Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:21

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ነጠላ ዜማዬ
በመከራ ዘመን - እየከዳኝ እግሬ
ደርሶ ሲያዳልጠኝ - ገና ከጅማሬ
ላልወድቅ ስውተረተር - በጤና ሰክሬ
በመሄጃው መንገድ - መመለስ ጀምሬ
እጄ ነፋስ አቅፎ - እብቅ እየዘራ
ገለባ እያነፈስኩ ........................
ድፍርስ ህልሜን ሁሉ - ጨምቄ ሳጠራ
እቴ እንደ ብሂሉ - ልቤ ተስፋ ጸንሶ
ያለ ቀን ቆጠራ .............................
ሲያምጥሽ ኖረልሽ - ህመሙን ታግሶ !

እለትና ቀኑ - ወርና ዘመኑ
እንደ ማቱሳላ - እድሜ እየረዘሙ
ተስፋና ምኞቴ .....................
ዘኬዎስን መስለው - አጥረው እየደሩ
ስንት ሸረሪቶች
ተጋብተው
ተዋልደው
ዓይን በዓይን አይተው
በገዛ ጸጉሬ ላይ - እልፍ ድር አደሩ? !

ጎልያድን መስሎ - ኑሮ ሲታገለኝ
አልወድቅም እያልኩኝ ......
ናፍቆትሽን ሳባብል - ቁዘማ የጣለኝ
እቴ እንደ ብሂሉ - እንደ አበው ንግርቱ
ደጁ ላይ ታድሞ ............................
ኮቴሽን ያደምጣል - ልቤ ጅልነቱ !

እና ቡና ይዘን
ቆሎ እየቆረጠምን
በእጣን መሀል ሆነን
ሳቅ እየቆረስን
<<ምንድነው ንግርቱ ?>>
ብትይኝ እቴዋ
የአደይ አበባ - ውብ ቀለም ተነክሮ
ቅጠል ያወጣ ቀን - ደምቆ ተሞሽሮ
እንዲህ ባለ ምትሃት
ከንፈሬን ጠምተሻት
ቀጠሮ ጠብቀሽ - ትመጫለሽ ብዬ
ለብቻ እያወራሁ - ከሰው ተነጥዬ
እያንጎራጎርኩኝ
እያሰላሰልኩኝ
አጸደ መሀል ሆኜ - ዛፍ እያጫወትኩኝ
በማላውቀው ዘፈን - ስምሽን እያሞኩኝ
እቀጽልሻለሁ - በአንገት በጉሮሮ
ያልታተመ ዜማ .....................
ነጠላ ዜማዬ ነሽ - የነፍሴ እሮሮ !

ከነፋሻው አየር - ከልስልስ ዝናቡ
ምክንያት እያበጀ ....................
ትዝታሽ ያካፋል - በሰበብ ሰበቡ!
ውልብ እያለብኝ - እንደ ልጅነቴ
ላወራሽ ናፈቀኝ ...................
<አንድ ሰው ነበረ> ..............
በሚለው ታሪኬ - በረጅም ተረቴ !

በፍቅሬ ቅጠል ላይ - ደምቀሽ የምትኖሪ
ፍካቴን ለማድመቅ - ቀለም የምትዘሪ
በአዳማዊ ክብሬ ..........................
እንደ ንጉስ አክሊል - ከላይ ምታበሪ
የመስከረም ጸጋ
የቀሪ ህይወቴ
ዳርቻ ኦሜጋ
እኔ አበባ ስሆን - የመስቀል ወፍ ሆነሽ - እኔ ላይ ስፈሪ!
(ነፃነት አምሳሉ)

Read 1648 times
Administrator

Latest from Administrator