡፡
አገራቸው በሩስያ እሳት ስትለበለብ በሩቅ ሆነው ማየት ያላስቻላቸው በመላው አለም ተበትነው የሚገኙ 66 ሺህ 224 ዩክሬናውያን፣ ሁሉንም ትተው ነፍጥ ለማንሳትና ለክብራቸው ለመሞት ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዝኒኮቭ ተናግረዋል።
የሩሲያ ጦር በዩክሬን ከተሞች ኬቭ፣ ቼርኒቭ፣ ሱሚ፣ ማሪፖል እና ካርኪቭ የሚገኙ ዜጎች ከነበሩበት ለመውጣት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ማድረጉን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ግን ጥቃቱን ማቀጣጠል መጀመሩንና ከዩክሬን ጦር ያልጠበቀው መከላከል እንደገጠመው ተነግሯል፡፡
አሜሪካ ዩክሬንን ጦር ሜዳ ድረስ ወርዳ ለማገዝ የምትፈልግ ከሆነ፣ ፖላንድ ያሉኝን ሚግ 29 ጀቶች በሙሉ ልልክላት ዝግጁ ነኝ ብላ በይፋ ቃል ብትገባም፣ አሜሪካ ግን ድጋፉን እንዳጣጣለችው ዘ ጋርዲያን የዘገበ ሲሆን፣ ብሪታኒያ በበኩሏ ለዩክሬን የምታደርገውን የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ በእጅጉ ማሳደጓን በመከላከያ ጸሃፊዋ ቤን ዋላስ በኩል ረቡዕ ዕለት አስታውቃለች፡፡
ዋላስን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ብሪታኒያ ካሁን ቀደም ለዩክሬን ከለገሰቻቸው 2 ሺህ ያህል ዘመናዊ ጸረ ታንክ ሚሳኤሎች በተጨማሪ 1 ሺህ 615 ሰጥታለች፤ የተለያዩ አነስተኛና መካከለኛ የጦር መሳሪያዎችና ትጥቆች እንዲሁም የደህንነትና የህክምና ቁሳቁስ በብዛት መላኳንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲአይኤ በበኩሉ፤ ሩስያ የዩክሬንን መዲና ኪየቭ ለመቆጣጠር ያሰበችው በ48 ሰዓታት ውስጥ ቢሆንም ሊሳካለት እንዳልቻለ የገለጸ ሲሆን፣ የሩስያ ጦር ያጋጠመውን የሎጅስቲክ ችግር አስወግዶ በቀጣዮቹ ቀናት ሃይሉን በእጥፍ በማሳደግ ወረራውን ሊያጠናክርና በንጹሃን ዜጎች ላይ ሳይቀር የከፋ ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል አስታውቋል፡፡

ባለ 5532 ማዕቀቧ፤ ዕዳ መክፈል ያቃታት ´ታላቋ ሩስያ´
ዩክሬንን መውረሯ ከመላው አለም የማዕቀብ ዶፍ ያስከተለባት ሩስያ፣ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማዕቀብ የተጣለባት ቀዳሚዋ አገር ለመሆን መቻሏ ተነግሯል፡፡
ለዚህ ጦርነት ነጋሪት ከመጎሰሟ በፊት በአገራትና በተቋማት 2 ሺህ 754 ያህል ማዕቀቦች ተጥለውባት የነበረችዋ ሩስያ፣ ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ ተጨማሪ 2 ሺህ 778 አዳዲስ ማዕቀቦች ተጥለውባታል ሲል ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት አዳዲሶቹን ጨምሮ 5 ሺህ 532 ያህል ማዕቀቦች፣ በተቋማቷና በግለሰቦቿ ላይ የተጣሉባት ሩስያ፣ በ3ሺህ 616 ማዕቀቦች በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረችዋን ኢራን በመብለጥ በማዕቀብ ብዛት ቀዳሚ መሆኗን ካስቴሉም የተባለ ተቋም ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ የጠቆመው ዘገባው፤ከተጣሉባት አጠቃላይ ማዕቀቦች መካከል 21 በመቶ ያህሉ ከአሜሪካ የተጣሉባት እንደሆነም አመልክቷል፡፡
የሩስያ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ ከ1991 ወዲህ እጅግ የከፋውን ቀውስ እያስተናገደ እንደሚገኝ የዘገበው ሮይተርስ፤ ተደራራቢ ማዕቀቦችና ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ዕዳ መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ እንዳደረሷት አንድ የጥናት ተቋም ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁንም አመልክቷል፡፡

እሳት የሆነ ነዳጅ
እና የማይቀመስ ምግብ
ሰኞ ዕለት ሩስያ፣ አሜሪካ የነዳጅ ማዕቀብ ከጣለችብኝ፣ በአውሮፓ አገራት ላይ የከፋ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ ብላ ብታስጠነቅቅም፣ አሜሪካ ግን በነጋታው ማለዳ ያለማወላወል ያሰበችውን መረር ያለ የነዳጅ ማዕቀብ በሩስያ ላይ መጣሏን ከነጩ ቤተመንግስት አውጃለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ ከአሁን በኋላ አንዲት ጠብታ የሩሲያ ነዳጅ ወደ አሜሪካ አይገባም ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህም ከዕለት ወደ እለት እየጨመረ ያለውንና በበርሜል ከ140 ዶላር በላይ የደረሰውን የአለም የነዳጅ ዋጋ የበለጠ ሊያንረውና ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ከእጥፍ በላይ ወይም 300 ዶላር ሊያደርሰው እንደሚችል መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሩስያ የአሜሪካን ውሳኔ መስማቷን ተከትሎ ምላሽዋ የከፋ እንደሚሆን በዛቻ የተናገረች ሲሆን፣ አሜሪካን ጨምሮ ከምዕራባውን አገራት ለተጣሉባት መሰል ማዕቀቦች ምላሽ ለመስጠት ለአውሮፓ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ መላኳን እንደምታቋርጥና በአለማቀፉ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቃለች፡፡
ብሪታኒያ በቅርቡ የሩስያን ነዳጅ ላለመግዛት ተመሳሳይ እርምጃ እንደምትወስድ ማስታወቋ የተነገረ ሲሆን፣ በዛ ያለ ነዳጅ ከሩስያ የምትገዛው ጀርመን በአንጻሩ መሰል እርምጃ የመውሰድ ሃሳብ እንደሌላት አልሸሸገችም፡፡
የአውሮፓ አገራት 40 በመቶ የሚሆነውን ጋዝ የሚያገኙት ከሩስያ መሆኑን እና አገሪቱ በየዕለቱ ለአለም ገበያ 7 ሚሊዮን ድፍድፍ ነዳጅ እንደምታቀርብ የጠቆመው ዘገባው፣ ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአለም የነዳጅ ዋጋ በ30 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና ሩስያ ምርቷን ለማቋረጥ ከወሰነች በአለማቀፉ ገበያ ላይ የከፋ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችልም ገልጧል፡፡
ታዋቂው የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ሼል  ከአሁን በኋላ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛቱን እንደሚያቆም ከሰሞኑ ማስታወቁም ተነግሯል፡፡
ጦርነቱ በአለማቀፉ የምግብ ዋጋ ላይ እጅግ የከፋ ተጽዕኖ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ እና የዩክሬን መንግስት እስከ አመቱ መጨረሻ ምንም አይነት የገብስ፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ ጨውና ሌሎች የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ወደ ውጭ አገራት ላለመላክ መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የሰላም ጭላንጭሎች
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያወጀችውን ጦርነት ለማቆም የሚያስችሏትን ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀመጠች ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ክሬሚያ የሩስያ ግዛት ለመሆኗ፣ ዶኔትስክና ሉሃንስክ የተባሉት ምሥራቃዊ ግዛቶች ሉዓላዊ አገራት ለመሆናቸው እውቅና ትስጥ፤ እንዲሁም የኔቶ አባል ላለመሆን ቃል ትግባ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ሁለቱ አገራት በ3 ሳምንት ውስጥ ለ3 ጊዜያት በተወካዮቻው አማካይነት በቤላሩስ ተገናኝተው መላ ለመምታት ውይይት ቢያደርጉም፣ ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ ተጨባጭ ውጤት ባይገኝም፣ ከሰብዓዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተደራዳሪዎቹ ተስፋ ሰጪ ነገር ማሳየታቸው ተነግሯል፡፡
ሩሲያና ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ከትናንት በስቲያ በቱርክ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፣ የሩስያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭና የዩክሬኑ አቻቸው ዲምትሪ ኩሌየቱርኩን ያገኛኙት ፕሬዚዳንት ረሲብ ጠይብ ኤርዶጋን ሁለቱን አገራት ለማግባባት ባደረጉት ጥረት…. (የተገኘው ውጤት ይጠቀሳል)፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ከደም አፋሳሹ ጦርነት ወጥተው ለሰላም በራቸውን እንዲከፍቱ ለማደራደር እንደምትፈልግ ከሰሞኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ማስታወቋን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል ከሩሲያው ፕሬዚዳንት አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በተኩስ አቁም ዙሪያ መነጋገራቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣  የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲም ከሰሞኑ ከፑቲን ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርገው እንደነበር አስታውሷል፡፡

“እርም ሩስያ” - ከ300 በላይ ግዙፍ ኩባንያዎች
ሩስያ በዩክሬን ላይ ያደረገችውን ወረራ በመቃወም ከአገሪቱ ጋር የነበራቸውን የንግድ ግንኙነትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማቋረጥ የሚወስኑ ታላላቅ አለማቀፍ ኩባንያዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት መጨመሩን የቀጠለ ሲሆን፣ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከ300 በላይ ኩባንያዎች ከሩስያ ጋር ንግዳቸውን ማቋረጣቸውን በይፋ እንዳስታወቁ የል ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
አየር መንገዶች፣ የመኪና አምራቾች፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ የፋይናንስ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች ከሩስያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያቋረጡና እየተዘጉ  ሲሆን ኮካ ኮላ ኩባንያ ሰኞ ዕለት ከሩስያ ገበያ መውጣቱን ሲያውጅ፣ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ታዋቂው ማክዶናልድ በሩስያ የሚገኙ 850 ያህል ሬስቶራንቶቹን ላልተወሰነ ጊዜ መዝጋቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ስታርባክስ በበኩሉ 100 ያህል የቡና መደብሮቹን ዘግቷል፡፡
ከሩስያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ካቋረጡ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች መካከልም ቦይንግ፣ ኤርባስ፣ ቢፒ፣ ጄኔራል ሞተርስ፣ ፎርድ፣ አዲዳስ፣ ናይኪ፣ አፕል፣ ዴል፣ ጎግል፣ ቲክቶክ፣ ዛራ፣ ሳምሰንግ፣ ፌዴክስና ማይክሮሶፍት ይጠቀሳሉ፡፡

ስደት እና ሰብዓዊ ጉዳት
ዩክሬናውያን ሩስያ ከምታወርድባቸው የጥፋት ዶፍ ለማምለጥ ቤት ንብረቴን ሳይሉ እግራቸው በመራቸው አቅጣጫ መሰደዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በዩክሬን የተመዘገበው ስደት ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ አቻ የማይገኝለት የአውሮፓ የስደት ቀውስ ነው ተብሏል፡፡
እስካለፈው ረቡዕ ድረስ ከአገሪቱ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ2.2 ሚሊዮን ማለፉን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን፣ ፖላንድ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰደተኞችን በመቀበል ቀዳሚነቱን መያዟን፣ ሃንጋሪ 191 ሺህ፣ ስሎቫኪያ 141 ሺህ፣ ሩስያ 99 ሺህ፣ ሞልዶቫ 83 ሺህ፣ ሮማኒያ 82 ሺህ፣ ቤላሩስ 453 ስደተኞች መቀበላቸውንና ከ83 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ወደሌሎች የአውሮፓ አገራት መሰደዳቸውን አስታውቋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ 335 በላይ ንጹሃን ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውና 474 ያህሉ ሲሞቱ 861 በሚሆኑት ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።
የአለም የጤና ድርጅት በበኩሉ በዩክሬን ሆስፒታሎች፣ አምቡላንሶችና የጤና ተቋማት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ ውድመት ማስከተላቸውንና ወሳኝ የሆኑ መድሃኒቶች እጥረት እየተከሰተ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የአለም ባንክ በጦርነት ኢኮኖሚያ ክፉኛ እየደቀቀ የሚገኘውን ዩክሬን ለመደገፍ በያዘው ዕቅድ፣ ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝና ጡረታ ክፍያ የሚውል የ723 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለዩክሬን የ1.4 ቢሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑ የተነገረ ሲሆን፣ የአሜሪካ ኮንግረስ በበኩሉ ባለፈው ማክሰኞ ባሳለፈው ውሳኔ ለዩክሬን 13.6 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚና ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡

Read 11044 times