Saturday, 22 January 2022 00:00

“ንጉሥ መንቀፍ፣ ነብር ማቀፍ”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 አንድ የትወና መምህር ስለሰውነት እንቅስቃሴ ሲያስተምሩ የሚከተለውን ተረትና ምሳሌ በአስረጂነት አቅርበው ነበር ይባላል። እነሆ፡-
“ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ በጣም ባለፀጋ፣  የናጠጡ ሀብታም ሰው ነበሩ። ብርቄ የሚባል አሽከር ነበራቸው። ከሚወዷቸው ባለቤታቸው የወለዱትም አንድ ወንድ ልጅም ነበራቸው።
ብርቄ እኚህን ሀብታም ሰው እጃቸውን ባስታጠባቸው ቁጥር፤
“ጌታዬ እርሶ ቢሞቱ ይህ ዓለም ይበቃኛል። በቃ፤ ገዳም እገባለሁ” ይላል።
ጌትዬውም፤
“ተው ብርቄ አታረገውም፤ ያልሆነ ቃል አትግባ” ይሉታል።
ብርቄም፤
“ይመኑኝ ጌታዬ እርሶ በዚህ ዓለም ከሌሉ፣ ቤቴ ገዳም ብቻ ነው” ይላቸዋል።
“በል እንግዲያው ለዚህ ታማኝነትህ ከሳጥኑ ውስጥ አንድ ኩታ አውጣና ልበስ። ሸልሜሃለሁ!” ይሉታል። ብርቄም ኩታውን ያመጣና እፊታቸው ይለብሳል። በተደጋጋሚ እጃቸውን ባስታጠባቸው ቁጥር፣ እንደተለመደው ቃል ይገባል። ጌታውም እንደተለመደው ይሸልሙታል።
መቼም ሰው ሆኖ መሞት አይቀሬ ነው - ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት ይሏልና ጌትዬው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ብርቄም እዚያው ቤት ለተተኩት ለቀጣዩ ጌታ ማገልገሉን ቀጠለ። ብዙ ጊዜም አለፈ። አንድ ቀን አዲሱ ጌታው ግብር አግብተው ሰው ሁሉ አረፍ ካለ በኋላ፤ በድንገት የዱሮ ጌታው በአፅም መልክ በፃዕረ-መንፈስ ተከሰቱና ብርቄን እንዲህ አሉት፡-
“ብርቄ፤ ደህና ነህ ወይ? ሚስቴስ ደህና ነች ወይ?
ልጄስ ደህና ነው ወይ? አንተስ? አልመነንክም?” ብለው ቢጠይቁት፤
ብርቄ እንዲህ መለሰ፡-
“ሚስትዎ ደህና ናቸው፣
ልጅዎትም አድጓል፤
ግን እኔ አልመነንኩም!” ብሎ ቢነግራቸው፤
(የእጅ ጣቶቻቸውን ወደታች ወደላይ እያወናጨፉ)
“አዬ ጉድ!
አዬ ጉድ!
አ… ዬ ጉድ!”
ያሉበት ረገፈ ጣታቸው።
*   *   *
ከነገር ሁሉ ከባድ እሰው ፊት ቃል መግባት ነው። በአደባባይ ቃል መግባት አደገኛ ነው። በተለይ በማያስተማምን ጊዜና ወቅት ውስጥ ተሆኖ፣ ቅጽበታዊ ውዳሴንና ሙገሳን አገኝ ብሎ፣ የማይፈጽሙትን ቃል መግባት፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበዛል። ለዛሬ የተሳካ ቢመስለንም እንኳ ነገ ዋጋ ያስከፍለናል። ያስሳጣናል። ተዓማኒነትም ያሳጣናል። አድሮም ያጋልጠናል። እንደዚህ ያለው ሁኔታ በመሪ፣ በፓርቲ፣ በድርጅትና በህዝብ ኃላፊ ዘንድ ከታየ ደግሞ አገር ይበድላል፤ ህዝብንም እጉዳት ላይ ይጥላል።
ለአንድ አገር አመራር መሻሻልና እድገት ወሳኝ ከሚባሉት ፍሬ ጉዳዮች አንዱ የልዩነት አፈታት ነው። ያ ደግሞ ልዩነት ላይ ካለን አመለካከት የሚመነጭ ነው።  በማናቸውም የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ልዩነት ሊከሰት ይችላል። ፈረንሳዮች፤
Vive la difference ይላሉ። “ልዩነት ለዘለአለም ይኑር” እንደማለት ነው። ማናቸውም የፖለቲካ ልዩነት በአግባቡና በወቅቱ ከተፈታ እንደ አንድ ለውጥ አንቀሳቃሽ ሞተር የሚታይ ነው። ምነው ቢሉ፤ አንድም የሰለጠነ ዘዴ በመሆኑ፣ አንድም ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከጦርነት  ይልቅ በሰላም፣ ከጦር ሜዳ ይልቅ በክብር ጠረጴዛ ዙሪያ ችግርን የመፍታት ሁነኛ ዘዴ በመሆኑ ነው። እንደሚታወቀው አገራችን ጦርነት ተለይቷት አያውቅም። ሁሌም “ Seize the time seize the gun” (ጊዜና ጠመንጃን ጨብጥ፣ ወይ ይዘህ ተገኝ) ነው መመሪያችን። “ብምርህ አይማረኝ!” ነው መፈክራችን። ከዚህ አስተሳሰብ ካልተላቀቅን በአግባቡ ረብ- ያለው ውይይት ለማካሄድ አንችልም። በትንሽ በትልቁ መጨቃጨቅ ከ”ጨረባ ተዝካርነት” አያልፍም። ሁሌ ብሶትን እያወሱ ሙሾ-አውራጅ መሆንም ከልብ መግዛት ይልቅ ደረት መምታትን ነው የሚያስተምረን።
“አንተ ችጋር የት ትሄዳለህ? ቢሉት፤ ሰነፍ ሰው ቤት አለ ይባላል”። አበው ይህን ተረት የነገሩን ትውልድ እንዳይሰንፍ ነው። ትውልድ ተግቶ እንዲሰራ ነው። በሥራውም ይበልጥ እንዲተጋና እንዲኮራ ነው። በመልካም ስራ እንዲፎካከር ነው። ለመፎካከር መተቻቸት፣ አዎንታዊ ነቀፌታ መስጠትን መልመድና ባህል ማድረግ ይገባናል። ማንንም ቢሆን በቀና ልብ መንቀፍ መቻል አለብን። “ንጉሥ መንቀፍ፣ ነብር ማቀፍ” እያልን በቸልታ ማለፍ የለብንም። ከሃሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል የሚለውንም የአበው አነጋገር አንርሳ!


Read 4602 times