Saturday, 05 March 2022 12:13

የተዘነጋው ሌላኛው የኢትዮጵያውያን የድል በዓል (የካቲት 26፣ 40ኛ ዓመት)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       የኢትዮ-ሶማሊ ጦርነት ተብሎ የሚታወቀው የኦጋዴን ጦርነት፣ ከሶማሌ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ጋር ሀምሌ 1969 ዓ.ም ተጀምሮ የካቲት 1970 ዓ.ም የተጠናቀቀ ጦርነት ነው፡፡ መጀመሪያ በሶቪየት ህብረት ቀጥሎም በ ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ኢትዮጵያን የወረረው የሰይድ ባሬ (ዚያድባሬ) ጦር  ‹‹የእናት ሀገር ጥሪ›› እያለ ከመላው የኢትዮጵያ ምድር በተሰባበሰበ ጀግናው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ድባቅ ተመታ፡፡ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሰራዊት በመልሶ ማጥቃት ካራማራ ተራራ ላይ ከባድ ውጊያ አካሄደ፡፡ ከዚያም ጅግጅጋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ከአራት ቀናት በኋላ ሁኔታው ያስፈራው ሰይድ ባሬ፣ የሶማሊያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ምድር ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ኢትዮጵያውያንም በድል ተመለሱ፡፡ በጦርነቱ ኩባ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ከ 16,000 በላይ የኩባ ወታደሮችም የታሪኩ ተካፋይ ናቸው፡፡ ታላቋ ሶማሊያም ፈራረሰች፡፡ የዚያድባሬ የመጨረሻ ቃልም ‹‹ Nothing is permanent on this world’’  በሚል ተቋጨ፡፡
በኢትዮጵያ ወገን ሆነው ጦርነቱን ሲመሩ ከነበሩት አዋጊዎችና የጦር ሜዳ ጀግኖች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር እንተዋወቅ
(አፈንዲ ሙተቂ እንደፃፈው)
1. ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም፡
ሊቀመንበር መንግሥቱ የኢትዮጵያ ጦር የበላይ አዛዥ ነበሩ፡፡ የጦርነቱን የዘመቻ እቅድ በመንደፍና ጦር በመምራት ሰራዊቱን ባያዋጉትም ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን አመራር በመስጠት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በየሀገሩ እየዞሩ መሳሪያ በመለመንና የኢትዮጵያን ህዝብ በመቀስቀስ ረገድ የአንበሳ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በተጨማሪም ሶስት መቶ ሺህ ሚሊሻ ጦር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰለጠነበትን የታጠቅ ጦር ሰፈር የመሰረቱት እርሳቸው ናቸው፡፡
ሊቀመንበር መንግሥቱ ተኩስ በሚደረግበት ትርዒት ውስጥ አልገቡም። ነገር ግን የሶማሊያ ጦር የሀረርን ከተማ ከቦ ሲያስጨንቃት በነበረበት ጊዜ በከተማዋ መሀል ላይ ባለው የሀረር የጦር አካዳሚ የጦር መሪዎቻቸውንና የሶቪየት ጓዶችን በመሰብሰብ ስለ ውጊያው ይነጋገሩ ነበር። ከዚህ እንደምንረዳው መንጌ ጭካኔ ቢኖርባቸውም ድፍረትም ነበራቸው። በጣም ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ጅጅጋን ከተቆጣጠረ በኋላ በማግስቱ ሊቀመንበር መንግሥቱ ከተማዋን መጎብኘታቸው ነው፡፡
2. ፊልድ ማርሻል ቫሰሊ ፔትሮቭ፡
ሶቪየት ህብረት ከነበሯት እውቅ የውጊያ ስትራቴጂስቶች አንዱ ነው፡፡ የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ የሶቪየት ምድር ጦር ምክትል አዛዥ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰነዶች ጄኔራል ፔትሮቭ ሶማሊያን ከኦጋዴን ያስወጣው ዘመቻ እቅድ ነዳፊ እና የሶስቱ ሀገራት ጥምር ጦር (ኢትዮጵያ፣ ኩባ እና ደቡብ የመን) ዋና አዛዥ ነበር ይላሉ። በደርግ በኩል ሆነው ታሪኩን የጻፉ ወገኖች ግን ማርሻል ፔትሮቭ አማካሪ ነው እንጂ የጥምር ጦሩ አዛዥ አልነበረም ነው የሚሉት፡፡
የማርሻል ፔትሮቭ (ኢትዮጵያ ሲመጣ ጄኔራል ነበር) ወታደራዊ ችሎታ ብዙ ተደንቆለታል፡፡ ነገር ግን ከኢትዮጵያ አዛዦች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችሎታ አልነበረውም፡፡ በተለይም ከአየር ሀይሉ አዛዥ ከኮሎኔል ፋንታ በላይ ጋር በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የውዝግቡ መነሻ የኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላኖች ሶማሊያ ድንበር ውስጥ ገብተው ጥቃት መፈጸማቸው ነው፡፡ ማርሻል ፔትሮቭ አውሮፕላኖቹ ሶማሊያ መግባታቸውን ይቃወማል፡፡ ኮሎኔል ፋንታ ደግሞ “መሬታችንን የያዘብንን ጠላት እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄደን የመውጋት መብት አለን” ባይ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ማርሻል ፔትሮቭ ክሱን ለሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማሪያም አሰማ፡፡ መንጌም “ፋንታ ያደረገው ትክክል ነው” በማለት ደገፉት፡፡ በዚህም አኩርፎአቸው ነበር ይባላል፡፡
ማርሻል ፔትሮቭ ባለፈው የካቲት ወር በ97 ዓመቱ አርፏል፡፡
3. ሌፍትናንት ጄኔራል አርላንዶ ኦቾዋ፡
ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኩባ ጦር አዛዥ ነው፡፡ ይህም ጄኔራል ግሩም የሆነ ወታደራዊ ችሎታ የነበረው ሲሆን ከኢትዮጵያ የጦር መኮንኖችም ጋር ተግባብቶ በመስራት ተደናቂነትን አትርፏል፡፡ እርሱ ያዘመተው ጦር ለፈጸመው ጀብዱ መታሰቢያ ይሆነው ዘንድ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ ኒሻን ተሸልሟል፡፡
ጄኔራል ኦቾዋ ወደ አንጎላ የዘመተውንም የኩባ ጦር ይመራ ነበር፡፡ ነገር ግን በአንጎላ ምድር በለስ ሊቀናው አልቻለም፡፡ በደቡብ አንጎላ በተደረገ አንድ ውጊያ ብዙ የኩባ ወታደሮች ሲሞቱ “ለውድቀቱ ተጠያቂው አንተ ነህ” የሚል ወቀሳ ከፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ቀርቦበታል፡፡ በዚሁ ጦስ ከስልጣኑ ወርዶ በቁም እስር ላይ እያለ “በአደንዛዥ እጽና በህገ-ወጥ የአልማዝ ንግድ ውስጥ እጁን ነክሯል” የሚል ክስ ቀረበበት፡፡ ክሱ በዝግ ችሎት ከታየ በኋላም የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ሀምሌ 7 ቀን 1981 በጥይት ተደብድቦ ተገደለ፡፡
4. ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ (የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና)፡
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ካፈራቸው ምርጥ አብራሪዎች አንዱ ነው፡፡ ስድስት የሶማሊያ ሚግ ጄቶችን በአየር ላይ በማጋየት ጀብዱ የፈጸመ ተዋጊም ነው፡፡ ሆኖም በመጨረሻው ዙር ባደረገው በረራ በሶማሊያ ድንበር ውስጥ ጥቃት አድርሶ ሲመለስ አውሮፕላኑ በመመታቱ ሊማረክ በቅቷል፡፡
ሶማሊዎቹ ጄኔራል ለገሠን ለአስራ አንድ ዓመታት ካሰሩት በኋላ በ1981 ለቀውታል። ጄኔራሉ በእስር ቤት ሳለ ከፍተኛ ስቃይ ስለደረሰበት ከእስር ተፈትቶ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ጊዜ ሰውነቱ አልቆ ከሞት የተነሳ አጽም ይመስል ነበር፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ጄኔራል ለገሠን በከፍተኛ ወታደራዊ ስነ-ስርዓት ከተቀበሉት በኋላ የሀገሪቱ የመጨረሻ ደረጃ ኒሻን የሆነውን “የህብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ” ሸልመውታል፡፡ ከጄኔራል ለገሰ ሌላ ይህንን ሜዳይ የተሸለሙት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው (አንደኛው ሊቀመንበር መንግሥቱ ራሳቸው ሲሆኑ ሁለተኛው ብ/ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያም ናቸው)፡፡
5. ሌ/ኮ/ ፋንታ በላይ
የኢትዮጵያ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሲሆን አየር ሀይሉ በሶማሊያ ባለጋራው ላይ የበላይነት እንዲቀዳጅ ያስቻለውን ወታደራዊ ስልት የነደፈ እውቅ መኮንን ነው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ አየር ሀይል በሶማሊያ ድንበር ውስጥ እየገባ የሶማሊያ ሰራዊት የእደላና የስምሪት መስመሮችን እንዲደበድብ የሚለውን ሃሳብ ያመነጨው እርሱ ራሱ ነው፡፡ በዚህም ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል፡፡
ሌ/ኮ/ ፋንታ በላይ በአየር ሀይል አዛዥነቱ እስከ 1979 አገልግሏል፡፡ በማዕረጉም እስከ ሜጀር ጄኔራል ደረጃ ደርሷል፡፡ በ1981 ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ዋነኛ ጠንሳሽ እርሱ እንደነበረም ይነገራል፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ ከሁለት ወር በኋላ ግን እስከ ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ በሆነ ሁኔታ ተገድሏል፡፡
• ሌሎች የኢትዮጵያ የጦር አዛዦች
6. ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረኪዳን፡ የኢትዮጵያ ታንከኛ ጦርን በማደራጀት ለውጊያው ያዘጋጀ መኮንን ነው፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬ ከጊዜ በኋላ በሌፍትናንት ጄኔራል ማዕረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ሆኗል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሀገር ጥለው ከሄዱ በኋላም ለስድስት ቀናት የኢትዮጵያ መሪ ነበር፡፡
ሌ/ኮ ሙላቱ ነጋሽ (በኋላ ሜጀር ጄኔራል)፡ ጄኔራል ሙላቱ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት በአዲስ መልክ የተቋቋመው የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ነበር፡፡
8. ሌ/ኮ/ ተካልኝ ንጉሤ፡ በድሬዳዋ እና በጀልዴሳ ግንባር የተሰለፈለውን የኢትዮጵያ ጦር የመራ መኮንን ነው፡፡
9. ኮሎኔል ተስፋዬ ሀብተማሪያም (በኋላ ብ/ጄኔራል)፤ በጭናክሰን ግንባር አስደናቂ ጥቃት በመፈጸም ለታላቁ የካራማራ ድል መንገድ የከፈተው የኢትዮጵያ የፓራኮማንዶ ሀይል አዛዥ አዛዥ ነበረ፡፡
10. ሌ/ኮ ደምሴ ቡልቶ (በኋላ ሜጀር ጄኔራል)፤ በደቡብ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ሰራዊት አዛዥ ነበር፡፡ ኮሎኔል ደምሴ በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ በነበረው ቆይታ እስከ ሜጀር ጄኔራል ማዕረግ ድረስ ለማደግ በቅቷል፡፡ በዚህ ማዕረግ የምስራቅና የሰሜን እዞች (አንደኛው አብዮታዊ ሰራዊትና ሁለተኛ አብዮታዊ ሰራዊት) ዋና አዛዥ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ግንቦት 1981 በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጦስ ተገድሏል፡፡
‹‹ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውድም›› የሚለው የሙሃመድ ዜማም የተቸረው ለዚህ ጀግና ወታደር ነበር፡፡
ክብርና ሞገስ ለሰማዕታቱ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ዘላለም ጥላሁን


Read 1344 times