Saturday, 22 January 2022 00:00

አሜሪካና እኛ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ - ከቤተ- ሳይዳ ሜሪላንድ፣ አሜሪካ
Rate this item
(4 votes)

ጠ/ሚኒስትራችን ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጋር ተነጋገሩ?
  
              ዜናው ሲፈተት  
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የአሜሪካው 46ኛ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን  ባለፈው ሰሞን በስልክ ተነጋገሩ የሚባለውን ዜና እዚህ ዋሽንግተን የምንገኘውም ከሰማነው በሁዋላ  ጥሞና ይዘናል፡፡ እርግጥ  ነው ዜናው ፈታ አድርጎናል፡፡ በውጭው ዓለም በሰልፍ የወጣንበት፣ አደባባይ የሞላንበት፣ ‘በቃን’ የተባለበት ቁጣ  ‘እጃችሁን ከእኛ አንሱ’ ጥያቄ - ምላሽ አገኘ ልንልም ቃጥቶናል፡፡ ቸኮላችሁ ካልተባለ፡፡ ያ ሰልፍ የተደረገው የአሜሪካ አስተዳደርን ‘አታናግሩን’ ‘አርፋችሁ ተቀመጡ’ ወይም የነጩን ቤተ መንግስት ደጅ ዘግታችሁ - አጥሩን አጥራችሁ ተዉን ብለን ለመጠየቅ ግን አይደለም፡፡ ለአሜሪካ የኢትዮጵያ ወዳጅነት ይሻላታል - እውነቱን ብትሰሙና ብትቀበሉ ይበጃችሁዋልም በሚል እንጂ፡፡ የሚገርመው የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ‘በመመረጥዎ  እንኳንም ደስ ያለዎ’ ሳይሉ የቆዩትና ጀርባ የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስልክ ከ’ጠቅላይ ሚኒስትሩ’ ጋር ተነጋገሩ ሲባል አንድ እግሩን መቀሌ ሌላ ጎኑን ተምቤን ዋሻ  ያደረገውን ቡድን  ‘ኸረ ጉድ ሆንን’ ሳያሰኝ አላለፈም፡፡
በዚያው ሰሞን ሌላ ዜናም ነበር። ለአፍሪቃ ቀንድ የነጩ ቤተመንግስት ልዩ መልዕክተኛ የተባሉት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ከዘጠኝ ወራት በላይ ካገለገሉበት ሀላፊነታቸው የመነሳታቸው ዜና ነው። በእግራቸውም አምባሳደር ዴቪድ ስታደርፊልድ እንደሚተኩም ተዘግቧል፡፡ በቱርክ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ በሳውዲት ዓረብ፣ በሊባኖስ፣ በቱኒዚያና በሶሪያ ያገለገሉ ሲሆን በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የመካከለኛ ምስራቅ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው እንደሠሩ ታውቋል፡፡ ከርሳቸው መተካት ጋር  ቱርክ ለኢትዮጵያ የታጠቁ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ሸጣለች በሚል ዋሽንግተን የከሰሰችበትን ዶሴ በተመለከተ ይበልጡኑ ይገፉበት እንደሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ የሆነው ሆኖ የጀፍሪ ፌልትማን ሚና (የአሜሪካ የፖሊሲ አቅጣጫም)  ከመስኩ እውነታ ጋር በተጻራሪ የቆመበት ሁኔታ ላለፉት ወራት ተስተውሏል፡፡ ፌልትማን የኢትዮጵያም ሆነ የሱዳን ቀውስ እጃቸው ላይ ሲወድቅና ሲሰጣቸው፤ ከፖሊሲው ማሰሮ ውስጥ በግልጽና በስውር እጃቸውን የሚያጠልቁ የመኖራቸውን ሁኔታ ይገምታሉ ብለን እናስብ፡፡  እና የተለያዩ ጥቅሞችን አስልተው ዙሪያ የተኮለኮሉት የሚያደርጉት ግፊት በአፍሪቃ ቀንድ ዙሪያ ዩ.ኤስ አሜሪካ መደናገርና መምታታት ዕጣ ዕድሏ አደረገባት እንዴ? አሰኝቷል። ከቶውንም የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበው እየሆነ ለወሬ ነጋሪ አስቸግሯል፡፡ በዚህ ረገድ በአፍሪቃ ቀንድ የኢትዮጵያ ሁኔታ ተጠቃሽ ነው፡፡
በነጩ ቤተ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ዘወትር ሲመደብ - የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳይ ዘርፉ - ሥራና ሙያቸው ዲፕሎማሲ በሆኑት ሠራተኞቹ ዘንድ ክፈተት ይፈጥራል። የሥራና የሀላፊነት መጣፋትና ባለቤት የማጣት ችግሮችን ይከስታል፡፡ እንደውም አንድ የሀገሬው ጸሀፊ እንዳለው «ፖምና ብርቱካን› ይሆናሉ አሠራራቸው፤ ዱባና ቅል እንደሚባለው አይነት፡፡ የፕሬዚዳንት ባይደን የብሄራዊ ጸጥታ ቡድን (አማካሪውን ጃክ ሰሊቫንን ጨምሮ) ልዩ መልዕክተኞችን ‘ቀውስ ጠገብ’ የሆኑና ‘ለቀውስ ያዘመሙ’ በሚባሉ አካባቢዎችና ጉዳዮች ዙሪያ ልዩ መልዕክተኛ መሰየምና መመደብ የጀመሩት ነጩ ቤተ መንግሥት ገና ጠቅልለው ሳይገቡ ነው፡፡  እና አንዱም የአፍሪቃ ቀንድ ዋነኛው ትኩረት የተሰጠው አካባቢ እንደመሆኑ - ይልቁንም ከአማጽያኑ ጋር ቅርበት ያላቸው ሹማምንትም ስላሉ ጉዳዩን በቅርብ ለመቆጣጠር የልዩ መልዕክተኛ ምደባው ተገቢ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በአፍሪቃ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያከናውነው በዚህ በኩል፣ በልዩ መልዕክተኛ የተያዘው ጥረት ደግሞ በዚያ ሲከወን፣ እርስ በእርስ የመጣረስ አደጋም ሳይገጥመው ግን አላለፈም፡፡ አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በኩል - አቤቱታ ጭምር የሚቀርብበት አጋጣሚ በርክቶ እንደነበረና በአንዳንድ የፖሊሲ አቅጣጫዎችም ልዩነቶች ይፋ የወጡበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለአብነትም በሱዳን ላይ ማዕቀብን በመጣል ረገድ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የአፍሪቃ ጉዳይና በልዩ መልዕክተኛው ፌልትማን ይፋ የወጣ ክፈተት ተፈጥሮም ነበር፡፡ 
 የአሜሪካ የፖሊሲ አቅጣጫ
በዩ.ኤስ አሜሪካ የተመረጠበት የጊዜ ገደብ ያገለገለው አስተዳደር ለተተኪው ተመራጭ ሲያስረክብ ብዙውን ጊዜ በውጭ ፖሊሲ ዙሪያ ብዙም የተለያየ አቋም ለወዲያው አይታይም ነበር። ይሁንና ከፕሬዚዳንት ትረምፕ ወደ ፕሬዚዳንት ባይደን በሚተላለፍበት ወቅት ላይ በኢትዮጵያ በተከሰተው ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ተቃርኖ  የተስተዋለበት ነበር። ለሰሜኑ የሀገራችን ግጭት ዋነኛው ምክንያት የቀድሞው የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለሰሜኑ የሀገራችን ግጭት ዋነኛ ምክንያት የመቀሌው ትህነግ (ህወሐት) እንደሆነ ይፋ አቋምና መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ድርጊቱንም በይፋ የኮነነበት ዜና አለ፡፡ በርክክብ ላይ የነበረው የፕሬዚዳንት ባይደን ስብስብ ግን የተለየ አቋም ያሳየው ያኔ ነበር፡፡ የሁዋላ ሁዋላ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ የሆኑት ጃክ ሰሊቫንን ጨምሮ ሌሎችም ‘አማጽያኑንና መንግሥትን’ አንድ መደብ ላይ ያስቀመጡበት ንግግር ጭምር ተሰማ፣ የፖሊሲ አቅጣጫውም ከእውነታው የተፋታ እንደሆነ ወዲያው ተስተዋለ፡፡ 
ከመስከረም 11 (Sept. 11) ጥቃት በሁዋላ በዩ.ኤስ የውጭ ፖሊሲ ቀዳሚ ትኩረት የነበረው የፀረ ሽብር ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በ45ኛው ፕሬዚዳንት ትረምፕ ዘመነ ስልጣን ደግሞ ‘ቀዳማይ አሜሪካ’ (America First) በሚለው እሳቤ እየተተካ የመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ የእርሳቸው ስልጣን በአራተኛው ዓመት ላይ ሲገባደድ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ባይደን ደግሞ የውጭ ፖሊሲ አቅጣጫቸው - የቻይናን ግስጋሴና ሩሲያን ጨምሮ የሪጅናል ሀይሎችን ሚና ማለዘብ የሚል ሆነ፡፡ የፖሊሲው ቀዳሚ የመተግበሪያ መነሻም ይኸው ሲሆን ከዚህ ጋር የተሰናሰሉ አካሄዶችን አብረው ይቀናጃሉ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያንና አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርን በቻይና ሳምባ የሚተነፍስ ለማስመሰል የሚደረገው ግፊትና ጥረት የጀመረውም ቀደም ብሎ ነው። የህወሐት ደጋፊ የ’አሜሪካ’ ሹማምንትም ስውር አጀንዳቸውን በዚህ ሸብልለውና ለብጠው ለማቅረብም ሳይሞክሩ አላለፉም። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን የርዕሰ ሀያሏና የቻይናና ሌሎች አውደ ግንባር የማድረግ ሴራም ተጠንጥኖበታል፡፡ እንደውም አሜሪካ ‘ተሸነፈች’ የሚል አንድምታ እንዲይዝ ለማድረግና ወዳልታሰበ አቅጣጫ - (ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ጨምሮ) ለመግፋትም ተሞክሯል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ባልተጠበቀ ሁኔታ ጠላቶች በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሴሩትንም ያከሸፈበትን አጋጣሚዎችን ፈጥሯል፡፡
ለዚህ አስረጂ የሚሆነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የነበረው የህግ ማስከበር እርምጃው የተከናወነበት ጊዜ ነበር። ህወሐት በውጭ ያቀነባበረው ትርክት የ›ዘር ማጽዳትና ማጥፋት› የሚለው ዘመቻ፣ ቀድሞ ታስቦበት ተዘጋጅቶ የነበረበት ሁኔታ ስለነበረ የኢትዮጵያ መንግሥት መቀሌን ለቅቆ ሲወጣ ያበሳጨው ህወሐትን ብቻ ሳይሆን የባዕዳን ተከታዮቹንም ጭምር ነበር፡፡ ለዚህም አንድም የምዕራብ ዲፕሎማት በመልካምነት የኢትዮጵያ መከላከያ መቀሌን መልቀቁን ‹ይበል› ያለ ያለመኖሩን ያስተውሏል። የኢትዮጵያን መንግሥትን የሚወነጅሉትና በዚያም ሰበብ እጃቸውን ሙሉ ለሙሉ አጥልቀው በጉዳዩ ሊዋኙበት ቋምጠው የነበሩትም ናቸው እጢያቸው ዱብ ያለው፡፡  የ›ዘር ማጽዳትና ማጥፋት› የሚለው የሕወሀት የፈጠራ ትርክት ውል ከውል እንዳይያያዝም ይህ ክስተት ረድቷል፡፡ ሌላው የቅርቡ የመልሶ ማጥቃትና ወደ ትግራይ ያለመዝለቅ ውሳኔ አለ፡፡ አሰፍስፈው የሚጠብቁት ሀይሎች - በየራሳቸው ምክንያት ኢትዮጵያን አውደ ግንባራቸው እንዳያደርጓት - እንደነሊቢያ - እንደነሶርያ እንዳትሆን የእነርሱንም መሰሪ ዕቅድ ያከሸፈ ድርጊት ነው፡፡ ይህ በመስኩ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በዲፕሎማሲያዊው ዘርፍ በተለይ ከዩ.ኤስ አሜሪካ ለተጽዕኖና ለግፊት የዘመቱትን ሳይቀር ‘ችግሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም’ ወደ ሚል አዝማሚያም የገፋቸው እንዳሉ ፍንጮች አሉ፡፡   
 የትህነግ የማንተብ ዘመቻ
ትህነግ በሰሜን መከላከያችን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሩ ጋር በትይዩ ዓለም አቀፍ ድጋፍና በተለይም ዩ.ኤስ አሜሪካንን ወገንተኛ የሚያደርጋትን አሠራሮችን የተለያዩ አጽመ ታሪክ ምስሎችን (Scenario) በመፍጠር ተመጣጣኝ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን፣ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የተደራጁ ተቋማትን፣ ታዋቂ አፍቃሬ ኢትዮጵያ የሆኑትን በተደራጀና በተናበበ ሁኔታ፣ የማህበራዊ መገናኛዎቹንም አንዳች አደጋ እንደመጣ በሚመስል ቅንጅትም የሚተገበሩበትን ሁኔታ ጭምር ወጥኖም ነበር፡፡ ለሀያ ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ እንዳሻው ሲገዛና ሲመዘብር የነበረው ይህ ቡድን፣ ስልጣን ከለለቀበት ጊዜ ጀምሮ በውጭው ዓለም የሽግግሩን ገጽታ በማጠልሸት ረገድ ሰፊ ዘመቻዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ በተመቸውና አገኘሁት በሚለው አጋጣሚ ሁሉ ያከናወናቸውን ወደ ፊት መሰነድ ይቻላል፡፡ አንድ  የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የተከታተለውን አስረጂ ላንሳ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአውሮፓውያኑ ቀመር  በኦሮምኛና በአማርኛ ባደረጉት ንግግራቸው ውስጥ የተካተተ አገላለጽ ነበር። በዚህ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ስርዓት የዘር መድልዎ አፍሪቃ አሜሪካውያንና አይሁድ አሜሪካውያን የደረሰባቸውን በደል የተንተራሰ ማብራሪያ ሲሰጡ በነበረበት ንግግር ውስጥ “ልዩነቱ” ብለው ጀመሩ፤ “ልዩነቱ ጂው (አይሁድ) ከሲቪል ራይትስ በሁዋላ ትንሽ መብት መታየት ሲጀመር ዘፈኑ፣ ግጥሙ. ፊልሙ፣ ድራማው ወደፊት ሆነ፡፡ እንዴት ዓለምን ኮንከር [Conquer] ማድረግ እንደሚቻል ኢኮኖሚክ ፓወር [econmic power] መፍጠር እንደሚቻል ያስባል፡፡ ጥቁር ደግሞ እዚያ ላይ ቆሞ  ትላንት እኮ ገረፉህ ገደሉህ እንዲህ አደረጉህ ይላል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ትላንትና ውስጥ እንዲኖር አደረገው” ይላሉ፡፡ ይህ የእርሳቸው ንግግር በኦሮምኛና በአማርኛ የተነገረ ሲሆን ተተርጉሞና በአግባቡ ተሰናድቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ በመንግሥቱ መዋቅር ውስጥ በባለስልጣንነት ለተሰየሙ የፖለቲካ ሰዎችና የሲቪል መብት ተሟጋቾች ሳይቀር እንዲያውቁት የተደረገበት ዘመቻ ነበር፡፡ ከአፍንጫው ስር ይህ ሲከናወን አንዳችም ማስተባበያና የአጸፋ ምላሸ ያልሰጠው የ’ኢትዮጵያ ኤምባሲ’፤ የትም አይደርስም በሚል ቸልተኛነት ተሸፋፍኖ ነው ያለፈው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ አወዛጋቢና ያልተገባ እንደሆነ ይቆየንና ቢያንስ አስተዳደሩ የዚህን ሀሳብ ደግፎ የቆመ መምሰሉ አደጋው የታያቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያንና የአፍሪቃ አሜሪካውያንን ግንኙነት ማሳላጥና ማጎልበት በሚገባበት ምዕራፍ ላይ ይህን መሰል ህጸጾች መገኘታቸው አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡ ማንም ሊረዳ እንደሚችለው በዩ.ኤስ አሜሪካ ውስጥ ያለው የአፍሪቃ አሜሪካውያን ማህበረሰብ በተጽዕኖው (በሁሉም ዘርፎች) ከፍ ያለ ነው፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ፕሬዚዳንት እስከ ማስመረጥ የደረሰ ጠንካራ ማህበረሰብ ነው፡፡ የጥቁር መብት ታጋዮች በትግላቸው ባበሩት ቀንዲል - ባፈሰሱት ደምና አጥንትም ነው ዛሬ ከአፍሪቃ ፈልሰን ለመጣን ስደተኞች ታዛና ነፃነት በዚህች ምድር ያገኘነው፡፡
ወደቀደመው ጉዳያችን ስንመለስ - የሕወሃት ቡድን ባለፉት ሦስት ዓመታት በማግባባቱና አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደርን የማቃረን ሥራዎችን ሲሠራበት የነበረበትንም ሁኔታ ለማሳየት ነው ምሳሌው የቀረበው፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ጥበብና ሥራ ያሻል
የዲፕሎማሲው ዘርፍ ትኩረት የተነፈገው እስኪመስል ድረስ ላለፉት ሶስት ዓመታት ቆይቷል፡፡ የማግባባትና ብሄራዊ ጥቅምን ያሰላ አካሄድ ሳይሆን - የግል ጠብ ወይም ቅራኔ ይመስል ‘ፈግጭው - ፈግጠው’ አይነት ሰልጥኖ እንደነበር ታዝበናል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በዲፕሎማሲ ጥበብ ሀገራዊ ፋይዳዎችና ጥቅሞች የተጠበቁበት የተከበሩበት ሁኔታን መለስ ብለን ማየት ይገባናል፡፡ በቅርብ እርቀት እንኳን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከፋሽስት ጣሊያን መባረር በሁዋላ እንግሊዝ በሞግዚትነት ለማስተዳደርና ይዞታዋን ለማስፋትና ለማራዘም ባሰላችበት ጊዜ እጅግ በረቀቀ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እንዴት የአሜሪካንን አጋርነት ኢትዮጵያ መጠቀም እንደቻለችና ውጤታማ እንደሆነች መመልከት ይገባል። በተለይ ዛሬ እርስ በእርሷ በተቆላለፈችው ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥበቧን በትጋት መጠቀም አለባት፡፡      
ይህ ሁሉ ሲባል ግን አንድ ቁም ነገር አለ። የርዕሰ ሀያሉዋ አሜሪካ የውጭ ፖሊሲ በመርሀ ጽድቅ የሚመራ አይደለም። እንደውም የውጭ ፖሊሲዋ - ለጠባብ ፍላጎቶቹ እጁን ባስረዘመ፣ የማግባባትና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ባቀላጠፈ ወገን የሚሾፈር ወይም የሚሽከረከር ነው፡፡ ከውጭ ሆነው ሲመለከቱትና ሲያስቡት ግር ያሰኝ ይሆናል እንጂ ከተሠራበትና ተከታታይ ትኩረት ካልተነፈገው የአሜሪካ የ›ፖሊሲው አቅጣጫ› በምክንያት የሚቀየር እንደሚሆን ብዙ ተወትውቷል፡፡ ችግሩ ያለው የህዝብ ግንኙነትና የግንኙነት ሥራዎችን በዲፕሎማሲያዊ ብልሃትና ጥበብ በኢትዮጵያ ወገን ያለማከናወን ድክመት አለ፡፡ ይልቁንም እርስ በእርሳችን የምንሰባበክበትና የምንፎክርበት ነገር ወደ ውጭው ሳይደርስ እየቀረ፣ የያዝነውን እውነት ለማጋባት ባለመቻልና ከእነርሱ (ከባዕዳኑ) ፍላጎት ጋር የሚያቆራኝ ተግባር ባለመተግበሩ ጭምር የሚከሰት ክፍተት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡
የእኛ ሀገር በታሪኳ ከዩ.ኤስ አሜሪካ ጋር ያላት ወዳጅነት ረዥም ዕድሜ ያለው ነው። ዛሬ ጥቂት ሀይሎች የድለላና የማግባባት ሥራቸውን ከእኛ በበለጠ በመሥራታቸው የተነሳ የተፈጠረው የፖሊሲ ክፍተት በ›ሴራ› ፖለቲካ ትርጓሜ አቃለን፣ “አይወዱንም” “ታሪካዊ ጠላት ስለሆኑ ነው” ምናምን እያልን የምንደመድመው አይደለም፡፡ በሀገር ግንኙነት ውስጥ ካልወደዱኝ አይባልም፡፡ ግንኙነቱ የጥቅም ነው፡፡ ይህንን ማስተሳሰር ላይ ነው መበርታት እንጂ ጥረታችን እንዲወዱን የሚል ቤሳ ህሳቤ አያስፈልገውም። ከቶ እኛም ምን አድርገናል? በሚለው ተግዳሮታችንን መቃኘት ይጠቅመናል፡፡ ዛሬ በአሜሪካ ምድር በዜግነት አሜሪካዊ የሆንን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ በየአካባቢያችን ያሉትን የምክር ቤት ተወካዮች የምናናግር፣ የህግ መወሰኛ ተመራጮችን የምናግባባ ስንት እንሆን? ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ትልቁ ሀብታቸው ‘ድምጽ’ ነው፡፡ በምርጫ ወቅት እመርጥሃለሁ - ለምርጫህ እተባበራለሁ ብሎ ተከታይን (ኮንስቲቲዌንሲ) ካሳዩ በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር አይከብድም፡፡
ቀደም ሲል እንደዘበት የጠቀስኩት ጉዳይ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማህበረሰብ የሚል፡፡ በዩ.ኤስ አሜሪካ ስርዓት ውስጥ በውጭ ፖሊሲ አውድ ብዙ መዘበራረቆች አሉ፡፡ ወጥና አቅጣጫ ያለው አሠራሩ ተለዋዋጭ የመሆኑና በተወሰኑ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማህበረሰብ አባላት የሚዘወር መሆኑ የፈጠረው ተግዳሮት በዘርፉ የሚገኙ በሳሎች የሚተቹት ጉዳይ ነው። ይሁንና ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ስርዓቶች ውስጥ ፖሊሲ በመንግሥት ብቻ የሚወሰን አይደለም። ይልቁንም የሲቪክ ተቋማትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትን አካቶ የሚተገበር ነው። የውጭ ፖሊሲ ማህበረሰብ የሚባለውም እዚህ ዩ.ኤስ አሜሪካ ውስጥ አራት መሰረታዊ መደቦች አሉት፡፡ የመጀመሪያው መደበኛ የሆነው የመንግሥት አካል ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የደህንነት ዘርፍ ወዘተ... ይመለከታል፡፡
ሁለተኛው ‘የአባላት ድርጅቶች’ የሚሏቸው ሲሆኑ በእነዚህ መደብ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ምክር ቤት፣ የቀድሞ ዲፕሎማቶች ማህበር የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ሶስተኛው ‘መማክርቶች’ (Think Tank) የሚባሉት እንደ ካርኒጊ፣ ብሩኪንግስ፣ አትላንቲክ ካውንስል የመሳሰሉት ይካተቱበታል። የመጨረሻውና አራተኛው ባለድርሻ አካላት (Interested Groups) የምንላቸው ሚዲያ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የመካነ ጥናት አዋቂዎች (አካዳሚያ) የያዘ ነው፡፡ እና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ እነዚህ ሁሉ ወደ ድስቱ ወጥንጨታቸውን የሚከቱ አካላት ናቸው።  የፖሊሲው ውይይት ከእነዚህ ሁሉ መንጭቶ ወደ አስፈጻሚ የሚጓዝባቸው መንገዶች ራሱን የቻለ ትኩረት የሚሻ፣ ዋነኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ለይቶ የማወቅን ብልሃት የሚጠይቅ ነው፡፡
ዩ.ኤስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በዋነኛ አጋፋሪነት አሁን የሚታዩት  ግለሰቦች በፕሬዚዳንት ክሊንተን አስተዳደር ብቅ ያሉ (ወጣቶች የነበሩ)፣ በፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን ያደጉ (የጎለመሱ)፣ በአሁኑ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጊዜ ደግሞ ባለስልጣንነት ያገኙ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች ቀድሞ ‘ዲሞክራሲያዊ’ ብለው ካቆላመጡት ቡድን ጋር ያለመነጠል ግብ ግብ የያዙበት ሁኔታ ነው የተከሰተው። ይህንንም ለመፈጸም እንዲያመች የ’ውጭ ፖሊሲ’ አቅጣጫውን አዲሱ የባይደን አስተዳደር ይዞት የመጣውን የቻይናንና የሩሲያን ተጽዕኖ ከማዳከም ጋር አቆራኝተው - የኢትዮጵያን መንግሥት ሰለባ ለማድረግ ያመቻቹት ይመስላል፡፡
እነዚህ በአሜሪካ የአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሹማምንት (በነጩ ቤተ መንግሥትም ይሁን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ) ከትህነግ ሹማምንት ጋር ባላቸው የግል ወዳጅነት (ፍቅር) ምንም ላለማየት የታወሩበት ክስተት ነው የተስተዋለው፡፡ በሃያ ሰባት ዓመታት ዝርፊያ ኪሱ የደለበው ትህነግ፤ በኢትዮጵያ ስም ቀድሞ የመሰረተውን የግንኙነት መስመር በመጠቀም - የመገናኛ ዘዴዎችን የሚያግባባና የሚነበቡ ዘገባዎችን የሚያዘጋጁ - የአሜሪካ ዋነኛ የፖለቲካው አንቀሳቃሾቹን የሚያባብልና ተጽዕኖ የሚፈጥር የአግባቢ ቡድኖችን በተለያዩ ስሞች ማቀናጀት - ቀደም ሲል በጠቀስናቸው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ማህበረሰብ ዘርፎች ውስጥ ተናበው የሚሠሩ አካላትን የመመልመል ሥራዎችን ነበር ያከናወነው። ለዚህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፊርማ ‘ለህክምና’ በሚል ከሀገር የወጡት የሕወሓት ሹም አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ዋነኛ አዝማች ፊታውራሪ ሆነው የተንቀሳቀሱበት ተውኔት ነው የተከናወነው። 
የገንዘብ አቅም ይዞ የተንቀሳቀሰውን ይህን የሕወሃት አግባቢና አማላይ ቡድን ደግሞ በአሜሪካ መንግሥት ዘርፎች በተቀጣሪነትና በተሿሚነት የተሰየሙ የ’ትግራይ ሕወሃት ደጋፊዎች’ የተጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ልክ አሁን በኢትዮጵያ ስም በዓለም ጤና ድርጅት ተሹመው መልሰው በኢትዮጵያ ላይ እንደዘመቱት ዶ/ር ቴዎድሮስ አይነት ማለቴ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሸልቦ የነበረው የኢትዮጵያ ዲያስጶራ መነቃነቅ ሲጀመርና እውነቱ ሲነገር፣ ኢትዮጵያውያንም ንፋስ እንዳይገባ ቀዳዳውን ሲደፍኑ - ፀሀይ እንደገላመጠው ቂቤ ሀሰቱ መቅለጥ ጀምሯል፡፡
የትህነግ ቡድን ልዕለ ሀያሏን አሜሪካንና የቃል ኪዳን ሀገሮቿን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡና ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ የሰሜኑን ጥቃት ከመፈጸሙ እቅድ ጋር በተጓዳኝ የቀየሰው እኩይ ሴራ ጨርሶ መምከን አለበት፡፡ በጎሳ አጥር የተከለሉ ትንንሽ መንግሥታትን የመመስረት ሴራ - በአፍሪካ ቀንድ የሚመክነው ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ የተላበሰ አካሄድና ጥቅሞቻችንን ከጥቅሞቻቸው ጋር የመፍተል ብቃት ሲኖር ነው፡፡




Read 1390 times