Friday, 21 January 2022 00:00

ጎንደር ለጥምቀት ከጠበቀችው በላይ እንግዶችን አስተናግዳለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም  ጀምሮ በጎንደር ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲከናወን የቆየው የጥምቀት ክብረ  በዓል ያላንዳች የፀጥታ ችግር   መጠናቀቁ ተገልጿል። ከተማዋ ለበዓሉ 1.5 ሚሊዮን እንግዶችን ጠብቃ የነበረ ቢሆንም፣ በበዓሉ የታደመው  ግን ከተጠበቀው ቁጥር በላይ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
  በህዝቡ ትብብር በአመራሩ ቅንጅትና በወጣቶችና  በፀጥታ አካላት ብርቱ ስራ በዓሉ ያለምንም ኮሽታ መጠናቀቁን  የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት ተናግረዋል። በዕለተ ጥምቀት በፋሲል ጥምቀተ ባህር ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  ይልቃል (ዶ/ር)፤ የውጭ ጠላቶቻችን በሚያሰራጩት የሃሰት መረጃ ምክንያት የተጠበቀውን ያህል የውጪ ቱሪስቶች ባይገኙም፣ ከተገመተው በላይ  ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እንዲሁም ከመላው ኢትዮጵያ ጥግ የመጡ ወንድምና እህቶች በበዓሉ መታደማቸውን ጠቁመው፤ ይህም እንደ ሃገር የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡
የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ጦርነቱና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ  በከተማውና በአካባቢው የተፈጠረውን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ማነቃቃቱም ተነግሯል።
ባለፈው አንድ ሳምንት የከተማው ሆቴሎች፣የባጃጅና የታክሲ አሽከርካሪዎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ ቡና ጠጡ ቤቶች፣ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ መሸጫ ሱቆችና  በአጠቃላይ ሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች የጥምቀትን እንግዶች በማስተናገድ ስራ ላይ ተጠምደው   የሰነበቱ ሲሆን በዚህም ሁሉም በየፊናው ተጠቃሚ መሆኑ ታውቋል፡፡
 በክልሉ እስከ ቅርብ ጊዜ  ድረስ ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መነሳቱና የፀጥታ አካላት የነቃ የፀጥታና የደህንነት ጥበቃ ስራ ዳያስፖራውም ሆነ የሃገር ውስጡ የበዓሉ ታዳሚ እንደልቡ እንዲንቀሳቀስና እንዲዝናና ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ያነጋገርናቸው እንግዶች ነግረውናል።
በተያያዘ ዜና፤ ከጥምቀት በዓል መጠናቀቅ በኋላ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ትብብር  “ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሃገራችን ዲፕሎማሲ፣ ሰላምና ልማት ላይ የሚኖራቸው ሚና እና በጎንደር ከተማ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች” በሚል ርዕስ በሐይሌ ሪዞርት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር  የውይይትና የምክክር መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በመድረኩ  በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በከተማዋ ባሉ የኢንስትመንት አማራጮችና በዲያስፖራው ሚና ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ጥናት በማጥናትና በማማከር ድጋፍ እንደሚያደርግ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደ ወይን  ቃል ገብተዋል። በዚህ መድረክ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ፣የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ም/ከንቲባና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ ማለደ፣ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ኘሬዚዳንት አስራት አፀደወይን እና ሌሎችም በርካታ እንግዶች ታድመዋል።
የዲያስፖራው ተወካዮች በበኩላቸው፤ በሃገራቸው ባሉት አማራጮች ኢንቨስት ለማድረግና በዲፕሎማሲውም ረገድ አበክረው ለመስራት ቃል ገብተዋል። በቀጣዮቹ ቀናትም ወልቃይትና አካባቢውን እንደሚጎበኙ ታውቋል፡፡


Read 773 times