Wednesday, 29 December 2021 00:00

ባለሃብቱ ስለጦርነቱና ውድመቱ፤ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    ጦርነቱ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል
       በጦርነቱ የፈረሱትን መልሶ ለመገንባት የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል


            ሸዋ ተወልደው አዲስ አበባ ነው ያደጉት። ትንንሽ ከሚባሉ ሥራዎች ተነስተውና ስራን አክብረው ሰርተው ዛሬ በጊፍት ግሩፕ ኩባንያ ውስጥ ያሉትን ከ6 በላይ ትልልቅ ኩባንያዎች ፈጥረዋል። እስከ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞችን ቀጥረውም ያሰራሉ። የዛሬ እንግዳችን የጊፍት ግሩፕ ኩባንያ መስራች፣ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረየሱስ ኢጋታ። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ ገብረየሱስ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለ ጊፍት ግሩፕ ኩባንያዎች፣ ስለ ወቅቱ የሃገሪቱ ሁኔታ፣ ጦርነቱ በኢኮኖሚውና በቢዝነሱ ላይ ስላደረሰው ውድመት፣ ባለፈው ሳምንት በአጣዬ ተገኝተው ለተፈናቃዮች ስላደረጉት ልግሳና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች። እነሆ፡-
                አብዛኛው ሰው ጊፍት ሲጠራ ወደ አዕምሮው የሚመጣው ጊፍት ሪል እስቴት ነው። ነገር ግን ሌሎች እህት ኩባንያዎችም እንዳሉት ይደመጣል። እስኪ ትንሽ ማብራሪያ ይስጡን?
ጥሩ፤ እንዳልሽው በጣም ጎልቶ የሚታወቀው ሪል እስቴቱ ነው። ነገር ግን ጊፍት ሪል ስቴትንም ሆነ ሌሎች  እህት ኩባንያዎችን የፈጠረው እናት ኩባንያችን “ጊፍት ትሬዲንግ” የተባለው ነው። በዚህ ኩባንያ ስራ ነው ሌሎቹ የተመሰረቱት።
ለምሳሌ ጊፍት ደረጃ 1 ኮንስትራክሽን የሚባል አለን። GNM የተሰኘ 22 ዓመታትን ያስቆጠረ ሽቦና ምስማር የሚያመርት ኩባንያችንም አለ። አሁን ወደ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እያሳደግነው እንገኛለን። ከ16 ዓመት በፊት የተመሰረተው ጊፍት ሪል ስቴት የሚባለውና  በጣም ይታወቃል የተባባልነው አለ። ሌላው ጊፍት ቢዩልዲንግ ማቴሪያል የሚባል ከግንባታና ከግንባታ አጨራራስ ጋር የሚያያዙ ምርቶችን የሚያመርት ኩባንያም አለን። በዚህ ኩባንያ  አሉሙኒየም፣ የእንጨት ሥራዎች፣ ሲሚንቶና የሲሚንቶ ግብዓቶች ያመርታል። ወደፊት እንደ ማርብል ጂብሰምና መሰል ተጨማሪ ምርቶችን ማምረት የሚያስችለውን አቅም እየገነባንለት እንገኛለን።
አሁን ደግሞ “ጊፍት ቱር ኤንድ ትራቭል” እና “ጊፍት ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት” የተሰኙ ኩባንያዎች እየተቋቋሙ ይገኛሉ። በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ብለን ነው የምንጠብቀው። ለዚህ ሁሉ መሰረቱ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ “ጊፍት ትሬዲንግ” የተባለው እናት ድርጅት ነው።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በ2013 ዓ.ም ከጥቅምት ጀምሮ ከህውሃት ጋር በተገባ ጦርነት ሀገራችን ፈታኝ ሂደቶችን እያለፈች ትገኛለች። እንዲህ አይነት ጫናዎች ደግሞ ከሚጎዷቸው ዘርፎች አንዱ የንግዱን እና የምጣኔ ሃብቱን ነው። እንደ ጊፍት ግሩፕ ኩባንያ በኮቪድ ጊዜ ሰራተኛ ሳትቀንሱ ችግሩን ለማለፍ ጥረት አድርጋችሁ እንደነበር ከዚህ ቀደም አጫውተውኝ ነበር። ለመሆኑ ጦርነቱና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ጊፍት ግሩፕ ኩባንያ ያደረሰው ተፅዕኖ በእርስዎ እንዴት ይገለፃል?
ጥያቄሽ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው። እንግዲህ አንድ ነገር ሲመጣ ተግዳሮት ይዞ ይመጣል። ኮቪድ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። አሁንም አለ። በእኛም አገር የራሱ የሆነ የፈጠረው ጫና አለ። የስራ መቀዛቀዝ  አስከትሏል። ኮቪዱ ባደጉት ሃገራት እንደነ አሜሪካና አውሮፓ ያሉ አገሮች ላይ የፈጠረውን ያህል ጫና በሀገራችን ፈጥሯከል ብዬ አላምንም። እርግጥ ነው ምልክቱ ነበረ፤ ሁኔታዎቹ ነበሩ ነገር ግን እንዳደጉት ሀገራት ያለ ጫና ፈጥሮ ነበር ለማለት  ለኔ ለራሴ ይከብደኛል። በሀገራችን የተሻለ ሁኔታ ነበር። በመሃልም የቢዝነሱ እንቅስቃሴ እየተሻሻለም ነበር። ነገር ግን በቅርብ ጊዜ  የተፈጠረው ጦርነት ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ምዕራፍ ነው። የቢዝነሱ መቀዛቀዝና ጫና ከዘርፍ ዘርፍ ይለያያል። አሁን እኛ የተለያየ ስራ ነው የምንሰራው። በሪል እስቴት የምናየውና በፋብሪካ አካባቢ የምናየው ይለያያል።
የትኛው ዘርፍ ላይ ይበልጥ ይበረታል?
ለምሳሌ በሪል እስቴቱ ዙሪያ ተወዳዳሪ ዋጋ ይዘን እስከ ቀረብን ድረስ ቤት እየሸጥን ነው። ነገር ግን ቤት ለመስራት በሚያስፈልጉ ግብአቶች ላይ ከፍተኛ ጫና አለው። የዋጋ ውድነት፣ የዋጋ፣ ግሽበት የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ ሁሉ ጫና አለው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ኤክስፖርት ተደርጎ የሚያመጣው የውጪ ምንዛሬ ከፍላጎቱ ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ይህ ትልቅ ጫና አምጥቷል። የኮንስትራክሽኑ ሲታይ ከሪል እስቴቱ ጋር ተቀራራቢ ነው። ወደ ፋብሪካ ሲኬድ ትንሽ የተሻለ ነው። ጥሬ እቃ አቅርቦቱ ትንሽ ችግር ቢኖረውም ሽያጭ ላይ የተሻለ ሁኔታ አለው። እንዳልኩሽ ተግዳሮትና ጫናው ከዘርፍ ዘርፍ ይለያያል። አሁን ወደ ጦርነቱ ከገባን በኋላ ያለው ሁኔታ ትንሽ ለየት ያለ ነው።
ሀገር ጦርነት ላይ ነው፣ ህዝቡ ትኩረቱ ሁሉ ወደዚያው ነው ያለው። ከሀገር የሚበልጥ ስለሌለ ሁሉም ትኩረቱን ወደ ጦር ሜዳ ማድረጉም የሚጠበቅ ነው።  ሰው ከዛሬ  ነገ ምን ይመጣ ይሆን የሚል ውጥረት ውስጥ ነው ያለው። እነዚህ በተለይ ወጣ ብለው ንበረት ለመግዛት የሚያስቡ ወይም የገዙ ሰዎች መሸማቀቅ ውስጥ  የነበሩበት ነው ማለትም ይቻላል። ሰው ገንዘብ አውጥቶ ቤትና ንብረት የሚገዛው ሰላም ሲኖር ነው። ጦርነት እና አለመረጋጋት ካለ ግን ነገ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም ወደሚል ሁኔታ ያዘነብላል። እንግዲህ ሌላው መሰረታ ፍጆታ ላይና ከእለት ዕለት ኑሮ ጋር የሚገኙ ነገሮች ላይ የዋጋ ንረት ቢኖርም ሰው መብላት መጠጣት ስላለበት እየገዛ ይጠቀማል። ወደ ንብረት መግዛት ስንመጣ ግን ሰው ቅድሚያ የሚሰጠው አይደለምና እየቀዘቀዘ ጫና እየፈጠረ ነው የሚሄደው። ይህ በግልጽ እየታየ ነው። ቀላል አይደለም። የንግዱ ማህበረሰብም ጉዳይ አገራችን እንዲህ አይነት የሕልውና ፈተና ላይ ስትወድቅ፣ ትኩረታችንን በሙሉ ወደዚያው አድርገን ምን ማድረግ አለብን ምንስ ማገዝ አለብን? ወደሚለው ነው የሄድነው።
አየሽ አገር ሰላም ሲሆን ነው ንግዱ የሚነገደው፣ ግንባታው የሚገነባው ኢንዱስትሪውም ሊያመርት የሚችለው፣ የተመረተውም የተገነባውም የሚሸጠው የተረጋጋ ሀገርና  ህዝብ ሲኖር  ነው። አጠቃላይ ወጥቶ መግባትና ሀብት ማፍራት የሚቻለው አገር ሰላም ሲሆን ነውና በጦርነቱ ምክንያት ሁላችንም ትኩረታችን ወደዚያው ነው። የደንበኛውም መነሳሳት እየቀዘቀዘ ነው። የዋጋ ንረቱም በኑሮው ላይ የፈጠረው ጫና አለ።
በሌላ በኩል፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ወንጀለኛውን ከደህነኛው ለመለየት በሚደረግ ቁጥጥር የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ ቀበሌ፣ ክፍለ ከተማና ውልና ማስረጃ የመሳሰሉት ካርታ አውጥተን በተናጠል ለደንበኞች እንዳንሰጥ፣ አዳዲስ ፈቃዶችን እንዳናገኝ ተደርጓል። መንግስት ስራውን ለመስራት እነዚህን አገልግሎት በማገዱ ላለፉት ሶስትና አራት ወራት ስራዎች እንዳይንቀሳቀሱ ሆነዋል። ይህን ሁሉ የፈጠረው ጦርነቱ ነው። የሀገርን ሰላም ለማስከበር ሲባል መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው። እርግጥ ነው መንግስት እነዚህ ነገሮች ይቁሙ ሲል የሚያስከትሉትን ነገር ያውቀዋል። ዝርዝሩንም የሚያውቀው መንግስት ነው። ነገር ግን በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ጫና ፈጥሯል። አንድ ሰው ካርታ አውጥቶ ባንክ የፈቀደለትን ብድር ለማግኘት ሂደቶች አሉ። እነዛ ሂደቶች አሁን ስለማይሰሩ ስራ አይሰራም። ብቻ በቀኝም ሆነ በግራ ጦርነቱ ከፍተኛ ጫና ነው ያመጣው።
ይሄ ደግሞ የንግዱን ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን መንግስትንም ነው የጎዳው። ለምን ካልሽኝ… እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑ ክፍያ አላቸው፤ መንግስት የሚያገኘው  ጥቅም  አለ። አሁን መንግስት ያንንም ጥቅም ነው ያጣው። ለምሳሌ ስም ሲዘዋወር፣ ሰው ውል ሲፈራረም፣ መታወቂያ ሲያድስ ሁሉ መንግስት ገቢ አለው። ይሄንን ገቢ ነው ያጣው። በአጠቃላይ ጦርነት አውዳሚ ነው። ጦርነት ሲነሳ አገርም ህዝብም ይጎዳል። ጦርነቱ በተራዘመና በቆየ ቁጥር ደግሞ የጉዳቱ መጠን ይበልጥ እየከፋና እየጎላ ይሄዳል። አሁንም ቢሆን ጦርነቱ ሲጀመር የነበረውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ጫና የተለያየ ነው። ጫናው እያደገ ነው ያለው ለማለት ነው።
ከጊፍት ግሩፕ ውስጥ አንዱ ጊፍት ኮንስትራክሽን ነውና በጦርነቱ የወደሙ ከተሞችና የመሰረተ ልማት አውታሮችን በመገንባቱ በኩል ምን አስተዋጽኦ ያበረክታል?
ትክክል ነው፤ ጊፍት  ኮንስትራክሽን አለ። ነገር ግን አሁን የደረሰው ውድመት በአንድ ድርጅት አስተዋፅኦ የሚሸፈን አይደለም። ይሄንን ውድመት መልሶ ለመገንባትም ቢሆን የደረሰው ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ለመንግስትም ብቻ የሚተው አይደለም። ይሄ እንደ ሀገር ልንረባረብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁን ለህልውና ዘመቻው ደጀን በመሆን ሁሉም በአንድነት እንደቆመው ሁሉ የፈረሱ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት፣ በጦርነቱ የተፈናቀሉትን መልሶ  በማቋቋም በጦርነቱ ጧሪያቸውን፣ ባላቸውን፣ ወንድማቸውን አባታቸውን ላጡ ወገኖች ሁሉ ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት ከደረሰባቸው ሀዘንና ሥብራት ለማውጣት የሁሉም ወገን እርብርብ ያስፈልጋል።
አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገር ሲመጣ ጉዳቱ ብዙ ቢሆንም የሚፈጥረው ትልቅ አጋጣሚም ይኖራል። ያንን የተፈጠረ አጋጣሚ መለየትና ለመልካም ነገር መጠቀም ደግሞ የእኛን አስተዋይነት ይጠይቃል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ላለፉት በርካታ ዓመታት በዘር በብሄር ተከፋፍለን ብዙ ችግር ውስጥ ነው የነበርነው፤ እርስ በእርስ ጥርጣሬ ውስጥ በመግባት ባለመተማመን ውስጥ ነበርን። ነገር ግን ይሄ ጦርነት መጥቶ ሁላችንም ለሀገራችን በአንድነት እንድንቆም አደረገን። በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ አገር ቤት ያለነው አንድ ሆነን፣ የሚዘምተው ህይወቱን ሳይሰስት ሲሄድ ባለሀብቱ በገንዘብና በሎጅስቲክ፣ እናቶች ስንቅ በማዘጋጀት፣ የከተማው ህዝብ የአካባቢውን ጸጥታ በማስከበር ደጀንነቱን እያሳየ ስትመለከቺ ይሄ የሚያስደንቅ ነው።
ዲያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ፣ መድኃኒትና ቁሳቁስ ለሰራዊቱ ከመለገስ በተጨማሪ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ሰልፍ በመውጣትና No More (በቃ) የተሰኘውን መፈክር አንግቦ ለሀገሩ ሉአላዊነት በመነሳት፣ የዓለም መንግስትን ሲያስጨንቅ እንደዚህ ዘመን አልታየም።
ታዲያ የጦርነቱን ጉዳይ ስንጨርስ ይህንን ለጦርነቱ ያሳየነውን አንድነት ወደ ልማቱም ማዞር ይጠበቅብናል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ጊፍት ግሩፕ ኩባንያ እንደ ሁልጊዜውም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እስከ ዛሬም በልማት ጥሪዎች፣ በህልውና ዘመቻው፣ በኮቪድ ጊዜም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ሃላፊነቶችን በመወጣት ረገድ ወደ ኋላ ብለን አናውቅም።
በቅርቡም ሃያት አደባባይ በሚገኘው የጊፍት ሪል እስቴት መንደር ሰራተኞቻችሁ ደም የለገሱ ሲሆን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው መዋጮ አድርጎ የ3. ሚ ብር ግምት ያለው ድጋፍ አጣዬ ድረስ ሄደው አስረክበው የወደሙ መሰረተ ልማቶችንም ጎብኝተው ነበር። እስኪ ምን ታዘቡ?
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ጦርነት አውዳሚ፣ ከሰው በታች የሚያደርግ አንገት አስደፊ ነገር ነው። በአጣዬም ከሌሎች የድርጅታችን የማኔጅመንት አባላት ጋር የእለት ደራሽ ምግቦች (ፓስታ፣ መኰረኒ፣ ሩዝ) ብርድ ልብስ ፋራሽና መሰል ድጋፎችን በ10 አይሱዙ ጭነን ሄደን ለግሰናል።
አጣዬን ለየት የሚያደርጋት ጦርነቱ ለስድስትና ለሰባት ጊዜ ያህል የወረደባትና የወደመች ከተማ መሆኗ ነው። ሰው በጦርነት ተሳቅቆ እኛ እዛ እስከተገኘንበት ጊዜ ድረስ ሙሉ ለሙሉ አልተመለሰም። የጎበኘሁት አጣዬ ሁለተኛ
ደረጃ ት/ቤት በእጅጉ ወድሟል። አጣዬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅም እንደዚሁ ለመናገር በሚያዳግት ሁኔታ ነው የወደመው። የቻሉትን ዘርፈው ሌላውን አውድመው ነው የሄዱት። እጅግ ያሳዝናል። በጣምም ያበሳጫል። እኔ የማኔጅመንት አባላቴን ይዤ ስጓዝ ያንን 3 ሚ. ብር የሚያወጣ ድጋፍ የወሰድነው ባዶ እጃችንን እንዳንሄድ ብለን እንጂ በዋናነት የሄድነው የጉዳቱን ስፋትና ትልቀት በአይናችን ለማየት ነበር።
ቀደም ብዬ እንዳልኩት አጣዬም ህዝቧም በጣሙን ነው የተጎዱት ትውልድ እንዳይማር፣ ያንን ት/ቤት ኮሌጅ እንደዚያ አድርገው ማውደም በጣም ነው የሚያሳዝነው። የሆነ ሆኖ ይህንን ጉዳት በአይናችን አይተናል፤ በመልሶ ማቋቋሙ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብም በውጪ ያለው ኢትዮጵያዊም የሚችለውን ሁሉ አድርጎ መሰረተ ልማቶቹን መገንባት ህዝቡን ወደ ቀዬው መመለስና ማረጋጋት ይኖርበታል። እኛም ይህን በማስተባበር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋን።
እንደ ኩባንያ ቀደም ሲል ገልጬልሻለሁ። የበኩላችንን ስናደርግ ቆይተናል ከሁለት ሳምንት በፊትም ሰራተኞቻችንና ማኔጅመንቱ ደም ለግሰዋል በገንዘብም ደረጃ ድጋፍ አድርገናል። ድጋፉ ይቀጥላል። አጣዬ ብቻ ሳትሆን ብዙ የወደመ መሰረተ ልማት፣ ብዙ የፈረሰ ከተማና የተፈናቀለ አለንና ተባብረን ሁሉን አስተካክለን ወደ ልማታችን መመለስ አለብን።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የጦርነቱ መቋጫ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ጦርነት መፈታት ያለበት በውይይትና በምክክር ነው። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በመንግስት በኩል ብዙ የተሞከረ ነገር እንደነበረ ሰምቻለሁ። ድርድርና ንግግር ግን በሁለቱም ወገን ይሁንታና ተቀባይነት ማግኘት አለበት እንጂ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ መሆን የለበትም። እንደሰማነው በመንግስት በኩል የተሞከረው ሙከራ በዚያኛው አካል በኩል ተቀባይነት በማጣቱ ተገደን የገባንበት ጦርነት ነው። እስካሁን በጦርነቱ ብዙ ጥፋት ደርሷል፣ ህይወት ጠፍቷል፣ ምንም የማያውቁ ንፁሃን ሞተዋል፤ ተፈናቅለዋል። ይሄ እንግዲህ የጦርነትን አስቀያሚነት በግልጽ የሚያሳይ ነው። በተራዘመ ቁጥር ደግሞ ጥፋትና ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነውና በአጭር መቋጨት አለበት። ለዚህ ሁሉ ንግግር ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ነገር ግን ውይይትና ንግግሩ በሁለቱም ወገን ይሁንታን ማግኘት ይኖርበታል።
እርስዎ በህይወት እያሉ ሀገርዎ የት ደርሳ ማየት ይፈልጋሉ?
እኔ ሀገሬ ካደጉት ሀገራት ተርታ ተሰልፋ አድጋና በልጽጋ፣ ተከብራ ማየት እፈልጋለሁ። ለዚህ እድገት እኔ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ እያደረግሁ ነው። ሌላውም የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅበታል። ለአገር እድገትና ብልጽግና ደግሞ ምስጢሩ ስራን መስራትና ስራን ማክበር ነው። እኔ ከትንሽ ስራ ተነስቼ ስራን አክብሬ በመስራት ነው እዚህ የደረስኩት። ጋዜጣ ማዞር፣ሱቅ በደረቴ መስራትና መሰል ስራዎችን እየሰራሁ ማታ ማታ እየተማርኩ ነው ያደግኩት። እግዚአብሔር ረድቶኝ ራሴን በስራ የሰራሁ ሰው ነኝ፡፡ አሁንም 30ውንም ቀን እሰራለሁ፡፡ ጠዋት የምነሳበት፣ ሳይት የምሔድበት፣ የቢሮ ስራዬን የምከውንበት ወደ ጂም፣ የምሔድበት ሰዓት ሁሉ በፕሮግራም የተቀመጠ ነው፡፡ ማታም አምሽቼ ሰርቼ ስራ ሳጠናቅቅ ነው ከቢሮ የምወጣው፡፡
ከሰራን፣ስራን ካከበርን ከተጋን አገራችን ታድጋለች ከብድርና እርዳታ ጠባቂነት ትወጣለች፡ የዓለም መንግስታት እጅ ጥምዘዛም ይቆማል፡፡ ስለዚህ እንስራ ስራን እናክብር የሚል መልዕክት አለኝ፡፡


Read 8545 times