Tuesday, 08 March 2022 00:00

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፤ “ለምክክር አይመቹም”።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  1.”በአገራዊ ምክክር” እና በሕገመንግስት ጉዳዮች ላይ፣ የጠ/ሚ አቢይ ንግግር፤
የአገራችንን ሕመሞች ለማከም፣ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት፣ “አገራዊ ምክክር” ያስፈልጋል። ጥሩ እድል ስለሆነ፣ ልናባክነው አይገባም ብለዋል።
በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ፣ “አገራዊ መግባባትን” መፍጠር ይቻላል። ካልሆነም፣ እልባት ማበጀት አለብን። ይሄኛው እና ያኛው ባንዲራ በሚል መገዳዳል እስከ መቼ?
ከምክክር በኋላ፣ በሕገ መንግስት ጉዳዮች ላይ፣ “ውሳኔ ሕዝብ” ይካሄዳል። ሁሉም ለውሳኔው ተገዢ ይሆናል ብለዋል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
2. “በጦርነት እና በድርድር” ዙሪያ፣ የጠ/ሚ ዐቢይ ንግግር
በጦርነት፣ ሕይወት ይረግፋል፤ ኑሮ ይወድማል። አማራጭ ሲጠፋና የግድ ሲሆን እንጂ፤ ጦርነት ክፉ ነው። ጦርነትን የሚገታ፣ ሰላምን የሚያሰፍን መላ ያስፈልጋል።
እስከዛሬ፣ በወጉ የተካሄደ ድርድር የለም። ነገር ግን ድርድር አይኖርም፤ ወይም አያስፈልግም ማለት እንዳልሆነ ለፓርላማው ገልጸዋል።
ድርድር፣ ጥቅሞች አሉት። ጦርነት የግድ ሆኖብን የተዋጋነው፤ ለአገር ህልውና ነው። ድርድርም፤ ለአገር ጥቅም ነው ብለዋል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ምክክርና ድርድር፤ በስክነትና በቅንነት ከተከናወኑ፣ ፍሬያማ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን፣በቀላሉ የሚሳኩ አይደሉም፡፡ ፈተና ይበዛባቸዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አለ፡፡ የሃይኖማት ፖለቲካም ከባድ አደጋ ነው፡፡ ምን ይሄ ብቻ!
የሰላምና የህግ፤ የኢኮኖሚና የኑሮ ችግር፣…ለምክክር ትልቅ ፈተና ናቸው፡፡ ንትርክን ይጋብዛሉ፡፡ ለምን?
ሕግና ስርዓት ሲደፈርስ፤ ሰላም ሲጓደል፣ ሕይወት ይጠፋል፤ ኑሮ ይናጋል። ሰዎች በመንደራቸው ወይም በጉዞ ላይ የጥቃት ሰላባ ይሆናሉ። ከኑሮ ይፈናቀላሉ። ንብረት ይወድማል፤ ይቃጠላል። ጅምር ስራ መና ይቀራል፤ ይስተጓጎላል።
ኢኮኖሚ ይቀዘቅዛል፤ ሲብስም ይቃወሳል። ኢንቨስትመንት ይዳከማል፤ ይከስራል። የስራ እድል ይቀንሳል፤ ይመናመናል። ስራ አጥነትና ድህነት ይበረታል። ተስፋ ይደበዝዛል፤ ይጨልማል።
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ እንደ ነባር ችግር የሚለማመዱት፣ እንደ ነባር ድህነት “ልቻለው ብለው” የሚሸከሙት እዳ አይደለም። በየቀኑ በየሳምንቱ እየከበደ እየበረታ፤ ለሸክምም ለመልመድም የማይቻል ይሆናል።
ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ፣ የህዝብ ቁጥር በ10 ሚሊዮን ጨምሯል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ፣ በየአመቱ፣ ስንት ሚሊዮን ወጣቶች ለስራ አጥነት ለስራፈትነት እንደተዳረጉ አስቡት።
ኑሮ ሲናወጥ፣ መነጫነጭና መበሻሸቅ፤ ማፌዝና ማላገጥ ይበረክታል፡፡
አለመረጋጋት ሲደጋገምና ሰላምን ሲያሳጣ፤ ህይወትና ንብረት ዘወትር ሲጠፋ፣ ኢኮኖሚ ሲቃወስና ኑሮ ሲናጋ፣ ችግር ያለፋታ ሲደራረብና ድህነት ሲከፋ፣… ይሄ ሁሉ፣ ከመጠን ያለፈ ትልቅ መከራ ቢሆንም፣… ያነሰ ይመስል፤ ተጨማሪ ችግሮችን ጎትቶ ያመጣል።
ታዝባችሁ ከሆነ፣ የአገር ኢኮኖሚ እየተቃወሰ ኑሮን ሲያመሳቅል፣ የብዙ ሰዎች መንፈስ ይደፈርሳል። ለወትሮ፣ ቁጥብና ጨዋ የነበሩ ሰዎች፤ እንዲሁ በሰበብ አስባቡ የመነጫነጭ አመል ይጀምራቸዋል። ያዩት ነገር ሁሉ ላይ እንዲሁ የማላገጥ ጨፍጋጋ ክፉ ስሜት ያድርባቸዋል።
የኑሮ ችግራቸው የሚመነጨው ከሌላ ነገር ነው፣ የሚነጫነጩት ግን ሌላ ነገር ላይ። ያጋጠማቸው ሰው ላይ ብስጭታቸውን ይጭናሉ። በአፀፋው የራሱን ብስጭት ያራግፍባቸዋል።
በቋፍ የነበረ የምሬት ስሜት፤ ሰበብ ሲያገኝ፤ ይገነፍላል። የማይተዋወቁ፣ የማይደራረሱ ሰዎች፣ በረባ ባልረባ ምክንያት፣ በሰበብ አስባቡ፤ ፀብ ፀብ ይላቸዋል።
አልያም፤ ሁሉንም ነገር ማቅለል፣ ማጣጣል ማላገጥ፤… ሁሉም ነገር ላይ መቀለድ፣ ያዘወትራሉ። ሊቋቋሙት የማይችሉት ስሜት ይሆንባቸዋል። ጉዳት የማያመጣ፣ ተራ ሳቅና ቀልድ ይመስላል። መነሻው ግን፣ የምሬት የንጭንጭ መንፈስ ነው።
 የማላገጥ አመል፣ ከንጭንጭ ጋር ልዩነቱ ምንድነው?  የማላገጥ አመል የጀመራቸው ሰዎች የኑሮ ምሬት ቢያንገበግባቸውም፣ ከንጭንጭ ከንዝንዝ ይልቅ፣ ወደ ቀልድ ወደ ተረብ ያመዝናሉ። በራሳቸው ምሬት ብስጭትጭት ከማለት ይልቅ፤ ማላገጥና እግረ መንገዳቸውንም ሌሎች ሰዎችን ማበሳጨትና ማብሸቅ ላይ ይበረታሉ። ያፌዛሉ፤ ይሳለቃሉ።
በየቀኑ የምናየው የመነጫነጭና የማላገጥ ስሜት፣ ከኢኮኖሚ ቀውስና ከኑሮ ችግር ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሊመስል ይችላል። ግን የተዛመዱ ናቸው። ከኑሮ ቅሬታ የመነጨ ምሬትና ፌዝ፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ እየተንተከተከ፣ በየአቅጣጫው እየተፈናጠረና እየገነፈለ፣ በአጠገቡ ያጋጠመውን ሁሉ ይላከፋል፤ ይተነኩሳል።
የኑሮ ችግርና የዋጋ ንረት፣ ለፀብ “ለነቆራ” የሚያቧድኑ ሰበቦች ይሆናሉ።
የኢኮኖሚ ችግር፣ ድርቅና ረሃብ፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ የፖለቲካ ቀውሶችን ይወልዳሉ ይባላል። ባይወልዱ እንኳ፣ ነባሩን የፖለቲካ ቀውስ ያባብሳሉ።
በኑሮ የተማረረ ሰው፣
በዚህም በዚያም፣ በትንሹም በትልቁም እየተበሳጨ፤ ነገር ነገር ይለዋል፤ ፀብ ፀብ ይሸተዋል።
በዚህም በዚያም ላይ እያላገጠ እየተሳለቀ፣ብሽሽቅን የሚያደምቁ የሳቅ አጃቢዎችን ይሰበስባል። ሌሎች ሰዎችን ያበሽቃል። አፀፋ ይመጣበታል። እሱም በተራው፣ የአፀፋ አጸፋ ያስከትላል።
በእርግጥ፣ ማላገጫው ይለያያል። የንጭንጭ ማራገፊያው፣ ብዙ አይነት ነው።
የሰው ልጆች ሁሉ ላይ  የሚነጫነጭና የሚያላግጥ አለ። በአጠቃላይ፣ ዓላማችንን ከጫፍ ጫፍ ያማርራል። ድንበር አያግደውም። የአንዳንድ ሰው ንጭንጭ ግን ወሰን አይሻገርም።  አገር ላይ የሚቀልድ ኢትዮጵያ ላይ ፣ የሚበሳጭ  ሰው፣ ጥቂት አይደለም።
ሃብታሞች፣ ነጋዴዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ባለስልጣናት፣… .. ጎላ ብለው የታዩት ሰዎች ላይ እርግማን የሚያወርድ ወይም የሚሳለቅም ሞልቷል።
እንደተለመደው፤ መንግስት ላይ የሚጮኹም ብዙ ናቸው። ገሚሶቹ በአቤቱታ ነው። ገሚሶቹ በወቀሳ። ከፊሎቹ በእሮሮ። ከፊሎቹ ግን፣ ሰበብ አገኘን ብለው ለማላገጥና ለማንቋሸሽ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ናቸው። መንግስት ለማሳጣት ይሯሯጣሉ፡፡ ደሞዝና ትርፍ የማያመጣ የሌት ተቀን መደበኛ ስራ ያደርጉታል የማፌዝና የማንቋሸሽ ስራ።
በዚያው ልክ፤ እንደተለመደው፤ የመንግስት ማስተባበሪያና ማብራሪያ፣ ሁሌም አለ። በቀውስ  ጊዜ ደግሞ፤ይበረክታል። በከፊል፤ መረጃዎችንና ትንታኔዎችን ለማቅረብ ነው። አንዳንድ ወቀሳዎችን ለማስተባበል፤ ሌሎች ወቀሳዎችን ደግሞ፣ ሰምቶ እንደተቀበለና ጥፋቱን አምኖ እንደሚያስተካክል ቃል ለመግባት ሊሆን ይችላል-የመንግስት ማስተባበያና ማብራሪያ።
ሁሉንም መረጃና ትችት እንደጥቃት የሚቆጥር፣ የመልስ ምት እንዲለጋ የተሾመ የሚመስለው ባለስልጣንም ይኖራል። ይሄ ብቻ አይደለም፡፡
ያለደሞዝ ያለሹሙት፣ የመንግስት ጠበቃ፣ ተሟጋችና ቲፎዞ ሆኖ የሚሰለፍ፣መንግስትን ለማወደስና 24 ሰዓት የብሽሽቅ አገልግሎት ለመስጠት ራሱን የሚመለመልም  ሰው፣ ብዙ ነው።
ትክክልን ማጽደቅ፣ ስህተትን መጠቆም የሚችል ሚዛናዊ ደጋፊ ወይም ሚዛናዊ ተቃዋሚ ቢበረክት መልካም ነበር። በእርግጥም፤ ይህንን ሚዛን ይዘው የሚጀመሩ ሰዎች ይኖራሉ። ብዙዎች ግን፣ አይዘልቁበትም፡፡ በጥንቃቄ ማሰብና ማመዛዘን፤ ከባድ ሸክም ይሆንባቸዋል።

 ሚዛኑን ጥለው፤ የተቀናቃኝ ጎራ ጭፍን ቲፎዞነትን ብቻ ይዘው ይቀራሉ። ሳይታወቃቸው፤ ጭፍን ተቃዋሚ ወይም ጭፍን ደጋፊ፤ “ተንኳሽ” ወይም “የመልስ ምት ተኳሽ” ይሆናሉ። የደመነፍስ ቅኝታቸው ይሆናል።
ሁሉንም ነገር የሚያዩት በብሽሽቅ ቅኝት ነው። አንዳች የአፀፋ ምት ካልተወራወሩ፣ ውስጣቸው እረፍት አያገኝም። አያስችላቸውም።
እናም፣የተረጋጋ ምክክር፣ የጨዋ ንግግር፣ ይጠፋል። ድንገት ቢፈጠር እንኳ፣ አፍታ ሳይቆይ ይደፈርሳል። የሆነ ሰው፣ “የዋጋ ንረት” ብሎ ቅሬታ ቢያሰማ፤ አንዱ ቲፎዞ፣ መንግስት ላይ ለማላገጥና ገዢውን ፓርቲ ለማሳጣት ይሽቀዳደማል። ሌላኛው ቲፎዞ ደግሞ፤ የመንግስት ተቆርቋሪ፣ የፓርቲ ተጠሪ አድርጎ ራሱን እየሾመ፤ አፀፋውን ይመልሳል፡፡
ይሄ የብሽሽቅ ሱስ፤ አዲስ ክስተት አይደለም። ነባር ነው። ኢኮኖሚ ሲቃወስና ኑሮ ሲመሰቃቀል ግን፣… የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሲባባስ ግን፣ የብሽሽቅ ሱስ፣ አጀቡ ይበዛል፤ ስካሩ ይጦዛል።
ከፊሉ እየተበሰጫጨ ከፊሉ እያላገጠና እየተሳለቀ፤ አዲስ አጨብጫቢ፣ አዲስ አራጋቢ ይሆናል። ከወዲያና ወዲህ ሆና፣… “በለው! በለው! በለው!” ይላል።
በኑሮ ቅሬታ ምክንያት የደፈረሰና የተወሳሰበ እንዲህ አይነት የማላገጥ ወይም የብሽሽቅ ክፉ መንፈስ፣ ለ”ምክክር” አይመችም። ትልቅ እንቅፋትና ፈተና ይሆናል እንጂ። ምን ይሄ ብቻ!
የጦርነት ፈተናና ችግርም አለ። በአንድ በኩል፣ ሕይወትን ይቀጥፋል፣ ኑሮን ያጎሳቁላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በቀላሉ የማይላቀቁት ክፉ ፀበኛ መንፈስን ያባብሳል - ከሰላም መንፈስ ያራርቃል። በጦርነት ድባብ ውስጥ፣ ስለ ጦርነት አጥፊነትና አውዳሚነት መናገር እንኳ፣ እጅግ ከባድ ፈተና ይሆናል።
የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ስራ አጥነት፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትም፣ ልክ እንደ ክፉ የጦርነት መንፈስ፣ ለምክክር አይመችም።Read 7465 times