Saturday, 22 January 2022 00:00

ሚስተር ቢስት 54 ሚሊዮን ዶላር በመከፈል 1ኛው ዩቲዩበር ሆኗል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአለማችን 10 ባለጸጎች ሃብት በዘመነ ኮሮና በእጥፍ ጨምሯል


              ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የአመቱን የዩቲዩብ ከፍተኛ ተከፋዮች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን ሚስተር ቢስት በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው የ23 አመቱ ጂሚ ዶናልድሰን በ54 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የ1ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
በዩቲዩብ የተለያዩ ቪዲዮዎችን በመልቀቅ የሚታወቀውና በአሜሪካና በካናዳ የፋስት ፉድ ዴሊቨሪ አገልግሎት የጀመረው ዶናልድሰን፤ በአመቱ ከአስር ቢሊዮን ጊዜያት በላይ በታዩት ቪዲዮዎቹ ብዙ ክፍያ በማግኘት ባለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት ቁጥር አንድ የዩቲዩብ ተከፋይ ከነበረው የ10 አመቱ ታዳጊ ዩቲዩበር ራያን ካጅ ክብሩን መረከቡን ፎርብስ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
ከቦክሰኝነት ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የተሸጋገረው ጃኪ ፖል በ45 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ 2ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የጌም ፈጣሪው ማርኪፕለር በ38 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
እስከ አስረኛ ደረጃን የያዙት የአመቱ ከፍተኛ ተከፋይ ዩቲዩበሮች በፈረንጆች አመት 2021 በድምሩ 300 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ ይህም ካለፈው አመት የ40 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የአለማችን ቀዳሚ 10 ባለጸጎች አጠቃላይ የሃብት መጠን የኮሮና ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በእጥፍ ያህል መጨመሩን ያስታወቀው ኦክስፋም ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም፤ ወደ ድህነት የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በአንጻሩ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ወረርሽኙ በተቀሰቀሰበት መጋቢት ወር 2020 የአስሩ ቢሊየነሮች አጠቃላይ ሃብት 700 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ተቋሙ፣ በህዳር ወር 2021 ይህ ሃብት ወደ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር ማደጉን የገለጸ ሲሆን፣ 160 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በአንጻሩ ወደ ድህነት መግባታቸውን አመልክቷል፡፡
የገቢ መቀነስ በመላው አለም በየቀኑ 21 ሺህ ያህል ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል ያለው ተቋሙ፣ የቢሊየነሮች ሃብት ግን በእጅጉ እያደገ መሆኑን በመጠቆም ለአብነትም የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤለን መስክ ሃብት በተጠቀሰው ጊዜ በ1000 በመቶ ማደጉን አስረድቷል፡፡


Read 1788 times