Monday, 21 February 2022 00:00

ከአገራዊ ምክክሩ ምን ይጠበቃል?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 "ሁሉም ችግር የሚመነጨው፣ ከህገመንግስቱና እሳቤዎቹ ነው"

           በቅርቡ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክር መድረክ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሰሜን ያለውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ማሰቡ ይነገራል፡፡ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ማለትም በብሔራዊ የምክክር ሂደቱ ዙሪያና በድርድሩ ጉዳይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣  ከአንጋፋው ፖለቲከኛና የዩኒቨርስቲ መምህር ንጋት አስፋው (ዶ/ር) ጋር ቀጣዩን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡

             በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያጋሩን?
የታሰበው ብሔራዊ የምክክር መድረክ በእውነቱ በሃቅና በግልፅነት የሚካሄድ ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ የዘመናት ችግር መፍትሔ በማስቀመጥ በኩል እጅግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አላማው በሚገባ ግቡን እንዲመታ ከተፈለገም ሁሉም አካሄድ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የኮሚሽኑ አባላት አመራረጥ ሂደት ለህዝብ በደንብ ግልፅ መሆን አለበት፡፤ የምክክሩ አላማ፣ ስለ ምክክሩ የወጣው ሰነድና ሃሳብ ወደ ህዝቡ ወርዶ፣ በሚገባ  ሊመከርበትም ይገባል፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሃራችንን የፖለቲካ ችግር የምንፈታው ሀሉም ነገር በግልፅ ለውይይት ሲቀርብና ፍሬያማ ውይይት  ማካሄድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የኮሚሸኑ የበላይ የሆነው ፓርላማው ስለ ኮሚሽኑና ስለ ምክክሩ ሃሳብና ሂደት አስቀድሞ ከህዝብ በተለያየ መንገድ አስተያየት በመሰብሰብ የበለጠ ውጤታማ ማድረግ ይቻላል፡፡
በዚህ ምክክር እነማን ተሳታፊ ቢሆኑ የበለጠ ግቡን ይመታል ይላሉ?
ሁሉም የፖለቲካ ንቃቱ ያለው ቢሳተፍ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን--ሁሉም ቢሳተፉ መልካም  ነው፡፡ በዚህ የውይይት ሂደት ፍፁም ጨዋነት ሊሰፍንና ላለመግባባት መግባባትም እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮችን በምክክር መድረክ መፍታት ይቻላል ብለው ያስባሉ?  ድርድር የተሻለ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ --
ምክክር እኮ በሠላም የመነጋገር፣ ሠላምን የመለማመጃ አንዱ መንገድ ነው፡፡ የፍቅር ምልክት ነው፤ የመግባባት ምልክትም ነው፡፡ ችግሮችንም አጉልቶ ያለ ገደብ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት ይረዳል፡፡ በምክክር ሂደት ነጥብ ማስቆጠር የሚባል ነገር አይኖርም፤ ስለዚህ ችግሮችን በሃቅ ለማውጣትና ለመነጋገር የሚገድበው ነገር አይኖርም፡፡ ድርድር ግን ከዚህ ትንሽ ለየት ይላል፡፡ አንዱ በአንደኛው የበላይ ሆኖ ለመውጣት ፍትጊያ ይኖራል፡፡ በቅድመ ሁኔታዎች የታጠረ ነው። እውነትና ሃቅን ለማውጣት ያስቸግራል፡፡ ነጥብ ለማስቆጠር ሲባል ሃቆች ሊደፈጠጡ ይችላሉ፡፡ በድርድር ሂደት ነፃ ሃሳብን ለማንሸራሸርም ያስቸግራል፡፡ በምክክር ግን ሁሉንም በነፃነት መስጠትና መቀበል ይቻላል፡፡
ለምሳሌ  አንዱ አወዛጋቢ ጉዳይ  ሰንደቅ አላማ ነው? ይሄ ችግር በምክክር መፍትሔ ሊያገኝ ይችላል?
ሠንደቅ አላማ’ኮ ብሔራዊ ምልከታ ነው። ኢትዮጵያ ሲባል ቀድሞን የሚመጣው ነው፡፡ የብዙዎቻችን ሥነ ልቦና የተገነባው በሠንደቅ አላማ ነው፡፡ ይሄ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ - አድዋ የዘመተ ባንዲራ ነው፡፡ ገበሬው እሱን ይዞ ነው የተዋጋው፡፡ የቅኝ ገዢዎችን ህልም ያጨናገፈና ያንበረከከ ሠንደቅ አላማ፣ የሃገሪቱ መለያ  ቢሆን ምንድን ነው ክፋቱ? ትልቁ ፀብ ከሰንደቅ አላማው በስተጀርባው ያዘለው የጀግንነት ታሪክ ጋ ነው፡፡ ይሄን ሠንደቅ አላማ ከአማራ ጋር አያይዞ የመጥላት አባዜ፣ ወያኔ የፈጠረው ነው፡፡ ይህ አመለካከት ከወያኔ ጋር መቀበር ነው ያለበት፡፡ ሠንደቅ አላማው፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የደም ዋጋ የተከፈለበት ነው፡፡ ይህችን አገር እዚህ ያደረሱት ይሄን ሠንደቅ አላማ  ምልክት አድርገው ነው፡፡ ይሄን ሰንደቅ  አላማ ደግሞ የሚቀበል በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አለን፡፡ የተወሰኑ ወገኖች ኮከቡን ስለደገፉ፣ ሌላው ያንን ይቀበል ማለት አይቻልም። ስለዚህ በምክክሩ ሂደት በተሻለ አሳማኝ ነጥቦች ያስረዳው ወገን ሃሳቡ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ግን ሂደቱ ቀላል ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ በኦነግ አስተምህሮ ያደገው ኦሮሞያ ያለ ወጣት ላይቀበለው ይችላል፡፡ ይሄ ታዲያ በሰከነ ውይይት ነው መፈታት ያለበት፡፡ ምክክሩም ያስፈለገው ለዚሁ ነው፡፡
በአጠቃላይ ከዚህ የምክክር ሂደት እርስዎ ምን ውጤት ይጠብቃሉ?
መመካከሩ በራሱ አንድ የሰላም ምልክት ነው፡፡ ብዙ ፈተኖች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ግን ምንም ቢሆን በውይይት የማይፈታ ነገር አይኖርም፡፡ ሁሉም ቀና ሆኖ ራሱን ለውይይት ካዘጋጀ፣ የማይፈታ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ በተለይ  በጎሳ የተደራጁ፣ ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ፣ያንን የሚጠቀሙበትን ህዝብ የማይጠቅሙ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በተለይ ይሄን አማራጭ በአግባቡ ቢጠቀሙበት መልካም ይሆናል፡፡ ይሄ እንዲሆን የእነሱም የሌላውም ቀናነት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ምልዐተ ህዝቡን ያሳተፈ እንዲሆን ማድረግ ከተቻለ፣ እኔ በበኩሌ ብዙ ተስፋ የማደርግበት ሂደት ነው፡፡ ብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚፈጥር ምክክር ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሌላ በኩል ከህወኃት ጋር ድርድር የማድረግ እንቅስቃሴ እንዳለ ይነገራል፡፡ ከህወኃት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ድርድር ምን ያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
እስካሁን በመንግስት በኩል ምንም የተሠጠ መረጃ የለም፡፡ በህወኃት በኩል ነው ድርድር አስበናል የሚል ነገር የተሰማው፡፡ ስለዚህ ስለ ጉዳዩ  ብዙ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ለኔ እንደ አጠቃላይ፣ ድርድር ጥሩ ነው፡፡ ከአጥፊው ጦርነት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መደራደር ለንፅፅር እንኳ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ግን ድርድር ሲካሄድ ምን ተይዞ ነው? አጀንዳውስ ምንድን ነው? እንዲያመጣ የሚፈለገውስ ውጤት ምንድን ነው? የሚሉት በሚገባ መታሰብ አለባቸው፡፡ ከህወኃት ጋር ድርድር ለማድረግ በመጀመሪያ የአሸባሪነት ፍረጃው ሊነሳለት ይገባል፡፡ ይሄ በምን ቅድመ ሁኔታ ነው የሚነሳው የሚል ጥያቄ ደግሞ ይፈጥራል፡፡ የአማራና የአፋር ህዝብ ቁስል ገና አልደረቀም፡፡ ከዚህ ሃይል ጋር የሚደረግ ድርድር፣ በቆሰለው ህዝብ ላይ ምን ስሜት ይፈጥራል? ከዚህ ሃይል ጋር የሚደረግ ድርድር ምን የተሻለ ውጤት ያመጣል? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በመጀመሪያ በሚገባ መጤን አለባቸው። በተለይ በሉአላዊነት ጉዳይ፣ በሃገር አንድነት ጉዳይ፣ በተለይ በመገንጠል ጉዳይ -- በምንም መልኩ ድርድር ሊካሄድ አይገባውም የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ከህወኃት ጋር የሚደረግ ድርድር ደግሞ በጣም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በሚገባ የታጠቀ ቡድን ነው፡፡ ይሄ ቡድን ትጥቁን መፍታት አለበት፡፡ በፌደራል መንግስት በኩል ደግሞ የትግራይ ህዝብ ሙሉ ዋስትና ሊያገኝ ይባዋል፡፡
ሙሉ ዋስትና ሲባል ምን ማለት ነው?
ህወኃት ትጥቁን ካወረደ በኋላ የማንም የጎበዝ አለቃ ትግራይን እንደማይነካ ዋስትና ሊሰጠው ይገባል፡፡ የትግራይ ህዝብ ወገናችን ነው፡፡ አሁንም እየተጋፈጠ ያለውን ችግር ማናችን ነን በሚገባ የተረዳንለት፡፡ ይሄ በእውነቱ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ በብዙ መከራ ውስጥ ያለ ህዝብ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ሙሉ  የደህንነት ዋስትና ያስፈልገዋል፡፡ ማንም እየተነሳ የሚፎክርበት፣ ሊያጠቃው የሚጣጣርበት እድል ሁሉ መዘጋት አለበት፡፡
ከህወኃት ጋር ብቻ የሚደረግ ድርድር ምን ያህል ጦርነትና ግጭትን ያስቀራል?
ይሄ የኔም ጥያቄ ነው፡፡ ከህወኃት ጋር ብቻ የሚደረግ ድርድር የራሱ ውጤት ቢኖረውም፣ በርካታ ትጥቅ ያነሱ ሃይሎች ባሉበት ሃገር፣ ሙሉ ለሙሉ የተረጋገጠ የሰላም ዋስትና አያመጣም፡፡ ሸኔን በለው ሌላ ትጥቅ ያነሳ ሃይል ሁሉ መሳሪያውን ጥሎ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ላይ ድርድር ያስፈልጋል፡፡ የማንነት ጥያቄ ያነሱ አሉ። ለእነዚህም ሁሉ ምላሽ የሚገኝበት ሰፊ የድርድር አውድ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የድርድር አውድ ወደ ብሔራዊ እርቀ ሠላም የሚወስደን መሆን አለበት፡፡ በዚህ መንገድ ከተጓዝን አሁን የገጠሙን ችግሮች ሁሉ ቀስ በቀስ መፍትሔ ያገኛሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
በአጠቃላይ በምክክሩም ሆነ በድርድሩ የትኞቹ አጀንዳዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ?
ህገመንግስት ዋነኛው ነው፡፡ ይሄ ህገመንግስት እኮ ነው እያባላን ያለው። የትም ሃገር የሌለ አይነት ህገ መንግስት ነው አሁን ያለው፡፡ ህገመንግስቱ የወያኔ ገፀ-በረከት ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው ትልቁ ውይይት ሊካሄድ የሚያስፈልገው፡፡ ሁሉም ችግር የሚመነጨው፣ ከህገመንግስቱና እሳቤዎቹ ነው፡፡ ስለዚህ የህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ዋነኛ አጀንዳ መሆን አለባቸው፡፡


Read 12198 times