Saturday, 29 September 2012 09:31

የራሔል እንባ

Written by  አገኘሁ አሰግድ
Rate this item
(3 votes)

ደስ ብሏታል! የህይወት ትርጉሟን ብትጠየቅ “እሱ ነው” ብላ የምትመልስበት ልጇ ሁለት ዓመት፤ ሞላው ዛሬ፡፡ ለልደቱ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከከተማ ለመግዛት ልትወጣ ነው፡፡ ልጇ ተኝቷል፡፡ ይዛው ብትሔድ ገዝታ ከምትመለሰው ዕቃ ጋር ስለማይመቻት ለጐረቤቷ ለሀዊ አደራ ብላት ሄደች፡፡

***

ከልጇ አባት፣ ከኤርሚያስ ምርር ያለ ፍቅር ነበራት፡፡ “አያገባኝ ይሆን?” በሚል ጥርጣሬ ሳትነግረው አረገዘች፡፡

ማርገዟ ግድ ብሎት እንደሁ እንጃ በአንዱ ቀን እንደሚያገባት ነገራት፡፡ በዛው እለት ከሰዓት ኤርሚ በመኪና ተገጨ፡፡ ሬሳውን አመጡላት፡፡ ታላቅ ደስታ እና ሃዘን ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጐበኝዋት፡፡ … ዛሬ የፍቅሯ ቅሪት የሆነው የሁለት ዓመት ልጇ ብቻ ነው  ያላት - አቤት ስትወደውው!!

***

የምትፈልገውን ገዛዝታ ወደ ቤቷ እያመራች፣ ሰፈሯ መዳረሻ ላይ ጩኸት የሰማች መሰላት፡፡ እርምጃዋን አፈጠነች፡፡ በትክክል ጩኸት ሰምታለች፡፡ የበለጠ ፈጠን ፈጠን አለች፡፡ ቤቷን ከርቀት ተመለከተችው “የፈጣሪ ያለህ!” የሚል ቃል ከአንደበቷ ወጣ፡፡ ትልቅ ቁሳዊ ሃብቷ የሆነው ቤቷ፣ በእሳት ይንበለበላል፡፡ እንደ ደመራ ጧ ብሎ እየነደደ ነው፡፡ ባላት ሃይል እየተጣደፈች ወደ ቤቷ ገሰገሰች፡፡

… ጐረቤቶቿ እሳቱን ለማጥፋት ይተጋሉ፡፡ አካባቢው የጩኸት ሰፈራ ቦታ መስሏል፡፡ ዙሪያዋን ማተረች፡፡ አንድ ነገር ከአዕምሮዋ አቃጨለ - ልጇስ!!

“ልጄስ!?” ስትል ጮኸች፡፡ የሰሟት ተደናገጡ፡፡ ይሄ ለነሱ አዲስ ነው፡፡ ልጇ፣ ልጇ… ያ ሲኮላተፍ የሚወዱት ህፃን … ያ የሁሉ ዓይን የሚሳሳለት ልጅ የት ነው ያለው? ከእሳቱ መሃል ሊሆን ይችላል? ምነው ታዲያ እስካሁን ድምፁን አልሰሙም? … ባለ በሌለ አቅማቸው እሳቱ ላይ ተረባረቡ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ፣ እሳቱ ጠፋ፡፡ ጥቂት ሰዎች ወደ ውስጥ ዘለቁ፣ ዙሪያቸው በጭስ ተሸፍኖ ለማየት ያዳግታል፡፡

እናት ከውጭ ሆና ትጣራለች፣ ትጮሃለች፡፡ ልጇን አደራ ያለቻትን ሀዊን ትፈልጋት ገባች፡፡ ሀዊ ምልክቷም የለ!

ወደ ውስጥ የዘለቁት ሰዎች ከጭሱ እየታገሉ ይፈልጋሉ፤ ህፃን ሙሴን፡፡ “እዚህ …እዚ…ጋር…” ሲል ተጣራ አንድ ወጣት፣ ወደ ኋላ እያፈገፈገ፡፡ ሁሉም ወደ እሱ መጡ፡፡ የገጠማቸው፣ የሚሰቀጥጥ ትዕይንት ነበር፡፡

***

“ኧረ እባካችሁ ልጄን…!?” ራሔል በዙሪያዋ ያለውን ሁሉ ትጠይቃለች፡፡ ወደ ቤቱ ገብተው የነበሩት ሰዎች አንድ ነገር በጨርቅ ተጠቅልሎ እንደያዙ እጅብ ብለው ወጡ፡፡ ራሔል ወደ ሰዎቹ ቀረበች፡፡ አተነፋፈሷ ልክ አይደለም፡፡ ሰዎች በጨርቅ የሸፈኑትን ለመግለፅ የፈሩ ይመስላል፡፡ አስፈሪ ድባብ …፡፡ በመሃል አንድ አባት በሚንቀጠቀጥ እጃቸው ጨርቁን ገለጡት፡፡ በእሳት የጠቆረ፣ ተለብልቦ የከሰለ የሰው ገላ፡፡ ከላዩ ጭስ የሚተን የህፃን ሙሴ ሰውነት፡፡ ከብቸኝነት ባህር ያሻገራት ሙሴ! የራሄልን ህይወት የሚመራው ሙሴ!

ራሔል ጮኸች፣ ጮኸች…! እንደ እብድ አደረጋት፡፡

ታላቅ ሀይል የተሞላች ዓይነት ለያዥ አስቸገረች፡፡ እልጇ በድን ላይ ትወድቃለች፣ ትዘላለች፣ ትፈርጣለች … እንደምን ይይዟታል፡፡

ሁኔታዋን እያዩ፣ ድንቡሽቡሽ ልጇን እያሰቡ የሚያለቅሱ ብዙ ነበሩ፡፡  የሙሴ በድን ግን ተጋድሟል፣ ከቃጠሎ የተረፈ ለአፍንጫ የሚከረክር ሽታ ብቻ ሆኖ፡፡

ራሔል … አቅሟ ዝልፍልፍ አለ … እግሯ በዝለት መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ መጮህዋን ግን አላቋረጠችም፡፡

ደግፈው ከአንድ ዛፍ ሥር አስቀመጧት፡፡ በተቆራረጠ ድምፅ “ኤርሚዬ …ኤርሚ … መሄድህ ሳያንስ … ልጃችንንም ጠራኸው? … እሺ … እኔስ ማን አለኝ? ከእንግዲህ ማን አለኝ?” መልስ የምትጠብቅ ዓይነት አፍታ ትቆይና የማይሰማ ነገር ታወራለች፡፡

የሚንከራተቱ ዓይኖቿ ዙሪያውን ከተበታተኑት ዕቃዎች መሃል አንድ ስዕል ላይ አረፉ፡፡ የገብርኤል ስዕል ነበር፡፡ ሶስቱን ደቂቅ ከእሳት ሲያወጣ፡፡ የሷ ልጅ ከሶስቱ ህፃናት መካከል የለም! በእሳት የጠለሸውን ስዕል እያየች ገብርኤልን ታዘበችው፡፡

ምነው የእሷን ልጅ ከእሳት አላወጣውም? ልጇ ምን አጥፍቶ ነበር? ለጣኦት የተሰዋ ምግብ መቼ ቀመሰ? ገብርኤልን በውስጧ ስትጠላው ይሰማታል፡፡ … በመሃል አንድ ነገር ጭንቅላትዋን መታው፡፡ ወደ ከተማ ከመሄዷ በፊት አብርታ የወጣችው ሻማ ትዝ አላት፡፡ ሳታጠፋው ነበር የሄደችው፡፡ አዎ ያ ሻማ ነው ልጇን ያቃጠለው፡፡ ወደ ገብርኤል ምስል አይኗን ስትመልስ፣ ገብርኤል የሚስቅባት መሰላት - የለበጣ ሳቅ፡፡ ብሽቀት ተሰማት፡፡ ብሽቀቷ ሳቅን ወለደ፣ ግራ የሚያጋባ ሳቅ፡፡ በዙሪያዋ ያሉት ግራ ተጋቡ፡፡ ትስቃለች፣ ታቆምና እንደገና ከት ብላ ትስቃለች - ጨለማ ውስጥ መወርወር የፈጠረው ሳቅ፡፡ … ፍንጥር ብላ ተነሳች … ተነስታ መሮጥ ጀመረች፡፡ ተከትለው ሊይዝዋት አልቻሉም፡፡ … ሮጠች … ሮጠች … ለጊዜው ወዳልታወቀ ዓለም፡፡

***

ህዳር 12 ጠዋት፡፡ እዚህም እዛም የተለኮሰ ቆሻሻ፡፡

በመንገዱ መሃል የምትጮህ፣ የምትለፈልፍ፣ ወዲህ ወዲያ የምትሮጥ ሴት፡፡ “ኧረ ተቃጠላችሁ! … ኧረ … እሳት…!...” የጀመረችውን አረፍት ነገር ሳትጨርስ “ልጄን … ልጄን … ልጄን አውጡልኝ፣ እሳት በላው ልጄን … ኡኡ…” እየተሯሯጠች የተቀጣጠሉትን ቆሻሾችን ለማጥፋት ትሞክርና ያቅታታል፣ ዙራያዋን እያየች ትጮሃለች፡፡ ስራዬ ብሎ የሚያያት የለም፡፡ ከተማው ለምዷታል፡፡ እሳት ስታይ ልምዷ ነው፣ በተለይ ህዳር ላይ፣ ህዳር ሲታጠን፡፡

 

 

 

Read 2911 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:41
More in this category: የተሼ ደብዳቤ »