Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:31

አዲሱ ባለ 5 ***** ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በጣም ሰፊ ነው፡፡ ስፋቱ ሲታይ ቪላ ቤት እንጂ የሆቴል ክፍል አይመስልም፡፡ የክፍሉ ዕቃዎች በሙሉ ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አልጋውን ያየን እንደሆን በየሆቴሉና በየቤቱ ከምናውቃቸው አጠር ያሉ ዘመናዊ አልጋዎች የተለየ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ሽቦ አልጋ ከፍ ያለው አልጋ ፎስተር ቤድ ይባላል፡፡ ይህ አልጋ ቀደምት ልፀላውያን ቤተሰቦች የሚጠቀሙበት ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ለአጐበር መወጠሪያ የሚሆን ረዣዥም ብረቶች ተተክለውበታል፡፡  ይህ ክፍል ሁለት ሶፋና ጠረጴዛ፣ የንባብና የጽሕፈት ወንበርና ጠረጴዛ፣  ስልክና ቲቪ፣ አሉት፡፡ ከአልጋው ራስጌ በስተጀርባ ባለው ክፍል በተለየ ዲዛይን የተሠራ የልብስና የካዝና ማስቀመጫ ቁምሳጥን ቆሟል፡፡ በስተቀኙ ደግሞ ስቲምና ሳውና ባዝ አለ፡፡ ፊት ለፊት ትንሽ ራቅ ብሎ ሰፋ ባለ ወለል ላይ ውሃ የተሞላ ጃኩዚ ተጋድሟል፡፡ ውሃው ታዲያ ዝም ብሎ የተቀመጠ አይደለም፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ጡቶች ውሃ እየረጩ ሰውነትን ያሻሉ፤ ያዝናናሉ፡፡ የሳሎኑም ስፋት ልዩ ነው፡፡

አራት ምቹና ሰፊፋ ሶፋዎች፣ እንዲሁም መሃል ላይ ተሽከርካሪ የምግብም ሆነ የአበባ ማስቀመጫ ያለው ጠረጴዛ ከአራት ወንበሮች ጋር ይዟል፡፡ በአንደኛው ጥግ፣ የተለያዩ መጠጦችና ሌሎች አስፈላጊ ዕቃዎች የተደረደሩበት ትልቅ ባር አለ፡፡ ከፊት - ለፊቱ ደግሞ ቲቪ፣ ይታያል፡፡ በዚህ ክፍል እንግዳው አብረዋቸው ከመጡ ባለሥልጣናት ጋር ስብሰባ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡

ከባሩ ጀርባ ቀለል ያለ ምግብ ማብሰያና ማዘጋጃ ኪችን አለ፡፡ ከምግብ ማብሰያው ጐን ባለው በር ደግሞ እንግዳው ከፈለጉ፣ ወጣ ብለው ንፁህ አየር እየሳቡና አካባቢውን እየቃኙ ዘና የሚሉበት በረንዳ (ባልኮኒ) አለ፡፡

ይህ ክፍል (ቤትም ማለት ይቻላል) የዛሬ ሳምንት የመዲናችን እምብርት እየሆነ በመጣው ካዛንቺስ አካባቢ የተመረቀው ባለ 5 ኮከብ ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል ለፕሬዚዳንት ወይም ለአገር መሪ ማረፊያነት ያዘጋጀው ፕሬዚዴንሻል ሱት ነው፡፡ ሆቴሉ፣ ለተከበሩ እንግዶችና ባለሥልጣናት (ቪአይፒ) አገልግሎት የሚሰጥና ከፕሬዚዴንሻል ሱት ጋር በአጠቃላይ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሌሎች ተጨማሪ ማረፊያ ክፍሎችም አሉት፡፡

ይህ ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል ከ21 ዓመት በፊት በመዲናዋ ከግል ዘመናዊ ሆቴሎች የመጀመሪያው ባለ 3 ኮከብ በመሆን አገልግሎት የጀመረው ቀዳማይ ዮርዳኖስ ሆቴል አካል ነው፡፡

በምረቃው ሥነ - ሥርዓት ወቅት የሁለቱ ሆቴሎች ባለቤት አቶ ታመነ ወልደየስ ባደረጉት ንግግር፣ ባለ 5 ኮከቡ ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል ከልጅነት እስከ እውቀት በግብርናና በንግድ ሥራ ተሰማርተው፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በፈጠሩት የተለያዩ የሥራ ግንኙነቶች ያካበቱትን እውቀትና ልምድ በማቀናጀት ያደረጉት ብርቱ ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፣ “ይህ ሆቴል የኢትዮጵያን የሆቴል ኢንዱስትሪ ልማት አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያስኬድ ይሰማኛል” ብለዋል፡፡

አቶ ታመነ ወልደየስ፣ በቀድሞዋ አርሲ ጠቅላይ ግዛት በዛሬዋ የአርሲ ዞን በሮቤ ወረዳ እንደቶና ገደምሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ በ1935 ዓ.ም ከገበሬ ቤተሰብ የተወለዱ ሲሆን፣ ዕድገትና ትምህርታቸውም እዚያው ነው፡፡

በወቅቱ ትምህርት እንደዛሬው በየወረዳውና በየቀበሌው አልተስፋፋም ነበር፡፡ በትምህርት ለመግፋት የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ልማዳዊ፣…ማነቆዎች አያራምዱም ነበር፡፡

ከአንደኛ ደረጃ በላይ ለመማር፣ ከቤተሰብ ተለይቶ፣ ከአካባቢ ርቆ ሩቅና ረዥም ርቀት መሄድ ይጠይቃል፡፡ ያን እንዳያደርጉ ደግሞ ሁኔታዎች አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ ከ7ኛ ክፍል በላይ መዝለቅ አልቻሉም፡፡

እየተማሩና በትርፍ ጊዜያቸው ገበሬ ቤተሰባቸውን እያገዙና እያረሱ ያደጉት አቶ ታመነ፤ 18 ዓመት ሲሆናቸው ሁለቱ ጥንዶች ሳይተዋወቁና ሳይስማሙ፣ በወላጆቻቸው ፍላጐት በ1953 ዓ.ም ከወ/ሮ ቀለሟ አስፋው ጋር ትዳር መሥርተው አራት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ልጆች በማፍራት የልጅ ልጅ አይተዋል፡፡

ባገቡበት ዓመት ለቤተሰብ ሲያርሱ ቆይተው፣ በቀጣዩ ዓመት ከቤተሰብ የእርሻ መሬት ተቆርሶ በተሰጣቸው ቦታ፣ ለራሳቸው አረሱና ብዙ ምርት ሰበሰቡ፡፡ በወቅቱ እህል ርካሽ ስለነበር ምርታቸውን በሁለት ሺህ ብር ሸጠው የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ከፈቱ፡፡ ያ ገንዘብ ነው እንግዲህ መነሻ ካፒታላቸው፡፡

ከዚያም፣ እርሻ እየሠሩ፣ ሸቀጣሸቀጥ እየሸጡና እህል ገዝተው እየነገዱ ኑሮአቸውን ተያያዙት፡፡ በዚህ ዓይነት ለተወሰነ ዓመት ከሠሩ በኋላ፣ አንድ የጭነት መኪና ገዙና የእህል ንግዱን ያጧጡፉት ጀመር፡፡ ጥረትና ትግላቸው ሰምሮ ትርፋማ ስለሆኑ ሁለተኛ የጭነት መኪና ደገሙ፡፡

በሁለቱ መኪኖች ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ካፒታላቸውም እያደገ ስለመጣ፣ ሥራቸውን በማስፋፋት ወደ ሕዝብና የነዳጅ መጓጓዣ አገልግሎት ፊታቸውን አዞሩ፡፡ ከዚያም ከእርሻው ጋር በተጓዳኝ የሚሠራ ነገር አስበው፣ የዱቄትና የዘይት ፋብሪካ አቋቋሙ፡፡ በማያያዝም፣ 500 ከብቶች የሚይዝ ማድለቢያ ከፈቱ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ወደ እርሻው ዘርፍ ከገባሁ አይቀር በሁሉም ልሳተፍ በማለት የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻም ጀመሩ፡፡

ሁሉም ሥራዎች የተያያዙና የተሳሰሩ ናቸው፡፡ “ባሌ ስንዴ አመርታለሁ፡፡ ስንዴው በቀጥታ ፋብሪካ ይገባና ይፈጫል፡፡ በአዲስ አበባ አምስት ዳቦ ቤቶች ነበሩኝ፡፡ የስንዴው ዱቄት መጥቶ ዳቦ ቤቶቹ ይገባና ይጋገራል፡፡ ገንዘቡን የማገኘው በዳቦ ነው፡፡ የአንዱ ተረፈ ምርት ለሌላው ግብአት ነው፡፡ ዘይት ሲጨመቅ የሚገኘው ፋጐሎና ከስንዴ የሚገኘው ፉሩሽካ ለከብቶች መኖ ይሆናል፡፡ የከብቶቹ ፍግ ደግሞ ለአትክልት ማዳበሪያ ይውላል፡፡ ብርቱካን፣ ቲማቲም፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣… እያመረትን ወደ ጂቡቲ እንልክ ነበር፡፡” ብለዋል አቶ ታመነ፡፡

በእንዲህ ዓይነት እየሠሩ ቆይተው በ1981 ዓ.ም የቅይጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ወጣ፡፡ በዚያን ጊዜ ኑሯቸው አዲስ አበባ ነበር፡፡ ለሆቴል መሥሪያ ቦታ ጠየቁና በአገሪቱ የመጀመሪያው የግል ሆቴል ዮርዳኖስ ሆቴል የተሠራበት 1000 ካ.ሜ ቦታ ተሰጣቸው፡፡ የዚያን ጊዜ የግንባታ ወጪ ቀላል ነበር፡፡ የአንድ ከረጢት ሲሚንቶ ዋጋ 15 ብር ስለሆነ ዓለምአቀፍ ደረጃ ያሟላና ባለ 3 ኮከብ የሆነውን ዮርዳኖስ ሆቴል ለመሥራት 4 ሚሊዮን ያህል ብር ብቻ እንደፈጀባቸው ተናግረዋል፡፡

ከሆቴሉ በሚገኝ ገቢና ሌላም ጨማምረው ባሌ ውስጥ ሰፊ እርሻ ጀመሩ፡፡ እርሻውን፣ ፋብሪካውንና ሆቴሉን አንድ ላይ እየሠሩ ቢቆዩም፣ ባሌ ያለውን እርሻና አዋሽ መልካሳ ያሉትን ፋብሪካዎች አንድ ላይ ማስኬድ አቃታቸው፡፡ የቱን መምረጥ እንዳለባቸው ሲያስቡ፣ ወደ ሆቴሉ አደሉና የተቀሩትን ሸጡ፡፡ “ፋብሪካዎቹን ቤተሰብ (ልጆች) ይሠሩበታል ብዬ ነበር፡፡ እነሱ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ አራቱ አሜሪካ ገቡ፡፡ እኔ ደግሞ ብቻዬን ሁሉንም ማስኬድ አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ እርሻውን፣ ፋብሪካዎቹንና ዳቦ ቤቶቹንም ሸጬ በገንዘቡ ላይ ጨመርኩና ይህን ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሠራሁ” ብለዋል፡፡

አዲሱን ሆቴል ሲሠሩ እንደበፊቱ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ዋናው ችግር የግንባታ ዕቃዎች ናቸው፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ የሲሚንቶ ዋጋ 150 ብር ነበር፡፡ ነገር ግን ሦስት እጅ ጨምሮ አንድ ከረጢት ሲሚንቶ 400 ብር ገባ፡፡ የብረትም ዋጋ በጣም ተሰቀለ፡፡ የሁሉም ነገር ዋጋ በጣም ስለተወደደ፣ ከውስጥ ዕቃዎች ጋር የሆቴሉ ግንባታ 200 ሚሊዮን ያህል ብር መፍጀቱን ገልፀዋል፡፡ ለግንባታው ዋጋ መጨመር ሌላው ምክንያት ደግሞ ሆቴሉ በትክክል ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲጠብቅ የተገጠሙለት ዕቃዎች የጥራት ደረጃ ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋውም የዚያኑ ያህል ውድ መሆን ነው፡፡

“ዕቃዎቹ በሙሉ የአውሮፓን የጥራት ደረጃ ያሟሉ ናቸው፡፡ ዕቃዎቹን በተመለከተ ኮንትራቱን የወሰዱት ጀርመኖች ናቸው፡፡ መስኮትና በር፣ ሌላውንም እዚህ መጥተው ለክተው ከሄዱ በኋላ ዕቃዎቹ ተሠርተው ሲያልቁ አምጥተው የገጠሙት የጀርመን ባለሙያዎች ናቸው፡፡

በዚህ በኩል የእኛ አገር ባለሙያዎች አልገቡበትም፡፡ የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ መሆኑን ለመግለጽ፣ በሆቴሉ እሳት ቢነሳ፣ በሮቹ አንድ ሰዓት ሳይቃጠሉ መቋቋም ይችላሉ፡፡

ሆቴሉ የ5 ኮከብ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን ባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ያወጣውን አዲስ የደረጃ መስፈርት እያየንና እየጠበቅን ነው የተሠራው” በማለት አስረድተዋል፡፡

ባለ 12 ወለሉ ግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል፣ 10ኛ ፎቅ ካሉት 10 የቪአይፒ ክፍሎች በተጨማሪ 14 ሱት፣ 7 መለስተኛ ስዊት 41 ደብል፣ 32 ሲንግል 4 ለቤተሰብ አገልግሎት የሚውሉ 2 ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የተሠሩ በአጠቃላይ 110 ክፍሎች አሉት፡፡

ሆቴሉ፣ 1000 እና 700 ሰዎች እንዲሁም አነስ ያሉ ተሰብሳቢዎችን የሚያስተናግዱ አዳራሾች፣ ጅምናዝየም፣ ልዩ የጃኩዚና የመታሻ አገልግሎት፣ ስቲምና ሳውና ባዝ፣ ኢንተርኔት፣ የውበት ሳሎኖች፣ የስጦታ ዕቃ መሸጫ ሱቆች፣ መኪና ማቆሚያ፣ … ያሉትና ለ200 ዜጐች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡

አቶ ታመነ፤ በግብርና በንግድና በሆቴል ዘርፍ ብቻ አይደለም ጀግንነታቸው፡፡ በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራም ከፍተኛ ተሳትፎና እውቅና ያላቸው ባለሀብት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ዮሴፍን ቤተክርስቲያን በግል ገንዘባቸው አሳድሰው ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት ገዝተው አስረክበዋል፡፡

በተወለዱበት አካባቢም ቤተክርስቲያናት አስገንብተዋል፡፡ እንደቶ በተባለው ስፍራ ከአንድ ሚሊዮን ብር በበለጠ ወጪ የቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ገደምሳ በተባለው ስፍራ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር ውጪ በማድረግ የመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በማሠራት መንፈሳዊ ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡

በማኅበራዊ ልማት ዘርፍም፣ ሕዝብ በማስተባበር፣ ማኅበር በማቋቋምና ከግል ኪሳቸው እስከ 100ሺህ ብር በማውጣት፣ በመንግሥት መ/ቤቶችና በሕዝቡ መካከል ትብብር እንዲፈጠርና እንዲጠናከር በማድረግ ክረምት ከበጋ አገልግሎት የሚሰጥ 62 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድና ድልድዮች በማሠራት ለሕዝቡ የቁርጥ ቀን አለኝታነታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ ታመነ አዲስ አበባ የገቡበት ታሪክም አላቸው፡፡ የደርግ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ መኖሪያቸው አዳማ (ናዝሬት) ነበር፡፡

አንድ ምሽት እኩለ ሌሊት ላይ ደህንነቶች በራቸውን አስከፍተው “እጅ ወደ ላይ” በማለት ወደ ጣቢያ ወሰዷቸው፡፡ ወደ ጣቢያው የተወሰዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እየተጠሩ ገብተው ተገርፈው ይወጣሉ፡፡

ተራቸው ደርሶ ተጠርተው ሲገቡ፣ “መሳሪያ ደብቀሃል፤ ለምን አምጥተህ አታስረክብም?”  አሏቸው፡፡

እሳቸውም፤ “በእርግጥ መሳሪያ ነበረኝ፤ ማዘጋጃ ቤት አስረክቤአለሁ፤ ያስረከብኩበት ደረሰኝም አለኝ” በማለት መለሱ፡፡ “ከምትገረፍና ከምትሰቃይ ብታመጣ አይሻልህም ወይ?” አሉ ደህንነቶቹ፡፡ እሳቸውም ኮስተር ብለው “ያለኝን አስረክቤአለሁ፤ ምንም መሳሪያ የለኝም፡፡ ስለዚህ ብትገርፉኝ ቀርቶ በእሳት ብታቃጥሉኝም ምንም አታገኙም” አሏቸው - በእርግጠኝነት፡፡

እርስ በርስ ተወያዩና “ይህ ሰው ወደ ቤቱ ይመለስ” አሉ፡፡ ይኼኔ ከመሃከላቸው አንዱ፤ “አሁን መጥቶ እንዴት ይመለሳል? ባይሆን እንኳ አድሮ ይሂድ” አለ፡፡ “ብታድር ቅር ይልሃል ወይ?” አሏቸው፡፡ እሳቸውም “ቅር አይለኝም” ብለው ሳይገረፉ አድረው በማግስቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከእሳቸው በኋላ እየተጠሩ የገቡ አምስት ያህል ሰዎችም ሳይገረፉ መመለሳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚያ የተነሳ “እየተሳቀቅሁ አልኖርም” በማለት ጓዛቸውን ጠቅልለው አዲስ አበባ ገቡ፡፡

 

 

Read 5925 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:41