Saturday, 05 March 2022 12:06

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀብር ሥነስርዓት መጋቢት 4 በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ይከናወናል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ባደረባቸው ህመም የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይተው ትላንት ዜና ዕረፍታቸው የተሰማ ሲሆን መጋቢት 4 በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የቀብር ስነስርዓታቸው ይከናወናል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በ1980 ዓ.ም ነሐሴ 29 ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ተብለው የተሾሙ ሲሆን በፖለቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከሃገር ከመውጣታቸው በፊት እስከ  ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ድረስ ለቤተክርስቲያን አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል። ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አገራቸው የተመለሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ ላለፉት 34 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል።
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ህልፈት ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶኛል ያሉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ተለያይተው የነበሩ ሁለት ሲኖዶሶች አንድ እንዲሆኑ ቅዱስነታቸው ወሳኙን ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ድረ-ገፃቸው ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት፤ ለሁላችንም መፅናናትን እመኛለሁ ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዜና ዕረፍት የተሰማቸውን ልባዊ ሃዘን ገልጸዋል።
“ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አምላካቸው ሄደዋል፤ ልባዊ ሃዘኔን ለቤተሰቦቻቸውና ለመላ ኢትዮጵያውያን እገልጻለሁ፤ ፈጣሪ  ነፍሳቸውን በገነት ያሳርፍልን፤ በክብር እንሸኛቸው” ሲሉ ፕሬዚዳንቷ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ እንዲሁ በቅዱስነታቸው ዜና ዕረፍት የተሰማቸውን ትልቅ ሃዘን በራሳቸውና በከተማ አስተዳደሩ ስም ገልፀው፤ የቅዱስነታቸውን ነብስ ፈጣሪ በአፀደ ገነት ያኖረው ዘንድ እንደሚመኙ በማህበራዊ ድረ-ገፃቸው ጠቁመዋል።



Read 11510 times