Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 September 2012 09:09

የርዕዮት ጣቶች ወዴት ያመለክታሉ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

እንደ ፈንዲሻ የፈኩ፣እንደ ተራራ ሰማይ የተናከሱ ምናብ-ወለድ የጥበብ ስራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ለሰስ ያሉ እውነቶች፣ፈርጣማ ሂሶችም ወደ አደባባይ ሲደርሱ የምናገኘው የእውነትና ውበት ማማ አለ፡፡ስለዚህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፈጠራ ጽሁፎች በተጨማሪ የህትመቱን አደባባይ የሞሉትን መጽሃፍት የማያቸው በጥሩ ጎኑ ነው፡፡ደግሞም የታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪኮች፣ ቀልዶችና ፖለቲካ- ነክ መጣጥፎች ወደ ህትመቱ ጎራ ብቅ ማለታቸው ሌላው የዕድገት እመርታ ነው፡፡ የቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ “ፍልስምና” 1 እና 2፣ የፍልስፍናና የሃይማኖት ዝንባሌ ያለው መጽኃፍ፣ የደርግ መኮንኖች ስለቀደመው ስርዓት አወዳደቅና ወታደራዊው ገድል የጻፉት ግለ-ታሪክ፣ የኢህአዴግ ሰዎች በነርሱ ወገን ስለነበረው ተጋድሎ የጻፉት ገድል፣ አሁን ደግሞ እነ ርዕዮት መንግስትን፣ ደራስያንንና ሙዚቀኞችን ያሄሱበትንና ሌሎች ጽሁፎችን ማየታችን እሰየው! የሚያሰኝ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በተለያየ መልኩ የታሪካችን አካል፣ የእርቃናችን መልኮች ናቸውና ልናነባቸው፣ እህ…ብለን ልናደምጣቸውና ልንፈርድላቸው ወይም ልንፈርድባቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ብቻ በዘርና በሃይማኖት የሚከፋፍሉን አይሁኑ!!

ዛሬ የኔም ቅኝት ከነዚህ ዝርያዎች አንዱ የሆነውን  የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን  “የኢህአዴግ ቀይ እስክሪብቶ” ፖለቲካ - ነክ መጽሃፍ ነው፡፡ በተለይ ይዘቱ ላይ ያተኩራል፡፡ የመጽሃፉ ሽፋን በማራኪ ምጥ የተወለደ ስለነበር ወዲያው ነው-የሳበኝ፡፡ ቆንጆና አስገራሚ ትርጉም ያለውም ነው-ከፍ ያለ!!...ንጽጽሩን በጣም አድንቄያለሁ!! ከየት አመጡት? ማለት አይደል ማድነቅ?…ለነገሩ መጽሃፉም ሶስቴ ታትሞ የለ

በመጽሃፉ ውስጥ ከተካተቱት መጣጥፎች ቀደም ብዬ ያነበብኩት ጥቂቱን ብቻ ስለነበር፣ ሁሉንም እንደገና ማንበብ ነበረብኝ፤ ፖለቲካ የጥበቡን ያህል ባይጥመኝም፣ ያገሬ ጉዳይ ነውና መቸም አላየሁም-አልሰማሁም አልልም፡፡ መጽሃፉን ሳነብ የገረመኝ አንዱ ነገር የዚች ወጣት ሳትታክት ብዙ መጽሃፎች፣ መጽሄቶች፣ ጋዜጦችና ጥናታዊ ጽሁፎች ማንበብዋ ነው፡፡ ከዚያም ያለፈ ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆኗ ደንቆኛል፡፡

ብዙ ሃሳብዋን የሚደግፉ ንባባት ለማግኘት ያደረገችውን ጥረት እንዳጤን ያስቻለኝ፣ በዘጠኝ መጣጥፎች ብቻ 37 ያህል ማጣቀሻዎች መጠቀሟ ነው፡፡ ይህ ጥረትዋ እስካሁን ካየሁዋቸው ጸሐፍት የተለየች ነች እንድል አስችሎኛል፡፡ ከስሜት ይልቅ ወደ እዉነታዎች ወይም መረጃዎች አዘንብላለች፡፡ የማከብረው ገጣሚ ወዳጄ እንደሚለው”የእረኛ ስድብ” አትሳደብም፡፡

መጣጥፎችዋ ይበልጡን ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ይሁን እንጂ ሁላችንንም የሚነኩ ነው፡፡ መንግስትን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን የሚያሄሱ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ መነሻ የተመዘዘላቸው፣ችግሩን ፈልቅቀው የሚያሳዩ፣ የለዉጥ መንገድ ለመጠቆም ችቦ የጨበጡና አሳማኝ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ስሜታዊ የሚያሰኙ መደዴ ቃላትን እንኳ  ያለመጠቀሟ ደስ አሰኝቶኛል፡፡ የመንግስትን ችግሮች ፈልፍላ ብትወቅስም መንግስት ቢቀጥልባቸው የምትላቸውን ቅን ሃሳቦች እንኳ በቅንነት ለመናገር ሞክራለች፡፡ (ለምሳሌ ገጽ 66 ላይ ያለው ሃሳብ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል፡፡) …የሰንደቅ ዓላማን አከባበር በተመለከተ የጻፈችው ላይ እንዲህ ትላለች፡- Ç‹በየትኛውም ምክንያት የሰንደቅ ዐላማን ቀን እንዲከበር ማድረጉ ያስመሰግነዋልÈ ብላለች፡፡ ሁሉን ነገር ኮሶ ከማደረግ ሚዛናዊነትን መለማመድ ጥሩ መሰለኝ፡፡ በሌላ ወገን ግን የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ማጤን ያቃተው ይመስለኛል፡፡ የተቃወመውን ሁሉ በዱላና በእስር ካስወገደ በዓይኑ ዉስጥ ያለውን ግንድ እውን ኢቲቪ ያሳየዋል? አይመስለኝም፡፡ መሪዎቹስ ቢሆኑ እንዴት ታግለንለታል የሚሉትን ዓላማ ያፈርሳሉ? ወጣትነታችንን ገብረንለታል የሚሉትን ህልም እንዴት ይጥላሉ? ..በአንድ ወቅት ስለሌሎች ነጻነት ሲዋጉ የነበሩ ሰዎች፣ ዛሬ መልሰው ነጻነትን እየተቃወሙ እንደሆነ አጡት ብሎ መጠርጠር ግራ ያጋባል!!in every country where man is free to think and speak ,differences of opinion will arise from difference of perception.È- ሰው በነጻ ለማሰብ፣ለመናገር ነጻ በሆነበት ሃገር የአስተሳሰብ ልዩነቶች የሚመነጩት ከተለያዩ አተያዮች ነው፡፡È ብሎ ጀፈርሰን ያምናል፤የኛም ህግ ያምናል፡፡

ጄምስ ዴቪድ ባርቤር የተባሉ ጸሃፊ እንደሚሉት”አንድ ፖለቲከኛ ሃይል ከተጠቀመ እንደመሪ ችግር ውስጥ ገብቷል ማለት ነው” እኔ መንግስታችን እንዲህ ባይሆንና የከፈለውን ዋጋ በአግባቡ ቢያጭድ ደስ ይለኛል፡፡

የሚገርመው ርዕዮት መንግስትን ብቻ አይደለም የተቸችው፡፡ ደራስያንን፣ ሙዚቀኞችንና ሌሎችንም ነው፡፡ ደራሲያንን ስትተች የምትጀምረው ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ይሁንና በዚያም ዘመን ሃዲስ አለማየሁ፣ አቤ ጉበኛና ዮሃንስ አድማሱን የመሳሰሉ ሃቀኞች ነበሩ በሚል ታደንቃለች፡፡ በቀጣዩ የደርግ ዘመንም በዐሉ ግርማን የመሰለ ሐቀኛ ነበረ ስትል ታሞግሳለች፤ ለዚህ የጠቀሰችው ግን “ኦሮማይ” መጽሃፍ ብቻ ነው፡፡

የአሁኑን ዘመን የጥበብ ሰፈር የተቸችው ጎመን በጤናÈ በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይሥማዕከ ወርቁን፣ አያልነህ ሙላትንና ቴዲ አፍሮን ከአድርባዮቹ ነጥላቸዋለች፡፡ በኔ እምነት አድርባይነት ያላየሁበት ይስማዕከ ነው፡፡ የሚፅፈው ከልቡ እንጂ የሰው ቀልብ ለመስረቅ አይመስልም፡፡ ሌሎቹን ግን በአጋጣሚ ወይ ለመወደድ ካልሆነ እንደራስዋ እንደ ርዕዮት ለህዝብ አዝነው ነው ማለት ይከብደኛል፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይዋ ሁሉም ጎመን በጤናÈ ብሎ የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት አቁሟል ባይ ናት፡፡ ስለዚህም በአብዛኛው የሚጻፉት ነገሮች ሁሉ በተቃራኒ ጾታ ላይ ያተኮሩ ናቸው ስትል ትወቅሳለች፡፡ ዋቢ ስትጠቅስም ከ1987-1990 ዓ.ም ድረስ ከታተሙት የሙዚቃ አልበሞች 200 ግጥሞች ውስጥ 146ቱ (73 ፐርሰንቱ)የተቃራኒ ጾታን የተመለከቱ ናቸው ብላለች (ይህ ወቀሳ የእኔም ጭምር ነው) ‹‹ምናልባት ፈርቼ ይሆን እንዴ ያልጻፍኩት›› ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አድርጋኛለች፡፡ …ግን አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ ኢህአዴግ ይለወጣል የሚል ተስፋ ስለቋጠርኩ ይመስለኛል፡፡ (ለለውጥ ሙከራዬ ግን በጋዜጦች ላይ ሚዛን ጠብቄ ለመጻፍ ሞክሬያለሁ) …ሌላው ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች ስለማይመቹኝ ይሆናል (እነርሱም እንደ ድል አጥቢያ ሆዳም ካድሬዎች አይስማሙኝም) ይልቅ ልቤ ለጋዜጠኞቹ ያደላል፡፡

ይሁንና ርዕዮት  ከአድር ባዮች ብዕር ባዶ ወረቀት እንደሚሻል በመንገር በመጨረሻም የበዐሉ ግርማን ጥቅስ ከደራሲው ተውሳ ትዘጋለች፡፡ ወይ ጉዳችን አድርባዮች ሆነን ይሆን? ማን ያውቃል? መመርመር ነው…ራሳችሁን!

የሃይማኖት አባቶችን የተቸው አንዱ የርዕዮት መጣጥፍ፣ በታሪክ ሃዲድ ወደ ኋላ ሄዶ እነ አቡነ ጴጥሮስን ሲያስታዉስ ትዝታው ይመስጣል፡፡ (ለኒህ ሰው ያለን ክብር ታላቅ ነዉና!)እኒያን ድንቅ ሰው በፍቅር ለመዘከር እንገደዳለን፡፡ በዚሁ ምዕራፍ የፍቅር እስከ መቃብሩን ቄስ ሞገሴን ከዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ያነጻጸረችበት መንገድም ይመቻል፡፡ ጥበቡ-ራሱ!! በዚህ መጣጥፏ “ቃና ዘገሊላ” መጽሄት ላይ የተጻፈውን ትንቢት መሰል ነገር አጣጥላዋለች፡፡ እዉነቷን ነው! ዛሬም በየሃይማኖት ተቋሟቱ ዙሪያ የሚቀባጥሩ ሞልተዋል፡፡ ይህ የሃይማኖት ሠፈር ቀዉስ በህብረተሰቡ ዘንድ ጸሃይ የሞቀው ስለሆነ ክርክር የለኝም፡፡

ልዩነቱ ርዕዮት እዉነቱን ለመናገር ቀድማለች፡፡ በሚጣፍጥ ምላሳቸው ስንቴ እንደሸጡን ፈጣሪ ይወቀው!!..አሁንም ጀፈርሰንን ልጥቀስ?…in every country and in every age ,the priest has been hostile of liberty. (ሁሉም ሃገር ላይ በየትኛውም ዘመን፣ የሃይማኖት አገልጋዮች የነጻነት ጠላቶች ናቸው እንደ ማለት ነው፡፡)

ከርዕዮት  ሃሳቦች በጣም አድርባይ ዝንባሌያችንን ያሳየኝ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በግንቦት 1984 ዓ.ም በተከታታይ ያወጣቸውን ፅሁፎች ነው፡፡ ጋዜጦቹ ከግንቦት 11 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 20 ያተሙትን አሳፋሪ መገለባበጦች አሳይታለች፡፡ ፕሬዚደንቱን አንዴ “አንቱ” ሌላ ጊዜ ደግሞ “አንተ” ሲሉ አሳይታናለች፡፡ በርግጥም እንጀራ፣ ረግጦ እንደገዛን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን አስሳ ማግኘቷም ግሩም ነው፡፡ …አድርባይነታችን አፍንጫችን ድረስ ደርሷል ማለት ነው

ቀጥላም አሁን ስላለው ፕሬስ ጽፋለች፡፡ በርግጥም አሁን ያለው ፕሬስ የይስሙላ ብቻ እየሆነ እንደመጣ እንኳን እኔ መንግስት ራሱ የሚያጣው አይመስለኝም፡፡ለዚህ ግን ቅጥ ያጣ ስድብ የሚጽፉ ሰዎች አስተዋጽዖ እንዳለበት እገምታለሁ፡፡ በኔ እምነት ስድብ ብቻ ለውጥ አያመጣም፣ መወቃቀስና ችግርን ማሳየት ግን ጥሩ ነው፡፡ ለዚህ ነው ርዕዮትን የወደድኳት፡፡ ርዕዮት ወደ ኋላ ሄዳ በምልሰት የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ሲይዝ የነበራትን የፕሬስ ነጻነት ጉጉት ታስታውሳለች፡፡ የፕሬስ መብት እንደሚከበር በመግለጹም ከላይ የተጠቀሰው የደርግ ዘመን አይነት አስደንጋጭ አድርባይነት እንደሚጠፋ መገመቱን ትዘክራለች፡፡ በወቅቱ የጊዜያዊዉ መንግስት ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ፣ የፕሬስ ነጻነትን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ተስፋ ሰጪ ስለነበር ብዙ ሰዎች ጉጉት አድሮባቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ… አሁን አሁን ግን እየመነመነ መምጣቱን አልደበቀችም፡፡

ሌላው የርዕዮት ርዕሰ ጉዳይ የሰላማዊ ትግል አደጋ ላይ መውደቅ ነው፡፡ ለዚህም የሰጠችው አስተያየት ሚዛናዊ ነው፡፡ በዚህ ውድቀት መንግስት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤የቀረውን ደግሞ ተቃዋሚዎች ራሳቸው!! ርዕዮት አሁንም ደስ ያለችኝ ሚዛናዊ የመሆን ዝንባሌዋን ሳይ ነው፡፡ ግና አሁንም ጀፈርሰን እንዲህ ይላል፡- Ç…each generation …has a right to choose for itself the form of government it believes the most promotive of its own happiness.È ጀፈርሰንን ከፕሬስና ዴሞክራሲ ነጥሎ መጥቀስ ወይም ከርሱ ሌላን ሰው ማስቀደም የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ስለ ሰላማዊ ትግል ስናነሳ ጋንዲንና ሉተር ኪንግን (እሱ እንዲያውም ጥቂት ስቷል) ቶልስቶይንና ሄነሪ ዴቪድ ቶሩን መተው የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ርዕዮት ሰፊ ሽፋን ከሰጠቻቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሌላኛው የሴቶች ጉዳይ ነው፡፡ በሴቶች ጉዳይ ሃይማኖቶችን፣ መንግስትን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሳይቀር ወቅሳለች፡፡ የርዕዮትን ሚዛናዊነት ወድጄ የደወልኩለት ወዳጄ፣ ጸሃፊዋን በግንባር ብታያት ትወዳታለህ ብሎኝ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ ብዙ አላውቃትም፡፡ ግን ድፍረትዋን፣ ቀናነትዋን ሁሉ ወድጄዋለሁ፤ መንግስትም ቢሆን የዚህ አይነት ቀና አተያይ ያላቸውን ሰዎች ሊያዳምጥና ሊያሳድግ እንጂ ሊያሳድድ አይገባም  ነበር፡፡ ዱላም በነርሱ የትግል ዘመን እንጂ በዚህ ዘመን የአሸናፊነት ምልክት አይደለም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ይህንን ኋላ-ቀር መንገድ ቢተወዉና ወደ ተሻለ መንገድ ቢመጣ፣ ለኛም ለራሱም ጥሩ ነው፡፡

ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቀን ወደ መደማመጥ፣ ወደ መሻሻል ብንሄድ ጥሩ ነው የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ የደርግ ባለስልጣናት እስራቸውን ጨርሰው መውጣታቸውን አድንቄያለሁ፤ ስላልተነካህ ነው እንዳልባል አባቴን ያሳጣኝ ደርግ ነው፤ ግን ምህረት ከሁሉ ይበልጣልና በምህረት አምናለሁ፡፡ እኛ አፍሪካዊያን ምህረትን ከማንዴላ እንኳ ልንማር ይገባ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት የደርግ ምክትል ፕሬዚደንት የነበሩት ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታና አቦይ ስብሃት በግጭት አፈታት ላይ ጽሁፎቻቸውን ሲያቀርቡ ተሳትፌ ያየሁት ነገር ቢኖር የምህረትን ውበት ነው፡፡ እውነት ምህረት እንዴት ደስ ይላል!!...ደርግስ ያኔ ይህን አድርጎ ቢሆን ምናለ? ሁለቱ ሰዎች የሚመሩዋቸው ፓርቲዎች ሰው ሳያልቅ በፊት ቢያደርጉት!... መንግስት ከዚህ መማር ያለበት ይመስለኛል፡፡ የሰራቸውን ጥሩ ነገሮች ብቻ ከመቁጠር ይልቅ ደካማ ጐኑ ላይ ቢያተኩር ሌላውም ወገን ከጥላቻው ነጻ ቢሆን! ከቂም በቀል የጸዳ ሃገር ይኖረናል፡፡ ለመጪውም ትውልድ ብሩህ ነገር ማውረስ እንችል ነበር፡፡ ጎበዝ ስለ ትውልድ እናስብ እንጂ! መንግስት ሆይ፤ መልካም ማድረግ ለህሊናም ለታሪክም በጎ ነውና ይልመድብህ፡፡ በፕሬስ ነፃነት ላይና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ላይ ያለህን አካሄድ አስተካክል!! ሌላ ጥንካሬ እንዳለህ ግን አምናለሁ፡፡ ምንም አልሰራህም ብዬ ከህሊናዬ አልጣላም!! ...ነገር ግን ቶማስ ጀፈርሰን እንዳለውÇ I own I am not a friend to a very energetic government.ነው ነገሩ!! ርዕዮት፤ አንቺም ዛሬም ነገም ታማኝ ሆነሻልና በርቺ!! ልብሽ አይውደቅ!!…

 

 

Read 2500 times Last modified on Saturday, 29 September 2012 09:16