Saturday, 15 January 2022 20:34

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች የምንኖርበትን ቤት ወደ ግል የማዛወር መብታችንን ተነፍገናል አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የኮተቤ ሜትሮፖሊን ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮችና ቴክኒካል ረዳቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን እንዲሆኑ የተሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አድሎአዊ በሆነ አሰራር በስማቸው አዙረው እንዳይጠቀሙ መደረጋቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በቁጥር 125 (አንድ መቶ ሃያ አምስት) የሆኑት የዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰሮችና ቴክኒካል ረዳቶች ቅሬታ የፈጠረባቸው ጉዳይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንን የቤት ችግር ለመቅረፍ ካዘጋጃቸው 5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 150 ያህሉ ማለትም 125 ለኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ መምህራን፣ 25 ለዳግማዊ ሚኒሊክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን አስቀድሞ በኪራይ እንዲኖሩበት የሠጣቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ አስተዳደር 125 ቤቶችን ተረክቦ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ የኪራይ መጠን ለመምህራን አከራይቶ መቆየቱንም በአቤቱታቸው ያስረዳሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በወሰነው መሰረት በኪራይ የነበሩ የመምህራን ቤቶች በወቅቱ የነበረውን የቤቱን ዋጋ ግምት በመክፈል መምህራን ቤቶቹን ወደ ራሳቸው እንዲያዞሩ መፍቀዱን ተከትሎ፣ መምህራን ይሄው መመሪያ ለእነሱም እንዲፈፀም የዩኒቨርስቲው አስተዳደርን ቢጠይቁም፣ ለጥያቄያቸው አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘታቸውንና መብታቸው መጣሱን ይገልጻሉ፡፡
የዩኒቨርስቲው አስተዳደር፣ ቤቶቹን ዩኒቨርስቲው በጀት መድቦ የገዛቸው የራሱ ንብረቶች እንጂ ከተማ አስተዳደሩ ለመምህራን ብሎ የገዛቸው አለመሆናቸውንም በመግለፅም ጥያቄቻቸውን ሊቀበላቸው እንዳልቻሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ፡፡
በአንጻሩ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ጋር 25 ቤቶችን የተከበረውና በራሱ በዩኒቨርስቲው አስተዳደር ስር የሚገኙ የዳግማዊ ሚኒሊክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ቤቶቹን ወደ ስማቸው እንዲያዞሩ እንደተፈቀደላቸው፤የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህም  በአንድ ተቋም ስር ሁለት አሠራር መኖሩን ከማመላከት ባሻገር የአስተዳደሩን ኢ-ፍትሃዊ አሠራር የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከዩኒቨርስቲው ጋር ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው የትምህርት ተቋማት-እንደ የአፍሪካ አመራር የልህቀት አካዳሚ ያሉት፣ ለመምህራን የተመደበውን የጋራ መኖሪያ ቤት መምህራኑ ወደ ግላቸው እንዲያዞሩ አድርገዋል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ለምን የኛ ብቻ ተለይቶ በመንግስት የተሰጠንን መብት ተነፈግን?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ቤቶቹን በኪራይ ከተረከቡ በኋላም በየግላቸው ከ73 እስከ 100 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ የማጠናቀቂያና የእድሳት ስራዎችን ማከናወናቸውን መምህራኑ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ፕሮፌሰሮች አስታውሰዋል፡፡
በህግ የተፈቀደልንን መብታችንን ተነፍገናል ያሉት መምህራኑ፤ ጉዳዩ ከከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔና ከመልካም አስተዳደር እጦት አንጻር ታይቶ የካቢኔው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው አበክረው ጠይቀዋል፡፡
በዚህ የዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰሮች እና ቴክኒካል ረዳቶች ቅሬታ ዙሪያ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ የዩኒቨርስቲውን አስተዳደር በስልክ አግኝተን  ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም።

Read 9206 times