Saturday, 01 January 2022 00:00

No More Black Market የባንክ ኤግዚቢሽን ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተደረገላቸውን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገራቸው የሚገቡትን 1ሚ ዲያስፖራዎች  ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው "No More Black Market" የባንክ ኤግዚቢሽን፣ በግሮቭ ጋርደን ዎክ ከጥር 3-5 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ የባንክ ኤግዚቢሽኑ ዲያስፖራው የሚፈልገውን የትኛውንም የኢንቨስትመንት ስራ ለመስራት ዋና አጋሩ ባንክ በመሆኑ ሁሉንም  የባንክ አገልግሎት በአንድ ቦታ በማግኘትና በመወያየት ወደ ስራ እንዲገባ እንደሚያስችለው የተናገሩት የኤግዚቢሽኑ ዋና አዘጋጅ የ"ሰፍ ኢቨንትስ" ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኮክ አሰፋ፤ እስካሁን በሀገራችን ካሉት ባንኮች 80 በመቶዎቹ በኤግዚቢሽኑ ለመሳተፍና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በመገናኘት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማስተዋወቅ ዝግጁ ናቸው ብለዋል።የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዶሰን ግርማ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከዲያስፖራው 3.6 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን አስታውሰው፤ ይሄም ከዲያስፖራው ከሚጠበቀው ሲሶው (1/3ኛው) ብቻ እንደሆነና ሌላው በጥቁር ገበያ እንደሚመነዘር ጠቁመዋል፡፡ በጥቁር ገበያ የሚመነዘረው ገንዘብ በሁለት መንገድ ኢትዮጵያን እንደሚጎዳት የገለጹት አቶ ወንዶሰን፤ አንድም መንግስት የውጪ ምንዛሬውን በቀጥታ አግኝቶ ያለበትን እጥረት እንዳይቀርፍ  ከመሆኑም ሌላ ዶላሩ በጠላት እጅ እየገባ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንደሚውል በማመልከት እንደ "No More Black Market" መድረኮች እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳሉም ብለዋል።
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ዶላር በጥቁር ገበያ እንዳይመነዘር ካስፈለገ ባንኮች የሬሚታንስ መላኪያ ዋጋውን ከ10 በመቶ እንዳይበልጥ መስራት  አለባቸው ብለዋል - አሁን የመላኪያ ዋጋው እስከ 14 በመቶ እንደሚደርስ በመግለጽ፡፡
አቶ ወንዶሰን  ጨምረውም፤  ዲያስፖራው ወደ አገር ሲገባ ገንዘብ ለመመንዘር እንዳይቸገር ባንኮች የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ማሽኖችን ማስቀመጥና ተጨማሪ መስኮቶችን ማዘጋጀት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል። ወ/ሮ ኮክ አሰፋ በበኩላቸው፤ ከጥር 3-5 ቀን 2014 ዓ.ም በሚቆየው የባንክ ኤግዚቢሽን ላይ በርካታ የስራ ትስስሮች በባንኮችና በዲያስፖራው መካከል ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅና ውጤታማ ስራ ይሰራል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።


Read 12334 times