Saturday, 15 January 2022 21:18

ኦሚክሮን በ2 ወራት ውስጥ ከአውሮፓ ህዝብ ግማሹን ሊያጠቃ ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘውና ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ  በአውሮፓ አገራት ከ7 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ማጥቃቱ የሚነገርለት አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ኦሚክሮን፣ እስከ መጪዎቹ 2 ወራት ከአህጉሩ አጠቃላይ ህዝብ ግማሽ ያህሉን ሊያጠቃ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡
ቫይረሱ በተለይ በአውሮፓ አገራት በከፍተኛ ሁኔታ በፍጥነት በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው የአለም የጤና ድርጅት፣ እስካለፈው ሰኞ ቫይረሱ በሳምንት የአገራቱን 1 በመቶ ህዝብ ሲያጠቃ እንደነበር ማስታወሱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ባለፈው ማክሰኞ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከ10 ሚሊዮን፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ232 ሺህ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፣ ወደ 200 ሚሊዮን የሚደርሱ ክትባቶች መሰጠታቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከአለማችን አገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ገደብ በመጣል ቀዳሚዋ እንደሆነች የሚነገርላት ኡጋንዳ በበኩሏ፣ ለሁለት አመታት ያህል ዘግታቸው የከረሙ ትምህርት ቤቶችን ከቀናት በፊት መክፈቷና ትምህርት አቋርጠው የኖሩ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ወደ ገበታቸው ማስመለሷ ተዘግቧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ በካናዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ እንደሞተባት የምትነገረዋ የኪዩቤክ ግዛት፣ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ባልወሰዱ ነዋሪዎች ላይ ከፍ ያለ ልዩ የግብር ቅጣት ልትጥል ማቀዷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ግሪክ በተመሳሳይ መልኩ፣ ክትባት ያልወሰዱ ዕድሜያቸው ከ60 አመት በላይ የሆናቸው ሰዎች በየወሩ 113 ዶላር እንዲከፍሉ ማድረጓን ያስታወሰው ዘገባው፣ ሲንጋፖር በበኩሏ ያልተከተቡ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የህክምና ወጪያቸውን ራሳቸው እንዲሸፍኑ የሚያስገድድ መመሪያ በስራ ላይ ማዋሏን አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1302 times