Monday, 14 March 2022 00:00

የኢትዮጵያ ፈተና፣” ወረራን ማውገዝ”፤ “ራሽያን አለማስቀየም”። የአውሮፓ አጣብቂኝ፣ ከኢትዮጵያ ፈተና ጋር ይመሳሰላል፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 በርካታ የአውሮፓ አገራት፣በራሽያ ወረራ ተቆጥተው “የኢኮኖሚ ማዕቀብ” እያወረዱባት ነው፡፡ ወረራው የህልውና ስጋት ሆኖባቸዋልና።
ነገር ግን  ዋናውን የራሺያ የኢኮኖሚ ምሰሶ “ንክች” አላደረጉትም። የነዳጅ ማዕቀብ መጣል፤ አውሮፓን ለጨለማና ለብርድ ይዳርጋል።
አውሮፓና አፍሪካ፣ አሜሪካና ኢትዮጵያ፣… ርቀታቸው የትና የት! አንዱ ለሌላኛው ማነጻጸሪያ፣ ምሳሌና መማሪያ፣ መቀጣጫና አርአያ ለመሆን፣ በትንሹ የሚመሳሰሉ፣ በጥቂቱ የሚቀራረቡ መሆን አለባቸው። የሰማይና የምድር ርቀት፣ የኤሊና  የነብር ልዩነት፣ለምሳሌያዊ ዘይቤም ያስቸግራሉ፡፡
እውነት ነው፡፡ “አሜሪካና አፍሪካ ምን አገናኛቸው!” ያሰኛል ርቀታቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ፣ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለስደት የሚሄድ እንጂ፣ ወዲህ የሚመጣ ሰው የለም፡፡ ከአውሮፓ ለአፍሪካ የሚመደብ እርዳታ፣ ከአሜሪካ ለኢትዮጵያ የተለገሰ እህል እንጂ፤ ወዲያ ግድም ባህር ተሻግሮ የሚጓጓዝ እርዳታ የለም፡፡
 ታዲያ፤ አንዱ አህጉር ለሌላኛው እንዴት ብሎ ምሳሌና መማሪያ፣ ማነጻጻሪያና ማስጠንቀቂያ ይሆናል? መሆን የሚችል አይመስልም፡፡
የስደተኞች ቁጥር ወይም የእርዳታ በጀት ለነአሜሪካ፣ አሳሳቢ ጉዳያቸው ነው።           ለነኢትዮጵያ ግን ጉዳያቸው አይደለም። የኢትዮጵያ የመንግስት በጀት፣ውስጥ ለሌላ አገር የሚመደብ ገንዘብ ወይም እርዳታ የለም። ጉዳያችን አይደለም። ሃሳቡ አይመጣልንም።  እውነትም፤ ኢትዮጵያና አፍሪካ ከአውሮፓና ከአሜሪካ፤ የሰማይ የምድር ያህል ነው ልዩነታቸው።
እንዲያም ሆኖ፣ “በምንም አይገናኙም” የምንላቸው አይደሉም፡፡ በተለይ በመሰረታዊ ነገሮች ላይ፤ ከምንገምተው በላይ የሚመሳሰሉ፤ በብዙ ጉዳይ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ የርቀታቸው ያህል አይለያዩም። የሃብት እና የኑሮ ልዩነታቸው የትየለሌ ቢሆንም፤ ተመሳሳነታቸው ይበልጣል። ስንዴና ዘይት፤ ነዳጅና የኮረና ክትባት፣ የሁሉም አገራት ጉዳይ ነው። የገንዘብ ህትመት ሲትረፈረፍ፣ ኢኮኖሚ ሲዳከም፣ የትም አገር፣ የዋጋ ንረት ይፈጠራል። ኑሮ ይወደዳል። ለሁሉም አገራት፣ተመሳሳይ ነው፡፡ ምናለፋችሁ! የእንጀራ የውሃ ነው ግንኙነታቸውና ቅርበታቸው። ምን ይሄ ብቻ! በሃሳብ በመንፈስ የተቆራኙ ናቸው፡፡
የራሺያና የዩክሬን ጦርነት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ማዕቀብ፣….ጉዳያችን ነው፡፡ ባህር ማዶ ተገድቦ የሚቀር ጉዳይ አይደለም። የተባበሩት መንግስታት ጉባኤና የአለም አገራት አሰላለፍ፣ የተቃውሞና የድጋፍ ድምጽ፣  ገለልተኛ ለመሆን ድምጽ ከመስጠት መቆጠብና መታቀብ፣ የነአውሮፓ ጉዳይ ናቸው። ግን….ኢትዮጵያን ይነካካሉ። በሩቅ በእግረ መንገድ ኢትዮጵያን ይነካካሉ  ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡  ከመነካካትም አልፈው፤ ያንገጫግጫሉ፤ ያስጨንቃሉ፡፡
ነገር ግን፣ከዚህም በላይ የሰፋና የጠለቀ ነው የግንኙነት ትስስራችን፡፡ በነዳጅ፣ በስንዴ፣ በምግብ ዘይት፣ በማዳበሪያ ገበያ ላይ የተፈጠረው ቀውስ፣ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ቀላል  አይደለም፡፡ ለሁሉም አገራት፣ ለኢትዮጵያና ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓና ለአፍሪካ፣ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ ንረት ከባድ መከራ ነው፡፡  ነገር ግን፣ የእንጀራ የኑሮ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የሃሳብ፣ የመርህ፣ የመንፈስ ጉዳይም ነው፡፡
እንዳያችሁት በተባበሩት መንግስታ ጉባኤ ላይ፣ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ድምፅ መስጠት ለኢትዮጵያ መንግስት፣ቀላል ጉዳይ አልሆነለትም። የራሺያና የዩክሬን ጦርነት፣ የአውሮፓ ስጋትና የአሜሪካ ቁጣ፣የባህር ማዶ ጉዳይ ነው፤ ለኛ ጉዳያችን አይደለም ማለት አይችልም- የኢትዮጵያ መንግስት።
ኢትዮጵያ፤ በአንድ በኩል፣የውጭ ወረራን የመቃወም፤ እንዲሁም የቅኝ ግዛት ጥቃቶችን በተጋድሎ የማሸነፍና የአገርን ነፃነት በአርበኝነት የማክበር ደማቅ ታሪክ  ያላት አገር ናት፡፡ ከ80 ዓመት በፊት የዘመተባት የፋሺስት ጦር  በአገራችን ላይ ያደረሰው ጥቃት እና ጥፋት ምን ያህል መራራ እንደነበረ፣ ከቶ ሊዘነጋ የሚችል ታሪክ አይደለም፡፡
የያኔዎቹ የአለም ነፃ አገራት፤ ወረራውን በፅናት ለመቃወምና ለማውገዝ ማንገራገራቸው፤ ለኢትዮጵያ፣ እጅግ የሚያንገበግብ የታሪክ ጠባሳ እንደሆነም አይካድም፡፡ የወረራና የነፃነት ጉዳይ፣ ለኢትዮጵያ የሩቅ የማዶ ጉዳይ ሳይሆን፣ እጅግ የሚቆረቁር የራስ ጉዳይ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፡፡
በመላ አፍሪካ፣ በአርአያነት የሚከበር፣ በምስጋና የሚዘከር ድንቅ ታሪክ የሰራችና ያስመዘገበች አገር ናት ኢትዮጵያ። የነፃነት ታሪክ ባለቤት ብቻ አይደለችም። የነጻነት ባለአደራ አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡
 በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ በቀይ፣በቢጫ በአረንጓዴ ቀለማት ሰንደቅ አላማቸውን ለማድመቅ የመረጡት፤ የኢትዮጵያ የነፃነት አርአያነትንና ውለታን በማክበር ነው። የአፍሪካ አንድነት መመስረቻ፣ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ለመሆን የበቃችውስ ለምን ሆነና!
በዓለም አቀፍ ደረጃም፤ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ፤ ከዚያም የዩናይትድ ኔሽንስ መስራች አባል ናት፡፡ ቅኝ ግዛትን ለመቃወም፤ ነፃነትንም ለማስከበር ቃል በመግባት  በቀዳሚነት የተሰለፈች አገር በመሆኗም፤ ከመልካም ዝና ጋር በሰፊው ትታወቃለች፡፡ ኢትዮጵያ፣ የዚህ ሁሉ ታሪክ ባለቤትና ባለ ክብር አገር ናት፤ የዚያኑ ያህልም ባለ አደራ አገር፡፡ የነጻነት አገር የነጻነት ባለአደራ ነውና።
በሌላ በኩል ደግሞ፤ የታሪኳ ያህል፣ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካና የጦር ሃይል አቅም የላትም፡፡ የሃያል አገራት ወዳጅነትንና ድጋፍን ትሻለች፡፡ ከሃያል አገራት ጋር ላለመጋጨት ብቻ ሳይሆን ላለመቃቃር ብትጠነቀቅ ተገቢ ነው።  
አሳዛኙ ነገር፣ ኢትዮጵያ በዩኤን ጉባኤዎች፣ የአሜሪካ ተቃራኒ በመሆን ከሚታወቁ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በደርግ ዘመን የተጀመረ፣ በኢህአዴግ ጊዜም፣ ብዙ ሳይሻሻል የቀጠለ የበርካታ ዓመታት ስህተትና ልማድ ነው፡፡ ቀስ በቀስ በጥንቃቄ ይህን ስህተት ለማስተካከል መጣር ያስፈልጋል፡፡
ከሃያል አገራት ጋር ወዳጅነትን ማሳመር እንጂ ጠላት ማብዛት ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡ ለቅራኔና ለጠላትነት ከሚያጋልጡ ሰበቦች፤ በተቻለ መጠን ለመራቅ መጣር ይገባታል፡፡ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ጋር ወዳጅነትን በአግባቡ ማጠናከር፣አላስፈላጊ ጠላትነትንም መግታት ተገቢ ነው፡፡ ከቻይና፣ ከራሺያ፣ ከህንድ ከጃፓን ጋርም እንዲሁ፡፡
በአጭሩ፤ ወረራን የምትቃወም የነፃነት ባለ አደራ ናት-ኢትዮጵያ፡፡ በዚያው ልክ አላስፈላጊ ቅራኔ ውስጥ ሳትገባ የሃያል አገራት ወዳጅነትን ማትረፍ ይገባታል፡፡
ለወትሮው፤ ይሄ ከባድ ወይም ፈታኝ ስራ አይደለም፡፡ ወረራን መቃወምና ወዳጅነትን ማዳበር፤ ነፃነትን መደገፍና ከጠላትነት መራቅ፣ ብዙ ጊዜ፣ አይከብድም፡፡
አንዳንዴ ግን፣ ፈተና ውስጥ ያስገባል፡፡ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና ተመልከቱ።
በአንድ በኩል፤ የነፃት ባለ አደራነቷን ለማስከበር፣ የራሺያን ወረራ የማውገዝ ሃላፊነት ሊኖርባት ነው፡፡
ነገር ግን፣ከራሺያ በኩል፣ የጠላትነት ስሜትን ሊያመጣባት፤ የወዳጅነትን ድጋፍ ሊያስቀርባት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሰላም ችግር ባይኖርባት ኖሮ፤ የራሺያን ወረራ ማውገዝ፣ ለአገራችን መንግስት ባከበደው! በጣም አሳሳቢ ባልሆነበት። አሁን ግን፤ ከባድ ነው፤ አሳሳቢ ነው፡፡
የራሺያ ወረራን የሚያወግዝ የውሳኔ ሃሳብ፤ በዓለም መንግስታት ፊት ሲቀርብ፤ የኢትዮጵያ መንግስት  ምን ይበል? ምን ያድርግ? ለራሺያ ወዳጅነት ሲል፤ ውሳኔውን መቃወም ወይም ድምፅ ከመስጠት መታቀብ አይችልም። ወረራን እንደመደገፍ ይቆጠራል ወይም ወረራን በቸልታ እንደ ማየት ይሆናል። የኢትዮጵያ ታሪክ እና የነፃነት ክብሯ ይህንን አይፈቅድም፡፡
ግን ደግሞ፤ ወረራውን በማውገዝ፣ የራሺያን የፖለቲካ ድጋፍ ማጣት ለኢትዮጵያ መንግስት ያሳስበዋል፡፡
እና ምን ተሻለ? የተባበሩት መንግስታት ስብሰባው ላይ አለመገኘት! መቼስ ምን ይደረግ! ችግር ነው።
የአውሮፓ አገራት የገጠማቸው ችግርስ፣ ከዚህ ጋር አይመሳሰልም?
ራሺያ ላይ ብዙ የኢኮኖሚ ማእቀብ አውጀዋል። ቀላል እርምጃ አይደለም። በፍጥነት እጅግ ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ ግን፣ ዋናው የማዕቀብ ኢላማ፣ የነዳጅ ንግድ ላይ ማነጣጠር ነበረበት።
ነገር ግን፣ የአውሮፓ አገራት፤ በራሺያ የነዳጅ ሽያጭ ላይ፣ ምንም ማዕቀብ አልጣሉም።
ከ30% በላይ የአውሮፓ የነዳጅ ፍጆታ፣ ከራሺያ  የሚመጣ  ነው። ይህንን የሚያቋርጥ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ፤ የራሺያ ኢኮኖሚን ሊያንኮታኩት ይችላል። ነገር ግን ሌሎቹ የአውሮፓ አገራትም፣ ከመዘዙ አያመልጡም። በኤሌክትሪክ እጥረት፤ የፋብሪካዎች ስራ ይስተጓጎላል። ትራስፖርት ይቃወሳል። የዜጎች መኖሪያ ቤት፣ ጨለማ ይውጠዋል፡፡ በብርዳማ ወራት፣ በቅዝቃዜ መኮማተር ይበረክታል።
የአውሮፓ አገራት፣ ይህን መከራ መሸከም አይችሉም። ወይም አይፈልጉም። የነዳጅ ማዕቀብ ላለመጣል የተገደዱትም በዚህ ምክንያት ነው።ችግር ነው። የአውሮፓ አገራት፤ “የአካባቢ ጥበቃ”፤ “የካርቦን ልቀት” በሚል ፈሊጥ፣ የነዳጅ ምርትንና ኢንቨስትመንትን ባያዳክሙ ኖሮ፣ የራሺያ ጥገኛ ባልሆኑ ነበር። በሌላ አነጋገር፤ የራስ ድክመት፤ ለፈተና ያጋልጣል። አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባል። -
ይሄ በኢትዮጵያም በአውሮፓም፤ እውነት ነው።

Read 8733 times