Saturday, 05 March 2022 12:10

የራሺያ ጦርነት፣ ለኢትዮጵያም መከራ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ነዳጅ፣ ስንዴ፣ የምግብ ዘይት ዋጋ፣ በዓለም ገበያ እየተተኮሰ ነው።
የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፣ በበርሜል ወደ 30 ዶላር ወርዶ ነበር - አምና። የዛሬ ወር፣ 80 ዶላር ሲሻገር፣ “ጉድ” ተብሏል። ባለፈው ሳምንት የራሺያ ወረራ ሲለኮስ፤ ሚሳየል ብቻ አይደለም የተተኮሰው። የነዳጅ ዋጋም እንጂ።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን ነው፣ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ፣ ከ100 ዶላር በላይ የተሰቀለው። በሳምንት ውስጥ ብሶበት፤ ሐሙስ እለት፤ ከ110 እስከ 119 ዶላር ገደማ ሆኖ ውሏል - ገበያው።    
ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር፣ ከሦስት እጥፍ በላይ ነው። ወደ አራት እጥፍ የተጠጋ። የዋጋ ግልቢያው፣ ለጥቂት ነዳጅ ሻጭ አገራት፣ ድንገተኛ ብስራት ሊሆን ይችላል። ለሌላው ዓለም ግን፤ ትልቅ “ዱብዳ” ነው። ኢኮኖሚንና ኑሮን ያንገጫግጫል።
እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት ደግሞ፤ ከባድ ማዕበል ይሆንባቸዋል።
ከቡና ከሰሊጥ፣ ከአበባ እና ከወርቅ ሽያጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ዶላር፣ በአብዛኛው ለነዳጅ ግዢ ነው የሚውለው። ግማሽ ያህሉ ማለት ነው።
ዘንድሮ ግን፣… የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ፣ በጦርነትም ዋጋው እየተተኮሰ፣ የአገሪቱን ዶላር ማራቆቱ አይቀርም። የዶላር እጦት፣ የነዳጅ እጥረትና የዋጋ ንረት፤ መርዛማ ናቸው። ኢኮኖሚን በሙሉ ከላይ እስከ ታች፤ ኑሮን ከጓዳ እስከ መርካቶ፣… ሁሉንም የሚያዳርሱ የሚያሳምሙ ጠንቆች ናቸው።
ውጭ ውጭውን ከመለብለብና ከማቃጠል አልፈው፤ አጥንት ድረስ ዘልቀው፤ መላ ሰውነትን፣ ኑሮን፣ ኢኮኖሚንና አገርን፣ ሁለመናን ያሳምማሉ። የሁሉም ነገር ዋጋ ይንራል። የሁሉም ስራዎች ወጪ ይጨምራል። ሁሉም ሰው ስራ ይዳከማል። የትራንስፖርት ችግርና ወጪ ብቻ እንኳ፤ መዘዙ ብዙ ነው። ግን፤ ነዳጅ ሲወደድ፣ የእርሻ ማዳበሪያም፣ ከዚያው ጋር አብሮ ዋጋው ይንራል።
በነዳጅ ሳቢያ፣ የአገሪቱ የዶላር ኪስ ሲመናመን፣ የመድሃኒት  መግዣ ጭምር ይቸግራል። የግንባታ ቁሳቁስ ይወደዳል። ጨርሶ የመግዛት አቅምም ይጠፋል - በዶላር እጦት። የብረታ ብረት እጥረት ለብቻው፣ የግንባታ ስራዎችን ያዳክማል። ለፋብሪካ የሚያስፈልግ የመለዋወጫ ቁሳቁስ፣ በፍጥነትና በበቂ መጠን ማሟላትስ እንዴት ይቻላል?
ከትራንስፖርት እስከ እርሻ፣ ከግንባታ እስከ ፋብሪካ፣… የትኛውም የኢኮኖሚ አቅም ወይም የኑሮ መተዳደሪያ ከመዘዙ አያመልጥም። በነዳጅ ችግርና በዶላር እጥረት ሳቢያ የሚፈጠር ቀውስ፣ የትኛውንም አይምርም።
በጣም የሚያስጨንቅ ችግር ነው። ብዙ አገራትን የሚያቃውስ፣ ለትርምስ ጭምር የሚዳርግ፣ ከባድ ፈተና ነው - ኢኮኖሚን የሚያብረከርክ፤ ለምህላ የሚያንበረክክ።
ችግሩ ይሄ ብቻ ቢሆን!
የስንዴ እና የዘይት ዋጋ፤ የማይቀመስ ሆኗል!
ዓምናና ካቻምና፣ ከዚያም በፊት፣ የስንዴ ዋጋ፣ በኩንታል ከ20 እስከ 25 ዶላር ቢደርስ እንኳ፣ ከዚያ አይሻገርም ነበር። እንዲያውም፤ ከነማጓጓዣ ወጪው ጋር፤ በ22 ዶላር ሂሳብ፣ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ ማስመጣት ይቻል ነበር።
ምናለፋችሁ፤ ላለፉት አምስት ዓመታት፣ የስንዴ የዓለም ገበያ፣ እጅግ የተረጋጋ ነበር። ዋጋውም በአማካይ በኩንታል 20 ዶላር ገደማ።
ዘንድሮ ግን፤ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ወደ 30 ዶላር አሻቅቧል- ከነዳጅ ጎን ለጎን።
አሁን ደግሞ፣ ከራሽያ ወረራ ጋር፣ በሳምንት ውስጥ፣ ከ40 ዶላር አልፏል- የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ።
የራሺያ ጦርነት፣ ቶሎ ካላበቃ ወይም በአጭር ካልተገታ፣ አካባቢው ካልተረጋጋ፣ የስንዴ ዋጋ ይብስበት እንደሆነ እንጂ፣ ይረግባል ተብሎ አይጠበቅም። ለምን?
ራሺያ እና ዩክሬን፣ ዋና የስንዴ አምራችና  ሻጭ አገራት ናቸው። በዓለማቀፍ የስንዴ ገበያ ውስጥ፣ የሁለቱ አገራት ድርሻ፣ 30% ነው። ይህ ሁሉ ሲስተጓጎል ወይም ሲደነቃቀፍ፤… ከባድ የእህል እጥረት ይከሰታል። የበቆሎ የዓለም ገበያ ውስጥም፣ የራሺያና የዩክሬን ድርሻ 25% ገደማ ነው።  
የምግብ ዘይት ምርት ላይም፣ ትልቅ ቦታ የያዙ አገራት ናቸው። አብዛኛው የሱፍ ዘይት የሚመረተው በዩክሬን ነው።
ታዲያ፣  እንደ ስንዴ የዘይት ዋጋ መናሩ ይገርማል? ጦርነቱ በአጭር ካልተቋጨ፣ ብዙ ፈተና ይጠብቀናል።
በእርግጥ፣ የነዳጅ እና የስንዴ ዋጋ፣ በትንሹም ቢሆን፣ ረጋ የሚሉበት እድል ይኖራል። በራሺያ የነዳጅ ምርትና ሽያጭ ላይ ቀጥተኛ ማዕቀብ አልተጣለም። የዩክሬን የስዴ ምርት፣ በአብዛኛው ወደ ዓለም  ገበያ የሚጓጓዘው፤ ከሐምሌ እስከ ታህሳስ ድረስ ባሉ ወራት ስለሆነ፤ ዘንድሮ ለትንሽ አምልጧል።
በሌላ አነጋገር፣ የራሺያ ወረራ፣ በስንዴ ዋጋ ላይ የሚያስከትለው ቀውስ፣ ለጊዜው  ላይባባስ ይችላል። ጦርነቱና ትርምሱ ከተራዘመ፣ እልቂትና ውድመቱ ከተስፋፋ ግን፤ ለኢትዮጵያም መከራ ነው።


Read 1335 times