Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 22 September 2012 10:47

ጫቁወው አው በይ ጊድ ጭመይ ኦይችን ጭቅዳጋ፤ ዎረነ በይስ ግን እ ጠይኮሽን ግን ጫቅስዳጋ ዎረነ ያጌስ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

(“አንተ መሀላ የት ትሄዳለህ” ይላሉ ሽማግሌ

“የማለውን ለመግደል” ይላል መሀላ፡፡“ካጣኸውስ?” ቢሉት፤ “ያስማለውን እገላለሁ” ይላል - (የአማርኛ ተመሳሳዩ)

ህንዶች የሚተርቱት አንድ አፈ - ታሪክ እንዲህ ይላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ  አካባቢ፣ አንዲት ነብሰ - ጡር እናት፤ ጊዜዋ ደርሶ ኖሮ፣ ሽንት ውሃዋ ፈሶ፣ በምጥ ትያዛለች፡፡

የሠፈር ሰው ሁሉ፤ “እንደምንም በደህና ትገላገል!” ይላል፡፡

“ማርያም ትዳብሳት!”

“ምነው የዛሬ ምጧን በሰላም በተወጣች?” እያለ እንደየአምልኮው ይማጠናል፡፡

በመጨረሻ በሰላም ወንድ ልጅ ተገላገለች! እልልታው ቀለጠ!

ልጁ ግን አስገራሚ ልጅ ሆኖ ተገኘ፡፡ መናገር የሚችል ልጅ!!

ሰዉ ተገርሞ ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡

“መናገር እንዴት ቻልክ?” አለው አንዱ ታዳሚ፡፡

“ሲፈጥረኝ እንዲህ ሆኜ ወጣሁ!” አለ፡፡

“አሁን ምን መማር ትፈልጋለህ?”

“ምንም!”

“ለምን?”

“ተወልጄ ገና መማር የሚያስፈልገኝ ከሆነማ እናቴ ያን ያህል ጊዜ ማህፀኗ ውስጥ አታቆየኝም ነበር፡፡ አምላክ ቢያመላክታት ነው!”

“እሺ፤ እንግዲያው ወደፊት ምኞትህ ምን እንደሆነ  ንገረና?”

“ምኞቴ ምን መሰላችሁ?” ብሎ ጥቂት አቅማማ!

“ግዴለም አትፍራ- ንገረን” አለ አንደኛው፡፡

“ኧረ ግዴለህም የምታስበውን ንገረን?” አለች ሌላዋ!

“እሺ ልንገራችሁ - እኔ የምመኘው:- አንደኛ - መሥራት፡፡ ሁለተኛ - መሠራት፡፡  ሦስተኛ - መሥራት፡፡

ሁሉም - “እሺ ከዛስ?” አሉና በጉጉት ጠየቁት፡፡

ልጁ - “ከዛማ በቃ ምንም የማወራው ነገር አይኖርም - ምንም አለማውራት ነው ምኞቴ!” አላቸው፡፡

***

በሥራ በመጠመድ የወሬ ጊዜ የምናጣበት ዘመን ይሆን ዘንድ መንገዱን ይክፈትልን! ትምህርታችንን

ይግለጥልን፡፡

የምንገኝበት ወቅት አዲስ አመራር ይዘን አዲሱ ዓመት ውስጥ የምንጓዝበት ነው፡፡ ለዚህ ይጠቅማሉ ያልናቸውንና ትላንትን እንድናይ፣ ዛሬን መሬት ወርደን እንድናስተውል፤ እንዲሁም ነገ ላይ ከወዲሁ አነጣጥረን እንድናተኩር ያግዛሉ ያልናቸውን ከወላይትኛና ከአማርኛ የተውጣጡ አንኳር ተረቶችን ለአብነት እየጠቀስን ትሁት አስተያየት ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ (ምናልባት ወደፊት እያንዳንዱን ተረት እንደ አንድ ጉዳይ በስፋት ለማየት እንሞክር ይሆናል፡፡)

ዛሬ አገራችን ባለችበት የለውጥ ሂደት ውስጥ በየትኛውም ደረጃ የሚመደቡ መሪዎች፤ በሙያዊ ብቃት፣ በህዝብ ወካይነት፣ በኢወገናዊነት፣ በፍትሐዊነት፣ በኢሙሰኛነት፣ ተቃራኒ ሀሳቦችን በማቻቻል፣ የሃይማኖት እኩልነትን በማክበር፣ ዲሞክራሲያዊ አመለካከትን በመያዝ፣ በዋናነት ህዝብና ሀገርን በማገልገል የሚመረጡ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ የመረጥናቸው አመቺ ዐቢይ ዐቢይ ተረቶች እነሆ:-

ሀሬ ሃሽን ፐረይ ገማ ኩንቴስ - (የወላይታ ምሳሌ)

አህያ እንሰት ሲፍቅ ፈረስ ቅመም ይጨምራል - (የአማርኛ ተመሳሳዩ)

ተመሳሳይ የሆንነው ሰዎች ብቻ አብረን መሆን አለብን በሚል አንድ ዓይነት ሀሳብ ብቻ ይስተናገድ የሚሉ ካሉ አበክሮ መመርመርና ማረም ያስፈልጋል፡፡የግለሰብም ሆነ የቡድን ሃሳቦች ያለአድሎ ተስተናግደው ለውጥ እንዲያመጡ እድሉን መስጠት አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው ፡፡

ሀርያረ ሀርቁዋ ማደ ፐራረ በንጋ መውሱ (የወላይታ ምሳሌ)

ከአህያ ጋር ብጣሪ (ዕብቅ) በልታ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች

ወፍ ነሽ እዩት ጥርሴን ፣ አይጥ ነሽ እዩት ክንፌን ከሚሉ ይሰውረን፡፡

በሁለት ቢላዋ ከሚበሉ ይሰውረን ዘንድ አመራሮቻችን በጥሞና ይቆጣጠሩ፡፡ የቢላዋዎቹን ስለትና ደነዝነት በጊዜ ያጥኑ፡፡

ሀርያ ላግድ ጐስያጐችድ ጌዱዋ ካልዮጌ ዬሳ መለቴስ (የወላይታ ምሳሌ)

አህያ እየነዱ፣ ቅል እየሳቡ፣ ከኋላ ሲከተሉ፤ ወተት ያለቡ ይመስላል፡፡

ሆዳም ቢሸከም የበላ ይመስለዋል  - እንደማለት ነው፡፡እንደወታደራዊ ሠልፍ ግራ ቀኝ፣ ግራ ቀኝ ሲሉ ቆይተው በመጨረሻ “ባለበት ሃይ” ከማለት የማያልፉ አስመሳይ ፖለቲኮችን በንቃት ማስተዋል ይገባል፡፡ እርምጃቸውን፣ አቋቋማቸውን በትጉ ዐይኖች ማጤን መልካም ነው፡፡

ሀርያ ቶግድ ኖር ጌነ (የወላይታ ምሳሌ)

አህያ ላይ ተቀምጦ ኖር አይልም፣ ያላዩ ልጅ ዳቦ ፍሪዳው ነው

ዛሬ ሹመት አገኘሁ፣ ስለዚህ ከህዝብም ካገርም በላይ ነኝ በማለት ንቀትን የሚያዳብር፤ አብሮ ለመሥራት የሚቆረቁር ግለሰብ በሹመት ሂደት ውስጥ ሊከሰት ይችላልና ቀረብ ብሎ ሥነምግባራዊ ክትትል ማድረግ እንደሚያሻ ልብ እንበል፡፡

ሀጐ ኔነ ኔ ጐደይ መይዜኔ ጊን በርዮ ጠይን ተነ፤ ዛሴሽን ተነ አውፔ መይዘኔ ጌስ - (የወላይታ ምሳሌ)

አንተ ሰው ጌታህ ልብስ አያለብስህም? ቢለው፤ ለራሱ አጥቶ እኔን እያስማማኝ ነው፤ ከየት አምጥቶ ያለብሰኛል ይላል

የኢኮኖሚ ችግራችን የት እንደደረሰ ሥራዬ ብሎ ማጤንና ተገቢውን የችግር መፍቻ ለማቀበል፣ ባለሙያ ማነጋገር፣ ጉዳዩ የሚመለከተውን እህ ብሎ ማዳመጥ፣ ህዝብን ከኢኮኖሚያዊ ምሬት እንደሚያወጣ እንገንዘብ!! ድህነትን ቀርፈናል ብለን ሳንገበዝ ረዥሙን ትግል መያያዝ ከመዘናጋት እንደሚያድነንም እንገንዘብ፡፡

ሃሬነ አጣሬ አይፌ ሀንዳ ሜስ-  (የወላይታ ምሳሌ)

ያላረባ ልኳንዳ አራጅ አይን የሆነውን (ጮማ) ይበላል -

በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች ከመንግሥት ውስጥም ውጪም መኖራቸው አሌ አይባልም፡፡

ተደጋግሞም ተነግሮናል፡፡ እንዲህ ያሉት ሙሰኞች ያልዘሩትን ለማጨድ ማናቸውንም መንግሥታዊ አውታርም ሆነ የግል አቓራጭ ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ በጠዋት መገንዘብ ተገቢ ነው! ረዥሙን መንገድ ባቋራጭ እንሂድ የሚሉና አጭሩን መንገድ ካላስረዘምን የሚሉ መኖራቸውን በወቅቱ መረዳት ከብዙ አባዜ ያድነናል!!

ህዬሳ ሞቶይ ይግባ - (የወላይታ ምሳሌ)

የድሀ ሙግት ይግባኝ ነው -

የፍትሕ መጓደል ከሀገራችን ዋና ዋና ችግሮች በጉልህ የሚወሳ ነው፡፡ ደሀ እንዳይበደል፣ ከወገናዊነት የፀዳ የፍርድ ሚዛን እንዲኖር መታገል የእያንዳንዱ ዜጋ ብቻ ሳይሆን በዋናነት የመንግስት ኃላፊነት ነው፡፡የህግ አካላትን ንፅህና በአይነቁራኛ ማየት አይነተኛ ተግባራችን ይሆን ዘንድ ወቅቱ ግድ ይለናል፡፡

ሀችስ ኬሀ ግዮጋፔ ምንቶስ ኬሀ ግስየባ ኦተ -(የወላይታ ምሳሌ)

ለዛሬ ደግ ነው የሚባለውን ትተህ ነገ ደግ ሊያስብል የሚችለውን ሥራ -

የቅርብ የቅርቡን ስናይ ሩቁንና ትልቁን ስዕል ላናይ እንችላለን፡፡ ይህም የተቀናጀ ትልቅ መረብ እንዳንዘረጋ ያደርገናልና አርቀን እናስብ፡፡ ነገን ሁሌም ከህሊናችን ሞተር አንለየው!!

ሀውላሾይ ሃተው ደፍን፣ ጠዴ ማተው ደፌስ

አዞው ወደ ውሃ ሲስብ፣ ጉማሬው ወደ ሳሩ ይስባል

ሀነነኔ ሀለተኔ በከነ ኦይሳ

ሻክ ትዮቶሶነሽን ኦመርስ ገለ በከነ ሰንተን ወሬቶሶነ -(የወላይታ ምሳሌ)

ሃናኔና ሃሊቴ የ5 ሳንቲም ቅቤ ተካፍለው ሲቀቡ ውለው፤

ወደ ማታ በ5 ሣንቲም ጐመን ይጣላሉ

የፓርቲና የፓርቲ፣ የድርጅትና የድርጅት፣ የአባልና የአባል፣ የሠራተኛና የሠራተኛ ሽኩቻን የሚያበረታቱ፣ አሊያም በር ከፋች የሆኑ ጉዳዮችን በአጭር መቅጨት ያስፈልጋል! ለሀገርም ለህዝብም አይበጁምና!

ሀነ አይብ ዱርሰ ዱረይ ግን ሶን ማዮይ ድግን አትዳሮ ቤአርኪ ጌስ -   (የወላይታ  ምሳሌ)

ይቺ እንዴት ትጨፍራለች? ቢባል ፤ ልብስ አጥታ እቤት የቀረችውን ባየህ

ምንጊዜም የተሾመውንና ለሥልጣን የበቃውን ብቻ ሳይሆን ያን ዕድል ለማግኘት ሁኔታዎች ያልፈቀዱለትን ወገን በማሰብ እንዴት እናሳትፈው ብሎ ማሰብ ብልህነት ብቻ ሳይሆን ተገቢም ነው! አገር የሁላችንም ናት ብሎ ቅድሚያ ሰጥቶ ጉዳዩን መመርመርና መፍትሄ መስጠት የዘመናችን ቀዳሚ እርምጃ እንዲሆን ከወዲሁ እንምከርበት፡፡

ሀኖ መይ አይቤ? ተመ

ሀኖ መይ አይቤ? ተመ

ያትን አይብስ ሀ ተመይ ሞሳፔ ሸሬተ ዎድኪ? (የወላይታ ምሳሌ)

ይህቺን ምን በላ? እሳት፣ ይህቺን ምን በላ? እሳት፣ታዲያ ለምን ከዚህ በእሳት ከምትበላበት ዘወር ብለህ አትተኛም?

የሥልጣንና የሹመት አንዱ ዐቢይና ቁልፍ ነገር ካለፈው መማር ነው! ሳይሾሙና ለወንበሩ ሳይበቁ በፊት ከህዝብ ጋር ሆነው ያሉትን፣ የተቹትን ሁሉ አለመርሳት ነው፡፡ አንድ ቀን ህዝብ ነበርኩና እንደህዝብ ምን አስብ ነበር?         እንበል፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ ስልጣን እንደህይወት ሁሉ ሂደት መሆኑን ማመንና ለተረኛ እስኪለቁ ድረስ ለህሊና ታማኝ መሆን፤ የማያሰሩ ሁኔታዎችን መታገል፣ በሠሩት አለመኩራራት፣ ስላልሰሩት መቆጨትና መትጋት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሥራን በማጋራት ሥልጣንን የጋራ ማድረግ፣ አገር የሁሉም መሆኗን ማረጋገጥ መሆኑን ከልብ ማመን ነው! በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ በተሻለ ለመተግበር ለመጣጣር፤ ማሠሪያው ቃል ነው፡፡ መሀላ ነው፡፡ መሀላው ከአንጀት መሆን አለበት፡፡ ያ ካልሆነ ግን፤

ጫቁወው አው በይ ጊድ ጭመይ ኦይችን ጭቅዳጋ፡፡ ዎረነ በይስ ግን እ ጠይኮሽን ግን ጫቅስዳጋ  ዎረነ ያጌስ - (የወላይታ ምሳሌ)

“አንተ መሀላ የት ትሄዳለህ” ይላሉ ሽማግሌ፡፡“የማለውን ለመግደል” ይላል መሀላ፡፡ “ካጣኸውስ?” ቢሉት፤ “ያስማለውን እገላለሁ” ይላል፤ የሚለው ተረት ደወል የሚደውልበት ጊዜ ይመጣል!

 

 

 

Read 3683 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 10:54

Latest from