Sunday, 20 February 2022 15:24

የልብ ማዲያቶች - “በዕልልታ እና ሙሾ”

Written by  ደ.በ
Rate this item
(0 votes)

 ግጥምን ሁሉም ሰው አንብቦ ለየራሱ የሚሰጠው ትኩስ ስሜት አለ፤ ወይ ይጠላል፤ ወይ ይወድዳል - ይላሉ የስነ ግጥም ሂስ ምሁር የሆኑት ኤስ ኤች በርተን፡፡ ይህ ግን ገና ድስቱ ምድጃ ሲነካ ነው፡፡ ደጋግመው ሲያጣጥሙትና፣ የቅመማውን ስልትና ይዘት ሲያጤኑ የሰውም ልዩነት፣ የጥበብም ቃና በጣም ይለያል፡፡
ግጥምን Good and bad በማለት አሊያም “Great, Good and bad” በማለት ሒሊየርና ፔረኔ ይለዩታል፡፡ የመጀመሪያው ግን እንዲህ ብለን ባንከፍለው በተሻለ ነበር ይሉናል፡፡ እንደገና “Major” “Minor” ስለሚባሉ ገጣሚያን ያወራሉ። እኛ ሀገር ገጣሚ አይደለሁም የሚል ሰው ስለሌለ፣ አንገታቸው ቀና ያለ፣ ዓይኖቻቸው ሕይወት መዝነው ስንኝ ጠርበው፣ የዜማ ቀለም የቀቡትን መለየት ከባድ ነው፡፡ የመጽሐፉ ብዛት የትየለሌ ነው (መጽሐፍ ካልነው) አንዳንዴም ነፍስ ያላቸው፣ የተወለዱና አበባቸው ውስጥ ፍሬ ያዘሉ ቀንበጦች ሳይታዩና ሣይጤኑ እንደ ሕልም ያልፋሉ፡፡ እናም በግልቦች ተርታ ሲወድቁ ስሜታቸው ይጐዳል፡፡ ውስጣቸው ይቀዘቅዛል፡፡ ከዚህ ለማዳን ብጥርጥር ያለ ሂስ ለመሥራት ጊዜውና ሁኔታው ባይፈቅድ እንኳ ፍካታቸውን ለአደባባዩ፤ ቁመናቸውን ለተደራሲ መሸሸግ አግባብ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህም መፃሕፍት ቤት በገባሁ ቁጥር ስለ ግጥም ልቤ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ አንዳንዶቹን በጨረፍታ አይቼ ቤት ሰልፍ ላይ ያስቀመጥኳቸውም ጥቂት አይደሉም፡፡ ይሁንና ግን ደግሞ ተስፋ ያነቦጡ አሉ፡፡ ለምሣሌ የትዕግስት ዓለምነህን የግጥም መጽሐፍ ሳየው፤ ሽፋኑ እጅግ ዘግንኖኝ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ በተገኘው መጽሐፍ ላይ (ሳይመርጡ) አስተያየት ለሚሰጡ ሰዎች ያለኝ እምነት ዝቅተኛ ስለሆነ ጀርባውን አይቼ እንደዋዛ አልፌው ነበር፡፡
የትዕግስት ጥራዝ ግን፣ ነፍስ የሚኮረኩሩ ማማሰያዎች አሉት፡፡
ምሣሌ ገፅ 25 “ጥሪ” የሚለውን ግጥም እነሆ፡-
የተሳሰሩበት ማገርና ፍልጡ፣
 የተቀጣጠለው ላልቷልና ምጡ፤
በጭድ ያልተቦካ፣ የመረሬ ልጥፍ ምርጉ እየወደቀ፤
ሰንበሌጥ  ክዳኑ፣ በድንገቴ ነፋስ ተመዞ እያለቀ፣
አዝምማለችና ያረጀች ጐጇችን፣
በቁር በሐሩሩ ከመበተናችን፣
 ጭቃውን ረግጠን፣ ቋሚና ወጋግራ በልኳ ተጠርቦ፣
ምሰሶዋ ሳይወድቅ፣ ትጠገን ቤታችን፣ እንውጣ በደቦ፡፡
ግጥሟን ሙሉዋን የወሰድኳት፣ እንዴት ተሽሞንሙና የተጠረበች እንደሆነች አይተን - እንድናጣጥማት ነው፡፡   
ዜማና ምት ብቻ አይደለም - የሀሳብ አወራረዱና ቅርፁ ሁሉ ሸጋ ነው፡፡ ቁምነገሩን ጭብጡን ስታዩት ሁለንታዊ (Universal) ነው፤ ለሀበሻ ብቻ አይደለም፤ ለሌላውም የሰው ዘር ይሆናል፡፡ ጐጆ ያልሠራ፣ ወይም የማይሠራ የለም፡፡ እንደተምሣሌት - ስታዩት ደግሞ ጀርባው ላይ ያለው ሥዕል፣ ውስጡ የደበቀችው ጥላ፣ ምናባዊ አቅምዋን የሚያሳይ ነው። ሼክስፒርን የማይበርድ የጥበብ እሣት ያደረገው የጭብጡ ትልቅነት እንደሆነ ግጥምን የተነተኑ ሁሉ መሥክረውለታል፡፡
“ስቆርጠው” የሚለው የትዕግስት ግጥምም እጅግ የሚመስጥና የሚመነዘር ነው፡፡
አንድ ሁለት ስንኞችን ብቻ ልውሰድ፡-
የልብህ መሬቱ ጭንጫ ነበር ለካ፣
ሥር አልይዝ ብሎኛል የተከልኩት ዋርካ።
 የልቡን ሚዛን ተመልከቱ፤ አስቸጋሪነቱን። ደግሞ የተራኪዋን ገርነት መዝኑት! በጭንጫ ልቡ ላይ፣ የተከለችውን ዛፍ ግዝፈት፡፡ ምናልባት ይህ ዛፍ የእምነት ስራ ነው ዘር እንደመበተን፡፡
ይህ የተከለችውን የፍቅር ዋርካ ስር እንዳይሰድድ ያጠጠረውን ሰው መልሳ እንዲህ ትለዋለች፡- አሁንም ፍቅር እንደ ጐርፍ ውስጧ እየፈሰሰ፡፡
አልሻውም ካልከኝ፤
አላስቸግርህም በፍሬ አልባሙግት፤
ባይሆን አትንቀለው፣
ይሆንሃልና ለርስትህ ምልክት፤
ግን አደራምልህ፣
ቅርንጫፉን ሁሉ በሆዴ
ከምረው፣ መልምልና ግንዱን
 ለ’ሳቴ እየማገድኩ እንዳልፍበት ብርዱን።
ግርምርም የሚል ነገር ነው፡፡ አሁንም ዛፉ ርስትህ ነው! ማለት፣ እንግዲህ ለሌላ ሰው አይሰጥም ዓይነት ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ የመጨረሻዎቹ መዝጊያ ስንኞች እንዴት ያለ ዜማ ነው ያላቸው!! ብዙዎቹ የትዕግስት ግጥሞች በሙዚቃና ምት ችሎታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡  የብዙ አማርኛ ግጥሞች ሠባራነትና ሽባነት ያለበትን ቦታ እርሷ ተወርውራ አልፋዋለች። ግጥሞቻችንን መርምሩ! ዋናው በሽታ ይህ ነው፡፡
“ጦም አዳሪ” የሚለው ግጥም የሀበሻን ይሉኝታ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
አድምጠኝ የኔ ዓለም…
ከልብህ በራፍ ላይ ለወራት ቆሜአለሁ፣
ስትከፍት ስትዘጋ፣ ስትዘጋ ስትከፍት፣ ዛሬም አይሃለሁ፡፡
ተወው አንዳከም ሐበሻነት ክፉ፣
ነይ ግቢ እስካላልከኝ፣ አላልፍም ከደፉ፡፡
ተራኪዋ ግብዣ ትጠብቃለች፣ ተፈቃሪው ራስዋ ትምጣ ይላል፡፡ ይተያያሉ፣ ግን ውሣኔ እንደውሻ በባህል ሰንሰለት ተጠፍሯል፡፡ በ “ባቢሎን በሳሎን” ኮሜዲ ቴአትር ላይ ባልና ሚስቱ ልባቸው እየተፈላለገ፣ በይሉኝታ ሳሎናቸውን አጥረው፣ በስቃይ ነፍሳቸው ተንጠልጥላ እንደምትቃትት አይነት ነው ነገሩ! እነዚህ ግን ገና አልጀመሩም። ይህንን ነው ገጣሚዋ የምትሸነቁጠው። በዚህ መሃል ደግሞ ነጣቂ ቢመጣ፣ ስሜት ቢላላ፣ የዕድሜ ልክ ፀፀት ነው፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው “እልልታና ሙሾ”ም የሚመረጥ ግጥም ነው፡፡
 አጠር ያለ ስለሆነም ለማየት ይቀላል፡፡
ደብቆ ’ሚያፋልግ ገድሎ የሚያረዳ፣
ከጐን ያለ መስሎ ሸምቆ’ ሚከዳ፣
ሙሾ እያወረደ፣ ያዞ እንባ እያነባ፣ ለምትጨፍር ነፍሱ፣
ዋይታዬን በ’ልልታ፣ ለውጦ
ሲያሰማት የስላቅ መንፈሱ
በረገዳችን ውስጥ ደስታው እንዳለፈ፣
የበደሉ አለንጋ እጄ ላይ አረፈ፡፡
እንቀጠቀጣለሁ! አርባ ልግረፍ መቶ፣
የሚበይንልኝ ፈራጄ ዘግይቶ  
እዚህ ግጥም ላይ መሠሪነትና ብቀላ አይን ላይን ተፋጥጠዋል፡፡ ተበቃዩ ወገን ግን ዳኛ ነው የሚፈልገው። ይኸ ዳኛ ከየት ይሆን…የሚመጣ!መዘግየቱ ሩቅነትን የሚጠቁም ይመስላል፡፡
ትዕግስት ብዙ በሽታዎችንና ግሣንግሥ ችግሮቻችንን ከነጥቀርሻቸው ታውቃቸዋለች። ከላይ የሚለብሱትን የበግ ለምድም ከቀበሮዎቹ ገፍፋ የማየት አቅም አላት። ግጥሞችዋ ማህበራዊ ሒሶች ይበዟቸዋል፡፡ “ገመና” የምንላቸው ሽንቁሮቻችንም ከአይኗ አልተሰወሩም። ፈልፋይና ቅንዐት (Zeal) ያላት ናት፡፡ ለብቻቸው ሞቀን ብለው፣ እሾህ ያንገበገበውን የሚረሣ ነፍስ የላትም። “ምናልባት “ሀገርህን ጥላት ልጄ” የሚል መጽሐፍ የፃፈውን ወጣት ደራሲ አይነት ነገር አይቼባታለሁ፡፡
ጆሮዎችዋ ወደ ውስጥም ወደ ውጭም የሚያዳምጡ ይመስላል፡፡ ግጥሞችዋ ከአንድ ሰሞን ወረት ያፈሠቻቸው አይደሉም። በሰው ልጅ ፍቅር የነደዱ ልቦች ላይ የከሰሉ ማዲያቶች ምስል ናቸው፡፡ ሳቆችዋ ይጣፍጣሉ፣ እንባዎችዎ አንገት ይነቀንቃሉ፡፡
ግጥሞቿ፤ እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል ላይ ላዩን አይነድዱም፤ ሥር ገብተው የልብን እምብርት ይቆነጥጣሉ፡፡ እንደ ጉንዳን ደም ውስጥ ይሄዳሉ፤ እየቆነጠጡ፡፡
ገጣሚዋ ትልልቅ ጭብጦች እጅዋን ሞልተውታል፣ ብዕርዋን ውጠውታል። ጥቅል ሰው፤ ሀገር፣ እና ያገር ሰው ጭብጦችዋ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ጉዳዮችዋ መሣጭና ቆንጣጭ ናቸው፡፡ “አዬ ኢትዮጵያዬ!” ብላ ሀገርዋን በቁልምጫ እየጠራች፣ ችግሯን የተጋራቻትን ግጥም ቀዳዳችሁ አንብቡት፤ ደጋግማችሁ፡-
“ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፣
የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ”
እንዲል ባለቅኔው ዕጣ ክፍልሽ ሆኖ፣ ይዘሽ እንደ ሲቃ፣
እንባሽ ወደ ውስጥሽ፣ መፍሰስ መንቆርቆሩ ዛሬም አላበቃ፡፡
ከልጅሽ ገዳይ ጋር፣ ድንኳን ተጋርታችሁ ደረት እያደቃሽ፣
 ማን ያባብልሻል አንቺም እሱም አልቃሽ፡፡
…እያለች ትቀጥላለች፡፡ በአንድ ድንኳን ውስጥ የሚጤሰው ጢስ ሀገር ይሞላል፤ ዘመን ይበላል፡፡ ደም አለ፣ ጐሚ አለ። በቅደም ጠቃሽ (Allusion) ጀምራ ወደ ሀገሯ ጐራ ስትል የተሸረጠ ነጠላ፣ አንገት የሚበላ ነጭ ክር፣ ጉሮሮ የሚፍቅ እህህታ፣ አንጀት ላይ የሚያነድ /ቁጭት ይታያል፡፡
እድርተኛ የሌላት ሀገር አታሳዝንም? ፊቷ ላይ ማዲያት ካርታ መሥራቱ እርግጥ ነው? የአልቃሽ አስለቃሽስ ጉዳይ? ግጥሞቿ የፍም ኮረት ናቸው!! የሀሳባቸው ወላፈን ያቃጥላል ታዲያ ልብ ላለውና ልብ ሊገዛ ለወደደ ነው።
“መንገድ ዐይኑ ይፍሰስ!” ትላለች በሌላ ግጥሟ፡፡ ጥቂት ስንኞች እንይ:-
አሸዋው ገደል ነው፣ እግርህን
ቆንጥጦ አያስቀርልህም፣
መንከው ያ ባሕር ማዕበል ደብቋል፣ አያሻግርህም፤
ዛሬ እንደወሰደህ ነገ አይመልስህም፡፡
 መሄጃውን ብቻ ድልድዩን አፍርሰው፣
እንዴት ባክኖ ይቅር ኖሮ ያላየ ሰው፡፡
እዚህም ጋ ጠቃሽ ዘይቤዎች ተጠቅማ፣ትናንትን ከዛሬ ጋር አቆራኝታ ለሰው ልጅ ለወገኗ በሚንገበገብ ልብ ትቃትታለች።
 መዘርዘር አያሻም፡፡ ካልተዘረዘረ አይገባም ግጥሟ፡፡ በመቶ በመቶ ደፍና ስንኞችዋን አሳብጣቸዋለች። ወደ ሃምሣ ከፍሎ ከዚያም ወደ አሥር ከዚያም… ከዚያም… እያሉ መውረድ ነው፡፡ ከግጥሞቿ ቅጥሮች ወዲያ ያሉት ትልልቅ ጥላዎች፣ ይህንን የሕይወት ዑደት ለማድመቅ ዙሪያቸውን የከበቧቸው መለከቶች፣ ነፍሳችንን የሚነዝሩት የበገና ቅኝቶች ብዙ ናቸው፡፡ እኔ ጥቂቱን ላመል አነሳሳሁ እንጂ በርካታ ግጥሞችዋ ውብና ሚዛን ደፊ ናቸው፡፡
ለደሴት ልቦች አጋር፣ ለባቡ ነፍሶች ከንፈር መጣጭ ናቸው ግጥሞቿ! ከረጅም ዓመታት በፊት መቅደስ ጀንበሩ በ“ንባስል” ለጠወለግነው ፍካት፣ አንገት ለደፋነው የሩቅ ሕልም ጠቁማን ነበር፡፡ ትዕግስት ደግሞ እንደ አልማዝ የሚቆፈር ውበትና እውነት አጭቃለች፡፡ ተምሳሌታዊነቷም የትየለሌ ነው።


Read 1115 times