Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:42

ከዋክብት ላይ አነጣጥር፤ ቢያንስ የዛፉን ጫፍ ትመታዋለህ!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ባለሟሎቻቸውን ይዘው ወደ አንድ ጥቅጥቅ ወዳለ ደን ይሄዳሉ፡፡

ከዚያም፤

“በሉ ዛሬ ዒላማና ማነጣጠር እንወዳደራለን፡፡ የምትፈልጉትን ዒላማ መርጣችሁ ምቱ” አሉ፡፡

በመጀመሪያ አንደኛው ባለሟል፤

“እኔ እዚያ ከሩቅ የሚታየውን ቅንጭብ ለመምታት እፈልጋለሁ” ብሎ አነጣጠረና ተኮሰ፡፡ የቅንጭቡን አንድ ቅርንጫፍ መታ”

ሁለተኛው ባለሟል፤

“እኔ ያንን ረዥም ባህር ዛፍ ነው የምመታው” አለና አልሞ ተኮሰ፡፡ አንዱን ትልቅ የባህርዛፍ ቅርንጫፍ ዘነጠለው፡፡

ሦስተኛው ባለሟል፤ “እኔ እዚያ መካከል የሚታየውን ዋንዛ ነው አነጣጥሬ የምጥለው! ባላው መካከል ላይ ብሰትረው ሁለት ላይ እከፍለዋለሁ!” አለ፡፡

የመጨረሻውና አራተኛው ባለሟል፤

“ንጉሥ ሆይ! እኔ አንድ መመሪያ አለኝ፡፡ ይኸውም በሀገራችን ለረዥም ጊዜ በተረትነት ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ተረቱ የሚለው “እጅህን ወደ ኩሬው ስደድ፡፡ ወይ አሣ ትይዛለህ አለበለዚያ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!” ስለዚህ እኔ እዚያ ደን መካከል የሚታየውን ቁልቋል በጥይት ነው በሳስቼ የምጥለው” አለና አነጣጥሮ ተኮሰ፡፡ ሙሉ በሙሉ ባይጥለውም እንዳለው በሳስቶታል፡፡

ንጉሡ የሁሉንም ዒላማ እና ተኩስ ካዩ በኋላ፤

“እስቲ ስለእያንዳንዳችሁ አስተያየት ልስጥ፤

ባለቅንጭቡ፤ ትንሽ ትቸኩላለህ፡፡ ቅንጭቡን አየህ እንጂ ግራና ቀኙ ላይ ምን ጉዳት እንደምታደርስ አልተገነዘብክም!”

ባለባህር ዛፉ፣ ግዙፍና ረዥም ስለሆነ አልስተውም አልክ እንጂ ምን ዓይነት የማነጣጠር ስልት እንደምትጠቀም አላሰላህም፡፡ ቢያንስ ከየት አቅጣጫ ሆኜ ልተኩስ ብለህ እንኳ አላመነታህም፡፡”

ባለዋንዛው ዓላሚ ደግሞ የዋንዛው ዋና ግንድ ባላው ነው ብለህ የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘህ ነው የተነሳኸው፡፡

ባላው በመካከል ጥይትህ ሊሄድ እንደሚችል አላስተዋልክም!” ከዚህ ቀጥሎ ባለሟሎቹ፤

“እሺ የርስዎን ዘዴ ይንገሩና?”

“እርሶ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?”

“ትምህርቱ ይሰጠን!” ሲሉ ተጫጫሁ፡፡

ንጉሡም፤

“አያችሁ ወዳጆቼ! አንድ አባባል አለ:-

ከዋክብት ላይ አነጣጥር ቢያንስ የዛፉን ጫፍ ትመታዋለሁ!” ይላል፡፡ ይህ ማለት የመጨረሻ የማይቻል የሚባለውን በመሞከር ከዚያ በታች ያለውን ትልቅ ነገር ታገኛለህ ማለት ነው!”

*   *   *

የዱሮ አስተማሪዎች Aim for an “A” at least you will get a “B” (ኤ አገኛለሁ በልና ሥራ፡፡ ቢያንስ “B” ታገኛለህ! እንደ ማለት ነው፡፡) ትላልቅ ነገሮችን ማለም፣ ትላልቅ ነገሮችን መመኘት ዛሬ ሀገራችን የምትጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ምዕራባውያን ከአቅማችሁ በላይ ተንጠራራችሁ (Over - ambitiousness) ቢሉ እንኳ ከዋክብት ላይ ማነጣጠራችንን መተው የለብንም፡፡ ኃያላኑ እንደሆን ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው፤

ሩቅ ትርጉሙ ጦር አጫሪ

አጭር ትርጉሙ ወራሪ

ድምር ትርጉሙ መሠሪ!

ነው፡፡ ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም ነው፡፡ እስከዛሬ ያልፈፀምነው ነገር ሁሉ ለምን አልተፈፀመም? ሁሉን ነገር Back to square one (ወደ ጀመርንበት) እንመልሰው ማለት አይደለም፡፡ ስለፍትሕ፣ ስለዲሞክራሲ፣ ስለ ፕሬስ ወዘተ ስንት ዘመን አወራን? ምንስ ለውጥ አመጣን? ዛሬ ወደ ቴክኖክራቲክ ትራንስፎርሜሽን በምንጓዝበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ትንሽ ቦታ ሰጥተን ሰውና ሰው፣ ድርጅትና ድርጅት፣ ገዢና ተቃዋሚ ምን ነክቶን ነው ይሄ ሁሉ መቃቃር? መነካከስ? መጃጃል? ማለት ማንን ገደለ? አንዱ ቅዱስ ሌላው እርጉም ሆኖ ሁሌ አይቀጥልም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ የእኛ ሰው ምሥጋናውም እርግማኑም ይከራል! በዚህ ሳቢያ አማካኝ መንገድ ከጠፋ ሰነበተ። መንግሥት ሆደ ሰፊነቱን ቢያሰፋው፤ ሌሎቹ መንግሥት እኛ ላይ የቃጣው በትር ነው ብሎ ከማሰብ ጋብ ብለው ህዝቡን የሚያደራጁበትን ፈለግ ቢፈልጉ፤ አሉታዊነቱን (Negativismን) ለተወሰነ ጊዜ እንኳ ጋብ አድርገን በእርግጥ ይሄ ዘመናት የዘለቀው ቅራኔ ለዛሬው “ሙሾ ማውረድ”ና ውሃ ወቀጣ የሚያበቃን ነውን? ካልሆነ ምን እናድርግ? ከሆነስ ምን እናድርግ? ዕውነት ይሄ ሁሉ ጭንቅላት ተሰባስቦ መፍትሔ አጥቶ ነው? ኮከብ ላይ ማነጣጠር ለምን አቃተን?

አዳዲሶቹን መሪዎች መልካም ጊዜ እንመኝላቸዋለን፡፡ “ወፍ የተሻለ ለማነጣጠር የምትችለው ወደ አየር ላይ ወጥታ ቁልቁል ስታይ ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ልብ ይላሉ ብለን እንገምታለን፡፡

“ዛሬ የእኛ ፈተናችን ከምንችለው በላይ መቻል፣ እንድንችል መገደዳችን…” ይለዋል ገጣሚው፡፡ በተለይ የውጪ ግንኙነታችንና ከዚህ ቀደም የእኛ የነበሩ የክብር ቦታዎች ሁሉ በጥንካሬና በፅንዓት ልንጠብቃቸው የሚገቡ ናቸው። የፓርቲና የድርጅቱ መደበኛ አካሄድ በሰላማዊ መንገድ እንደወትሮው መቀጠሉ ተገቢ የመሆኑን ያህል አዳዲስ ግንኙነቶችንና ውይይቶችንስ መስመር ለማስያዝ ምን ይገደናል? አሳታፊ ዲሞክራሲ እንዳናራምድ ምን ያግደናል? የህዝብን ፍቅር ያለማሰለስ እህ ብሎ ማዳመጥ ተገቢ አይደለምን? ዋናው ነገር ቀና ቀናውን ማሰብ ነው፡፡ ከዋክብት ላይ አነጣጥር ቢያንስ የዛፉን ጫፍ ትመታዋለህ! ነው ነገሩ፡፡

 

 

Read 4969 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:50