Saturday, 05 February 2022 12:08

ግራ የሚያጋባው "የፒጃማ ቀን" በት/ቤት

Written by  ብርሃኑ አሰፋ በላቸው
Rate this item
(1 Vote)

  "የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው" እንዲሉ፣ በመዲናችን አንድ ትምህርት ቤት "የፒጃማ ቀን" መከበሩን ሰምቼ  ግራ ተጋባሁ፡፡ አሰብኩ፣ አሰላሰልኩ ግን ዓላማው ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ይሄ እንግዳ ነገር የተከናወነው ቦሌ አካባቢ ነው፡፡ በጉዳዩ ዙርያ ወላጆች በሁለት ጎራ ተከፈሉ፡፡ አንደኛው ወገን #ምን አለበት! fun ነው; ብለው ለልጆቻቸው ፒጃማ ገዝተው፣ ከቤት እስከ ት/ቤት በፒጃማ እንዲሄዱ፣ ከዚያም በት/ቤት ውስጥ በፒጃማ እንዲውሉ ፈቀዱ። በሌላኛው ወገን ያሉት ደግሞ "ትምህርት ቤቱን መለወጥ ባንችልም ልጆቻችንን እንጠብቃለን" ብለው ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት አስቀሩ፡፡ በሁነኛ መሰረት ላይ የተገነቡ ካልሆነ በስተቀር በቤት የቀሩት ተማሪዎች በቀጣይ ቀን ከሌሎች ጋር ሲቀላቀሉ ለአቻ ግፊት ጫና (Peer pressure) መዳረጋቸው አይቀርም፡፡ ይህም የወላጆችንና  የልጆችን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል፡፡
ፒጃማ የለበሱት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሲሆኑ በእለቱ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ፎቶ ተነሱ፤ እነሱ እንደሚሉት፤ “fun” አደረጉ - ተዝናኑ፡፡ ከዚያም ከቀኑ ስድስት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ለመሆኑ ምን ያህሉ ወደ ቤታቸው ተመለሱ? “fun” እንዲያደርጉ ሌላ አማራጭ የለም ወይ? ለመዝናናት የፒጃማ ቀንን ማክበር ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በተለይ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ትምህርት በተስተጓጎለበት፣ ተፈታኝ ተማሪዎች  ማካካሻ በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት የፒጃማ ቀን ለማክበር ጊዜ መገኘቱ ጥያቄ ያጭራል፡፡
"የፒጃማ ቀን" ታሪካዊ ዳራ
የፈረንሳዩ ፋሽን ዲዛይነር ፖል ፓይሬት እ.ኤ.አ በ1911 ነበር፣ የፒጃማ ቀንን ያስተዋወቀው፡፡ “It happened one night” የተሰኘው ፊልም ደግሞ የተለያዩ ዲዛይኖች ያሉት ፒጃማ እንዲተዋወቅ በር ከፈተ፡፡ በተማሪዎች የፒጃማ ቀን ከሚከናወኑት ኹነቶች መካከል፡-
ቀኑን ሙሉ በፒጃማ መዋል
ትምህርት ሰጪ ፊልሞች ማሳየት
ስለ እንቅልፍ ማስተማር
በሆስፒታል ለሚገኙ ልጆች ገቢ ማሰባሰብ ናቸው፡፡
ከላይ ለቀረቡት ቅን የሚመስሉ ዓላማዎች ለምን ፒጃማ ማስለበስ ተፈለገ ? ስውር የውስጥ አላማ ከሌላቸው በስተቀር፡፡ የኛዎቹ ግን ገቢ አላሰባሰቡም፤ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ፎቶ ተነሱ እንጂ። ይህ ሲሆን ደግሞ ታናናሾቻቸው ተመልክተዋል። ከዚህ ምን ይማራሉ?
የፒጃማ ቀን በምዕራባዊያን ዘንድም ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ለአብነትም በአሜሪካ ኢሊኖስ ተማሪዎች ፒጃማ ለብሰው ትምህርት ቤት መግባት እንደማይችሉ ህግ ወጥቷል፡፡ ለዚህም ምክንያት የሆነው በበይነ መረብ (Zoom online ) ፒጃማ ለብሰው ትምህርት መከታተላቸው ቁጣ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው፡፡ እናም በርቀት በበይነመረብና በአካል የትምህርት ጊዜ የአለባበስ ደንብ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በቀን ፒጃማ መልበስና ስነልቦና
የሃርፎርድሺር ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ካሬን ፒኔ እንደሚሉት፤ አለባበስ የአእምሮ አስተሳሰብን የመለወጥ አቅም አለው፡፡ ፕሮፌሰሯ “Mind What You Wear: The Psychology of Fashion” በሚለው መፅሐፋቸው፤ የሱፐር ማን ምስል ያለው ቲ-ሸርት የለበሰ ተማሪ ራሱን ከሌሎች ተማሪዎች የበላይ አድርጎ የማሰብ ስነልቦናዊ ውቅር አለው። እንደ ፕሮፌሰሯ ከሆነ፤ ተማሪዎች በልብሶቻቸው ስሜቶቻቸውንና አመለካከቶቻቸውን ይገልፃሉ፡፡ ልብሶች የማንነት መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት መሆን የሚፈለገውን የመቅረጽ አቅም አላቸው፡፡ እናም የለበስነውን የመሆናችን እድል ሰፊ ነው ይላሉ፡፡
የኖርዝ ካሮሊና ኒውፖርት ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ጄኔፈር ዱራጎንቴ፤ የሌሊት ልብስ የሆነውን ፒጃማ በቀን መልበስ አሉታዊ ተፅኖ አለው ይላሉ፡፡ በጥናት እንደተረጋገጠው፤ ፒጃማ በቀን መልበስ የስራ ውጤታማነትን ይቀንሳል፣ በራስ የመተማመን አቅምን ይሸረሽራል፣ የእንቅልፍ ልማድን ያዛባል፡፡
የባህል ጦርነት?
የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጦርነት ብቻ ሳይሆን የባህልም ጦርነት አለ፡፡ ይህም ያለንን መልካም ባህል ቀስ በቀስ በማስጣል ሌላ እንግዳ ባህልን በማስተዋወቅ ይገለፃል። ፒጃማን በአደባባይ መልበስ እንግዳ ልምምድ ነው፡፡ ፒጃማ የሌሊት ልብስ ነው፡፡ ቁምጣ ሊሆን ይችላል፤ ስስ ነው፤ ገላን ሊያሳይ ይችላል፡፡ እናም ተማሪዎች ይደሰቱ ይዝናኑ ተብሎ ትምህርት ቤት ፒጃማ እንዲለብሱ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ፒጃማ የለበሱ ተማሪዎች ከዚያ ምን እንዲያደርጉ ነው?
በጉዳዩ የተብሰለሰሉ አንድ ወላጅ፤ "ነገ ደግሞ Sleepover with pajama” ይመጣል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።  እኔም ይህንን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ልጆቻችን በሥነምግባር የሚታነጹበት ሥፍራ እንጂ ናይት ክለብ አይደለም፡፡ እናም ጉዳዩ ወደ ከፋ ደረጃ ሳይደርስ ከወዲሁ እልባት ሊያገኝ ይገባል እላለሁ፡፡ ሰላማችሁ ይብዛ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በ#Holistic Child Development; የሁለተኛ ዓመት የማስተርስ ተማሪ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 5652 times