Saturday, 12 March 2022 14:20

“አፍሪካና ቤቴ” የስዕል አውደ ርዕይ በ6 ኪሎ ዩኒቨርሲቲ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሰዓሊ በረከት አንዳርጌ “አፍሪካ ናት ቤቴ” በሚል ርእስ “ጥቁርና ነጭ” የስዕል አውደ ርእይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 6 ኪሎ ግቢ ውስጥ አዘጋጅቷል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገነተ ልዑል ቤተመንግስት ራስ መኮንን አዳራሽ ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት የወሰነው ቦታውን የመረጠው የስነጥበብ አፍቃሪው ቅርሱን እየተመለከተ ስዕሎቼን እንዲጎበኝ በመፈለጌ ነው ብሏል፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ ነገ መጋቢት 4 ላይ በይፋ የሚከፈት ሲሆን እስከ መጋቢት 10 ለህዝብ እይታ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይና በአፍሪካና በባህላዊ አለበባስ ጎብኝዎች ቢመጡ ደስተኞች ነን ሲልም ተናግሯል፡፡
“አፍሪካ ናት ቤቴ” በሚል ርእስ አውደ ርዕዩን ያዘጋጀሁት “የሰው ልጆች በዘረኝነትና በጎጠኝነት አንሰን ፤ ታላቋን ኢትዮጵያ ለመበተን አንባክን” የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ለእይታ የሚቀርቡት ስዕሎች በጥቁርና ነጭ ቀለሞች ብቻ የተሰሩ ናቸው፡፡ መነሻውም ከአይናችን የተወሰዱ ሁለቱ  ቀለማት  እንደሆነም ሰዓሊው ይናገራል፡፡
‹‹አይናችን  ጥቁር ብቻ ወይንም አይናችን  ነጭ ብቻ ቢሆን ምን ይመስላል? አንዱ ከአንዱ ጋር የሚመሳጠርበት ምክንያት  ለበጎ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሄር ምድር ላይ የሰጠን ሁሉም ነገር ተከባብረን እንድንኖር ነው  የሚለውን መልዕክቴን የሚዳስስ ነው፡፡ ሁለተኛው  መልዕክቴ ደግሞ ትዝታ ትውስታ ነው፡፡ የድሮውን የሚገልፅልኝ ጥቁርና ነጭ ነው፡፡ ትናንት የነበረው የኛ ማንነት መከባበር መደማመጥ …ወዘተ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ ስራዎቼ የአፍሪካን እናቶች ስያቸዋለሁ፡፡ የህይወት ውጣ ውረዳቸውን፤ አለባበሳቸውን፤  ሲያጌጡ እንደሚያምርባቸው ስቃያቸውንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለመግለፅ ነው፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ጥቁር፤ እረፍት  ፅናት ማለት ነው፤ ነጭ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ተስፋ ነው እነዚህን ሃሳቦች ያመለክትልኛል›› በማለት ለእይታ ስለቀረቡት ስዕሎቹ ሰዓሊ በረከት አንዳርጌ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
በባህርዳር ከተማ ተውልዶ ያደገው የስዕልና የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያው በረከት አንዳርጌ፤  ከ18 በላይ አውደርዕዮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ሲሆን በጀርመን፤ በእንግሊዝና በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ስዕሎቹን ለእይታ አቅርቧል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጎንደር ፤ ባህርዳር፤መቀሌ፤ ደሴ፤ ሃዋሳ፤ በጅጅጋ ከተሞች ስዕሎቹን ያሳየ ሲሆን በአዲስ አበባ አውደርእይ ሲያቀርብ ጥቁር የአሁኑ አራተኛው ነው፡፡


Read 1003 times