Saturday, 05 March 2022 12:14

ማጠቃለል ተገቢ ባይሆንም፣ የ’ሸኔ’ ነገር ግን.....

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ (ከቤተሳይዳ ሜሪላንድ አሜሪካ)
Rate this item
(2 votes)

     በፖለቲካው አስተምህሮ ውስጥ ጭልጥ ያለ አንድ ጥቅል አገላለጥን መናገር ወይም መግፋት እጅግም አይበረታታም፡፡ በተለይ እዚህ እምኖርበት አሜሪካ አንድ ክስተትን ‘እንዲህ ነው’ ብሎ ማጠቃለልና መናገር ክፉ እንደሆነ አስተውያለሁ፡፡ ‘ፖለቲካ ቆሻሻ ነው’ የሚል አገላለጥ አይነት ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን አካሄድ በአንድ ጠቅልሎ ‘እንዲህ ነው’ ብለው የመበየን አገላለጾችን እዚህ ላይ አስቧቸው፡፡ ጥቅል መደምደሚያዎች ማድረግ ስሜታዊነትን ለማጫር ይመቻሉ። ለፖለቲካ የ’ሴራ ተረተኞች’ (ፋብሪካዎች) መንገድ ይከፍታሉ። ትልልቁ የሀገርና የሕዝብ ጉዳይም ይጠለፍና ከችግር ይወድቃል፡፡ ለኑሮው ደፋ ቀና የሚለው ሕዝብ ደግሞ መላ ጊዜውን በፖለቲካ አውድ ውስጥ የሚያሳልፍ ባለመሆኑ ሲመቸውና ሲሳካለት ነው ስለ ሀገሩ ፖለቲካ ሁኔታ የሚያደምጠው። ተባለ ተነገረ የተባለውን የሚያብራሩና በዘመነኛው አጠራር ‘ተንታኞቹ’ ሲናገሩ ደግሞ ‘እንዲህ የተባለው እንዲያ ለማለት ነው’ ብለው ከሚያወነባብዱት እጅ ላይም በቀላል መውደቅ ይመጣል፡፡ በዚህ የተነሳ አንድ ጭልጥ ያለ ጥቅል አገላለጥን ህብረተሰብ ይዞ ለመንጎድ ያለው ዕድል ይሰፋል፡፡ ሀገራዊ ጉዳዮች ግን ውስብስብ ናቸው፡፡ በተለያዩ ክስተቶች ውስጥ ያላቸው ንክኪና መወሳሰብ በቅጡ ካልመረመሩት ብዙ ግር የሚያሰኙ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ የፖለቲካው አድማስ ንቁ አይኖችን ይሻል፡፡ ሲመችና ሲሳካ በሰሙት ተርጉመው፣ አበቃ ብለው የሚደመድሙት አይደለም፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ እጅግ አስከፊ ግጭት ውስጥ ገብታ አሁንም ለመውጣት እየሞከረች ነው፡፡ ጦርነቱ ይለቅም አይለቅም የሚያውቅ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ «ሟች ብቻ ነው የጦርነትን መጨረሻ ያየ» ያለው የፕላቶን አገላለጥ ያስታውሰኛል፡፡ በእኛ ሀገር ጦርነት (የእርስ በእርስ ግጭት) ሙሉ ለሙሉ ከስሞ፣ ፍሙ አመድ ሆኖ የታየበትን ወቅት መቁጠር በእርግጥ ያስቸግራል፡፡ በአንዱ ወገን ‘እንደማሸነፍ ያለ አንፃራዊ መደላደል ከፈጠሩ በሁዋላ - የሚከሰቱ አነስተኛ ቁርቋሶዎችን “ይህችን መሰል ግጭት ብዙም የምታስፈራ አይደለችም” ሲባል ግን እንሰማለን፡፡ እና በዝምታ ጊዜው ያልፍና ሌላ ጊዜ - ሌላ አጋጣሚ ላይ ከተዳፈነበት ፍሙ ተርከክ ብሎ እሳቱ ለመለብለብ ይደርሳል፡፡ ጦርነት (ግጭት) የማለቁ ምልክት ህመሙ ይመስላል፡፡ በህመም የተዘጋ የሚመስል ጦርነት ወይም ግጭት በውስጡ በቀልና ምሬትን ይዞ ከሆነ ክፉ አደጋ አለው፡፡ እና ትልቁ ጥበብ - መጨረሻውን ማወቅ ነው። መጨረሻው ሲባል ደግሞ ‘ማሸነፍ’ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ትላልቅ የሀገር ጉዳዮችን ለመረዳትና ለመተንተን አንድ ገጽ ብቻ አይደለም ያላቸው። በአንድ አድባሬ ተረት (ሚቶሎጂ) ላይ ዝሆኑን ዘጠኝ ዓይነ ስውራን የተለያዩ አካሉን ነካክተው - ሁሉም እንደነኩት አካል የሚያወጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ኩምቢውን የነካ ግንድ ነው ቢል - መቀመጫውን የነካ ተራራ ቢያደርገው ዝሆኑን እንደማይገልጸው ሁሉ የሀገርን ጉዳይ በነጠላ ገንጥለው ሊመለከቱት ሲሹ ብዙ ነገር ያመልጣል፡፡ የተሟላም ስዕል አይሰጥም፡፡ ይህ ማለት ግን የተለያዩ ክስተቶች አይስተዋሉም - እነርሱን መግለጽና መተንተን አይገባም ማለት ግን አይደለም። የክስተቶቹን ምንነት መግለጥና ለማወቅ መትጋት የችግሩን ዋነኛ ምንጭ ለመረዳት የሚረዳ አስረጂም እንደሆነ ታሳቢ ያደርጋል። እንደ ጥቅል መግለጫ አድርጎ ከመውሰድ ግን መቆጠብ ይገባል፡፡
የሸኔ ነገር.....
አንዳንድ ‹ትንቢት› መሰል ንግግር ወይም አገላለጽ ባሉት መንገድ እውን ባይሆን ባላሰቡት ብቅ ይላል፡፡ የግራ ዘመም ፍልስፍና  አባቱ ካርል ማርክስ፣ ስለ ስልተ ምርት መጻኢ ዕድል በተነተነበት መድበል -  ብሎ ብሎ መንግሥት ይሉት ነገር ይከስማል ወይም ይጠፋል የሚለው ‘ትንቢት’ን እያስታወስኩ ነበር።  የሁዋላ ሁዋላ የማርክስ ተከታይ ነን ያሉና ሲምሉ ሲገዘቱ የነበሩ በ’ወዝአደሩ ስም’ መጥተው አጥሩንና በሩን አጥብቀው ጭራሽ መንግሥት እንዳይጠፋ አድርገው የመሄዳቸውን እውነታ ሳስበው ደግሞ ይገርመኛል፡፡ ታዲያ ፈላስማው ባለው የታሪክ ሰንሰለት እውን ባይሆንም እንኳን በአፍሪቃ አብዛኛው ክፍለ ቦታ ውስጥ መንግሥት በሌላ ምክንያት እየጠፋ - ያለመንግሥት የመኖር ነገር እየተዘወተረ መምጣቱን ሕዝቡም እየለመደው መምጣቱን ታዝቤያለሁ፡፡ አንዳንዱ የአፍሪቃ መንግሥት ማዕከሉንና ጥቂት መሬቶችን እያስተዳደረ እንጂ ሁሉን መቆጣጠር ያለመቻሉ ሁኔታ ብዙ ያነጋግራል፡፡ ደግሞም ለይስሙላ መዋቅሩና አለሁ ብሎ የመፎከር አዚሙ ቢታይም - ‘እየገዙ’ ወይም ‘እያስተዳደሩ’ ናቸው ብሎ ለማለት እየከበደ የመጣበትን ፈተና እረዳለሁ፡፡ አማጽያን ይነሳሉ - ሽፍቶች ይቀሰቀሳሉ - በዚያ ይተኩሳሉ - በዚህ ያሴራሉ፤ መንግሥታቱ ደግሞ ደህንነታቸውን ሲያሰላስሉ ገዢና ተገዢ ተለያይቶ ይቀራል። ሽፍቶቹ አንዱን ክፍለ ቦታ - በከፊልም በብጫቂም ለነገሩ አንዳንዴ የማርክስ መንግሥት አልባ ስርዓት የሚመችበት አጋጣሚ የአፍሪቃ ሀገራቱ ውስጥ የሚታይበት ሁኔታ አጓጊ ይመስላል፡፡ ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና በዘመናችን አይተናል፡፡ ‘መንግሥት አለ እንዴ?’ የሚያሰኘው ሁኔታም - መንግሥት እንደ መንግሥት ይንቀሳቀሳል፣ ቁመናው አለ ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር የመቻልንም ነገር ያስቡታል፡፡
እኛ ግን መንግሥት አለን እንላለን። እንደኔ እምነት አዎን ወጣት መንግሥት አለን። ሀገሪቱ ደግሞ ውስብስብ ናት፡፡ ብቻ አንዳንዴ የምንሰማውና የሚገጥመውን ሲፈትሹት - ኸረ የመንግሥት ያለህም ሲባል - ‹አለ እንዴ?› ብለን እንዳንጠይቅ መስጋት አለብን። ዜጎች ‹መንግሥት አለ እንዴ?› የሚያሰኝ ግፍ ሲፈጸምባቸው - በሰላም ከሚኖሩበት በግፍ ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ጩኸታቸው ሳይሰማ ሲቀር አደጋ አለው። አይሁዳውያን በላያቸው ላይ የበደል ናዳ ሲወርድባቸው ‘ሰውስ እግዚአብሔርስ የታለ?’ ነበር ያሉት፡፡ ያ እንዳይሆን ነው ማሰብና መትጋት ያለብን፡፡
ዘመናችን ክፉ ሆነና አረፍ ስንል የሚንጠን - ተራመድን ሲባል የሚያደናቅፈን ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ደግሞ በእኛ ሀገር ገና ያልቋጨነው - በይደር ያቆየነው ብዙ ችግር አለ፡፡ ጊዜውን እየጠበቀ ሲፈነዳ ሩጫ እንይዛለን፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ሲሰለጥንብን - አጥር እየተበጀ እዛና እዚህ ስንባል «የትም አይደርሱም» የተባለበት ትርክት፣ የት ላይ እንደጣለን አሁን እያየን ነው፡፡ በወቅቱ ጆሮ ሰጥቶ የሚሰማ፣ መፍትሄ የሚሻ በማጣት ብዙ አረንቋ ውስጥ ገብተን ወጥተናል፡፡ ከቶም በ›ዘመቻ› መልክ ‹ሆ› ብለን ዘላቂ ዕቅድ ሳንይዝ ጀምረን የተውነው ብዙ አለን፡፡ የትም አይደርሱም - እየተባለ እንደዘበት የታዩ ክስተቶች ሀገርን ሲያተራምሱ አይተናል፡፡  ዛሬ ዛሬ በ’ሸኔ’ ዙሪያ ደረሰ የሚባለው ግድያና መፈናቀል ብዙ የማይገቡኝን ነገሮች አምጥቷል፡፡
በዲያስጶራ ጥሪ ወደ ሀገር ቤት የተጓዘ ወዳጄ፣  ወዲህ አሜሪካ ተመልሶ ያወጋኝን አብነት አደርገዋለሁ፡፡ ኹነቱ የገጠመው ክፍለ ሀገር ወጣ ብሎ ጎብኝቶ ሲመለስ ነው፡፡ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ በግል ተሽከርካሪ ከሌሎች ወዳጆቹ ጋር እየተመለሱ ሳለ ቀደም ብሎ በሸኔ ሽፍቶች በአባይ በርሃ አደጋ ሊገጥማቸው የመሆኑን ሁኔታ ሰምተው ይሸበራሉ፡፡ እና አይዟችሁ ተብለው ተሽከርካሪያቸውን ይዘው እየመጡ ናቸው፡፡
- “ያ ጉዟችን እጅግ አስፈሪ ጉዞ ነበር; አለና ጀመረ፡፡ "ይገርምሃል መቼና እንዴት አደጋ እንደሚደርስ አታውቅምና ሁሌ ሰግተህና ሰውነትህን ጨርሰህ ነው የምትጓዘው። በተለይ ወደ ፍልቅልቅ የምትባል ቦታ ወዲህ ስትመጣ ሸኔዎች ይመጣሉ በሚል ስጋት ትናጣለህ፡፡ ሸኔዎቹ አሉ የሚባልበት አካባቢ እየታወቀ ... ካሁን አሁን ይመጣሉ ብሎ እየሰጉ የምትኖረው ኑሮ ልክ ኩኩሉ የመጫወት ያህል መሆኑን ስታስበው ግራ ይገባሃል... ያ የአባይ በርሃ በቃ አደጋው አይጣል ነው...
- ‘እንዴት? የምን አደጋ?’ እጠይቃለሁ ነገሩን በማራዘም አይነት፡፡
- ‘በቃ...ሸኔ ነው የሚሏቸው ገደሉ - አገቱ መኪና አፈነዱ እየሰማህ ነው የምትሄደው፡፡’
- ‘ድሮ ድሮ አባይን ሲሻገሩ ‘እግዚኦ’ እያሉ እንደሚማማሉት አያቶቻችን አይነት መሆኑ ነው?’
- ‘ይገርምሃል .... ሸኔ የሚሏቸው ሽፍቶች ይሁኑ አንዳንድ የመንግሥት ታጣቂዎች ሰው ግራ እንደተጋባ ነው የምነግርህ፣ ደግሞም አይፈረድበትም፡፡’
- ‘እንዴት?’
- ‘ምን ሆነ መሰለህ.... በእግረ መንገዳችን አንድ የሀገሬው ፖሊስ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ትራንስፖርት የሚጠብቅ ሲጠይቀን ግባ ብለነው ጎሃ ጽዮን ላይ አሳፍረነው ነበር... እና እግረ መንገዳችንን ስለ ሸኔ ጠየቅነው ..አገላለጹ ይበልጥ አስፈራን...’
- ‘ምን አላችሁ?’
-‘ሸኔዎቹ (በምንሄድበት የአባይ በርሃ በአንዳንድ ስፍራዎች  በቁጥቋጦና በጥሻዎቹ  እያመለከተን) በዚህ ውስጥ መገኘት ብቻ ሳይሆን  ማሰልጠኛ ሳይቀር አላቸው....’ ብሎን አረፈ....ተደናግጠን ‘እና እናንተም ያሉበትን ታውቃላችሁ?’ ብለን ብንጠይቀው ... ‘በደንብ እንጂ’ ብሎ አስረገጠልን! ‘እና ታዲያ ምነው ዝም አላችኋቸው?’ ብንለው .. ‘ሂዱና አባራችሁ ተመለሱ’ የሚል ኦፕሬሽን ይሰጠንና  እሺ ብለን እንሄዳለን፡፡ ጥቂት እንደጀመርን አንዳንድ አለቆቻችን ‘በሉ አሁን በቃ ተመለሱ ይሉናል...’.አለን፡፡
-‘ለምንድን ነው ተልዕኮውን ሳይጨርሱ እንዲመለሱ የሚደረገው?’ ብላችሁ አትጠይቁትም ነበር፤ ምናልባት ምክንያት ካላቸው’ ብዬ ጣልቃ ገባሁ፡፡
- ‘ጠየቅነውና .. ‘እኛ ፖሊስ ነንና መታዘዝ ብቻ ነው’ ብሎን በቅርታ ዝም አለብን፡፡
- ‘እና ታዲያ አስተኝተው እንዲመጡ ነዋ ኦፕሬሽኑ’ - እላለሁ ነገሩን ለማዋዛት፡፡
- ‘ያሳዝናል እባክህ ... በበነጋታው መግለጫ በይፋ ስትሰማም  ... ‘ ሸኔ ሊሰነዝር የነበረውን ጥቃት አክሽፈንና ተገቢውን ቅጣት ሰጥተን ወደ ነበረበት መልሰነዋል’  የሚል እኮ ነው .... የነበሩበት ማለት እንግዲህ ጫካቸውና ዋሻቸው አይነካም ማለት ነዋ....› ብሎ ፈገግ አለ፡፡ ግን አነጋገሩ የመመረር ቃና ነበረው፡፡
ይህ አስረጂ ብዙ ነገር ይናገራል፡፡ ያስነብባልም፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ግን አጠቃሎ መመልከት አይገባም፡፡ እንደ አንድ ህማም አድርጎ መውሰድ እንጂ፡፡
እዛች  ሀገር ውስጥ ግጭትም ሆነ ቁርቋሶው በዚህና በዚያ መፍትሄ አግኝቶ ወይም ተቋጭቶ ተደመደመ ያለመባሉ እንቆቅልሽ ከሚገርማቸው ሰዎች መካከል እገኛለሁ፡፡ ሕዝብ ችግሬ ያለውንና እንደጎን ውጋት የያዘውን መንግሥቴ የሚለው ለማቃለልና እፎይ ለማሰኘት ካልቻለ፣ ጩኸቱ ካልተሰማለት መንግሥትም አለ እንዴ? ማለት ይጀምራል። ብዙውን ጊዜ ባለስልጣናቱ ችግሩን ቢያንስ መረዳታቸውን - ለብሶቱ ማቃለያ ህዝቡን ያሳተፈ መፍትሄ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ያለመግለጽ፣ እንደውም ያዩ የተሰማቸው የማይመስሉበት አንዳንድ አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ ባለስልጣናት የሚሠሩት ስህተት አደጋ ያለው ይመስለኛል፡፡ ፖል ኬሄሎ የተሰኘ ምጡቅ ደራሲ “ስህተትን ከደገምከው ስህተት መሆን ያበቃለታል፡፡ ይልቁንም ውሳኔህ ይሆናል” ይላል፡፡ በዚህ በእኛ ትውልድ ከትላንት እስከዛሬ በምናየው የታሪክ ፈሰስ ውስጥ በተመሳሳይ መንገድ በመሄድ የተቀየረ ውጤት የምንጠብቅበት አዚም ይታያል። ወይም ሁሌ ከትላንቱ ያለመማርና ጉሽ በሆነው ሕሳቤ መሸከርከር ይቃጣናል፡፡
በዚህ በሸኔ ጉዳይ በግልጽ ሰለባ የሆኑት የሀገሬው ሰዎች የሚናገሩትና በአደባባይ ሲመሰክሩ የሚሰማው - ‹ቀን ቀን ፖሊስ - ጀንበር ስታዘቀዝቅ ሸኔዎች› ናቸው ያሉትን ብሶት መላልሼ አደምጠዋለሁ፡፡ የዚህ የወሮበላ ቡድን ሰለባ የሆነ ሕብረተሰብ ከኖረበት የሚነቅሉትን - በጅምላ መቃብር የሚከቱትን - በቋንቋው መርጠው የሚገድሉትን ለመለየት የሚችል እንደሆነ አይጠረጠርም፡፡ እኒያ አዛውንት እንባ ባቀረረ ዓይናቸው፣ ተስፋ ባጣ አንደበታቸው ግፍና በደል የሚያደርስባቸውን ‹ቀን ቀን ፖሊስ ማታ ማታ ሸኔ› ብለው ሲናገሩ ቆም ብሎ ማድመጥ ይገባል፡፡ ታሪክም ሕዝብም ይህን ቃል - ይህን ምስክርነት የሚሰማበትና የሚፈርድበት ጊዜ ቢኖርም፣ ዛሬ ጩኸቱን ማድመጥ ግን ተገቢ ነው፡፡ ቀን ቀን ፖሊስ ሲሉት የተከበረውን የሕዝብ ፖሊስ በጅምላ ፈርጀውት ሳይሆን በስርዓቱ ውስጥ ተወሽቀው የጎሳ ቋንቋ ከለላቸውን ታጥቀው በገዛ የሀገሪቱ ዜጎች ላይ የዘመቱ ሸኔዎች መኖራቸውን አመልካች ነው - ከቶም። በብዙ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው ሌባው አብሮ ሌባ እያለ ከንጹሃኑ ጋር መሮጡና መደባለቁ የእኛ የዛሬውን የታሪክ ጉዟችንን ያወሳስበዋል። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ንግግራቸው ‘የፖለቲካውን ሥራና ወታደራዊ ሥራውን አስታርቆ መሄድ ያስፈልጋል’ ያሉትን ሀሳብ እጋራለሁ፡፡ ይሁንና ሥራውም በተለይ የመንግሥት እንደሆነ አምናለሁ፡፡
‹›ሸኔን› ወደመጡበት መለስናቸው›፣ ‹ሸኔዎችን ለመደምሰስ ቆርጠው ተነሱ› የሚሉና የመሳሰሉት ዜናዎች በኢትዮጵያ ዜና አውታሮች ውስጥ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ በድርጊት መፍትሄ መፈለጉ ላይ ነው።
ሞቱና መፈናቀሉ እየቀጠለ ሲሄድ ግጭቱ እየሰፋና ሀገራዊው አደጋ እየከፋ ይመጣልና ቆም ብሎ ማሰቡ ይገባል። በነገሬ ላይ ቀን ቀን ‹ፖሊስ ማታ ማታ ሸኔ’ የተባለውን በዓይነ ቁራኛ ነው የማየው።
ይህን በመሰሉ ችግሮች ውስጥ ከውጭ የሚመጣው ሳይሆን ውስጥ ውስጡን የሚሄደው ነው አደገኛው፡፡

Read 1117 times