Sunday, 27 February 2022 00:00

አገራትና የስም ፖለቲካ (ስም ውስጥ ምናለ?)

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

  ሮሚዮ ሮሚዮ የልቤ ወለላ
እባክህ ለውጠው ስምህን በሌላ
ሮሚዮና ጁሊየት - ትርጉም በከበደ ሚካኤል። ይህ የሼክስፒር ዝነኛ ድርሰት “ስም ውስጥ ምናለ?” የሚል አነጋገርን ፈጥሯል። ሰሞኑን ቱርክ ስሟ ውስጥ ምን እንዳለ እየፈለገች ትመስላለች፡፡ የማሻሻያ ዘመቻም ጀምራለች። ታሪካዊው በሆነው ስሜ #ቱርኪየ; ልባል እያለች ነው። ቱርክ አንድ እግሯ እስያ ሌላው አውሮፓ የረገጠ፤ 85 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት ታሪካዊ ሀገር ናት። ኢስታንቡልን የጎበኙ ወዳጆቻችን ስለ ውበቷ ተናግረው አይጠግቡም።
የዚህ የስም ለውጥ እንቅስቃሴ ዋነኛ ምክንያት፣ ከአሜሪካኖቹ የዶሮ ዝርያ ጋር መምታታት አለመፈለግ ነው እየተባለ ይነገራል። አሜሪካኖች በምስጋና ዕለት (Thanks giving day) ማዕድ የሚሰበሰቡት ተርኪ የሚሉትን ዶሮ አሰናድተው ነው። በአፃፃፍም ሆነ በአነጋገር ዶሮዋና ሀገሪቱ አንድ መሆናቸው ቱርክን ሳያበሳጭ አልቀረም። በሌላም በኩል፤ መንግሥት በዋጋ ግሽበት የተነሳ እያዛጋ ያለውን ገበያ ለማነቃቃት፣ ጎብኚዎች በብዛት እንዲመጡ የተጠቀመበት የማሻሻጥ ሥራ ነው የሚሉም አሉ።
ጉዳዩ ግን እኛን አይመለከትም -  ተርኪ ብለን አናውቅም፤ ሁሌም ቱርክ እያልን ነው የምንጠራት፡፡ ተርኪ የተባለውን የዶሮ ዝርያም ቢሆን ምናልባት ጅግራ ሳንለው አንቀርም። ከዚህ በፊትም ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቼኪያ በሉኝ ባለች ጊዜ ብዙም ቀልቡ የተሳበ አልነበረም። በዛ ላይ ደግሞ ለበርካታ ሀገሮች የእኛው የሆነ ስያሜ ወይም አጠራር አለን። ግብፅ፥ ሊባኖስ፥ ሕንድ፥ ዮርዳኖስ፥ ፋርስ፥ መቄዶኒያ፥ ቆጵሮስ፥ ጣሊያን፥ ጀርመን፥ እንግሊዝ፥ ፈረንሣይ፥ አህጉሪቷን አፍሪካ እንኳ አፍሪቃ የምንልባቸው ጊዜዎች ነበሩ።
እርግጥ በጊዜ ሂደት እኛም ቀስ በቀስ የእንግሊዝኛውን አጠራር እየወረስን ነው። ከድረገፅ ትስስር መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንግሊዝኛ የነገሰበት ዘመን በመሆኑ ተፅእኖው ቀላል አይደለም። እነዛ የግድ ትክክለኛ ናቸው ባይባልም፣ ሰልፍ ማሳመር ሥልጣኔ ይመስላል። ለምሳሌ ሩሲያውያን መናገሻቸውን መስክቫ እንጂ ሞስኮ አይሉም። ጀርመኖች ሀገራቸውን ዶችላንድ ይላሉ። አይቮሪ ኮስት በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተጽዕኖ ይመስላል ኮትዲቯር በሉኝ ትላለች። ቻይናም ራሷን የምትጠራው በሌላ ስም እንደሆነ ይታወቃል።
…አፍሪካ  አገራችን
የስም ለውጡ ላይ አፍሪካ ውስጥ ከሚታወሱት አንዱ የላይኛው ቮልታ የሚባለው ሀገር ነው። ፈረንሣዮች ይህንን ቅኝ ግዛታቸውን ለ’ኦት ቮልታ ሲሉት፣ እንግሊዞች ደግሞ አፐር ቮልታ ይሉታል። ቶማስ ሳንካራ የተባለ የአየር ወለድ መኮንን እ.ኤ.አ በ1983 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ሲይዝ፣ “የምን የላይ የታች ነው፤ እኛ ‘የቅን ህዝቦች ሀገር’ ነን” አለ። ባገሩ ቋንቋ  -ቡርኪናፋሶ። ዜጎቹ ደግሞ-  ቡርኪናቤ። ሳንካራ አራት አመት ያህል መርቶ በመፈንቅለ መንግሥት ቢገደልም የሀገሪቱ ስም ግን ተተክሎ ቀርቷል።
ኮንጎ ጫማን፥ የስታዲየሙ ካታንጋን፥ ቾምቤ የምንለውን ቅፅል ስም የሰጠችን ኮንጎም እንዲሁ ትታወሳለች። ከሌላኛው ኮንጎ ለመለየት ኮንጎ ኪንሻሳ አንዳንዴም ዲአርሲ ብትባልም፣ ከስም ጋር ተያይዞ የራሷ ታሪክ አላት። ሀገሪቱ ከቤልጂየም አገዛዝ ነፃ ስትወጣ፣ በታላቁ ወንዟ - ኮንጎ - ነበር የምትባለው። ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ በቤልጂግና በአሜሪካ ድጋፍ መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣናቸውን ሲያደላድሉ፣ ሁሉም ነገር አፍሪካዊ መሆን አለበት የሚል ዘመቻ ጀምረው ነበር። እሳቸው ‘ኦተንቲሲቴ’ በሚሉት ‘የጥንቱ ትዝ አለኝ’ አይነት ፈሊጥ፣ በርካታ ከተሞች ስማቸው ተቀይሯል። በአለባበስም ቢሆን እነ ማኦ ያስተዋወቁትን አጭር ኮሌታ ያለው ከላይ ጀምሮ የሚቆለፈው ‘አባኮስት’ ደንብ ሆነ። አባኮስት በቀጥታ ትርጉሙ ‘ሱፍ ይውደም’ ማለት ነው። የመሪውም ስም ከጆሴፍ ደዚሬ ወደ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ንግቤንዱ ኩኩ ዋ ዛባንጋ ተቀየረ። ቴሌቪዥኑም በየምሽቱ ዜና እወጃው ይህንን ስም ያስተጋባ ነበር። የሀገሪቱም ስም ዛየር ሆነ - ለሩብ ክፍለ ዘመን! ሞቡቱ አማፂዎችን ሸሽተው ሞሮኮ ከተሰደዱ በኋላ ሥልጣኑን የጨበጡት የካቢላ ቤተሰቦች፣ የሀገሪቱን መጠሪያ ወደ ኮንጎ መልሰውታል።
አፍሪካ ታሪኳ ከቅኝ ግዛት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ አብዛኞቹ ስሞች፣ ገዢዎቹ እንደታያቸው አንዳንዴም በዋና አስተዳዳሪዎች ስም የተሰየሙ ነበሩ። ሮዴሽያ፥ ሶልስበሪ፥ ዳሆሜ፥ ባሱቶላንድ፥ ኒያሳላንድ፥ ጎልድ ኮስት፥ በችዋናላንድ (ዚምባብዌ፥ ሀራሬ፥ ቤኒን፥ ሌሴቶ፥ ማላዊ፥ ጋናና ቦትስዋና - የዛሬ ስማቸው በቅደም ተከተል) ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።
ሁለት ለመንገድ…
በቀድሞው ጊዜ ሀገራችን ውስጥ ‘የሲሎን ሻይ’ ይባል ነበር። ሲሎን የስሪላንካ የድሮ ስም ነው። በ19ኛው ክፍለዘመን ቻንግና ኢንግ የተባሉ የተጣበቁ መንትዮች በታይላንድ ተወልደው ነበር። ቻንግና ኢንግ ከመንደራቸው ወጥተው በአሜሪካና አውሮፓ እንደ ትርዒት ሲታዩ ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ በየትም ሀገር ከደረታቸው ጀምሮ ተጣብቀው የሚወለዱ መንትዮች፣ ‘ሲያሚዝ ትዊንስ’ ይባላሉ። ቀድሞ ታይላንድ ሲያም ተብላ ትጠራ የነበረበትን ጊዜ በማስታወስ። ጳውሎስ ኞኞ "አስደናቂ ታሪኮች" በሚል ባወጣቸው ቅፆች በአንደኛው ላይ የነሱ ታሪክ ሰፍሯል።
ጽጌረዳ በፈለገው ስም ብትጠራ ውብ መዓዛዋን አትለቅም ይላል፤ ወግ የጀመርንበት ሮሜዎና ጁሊየት። ቱርክም በፈለገችው ስም ብትጠራ፣ ሁሌም የኦቶማኖች ሀገር ናት።


Read 1157 times