Saturday, 22 January 2022 00:00

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ለሱዳንና ግብጽ ጥሪ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በመቀራረብና በትብብር መንፈስ እንዲሰሩ ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር ዐቢይ ባስተላለፉት መልዕክት የጠየቁ ሲሆን በግድቡ ዙሪያ ያሉ ትርክቶችን ወደ ሠላም ግንባታ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት መለወጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በግብርና ማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ ኢኮኖሚ የመገንባት ህልም እንዳላት ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህን ህልም እውን ከሚያደርጉ ፕሮጀክቶች መካከል የህዳሴው ግደብ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ 53 በመቶ ወይም 60 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ምንም አይነት የኤሌክትሪክ  ብርሃን አይተው እንደማያውቁ በመልዕክታቸው የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በየትም ሃገር ይሄን ያህል  ህዝብ በጨለማ ውስጥ እየኖረ ድህነትን ማሸነፍና ሁሉን አቀፍ እድገት ማስመዝገብ እንደማይቻል እሙን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አንጻር የህዳሴ ግድቡ 60 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር እንዲሁም ሃገሪቱ የምታልመውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ፕሮጀክት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ግድቡ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ ያለ የትብብር ምሳሌ መሆኑን በመግለፅ፤ ጠቀሜታውም  ከኢትዮጵያ ባሻገር ለግብፅና ለሱዳን ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ነው ብለዋል፡፡
የግድቡ ውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው የክረምት ውሃን በመጠቀም መሆኑንና በታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለው  ያረጋገጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ ግድቡ በተለይ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያሉትን ጥቅሞች በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ወቅቱ ሶስቱም ሃገራት ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን ከእርስ በእርስ ጥርጣሬ ይልቅ ግድቡ ለሁሉም ሃገራት ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት በግድቡ ዙሪያ ያሉ ትርክቶችን ወደ ሠላም ግንባታ፣ትብብርና የጋራ ህልውና እና ልማት ማዞር ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፡፡


Read 3578 times