Saturday, 29 January 2022 00:00

ESOG…የስነተዋልዶ ጤናን ለማሻሻል ድጋፍ አደረገ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው እትም ግጭት በሚከሰትባቸው ቦታዎች የስነ ተዋልዶ ጤና ምን ያህል አስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚደርስ አስነብበናችሁዋል፡፡ ጦርነት በሚደረግባቸው አካባቢዎች ለአጠቃላይ የጤና ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት ችግር የሚኖር ሲሆን በተለይም ሴቶችና ልጃገረዶች በስነተዋልዶ ጤና ጉዳይ አስከፊ ሁኔታ ላይ መውደቃቸው ምንም ጥርጥር የለውም የሚለው የዛሬው ምንጫችን ኬር ኢትዮጵያ April 04, 2021] እና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ድረገጽ ነው፡፡  
ግጭት በሚኖርባቸው አካባቢዎች የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም።  የእናቶችና ጨቅላ ልጆቻቸውን ደህንነት በሚመለከት አገልግሎት መስጠት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ እና አደገኛ የሆኑ የወሲብ ባህርይዎችን መከላከል ከባድ ይሆናል፡፡ የስነተዋልዶ ጤናን እንዲጠበቅ ማድረግ በተለይም ለሴቶች የሰብአዊ መብትን ከማክበር ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህንን መብት አለምአቀፍ አካላት የተቀበሉትና በአለምአቀፍ ግብ እንዲሟላ ስምምነት የተደረሰበት እንዲሁም የሚተገብሩት ነው፡፡ ነገር ግን በሚነሱ ግጭቶች ሳቢያ ይህ መብት ስለሚሸራረፍ በአለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም አባል ሀገራት የስነተ ዋልዶ ጤናን በማሟላት እስከ 2030 ድረስ የሚጠበቀውን የእናቶችንና ጨቅላዎችን ሞት በእጅጉ መቀነስ የሚለውን ግብ ለማሳካት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
ሴቶች፡-
ሴቶች ቤታቸውን ለቀው ከወጡና ከብዙ ሰዎች ጋር በአንድ ካምፕ እንዲቀመጡ ከተገደዱ ድርብ ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ የምግብ እጥረት፤ የጤና ችግር፤ የአእምሮ መረበሽ እና ፍርሀት፤ ጭንቀት፤ ድብርት፤ በቅጡ የመተኛት ችግር፤ ስለራሳቸው ደህንነት ጥንቃቄ ማድረግ አለመቻል ይከሰታል።  ወደሚያርፉበት አካባቢ ለመሄድ በመንገድ ላይ እያሉ ወይንም ከሚያርፉበት ቦታ እንደደረሱ ልጅ ለመውለድ የተገደዱ ሴቶች ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ልጃቸውን ያጡም አሉ፡፡ ጠለፋ ሌላው በሴቶች ላይ የደረሰ ችግር ነው፡፡ በድንገት በሚሰነዘረው ግጭት ሳቢያ እግር ወዳ መጣበት ሽሽት ሲኖር ከቤተሰብ እንዲሁም ከልጆቻቸው የሚለዩ ሴቶች እና ልጃገረዶች አሉ፡፡  
ልጃገረዶች፡-  
ልጃገረዶች በስደት ወቅት የሚደርስባቸው ችግር እንደማንኛውም ሰው ከምግብ እጥረት ይጀም ራል፡፡ የትምህርት መቋረጥ፤ ረሃብ፤ ሞት የመሳሰሉት ችግሮች ይደርስባቸዋል። በተጨማሪም ከቦታ ቦታ በሚደረገው ስደት ከበድ ያሉ እቃዎችን መሸከም ሌላው በጤናቸው ላይ ችግር ሊያስከትል የሚችል ጉዳት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሚደርስባቸው ተገዶ መደፈር እና ወሲባዊ ጥቃት መፍትሔ ያልተሰጠው እና ለቀጣይ ችግር የሚዳርጋቸው እንደሚሆን ይጠበቃል፡ ያልተፈለገ እርግዝና፤ ለሕመም መዳረግ፤ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስን ማቋረጥ የመሳሰሉት ችግሮች በወደፊት ሕይወታቸው ሊያጋጥሙአቸው ይችላሉ፡፡ በሌሎች አገሮች እንደታየው ከሆነ በዚህ መንገድ ሕይወታቸው የሚሰናከልባቸው ልጃገረዶች በተለያዩ ከተሞች ወደ ልመና የሚገቡ፤ የሴተኛ አዳሪነት ስራን የሚቀላቀሉ፤ በቤት ሰራተኝነት የሚቀጠሩ መኖራቸው አይካድም፡፡
በኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በአማራና አፋር የሚሊዮኖች ሕይወት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መውደቁ እሙን ነው፡፡ በተለይም ሴቶችና ልጃገረዶች በበለጠ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ኬር ኢትዮጵያ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አረጋግጦአል፡፡ ስለዚህም አስቸኩዋይ መፍትሔ እንደ ሚያስፈልግ ለንባብ ባለው ጽሁፍ ላይ ጠቁሞአል፡፡
በተከታይ የመረጃ ምንጫችን የሚሆነው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር መረጃ ድረገጽ ነው፡፡ ESOG ከአዋላጅ ነርሶች ማህበር እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በግጭቱ ወደተጎዱ አካባቢዎች በመድረስ ጉዳቱ የደረሰባቸው ሴቶችና ልጃገረዶች የስነተዋልዶ ጤና ለመጠበቅ የሚያስችል ድጋፍ አድርገዋል፡፡   
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ለደሴ ሆስፒታል እ.ኤ.አ ዲሴምበር 25/2021 100 የሚሆኑ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን አበርክቶአል። ይህ ድጋፍ በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ለተፈናቀሉ አካባቢዎች ከሚደረገው አስቸኳይ ምላሽ አንዱ የሆነውን ድጋፍ ሲያስረክብ በአካባቢው የሚገኙ ሴቶች የጾታ ጥቃት ችግሮችን ለመቋቋም እንደሚያስችል ታምኖበት ነው። ድጋፉ የአፋር ክልልንም የጨመረ ሲሆን በአፋር ከልዋን እና ጭፍራ ያሉ የጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ችግርም ቡድኑ ተመልክቶአል፡፡  
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በአሁኑ ወቅት የተደረገው ድጋፍ በቀጣይነት one stop center የተባለውን ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴት ልጆች በአንድ ተቋም የስነ ልቡና፤ የህግ፤ እና የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን ተቋም መመስረትን አላማው ያደረገ መሆኑ ታውቆአል፡፡ ለዚህም ስራ በኃላፊነት የተቀመጡት በአገልግሎታቸው ምስጉን የሆኑት ዶ/ር የሱፍ አህመድ ናቸው፡፡ ዶ/ር የሱፍ በደሴ ሆስፒታል በከባድ የፀጥታ ሁኔታዎች ውስጥ ማህበረሰቡን ማገልገል የቀጠሉ ጀግና የህክምና ባለሞያ ሲሆኑ ባልተሟላ ሁኔታ እስከ december 25 ድረስ በ15 ቀናት ውስጥ ወደ 200 የሚደርሱ ሴቶችን በማዋለድ ለተጎዱ የመድረስ ጥረቱን ያሳዩ ባለሙያ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ግጭት በተካሄደባቸው እና በስደት ምክንያት የስነተዋልዶ ጤና ችግር ለደረሰባቸው አካባቢዎች የሚሰጠውን ድጋፍ የአማራ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አባተ እና ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪ ሞች ማህበር ወደስፍራው ያቀኑ ባለሙያዎች በኮምቦልቻ፤ ሐይቅ፤ መርሳ፡ ኮቦ፡ሸዋሮቢት፤ አጣዬ እና ወልድያ ላይ እና ሌሎችም ጋር በወቅቱ ያለውን ችግር በሚመለከት እና ወደፊት ምን ማድረግ ይገባል የሚለውን ውይይት አድርገዋል፡፡  
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞቸ ማህበር በደረሰው ግጭት እና ስደት ምክንያት በሴቶች ላይ የደረሰባቸውን ጾታዊ ጥቃት እና በአቅራቢያቸው ያሉ የጤና ተቋማት ያሉበተን ሁኔታ የተመለከተ ሲሆን ለዚህም ተገቢውን እርዳታ ለማድረግ በአማራ ክልል በደብረብርሀን፤ ሸዋ ሮቢት፤ ኮምቦልቻ፤ ደሴ እና ወልድያ እንዲሁም በአፋር ሁለት አካባቢዎች ላይ one stop center የተባለውን ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴት ልጆች በአንድ ተቋም የስነልቡና፤ የህግ፤ እና የህክምና አገግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ተቋም ለመመስረት ተስማምቶአል፡፡
ESOG ከሚሰጠው ድጋፍ ጎን ለጎን የእናቶችና የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት በተመረጡ የጤና ተቋማት ለመጀመር ዝግጁ ሲሆን one stop center በደብረብሀን ሆስፒታል mid-December, 2021. ማለትም ባለፈው ወር መጀመሩን መረጃ ያደረግነው የኢሶግ ሪፖርት ይጠቅሳል፡፡ ESOG የጤና አገልግሎት ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ በተመረጡ ጤና ጣቢያዎች የማቴሪያል እና መልሶ የማቋቋም ስራም እየሰራ ይገኛል፡፡ ከተደረጉት ድጋፎች ውስጥ መድሀኒቶች፤ የውሀ መያዣዎች፤ ብርድልብሶች እና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ይገኙበታል፡፡  
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር (ESOG) ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ባሉ የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት እና ውድመት ምን ያህል እንደሆነ በዳሰሳ የተመለከተ ሲሆን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና አብሮ የተጓዘው ቡድን በተሳተፈበት ወደ ፊት ለማስተካከል በምን መንገድ መሳተፍ እንደሚገባ ተወያይቶአል፡፡      
ESOG በፕሬዝዳንቱ ቀጥተኛ ሱፐርቪዥን ስር የሚገኙ ሰራተኞቹ፣ አባላቶቹ እና በጎ ፈቃደኞቹ የተጠያቂነት ድንገተኛ ምላሽ ቡድን አቋቁሟል። የድንገተኛ ጊዜ ምላሽ ቡድኑ በተከታታይ ግምገማና ስብሰባዎችን በማካሄድ GBV በጾታዊ ጥቃት ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ የሚውል ቁሳቁስ እና የጤና አገልግሎቶችን በተመረጡ የጤና ተቋማት ለማጠናከር የሁለትዮሽ እቅድ አውጥቷል፡፡
ESOG በተጎዱ አካባዎች ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎችና ጾታዊ ጥቃትን በሚመለከት ላደረገው ድጋፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅናን ሰጥቶታል፡፡ በተለይም የእናቶችን ደህንነት ማረጋገጥን በሚመለከት የተለያዩ የድጋፍ እንቅስቃሴዎች እንዲደረግበት በተያዘው አመታዊ ጊዜ ማለትም January/2022 በተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደረገው የንቃተ ህሊና ማዳበሪያ እና ሌሎ ችም ድጋፎች ጎን ለጎን ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እውቅናን ሰጥቶአል፡፡

Read 2215 times